ርዕዮተ ዓለም እንኳ የሌለው ይሉታል የሚቃወሙት ወገኖች፡፡ እሱ ግን ኢትዮጵያን ከማበልፀግ ወደኋላ የሚመልሰኝ አንዳችም ኃይል የለም ይላል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ብልፅግና እንደሚለው በብልፅግና ጎዳና እየተረማመደች ነው? ወይስ በቀውስ አዙሪት እየዳከረች? የሚለው ጉዳይ ብዙ እያጠያየቀ ነው፡፡ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ የአገር ህልውናም ሆነ አንድነት ጠብቆ ማስቀጠሉን የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡
እንደ ሰሞኑ ዓይነት አገራዊ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ደግሞ የብልፅግና ዓላማና ፍላጎት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ጎልቶ መነሳቱ የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር በተገናኘ፣ ብልፅግና ቤተ ክርስቲያኒቱን የማፍረስ የቆየ ድብቅ ዓላማ አለው በሚል ብዙ ወቀሳ ሲሰነዘር ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስቀድመው በሁለተኛው የመደመር መንገድ መጽሐፋቸው፣ ሃይማኖትን መቆጣጠር አገር መቆጣጠር ነው ብለው ጽፈዋል እየተባለ ለዚህ ውንጀላ በማጣቀሻነት ሲቀርብም ሰንብቷል፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግርና አደጋ በተፈጠረ ቁጥር የፖለቲካ ሥርዓቱ ምንነትና ዓላማን በተመለከተ ጠንካራ ጥያቄ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ወገን አገር የሚመራው የፖለቲካ ኃይል ራሱን በግልጽ ካለመበየኑ ጋር ሲገናኝ ይታያል፡፡ አንዳንዴም አገር የሚመራው ኃይል እመራበታለሁ ብሎ ካስቀመጠው መስመርና አቅጣጫ ውጪ ራሱን በገቢር ከመግለጡ ጋር ሲያያዝም ይስተዋላል፡፡
ብልፅግና ወይም የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ለኢትዮጵያ የተስማማውን ሐሳብ ከሁሉም ወስዶና ቀምሮ የሚመራ እንጂ፣ ወጥ ርዕዮተ ዓለማዊ ማንነት እንደሌለው የገለጸበት አጋጣሚ የሚታወስ ነው፡፡ በየመንገዱ አገራዊ መንገራገጭ በተፈጠረ ቁጥር ግን አስተዳደሩ ሊፈጥራት የሚፈልጋት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ናት? የሚል ጥያቄ መነሳቱ ቀጥሏል፡፡ ይህ ደግሞ አስተዳደሩ በቅጡ ስለራሱ ተንትኖ አላስቀመጠም የሚል ብቻ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ቃል የሚገባውና የሚሠራው የሚጣረስ ነው በሚልም ባለፉት አራት ዓመታት ሲያስተቸው ነው የቆየው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የራሳቸው መልስ አላቸው፡፡
በ2012 ዓ.ም. ‹‹መደመር›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ በክፍል ሁለት ምዕራፍ አምስት ጭቆናና የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ህልውና በሚል ባቀረቡት ሀተታ፣ ‹‹አንድ የፖለቲካ ሥርዓት በሌላው በተተካ ቁጥር በሚፈጠሩ ምስቅልቅሎች ምክንያት የአገራችን ህልውና አገረ መንግሥቱን የማስተዳደር ሥልጣን በጊዜያዊነት ካገኘው ቡድን ጋር የተቆራኘ ይመስል፣ ሥርዓት በተቀየረ ቁጥር ስለአገራችን ህልውና ቀጣይነት ዘወትር ስንቆዝም የምንኖር ሕዝቦች ነን፤›› በማለት ጉዳዩ ከምን እንደሚመነጭ አመላክተዋል፡፡
