Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሕግና ለሥርዓት ቦታ አለመስጠት ዋጋ ያስከፍላል!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ከሚታወቅባቸው አኩሪ ባህሪያቶቹ መካከል አንደኛው ለሕግና ለሥርዓት ያለው ክብር ነው፡፡ ‹‹በሕግ አምላክ›› ሲባል መቆም ወይም ከማንኛውም ድርጊት መታቀብ የተለመደ በመሆኑ፣ ሕገወጥነት ወይም ሥርዓተ አልባነት በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ ለመንግሥት ትልቅ ግምት ስላለው፣ የሰላሙንም ሆነ የደኅንነቱን ጉዳይ የሚተወው ለመንግሥት ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ደግሞ በማኅበራዊ መስተጋብሮቹ በሚፈጥራቸው የጋራ መሰባሰቢያዎቹ፣ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ግንባር ቀደሙን ሚና ይጫወታል፡፡ በቀድሞው ጊዜ እንደ ዕድር የመሳሰሉ ማኅበራዊ ተቋማት ለዚህ ተግባር ከማገልገላቸውም በላይ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ኢሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ ግድፈቶች እንዳይከሰቱ የበኩላቸውን ኃላፊነቶች ሲወጡ ኖረዋል፡፡ የእምነት ተቋማትና አገልጋዮችም ግለሰቦችም ሆኑ ማኅበረሰቦች ከሕገወጥ ድርጊቶች እንዲርቁ ትልቅ ሚና ነበራቸው፣ አሁንም አላቸው፡፡ ይህ ሁሉ ጠቃሚ አገልግሎት በሚበረከትባት አገር ውስጥ፣ የምሁራንም ሆነ የፖለቲካ ልሂቃን አስተዋጽኦ ምን ያህል ነበር ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ በጣም አሉታዊና አሳዛኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ጨዋ፣ አስተዋይ፣ ታጋሽ፣ አገሩን የሚወድ፣ ብልህና ጀግና ሕዝብ ቢኖራትም በፖለቲካው መስክ ግን አልታደለችም፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ የሕዝቡ ነፀብራቅ መሆን ሲገባቸው፣ ከሕዝቡ ዕድሜ ጠገብ አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶች ተቃራኒ የሆኑ የክፋት ድርጊቶች እየፈጸሙ ከፍተኛ በደል እያደረሱ ነው፡፡ ለሕግና ለሥርዓት መስፈን ትልቅ ኃላፊነት መቀበል ሲገባቸው፣ ሕዝብን በብሔርና በእምነት እየከፋፈሉ ለማፋጀት የሚያደቡ ፖለቲከኞች መብዛት ያሳስባል፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ሳታጣ የድህነትና የኋላቀርነት መጫወቻ የሆነችው፣ ከሚፈልጉት ሥልጣንና ጥቅም በላይ ለአገር ደንታ በሌላቸው ፖለቲከኞች ምክንያት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ከእርስ በርስ ሽኩቻቸውና ትንቅንቃቸው ባልተናነሰ የማይመለከታቸው ጉዳይ ውስጥ ጥልቅ እያሉ፣ የብሔርና የሃይማኖት ቀውስ በመፍጠር ሕግና ሥርዓት እንዲጣስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥ ሌብነት፣ ውሸት፣ አሉባልታ፣ ሐሜትና ሴረኝነት የተለመዱ ድርጊቶች እንዲሆኑ ያበረታታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ለደረሱ ሰብዓዊ ቀውሶች፣ ዋነኞቹ ምክንያቶች እነሱ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሃይማኖቶች ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት በሕግና በሥርዓታቸው መሠረት፣ ተልዕኮአቸውን ማከናወን በሕግ የተሰጣቸው መብታቸው ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥማቸውም የማንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖርባቸው በራሳው መፍታት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ፖለቲከኞች በአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እያመሱዋቸው ትርምስ ይፈጥሩባቸዋል፡፡ ዓለማዊውን ከመንፈሳዊው ጋር በማደባለቅ ጭራሽ በራሳቸው መንገድ ሊመሯቸው ሲነሱ፣ ከአገልጋዮችና ከሰፊው ምዕመን ጋር የመረረ ጠብ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን ጥርት አድርጎ የደነገገ ቢሆንም፣ የፖለቲከኞች ሃይማኖቶች አካባቢ ማንዣበብ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ከፍተኛ ቅራኔ እየተፈጠረ ነው፡፡ ቤተ እምነቶች ውስጥ ያሉ አገልጋዮች ራሳቸውን ከፖለቲከኞች ተፅዕኖ የማያላቅቁ ከሆነ፣ ቅራኔው የበለጠ እየሰፋና እየተንሰራፋ ለአገር አደጋ መደቀኑ አይቀሬ ነው፡፡ ፖለቲከኞች አገርን ወደፊት የሚያራምዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ማተኮር ሲጠበቅባቸው አገር አፍራሽ ሲሆኑ በሕግ ማለት ይገባል፡፡ ሕግና ሥርዓት ሳይኖር ዕድገት አይታሰብም፡፡

