በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሞክሯል በተባለው መፈንቅለ ሲኖዶስ ጋር በተያያዘ፣ ያደረጉት እንቅስቃሴ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል የማፍረስ የሽብር ወንጀል እንቅስቃሴ አድርገዋል ተብለው ተጠርጥረው ላለፉት 11 ቀናት በእስር ላይ የነበሩት እነ መምህር ምሕረትአብ አሰፋና ወ/ሪት ፌቨን ታሪኩ ትናንት ምሽት ላይ ከእስር ተፈቱ፡፡
ምርመራውን እያደረገ የነበረው መርማሪ ፖሊስ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት አቅርቦ 14 ቀናት ጠይቆባቸው የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩን እያየው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ስምንት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ነበር፡፡
ፖሊስ ትናንት የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዳስረዳው በተሰጠው ጊዜ የሁለት ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ለተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ መጻፉን፣ የተጠርጣሪዎችን ንግግር ወደ ሲዲ መቀየሩን፣ ብርበራ አድርጎ ያገኛቸውን ማስረጃዎች በኤግዚቢትነት መያዙን አስረድቷል፡፡ በቀጣይ ግብረ አበሮቻቸውን መያዝ እንደሚቀረው የወደሙ ንብረቶችን ግምት ማሠራት፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ጉዳተኞች ቃል መቀበል እንደሚቀረውና በሻሸመኔና ወለቴ አካባቢ የደረሰውን ጥፋትና ጉዳት የሚመረምር ቡድን ስላላከ ምላሻቸውን ለመጠባበቅ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡
ተጠርጣሪዎቹን ወክለው 11 ጠበቆች የቆሙ ሲሆን፣ በሰጡት ምላሽም ሲጀመር ፖሊስ የወንጀል ጥርጣሬ መነሻ እንደሌለው እያቀረበ ያለው መከራከሪያ ግምት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የወንጀል ጥርጣሬ መነሻ አለው ቢባል እንኳን ተሰጥቶት የነበረው ጊዜ ከበቂ በላይ ቢሆንም፣ ፖሊስ የሠራው በሰዓታት ውስጥ መሠራት የሚችል ደብዳቤ መጻፍ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59 ድንጋጌ መሠረት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ በማስረዳት ከሦስት ሰዓታት በላይ የፈጀ ክርክር አድርገዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ‹‹ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?›› የሚለውን መርምሮ ብይን ለመስጠት በዕለቱ ከሰዓት በኋላ ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም ቀኑ በመምሸቱ ለዛሬ የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ በእነ ፌቨን መዝገብ የተቀጠሩ ተጠርጣሪዎች ቀኑ በመምሸቱ በዕለቱ ጉዳያቸው ሳይታይ ቢቀርም መምህር ምሕረትአብ አሰፋና የካሜራ ባለሙያው አቶ ኪሩቤል አሰፋን ጨምሮ ምሽት ላይ ፖሊስ ከእስር እንደፈታቸው ታውቋል፡፡