ብልፅግና ዓላማዬም ግቤም የበለፀገች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው ቢልም፣ ኢትዮጵያን ከማበልፀግ ይልቅ እያፈረሳት ነው የሚለው ከባድ ትችት ሲከተለው ይታያል፡፡ በብልፅግና ዘመን ኢትዮጵያ በግጭትና አለመረጋጋት ውስጥ ወድቃ ከመዝለቋ ጋር በተገናኘ፣ አስተዳደሩ አገሪቱን ወዴት እየወሰዳት ነው የሚለው ጥያቄ እየቀረበለት ነው፡፡
የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ደጋግሞ እንደሚለው ከሆነ ግን ይህን መሰሉ ውንጀላ ከሚጨበጥ ሥጋት የመነጨ አይደለም፡፡ ‘ብልፅግና አገር አፍራሽ ነው የሚሉ ኃይሎች በሕዝቡና በመንግሥት መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ጉዳዩም እነዚህ ኃይሎች የፖለቲካ ሴራና ደባ ነው’ ሲል ይደመጣል፡፡ አገራዊ ለውጡን እንዲሁም የዴሞክራሲ ሽግግሩን ለማደናቀፍ የተነሱ፣ አንዳንዴም የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚላቸው ወገኖች ይህን መሰል ውንጀላና ክስ እንደሚያቀርቡ አስተዳደሩ ያስታውቃል፡፡ ይህንን ግን የሚቃወሙ አሉ፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ ‹‹በእኔ እምነት ብልፅግና የራሱ የሆነ ፍልስፍና ወይም የሥነ መንግሥት ዕሳቤ ለመፍጠር በቅጡ ያሰበበት አይመስለኝም፡፡ ብልፅግና ራሱም እንደተናገረው በግርግር ነው የመጣው፡፡ የመጣው ደግሞ ከኢሕአዴግ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ በመውጣቱም ፌደራላዊ ሥርዓትን የኖረበት ነው፡፡ ሆኖም የኖረበትን ሥርዓት ሪፎርም አደርጋለሁ ብሎ ተነሳ፡፡ መደመር የሚባል ፍልስፍና ይሁን ርዕዮተ ዓለም ግራ የሚያጋባ ነገር አምጥቶ እንደ ወንጌል ሰበከ፡፡ ይህ ሒደት በወቅቱ የማነቃቂያ ንግግር ካልሆነ በቀር በቅጡ የታሰበበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትልሞችን መተግበር የሚያስችል ፍልስፍና ወይም ርዕዮተ ዓለም አይመስለኝም፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡
በወቅቱ ብልፅግና ወደ ሥልጣን ሲመጣ ርዕዮተ ዓለሙ መደመር ተራማጅ ዕሳቤ መሆኑንና ከሁሉም ይወስዳል በሚል መነገሩን አቶ በቴ ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም የዓለም እውነታ እንደሚያሳየው ተራማጅ (ፕራግማቲስት) ርዕዮተ ዓለም መከተል ሲባል ከወቅቱ ጋር፣ እንደ አካባቢው ሁኔታና ተጨባጭ እውነታ ርዕዮተ ዓለምን እያሻሻሉ መሄድን እንጂ ርዕዮተ ዓለም አልባነት ማለት አለመሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
የፖለቲካ ተንታኝና ጸሐፊ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ ብልፅግና ርዕዮተ ዓለም ባይኖረውም የፖለቲካ ፍላጎቱና መፍጠር የሚፈልጋት ኢትዮጵያ በግልጽ እንደሚታወቅ ነው የሚናገሩት፡፡