ሕግና ሥርዓት ለማክበርም ሆነ ለማስከበር የመጀመሪያው ኃላፊነትና ግዴታ የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ከምንም ነገር በፊት ውስጡን ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡ እያንዳንዱ ተቋም፣ ተሿሚና ሠራተኛ በሕግና በሥርዓት የሚመራበትን አሠራር ማፅዳትና ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ ተቋማት ጠንካራ ሆነው በሥርዓት ሊመሩ የሚችሉት፣ አመራሮች በዕውቀትና በልምድ በልፅገው አገልጋይ የሚሆኑት፣ ሠራተኞች እንደ ሙያቸው ተሰማርተው የሚፈለግባቸውን በቅንነትና በኃላፊነት የሚያበረክቱት ለሕግና ለሥርዓት ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ ሌብነትና ሥርዓተ አልበኝነት የሚንሰራፉት ግን አድሎአዊና አግላይ ብልሹ አሠራሮች ሲበዙ ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ሌብነት የተስፋፋውና ኢሞራላዊ ድርጊቶች የተበራከቱት በሕግና በሥርዓት መምራት ባለመቻሉ ነው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋለው ስብራት ትልቁ ምክንያት፣ ሕግና ሥርዓት ገለል ተደርጎ ሌብነትና ኩረጃ ዋነኛው አቋራጭ መንገድ መደረጉ ነው፡፡ ትምህርት እንዲህ መቀለጃ ሆኖ በሥርዓት የተሰጠ ፈተና ገመናችንን ገላልጦ ሲያሳይ፣ ያለንበትን ትክክለኛ ደረጃ ለመገንዘብ አያዳግትም ማለት ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ ውጤቱ ውድቀት ነው፡፡

በዚህ ዘመን ዜጎች ከምንም ነገር በላይ ለሕግና ለሥርዓት መስፈን ማንኛውንም አስተዋፅኦ ከማበርከት መቆጠብ የለባቸውም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከገዛ ቤተሰቡ ጀምሮ ሕግ እንዲከበር፣ የሰዎች መብትና ነፃነት እንዳይጣስ፣ አገርን የሚጎዳ ምንም ዓይነት ድርጊት እንዳይፈጽምና ለሰላም መስፈን የሚፈለግበትን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ቤተሰብ የአንድ አገር የመጀመሪያው ተቋም እንደ መሆኑ መጠን፣ የቤተሰብ አባላት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሙስናም ሆነ ሌብነት፣ እንዲሁም ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች በቤተሰብ ደረጃ በእንጭጩ ካልተቀጩ መከራው የሚተርፈው ለአገር ነው፡፡ ኢሞራላዊና ኢሥነ ምግባራዊ ድርጊቶች የሚበራከቱት በቤተሰብ ደረጃ አስፈላጊው ሥራ ሳይከናወን ሲቀር ነው፡፡ ቤተሰብ ልጆችን ከማብላት፣ ከማጠጣት፣ ከማልበስና ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ በተጨማሪ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር አለበት፡፡ ወላጆችም ለልጆቻቸው አርዓያ ለመሆን ከማናቸውም ሕገወጥ ድርጊቶች መራቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ ወደ ማኅበረሰብ የሚዘልቀው መልካም ባህሪይና ሥነ ምግባር፣ ወደ አገር ደረጃ እያደገ ሲሄድ ሕግና ሥርዓት ይከበራል፡፡

ጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ቅድሚያ በመስጠት በክፉም ሆነ በደግ ጊዜያት አብረው ኖረው፣ ለተከታዩ ትውልድ መልካም የጋራ እሴቶቻቸውን እያስተላለፉ እዚህ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም ለአገርም ሆነ ለሕዝብ የማይጠቅሙ ነገሮችን ወደ ጎን በማለት፣ የአርቆ አሳቢዎቹንና የአስተዋዮቹን ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ መልካም ተግባራት መውረስ አለበት፡፡ የተፈጸሙ ስህተቶችን በማረምና መልካሞቹን በማጎልበት አገሩን ታላቅ ለማድረግ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ለክፋትና ለሴራ የሚያገለግሉ ጠቃሚ ያልሆኑ ትርክቶችንና ዕሳቤዎችን በማስወገድ፣ ለመጪው ትውልድ ቅርስ የሚሆኑ አበርክቶዎች ላይ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ ነጋ ጠባ ቅራኔ ከመፈልፈልና እርስ በርስ ከመተናነቅ ይልቅ፣ ለነገዋ የእኩልነት አገር በጋራ ተሠልፎ የመሥራት ጥበብን መቀዳጀት የግድ መሆን አለበት፡፡ በማይረቡ ጉዳዮች መጨቃጨቅና መታገል ያተረፈው ነገር ቢኖር ዕልቂትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ አብሮ መኖርና መሥራት ሲለመድ ግን፣ ለማመን የሚያዳግቱ ውጤቶች እንደሚገኙ መገንዘብ ይገባል፡፡ ከሕግና ከሥርዓት ማፈንገጥ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...