ለደራስያን በሙሉ የምመክረው አንድ ነገር አለ፡፡ ንቃትም፣ ትጋትም ያጠጠበት ዘርፍ መስሎ የታየኝ ነገር ስላለ፡፡ ድርሰት ትልቅ ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ ከዝግጅቶቹ አንዱና መሠረታዊው ዕውቀትን በመመልከት፣ ዙሪያን በመቃኘት፣ በተለይ ደግሞ በማንበብና ያነበቡትን አጣጥሞ ራስን በመመርመር አዕምሮን ከልቡና ጋር ማዳበር ነው፡፡ ዝም ብለን፣ አንድ ቀን ወፈፍ ጨምደድ ያደረገን ዕለት ተነሥተን እስቲ ወደ ገበያ ልውጣ እንደሚባለው፣ እስቲ ድርሰት ልጻፍ አይባልም፡፡
ድርሰት ከባዶ ስለማይፈልቅ፣ ያለፉትን፣ የቀደሙትን ዘመናትና ደራስያን ድርሰቶችን ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት በሚለው ላይ ስንፍ ይዞ ድርሰት የለም የሚለውን እጨምራለሁ፡፡ አፈ ታሪኩን፣ ተረታ ተረቱን፣ ሚቶሎጂውን፣ ሃይማኖታዊ መጻሕፍቱን፣ ታሪክን፣ ፍልስፍናን ማንበብ ለደራሲ የምርጫ ጥያቄ መሆን ያለበት አይመስለኝም፣ ሙያዊ ግዴታም፣ የሰብዓዊነት መርህም እንጂ፡፡ ዕውቀታችን ግልብ ከሆነ፣ ድርሰታችን እንደዚያው ቀላል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የንባብ ዋጋ ከመድረስ ዋጋ ቢበልጥ እንጂ አያንስምና ቀደምት ድርሰቶች ዘርታችሁ ልታፈሩ ላሰባችኋቸው ድርሰቶች ግብዓት ይሁኗችሁ፡፡
– ዮናስ አድማሱ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ‹‹መድበለ ጉባኤ›› (2001)