‹‹ብልፅግና ይህ ነው የሚባል ርዕዮተ ዓለም የለውም፡፡ የሚዳሰስና የሚጨበጥ እጅና እግር ያለው ርዕዮተ ዓለም የለውም፡፡ ሁሉንም አጋጣሚ መጠቀም ነው የሚፈልገው፡፡ መጀመሪያ በዴሞክራሲ ግንባታና የበላይነትን በማንበር (ሄጂሞኒ) መካከል ሲዋልል ነበር የቆየው፡፡ በሒደት ግን ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ሳይሆን ኦሮሚያ የሆነች ኢትዮጵያን ነው መፍጠር እንደፈለገ የታየው፡፡ ሁሉንም ነገር የመጠቅለል፣ የመውረርና የመንጠቅ አባዜ ይታይበታል፡፡ የቀደመው ኢሕአዴግ የሕወሓት ወይም የትግራይን የበላይነት አጀንዳ በሥውር ለማስፈጸም ተግቷል፡፡ የአሁኑም በተመሳሳይ የኦሮሚያን የበላይነት ለማስፈን እየተጋ ነው፡፡ ሌላው ብልፅግና በቀውስ ውስጥ እያተረፈ መሄድ ነው የሚፈልገው፡፡ ለሺሕ ዘመናት ረግተው የቆሙ ተቋማትን እየናጠ በዚያ ቀውስ ውስጥ አዲስ ውርስ እያስቀመጠ መሄድ ነው የሚፈልገው፤›› በማለት ነው አቶ ሙሉዓለም የተናገሩት፡፡
እንደ ምሳሌ ከሰሞኑ የታየውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ውዝግብ ያነሱታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን በማናጋት ነባሩን የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ህሊና ለመንካት ስለተፈለገ የተደረገ ዘመቻ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡
የብልፅግና መንግሥት በሕዝቦች የለውጥ ጥያቄና መስዋዕትነት ተንጠላጥሎ ሥልጣን በመያዝ፣ ለውጡን ጠልፏል የሚለው ክስ ከሁሉ ቀድሞ ሲነሳበት ቆይቷል፡፡ የዴሞክራሲ ሽግግሩን ትርጉም ባለው መንገድ መምራት አቅቶታል፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን አሰናክሏል ሲባልም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በአጠቃላይ የሕዝቡን የዴሞክራሲና የለውጥ ተስፋ አምክኖታል እየተባለም አስተዳደሩ ሲወቀስበት ቆይቷል፡፡
ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፈጠሩት መንግሥታዊ ሥርዓት በአገኘው አጋጣሚና ቀዳዳ ሥልጣኑን ለማቆየት የሚችልባቸውን ቀዳዳዎች የሚጠቀም እንጂ፣ ዘላቂ አገራዊ ዕቅድም ሆነ ግብ የሌለው ነው የሚሉ አሉ፡፡ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ደግሞ የፖለቲካ መሠረቱን ከአንዱ ወደ ሌላው ማፈራረቅን ይጠቀማል ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ የፖለቲካ ኃይል ወዳያለበት በየጊዜውና በየወቅቱ በማዝመም ወንበሩን ተቆናጦ መቆየት የፖለቲካ ታክቲኩ ነውም ይሉታል፡፡ በሌላ በኩል የብልፅግና መንግሥት ለሥልጣኑና ለወንበሩ እስከጠቀመ ድረስ የቀውስ አዙሪት በመፍጠር፣ ሕገወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ እስከማድረግ የሚሄድ ነው ሲሉም በከባዱ ይወቅሱታል፡፡
የኦነግ ፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ እንደሚሉት፣ ደግሞ ብልፅግና በፌደራላዊና በአሀዳዊ ኃይሎች መካከል እያምታታ ነው የመጣው፡፡ ‹‹ፌደራላዊ ሥርዓቱ አይነካም ይልና ባህር ዳር ሲሄድ ደግሞ የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ነው የኢትዮጵያ ችግር ይላል፡፡ የቀድሞ ነገሥታትን እያወደሰ፣ ኢትዮጵያዊነትን አለቅጥ እየካበ፣ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ገናንነት ትመለሳለች፣ አንተ ትፈርሳለህ እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም›› የሚል ትርክት ይዞ መጣ፡፡ ይህ ደግሞ የቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ የበደል ታሪክ ነው ከሚሉ ፌዴራሊስቶች ጋር አጋጨው፡፡ የትግራይ ጦርነትም ይህን መሰል አሀዳዊ ትርክት አንዱ መነሻው ነው፡፡ እኔ የሚገባኝ ያን ትርክት የሚመራበት ሆኖ ሳይሆን የሚቀናቀነውን ለመምታት አስቦ ያደረገው ነበር፡፡ ነገር ግን ከውስጥም ከውጭም ሲላተም ተገዶ ወደ ፌዴራላዊ ቁመናው ተመልሷል፡፡ በፊት አሀዳዊያኑን ሲያስደስት ነበር፡፡ አሁን ግን ተገዶ ወደ ፌዴራላዊ ኃይሎች ተመልሷል፡፡ ሥርዓቱ የሚፈልገው ሥልጣን ነው፡፡ ተራማጅ ነኝ ቢልም በየወቅቱ ይጠቅመኛል ከሚለው ጋር የማበር ታክቲክ ነው የሚከተለው፡፡ ይህ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ኖሮት ሳይሆን ሥልጣንን በማንኛውም መንገድ ለማቆየት ካለው ፍላጎት የሚመነጭ ነው፤›› በማለት ይተቹታል፡፡
አቶ በቴ እንደሚሉት፣ ብልፅግና እንደ ኢሕአዴግ የአንድ ወገን የፖለቲካ የበላይነትን ለማስፈን ፈልጎ ሳይሆን ለሥልጣን ሲል ነው ከአንዱ ወደ ሌላው የድጋፍ መሠረቱን የሚለዋውጠው፡፡ ‹‹አንድ የፖለቲካ ቡድንን ለመጥቀም ወይም የኦሮሚያ ሪፐብሊክን ለመፍጠር ከጅሎ ነው የሚሉት ወገኖች የተሳሳቱና ባህሪውን ያላወቁ ናቸው፡፡ አሀዳዊያን ዛሬ አዲስ ሆኖባቸው እንጂ ከበፊትም ብልፅግና ካመቸው ጋር ተጣብቆ ሌሎችን ማፈኑን ስንጮህበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ቡድን ለመጥቀም ወይም የኦሮሚያ ሪፐብሊክን የመመሥረት ፍላጎት ቢኖረው ሲያደርግ የምናያቸው ብዙ ምልክቶች ይኖሩ ነበር፡፡ ብልፅግና ከዚያ ይልቅ ሥልጣን አፍቃሪ ነው፤›› ያሉት፡፡
ብልፅግና ለሥልጣን ሲል ጥቅመኛ (ኦፖርቹኒስት) የሆነ የፖለቲካ ታክቲክ ይከተላል የሚለውን ብይን አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅንም ይስማሙበታል፡፡ ይሁን እንጂ ብልፅግና እንደ ኢሕአዴግ ለአንድ ወገን ፍፁማዊ የበላይነት የሚተጋ አይደለም የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉትም፡፡ ‹‹ብልፅግና የበላይነትን ማስፈን (ሄጂሞኒ) ነው ፍላጎቱ፡፡ በፖለቲካ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም፣ በባህልም የኦሮሚያን ፍፁማዊ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው ፍላጎቱ፡፡ ያን ደግሞ በቀውስ አማራጮች ለማስፈጸም ነው የፈለገው፡፡ በተነቃበት ቁጥር ደግሞ ለሁሉ ነገር የጥፋት አቻ ፍለጋ መዞር ሆነ ሥራው፡፡ ለኦነግ አብንን፣ ለጃዋር እስክንድርን፣ ለሸኔ ፋኖን ማምጣት፣ አሁን ደግሞ ለሲኖዶሱ ደግሞ ተቃራኒ ሲኖዶስ አመጣ፡፡ ብልፅግና ከቀውስ አተርፋለሁ ብሎ የሚሮጥ፣ ካለፈ ስህተቱም የማይማር መንግሥት ነው፤›› በማለት ነው አቶ ሙሉዓለም የብልፅግና ፍላጎትን የተናገሩት፡፡
ብልፅግና የለውጡን ተስፋ አመከነ የሚለው የተቃዋሚዎች ውንጀላ በሒደት እንደታየው ከሆነ ይዘቱ እየተቀየረና እየጠነከረ ነው የሄደው፡፡ ብልፅግናም ሆነ መሪው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መገንባት የሚፈልጉት ሥርዓትና አገረ መንግሥት የሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን ጥቅም ያላማከለ ነው ወደ ሚል ትችት ተቀይሯል፡፡ አገር ለማፍረስ ፕሮጀክት ቀርፀው የሚሠሩ እየተባሉም መብጠልጠል ጀምረነዋል፡፡ አለፍ ሲልም የአንድ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም የፖለቲካ ቡድን የበላይነት ለማስፈን የሚተጉ ናቸው የሚል ከባድ ውንጀላም ይሰማል፡፡
በኢሕአዴግ ዘመን የሕወሓት የበላይነት በሥርዓቱ ውስጥ ነገሠ ሲባል ኖሯል፡፡ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት ስም የአንድ ወገን የበላይነትን ለማንገሥ የሚሠራ ነው ሲባል ይወነጀል ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የሥርዓቱ ደጋፊና አባላትን ለመጥቀም አለፍ ሲልም የትግራይንን የበላይነት ለማረጋገጥ የሚሠራ ነው የሚለው ወቀሳ፣ ብዙዎች ሥርዓቱን እንዲታገሉትና በስተመጨረሻም ከሥልጣን እንዲለቅ እንዳደረጉበት ይታወሳል፡፡
በኢሕአዴግ ውድቀት ማግሥት ሥልጣን የጨበጡት የለውጡ መንግሥት መሪ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ራሳቸው፣ የአንድ ወገን ጥቅምን ለማስጠበቅ ሥርዓቱ መትጋቱ ለውድቀት እንደዳረገው በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በአንድ ወቅት በፓርላማ በነበራቸው ውሎ፣ በሠራዊቱ ውስጥ ሰፍኖ የቆየውን ያልተመጣጠነ የአመራር ውክልናና የአንድ ወገን የበላይነት በሰፊው ይፋ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ይህ ብልፅግና አደገኛ ሲለው የቆየው የተዛባና አድሏዊ የፖለቲካ አወቃቀር ደግሞ መልሶ መከሰቱንና ብልፅግናም እየተፈተነበት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ብልፅግናም ሆነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአንድ ብሔር ወይም የፖለቲካ ቡድን ፍላጎትን ለማሟላት የሚሠሩ ናቸው በሚል የሚከሳቸው እየበረከተ ነው፡፡
አቶ በቴ እንደሚናገሩት፣ ብልፅግናን በዚህ ጉዳይ ከመበየን በፊት በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ቅራኔ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ በእሳቸው እምነት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ፍልሚያ አንድ አሀዳዊ ሥርዓት፣ ሁለት ፌደራላዊ ኃይል፣ እንዲሁም ሦስተኛ ነፃ አገርን የመመሥረት ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የሚያካሂዱት ሽኩቻ ነው፡፡ በእነዚህ ኃይሎች መካከል ያለው ትንቅንቅ ኢትዮጵያን እየፈተናት መሆኑን ይህም በፖለቲካ፣ በታሪክ፣ በባህልም ሆነ በድንበር የሚገለጽ ትንቅንቅ እንደሆነ ነው ፖለቲከኛው የሚናገሩት፡፡
አሀዳዊው የሚባለው ኃይል አንዲት ኢትዮጵያን መፍጠርን ያልማል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ይጠላል፣ መሻሻል የማይችል ነው ይላል፣ ፌደራል ሥርዓቱንም ይቃወማል፡፡ አማርኛ ተናጋሪነትና ኦርቶዶክሳዊነትን የበላይ ለማድረግ ይተጋል ይሉታል፡፡ ለዚያም ደግሞ የቻለውን ሁሉ ቀውስ ይፈጥራል ይላሉ፡፡
የፌደራል ኃይሎች ደግሞ የነበረውን ቅራኔ በተወሰነ መንገድ የብሔር ጭቆና ነው ብሎ የመደበ ነው፣ ይህ የብሔር ጭቆና ደግሞ በኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት የተወሰነ ምላሽ አግኝቷል፣ ስለዚህ ይህን ሥርዓት አብረን እናፅናው ብሎ የሚያምን መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡ ብልፅግናም ከእነዚህ ወገን ይመደባል ይሉታል፡፡
በሦስተኝነት ያለው የትኛውም ሥርዓት ይኑር ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ዕድል ይፈጠር ብሎ የሚታገል የነፃነት ኃይል ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎችም በሕዝቦች ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አገረ መንግሥት ይኑር የሚሉ ናቸው ይላሉ፡፡
በዚህ የሦስት ወገን ትንቅንቅ መካከል ብልፅግና መውደቁን የሚጠቅሱት አቶ በቴ፣ አሁን መንግሥት በአነዚህ መጓተቶች መካከል ወዴት እንደሚያዘነብል ግራ መጋባቱን ያሰምሩበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲኖር ከተፈለገ ግን ሁሉንም አቻቻይ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የበለጠ ዴሞክራሲያዊ አድርጎ መቀጠል እንደሚያዋጣ ነው የጠቆሙት፡፡
አቶ ሙሉዓለም በበኩላቸው፣ ብልፅግና አንድ ወገንን እጠቅማለሁ ወይም አስደስታለሁ በማለት እንደ ቀደመው ኢሕአዴግ ዓይነት ስህተት እየፈጸመ ነው ይሉታል፡፡
‹‹አሁን ያለው የብልፅግና መንግሥት ራሱን የኦሮሚያ ጠበቃ ሆኖ ለመታየት ቢጣጣርም፣ ነገር ግን በእሱ ዘመን በኦሮሞ ላይ የከፋ ዕልቂት እየተፈጸመ ነው፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ጠቀምኩ እያለ የሕዝቡን እሴት እየናደና አንድነቱንም እያፈረሰ ነው፡፡ ወለጋ ላይ የሆነው ሁሉ ያማል፡፡ አሁን ያለው አገዛዝ በቀውስ ለመነገድ የሚፈልጉ ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን ስብስብ ነው፤›› በማለት አቶ ሙሉዓለም አስረድተዋል፡፡
ይህ የብልጽግና አካሄድ ደግሞ በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ አገር እንዲህ ነው እንዴ የሚመራው የሚል ጥያቄ ፈጥሯል ይላሉ፡፡ በብልፅግና ዘመን በየዕለቱ በሕዝቦች መካከል ያለው ቅራኔ እያደገ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ፡፡ የብልፅግና የፖለቲካ አካሄድ ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ እየገባ እንደሚገኝም ይናገራሉ፡፡ አስተዳደሩ በራሱ ውስጥም ቢሆን አንድነቱን አስጠብቆ መዝለቁ እንደሚያጠራጥር፣ ይህ ደግሞ በሠራዊቱም ሆነ በሲቪል ሠራተኛው ውስጥ ያለው ቅሬታ ገንፍሎ በሥርዓቱ ላይ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋታቸውን ያወሳሉ፡፡ ይህንን ዓይነት አደጋ ለማስቆም እኩልነትን መለማመድና ፍላጎትን በግድ ከማስፈጸም መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
‹‹አመራሩ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ኖሮት የጋራ ሰላምን፣ የጋራ ልማትን አልሞ የሚንቀሳቀስ ኃይል አይደለም፡፡ የሚነካካቸው ነገሮች በሙሉ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን መሠረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ አንድ ነገር ያመጣና አጨናንቆና ወጥሮ ፍላጎቴ ያለውን አሳክቶ ወደ ሌላው ነው የሚሄደው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ እግራቸውን ቤተ መንግሥት ሌላውን ቤተ እምነት ላይ ማድረጋቸው ትልቅ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መዳኛ በሃይማኖትና በፖለቲካ መካከል ርቀት መፍጠር ነው፤›› በማለት፣ የብልፅግና መንግሥት የኢትዮጵያን ነባር ማኅበራዊ መሠረቶች ማናጋቱን እንደቀጠለና ይህም አደገኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት በኢቢኤስ ከሰይፉ ፋንታሁን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹አቡዳቢን ካየኸው አገሩ ራሱ ማን እየመራው እንዳለ ይናገራል፡፡ የዜጎችና የሰዎች ደስተኝነትና የተደላደለ ኑሮ የመሪውን ማንነት ይናገራል፤›› ነበር ያሉት፡፡ አሁን እሳቸው የሚመሯት ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች? የመሪውን ማንነትስ በምን መንገድ ትናገራለች? የሚለው ግን የወቅቱ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት የጠራ ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ አቅጣጫ የሌለው ነው ቢባልም፣ በተለይ በሁለቱ የመደመር መጽሐፎቻቸውና በተለያዩ መድረኮች የተናገሯቸው ንግግሮች የመንግሥታቸውን ማንነት የሚበይን መሆኑ ይነገራል፡፡
በ2012 ዓ.ም. ባሳተሙት ‹‹መደመር›› መጽሐፍ ምዕራፍ አምስት ጭቆናና የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ህልውና ብለው ባስቀመጡበት ከገጽ 77 እስከ 90 ያለው ሐሳብ እሳቸው ሊፈጥሩት ያሰቡት አገረ መንግሥት ምንነትን ጠቋሚ ተደርጎ ሲቀርብ ይታያል፡፡
‹‹የአገር ህልውና ሥጋት የሚገጥመን ለምንድነው? ከግራም ከቀኝም ጽንፍ የረገጡ ሐሳቦችን ለማስታረቅና የፀና አገረ መንግሥት ለመመሥረት ጥረት ያደረጉ ሚዛናዊ ዜጎች ቢኖሩም፣ ከሁሉም አቅጣጫ ጥላቻና ውግዘት ነው የገጠማቸው…›› የሚሉት ዓብይ (ዶ/ር) ይህ ለምን እንደሆነ ደግሞ ምክንያቶቹን ይዘረዝራሉ፡፡
አንደኛው ችግር ሰው ወለድ ጭቆና በኢትዮጵያ ለ50 ዓመታት የዘለቀ መሆኑን፣ ከሰዎች ክፉ አሳቢነት የመነጨ በፖለቲካ ሴራ፣ በጦር መሣሪያ፣ በዘር፣ በዝምድናና በቀዬ በመሰባሰብ የሚፈጸም ሥልጣን የማስጠበቅ ፍላጎት መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ሰው ወለድ ጭቆና የሚተገብሩ ኃይሎች እነሱ የወጡበት ሃይማኖት፣ ብሔርና አካባቢ በከፍተኛ ጉስቁልና ውስጥ ቢሆንም የጨቋኝነት ስሙ ግን ከእነሱ ራስ አይወርድም፡፡ ሕዝቡ በጨቋኞች ላይ ያለውን ብሶትና ምሬት ጨቋኞቹ የወጡበትን አካባቢ ሕዝብ በማማረርና በመተቸት ነው የሚወጣው በማለትም ያስቀምጡታል፡፡
ይህ ጭቆና ተቋማትን የሚያከስም፣ የአገር ቀጣይነት አደጋ ላይ የሚጥል፣ የዴሞክራሲ የግልና የቡድን መብት ጥያቄን ያነሱ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑበት ችግር እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
ሌላኛው የጭቆና ዓይነት ብለው ያስቀመጡት መዋቅር ወለድ ጭቆና ደግሞ፣ ከሥርዓት ወይም ከመዋቅር የሚመነጭ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊ አገሮችም የሚፈጠርና ጭቆናው ሆን ተብሎ የማይከወን ሊሆንም ይችላል ይሉታል፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ ተቋማትም መገልገያ ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ፡፡ በግለሰቦች ላይ ቢከወንም በአብዛኛው በቡድኖች ላይ ነው የሚፈጸመው፣ የሰው ልጅ ግንኙነት የተዛባ እንዲሆን ያደረጉ መዋቅሮችን መረዳትና የተዛባውን ጎኑን ማስተካከል ይጠይቃል ሲሉም ያክላሉ፡፡
‹‹በአጠቃላይ አገራችን መዋቅራዊ ጥገና የሚፈልጉ ዘጠኝ የቡድን ማንነቶች አሉባት፡፡ ብሔር፣ አካባቢ/ክፍለ አገር፣ የአካል ጉዳት፣ የመሀል/የጠረፍ ነዋሪነት፣ መደብ፣ ሥርዓተ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ከተሜነት/ገጠሬነት፣ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ቢያንስ ለጊዜው በጉልህ የሚገኙትና የሚጨበጥ መዋቅራዊ ጭቆና የሚስተዋልባቸው እነዚህ ዘጠኝ ማንነቶች ናቸው፡፡ ወደፊት የእነዚህ ቡድኖች ማንነቶች አዳዲስ ገጾችም ይሁኑ እንደ አዲስ የሚፈጠሩ ሌሎች የቡድን ማንነቶች መፈጠራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ በመዋቅሩ ላይ ተከታታይ ጥገና ማድረግ አስፈላጊ ነው፤›› በማለት ነው በኢትዮጵያ መቀየር ስላለባቸው መዋቅራዊ ገጾች የሚዘረዝሩት፡፡
ዓብይ (ዶ/ር) አለ ያሉትን ግለሰባዊና መዋቅራዊ ጭቆና በመታገል ሒደት ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር በማስቀመጥ ነው ይህን ሐሳባቸውን የሚቋጩት፡፡ ቡድናዊ አክራሪነትና አጸፋዊ ጭቆና ብለው ባተቱበት በዚህ ግርጌም፣ ‹‹የቡድን ማንነትን ይዞ ከጭቆና ለመላቀቅ የሚደረግ ትግል የቡድን አክራሪነትን በመፍጠር ከሚፈታው ይልቅ፣ የሚፈጥረው ችግር በአገራችን እየባሰ ሄዷል፡፡ የአገር ሰላም እያናጋ ዜጎች ተቻችለው እንዳይኖሩ የሚያደርግ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አጸፋዊ ጭቆና እያስከተለ ይገኛል፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ያነሳሉ፡፡
‹‹ተጨቁነናል የሚሉ ወገኖች ትግላቸው ገደቡን አልፎና መስመሩን ጥሶ፣ እነሱም በምላሹ ለመጨቆን ሲሞክሩ የሚከሰት ችግር ነው፤›› ሲሉም የሥጋቱን ምንነት ያብራራሉ፡፡
የሱፍ ያሲን ‹‹ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት›› በሚል ርዕስ በ2009 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ፣ አገሪቱ ያስፈልጋታል የሚሉትን አቻቻይና አቀራራቢ ሐሳቦች በሰፊው አንስተውበታል፡፡ ጸሐፊው በዚህ መጽሐፋቸው ለአንድ ሰው ወይም ማኅበረሰብ ወሳኝና አይነኬ የሚባሉ ጉዳዮቹ ምን እንደሆኑ ከሥልጣኔ ግጭቶች (ክላሽ ኦፍ ሲቪላይዜሽን) መጽሐፍ ደራሲው ከሳሙኤል ሀንቲንግተን በተዋሱት ሐሳብ ነው የሚተነትኑት፡፡
‹‹ሳሙኤል ሀንቲንግተን ዞሮ ዞሮ ለሰው ወሳኙ የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ወይም የኢኮኖሚ ጥቅም አይደለም፡፡ ሰው እስከ ሞት ድረስ መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ የሚሆነው ለዕምነቱ፣ ለቤተሰቡ፣ ለደም ትስስሩና ለሚያምንበት ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ወገንተኛነቱን ላረጋገጠለት ቁም ነገር ይዋጋልም ይሞታልም (what ultimately counts is not political ideology or economic interest. faith and family, blood and belief are what people identify with and what they will fight and die for.) ብሎ ነው ያስቀመጠው፣›› ሲሉ የጻፉት ጽሑፍ፣ እነዚህን አይነኬ ጉዳዮች ደግሞ አንድ መንግሥት መጠበቅ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡ አሁን ብዙዎች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ የብልፅግና መንግሥት በእነዚህ ተቃርኖዎች መካከል እየዋለለ ነው፡፡