Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአማርኛን የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ ለማድረግ እንደምትሠራ ኒጀራዊቷ የፊልም ባለሙያ ገለጸች

አማርኛን የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ ለማድረግ እንደምትሠራ ኒጀራዊቷ የፊልም ባለሙያ ገለጸች

ቀን:

በአበበ ፍቅር

አማርኛን የአፍሪካ ኅብረት ይፋዊ የሥራ ቋንቋ ለማድረግና በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ እየሠራች እንደሆነ ራማቶ ኪታ የተባለች ኒጀራዊት የፊልም ባለሙያ አስታወቀች፡፡

ለአማርኛ ቋንቋ ተቆርቋሪ የሆነችው ራማቱ ‹‹አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ እስኪሆን ጥረቴን አላቋርጥም፤›› ብላለች፡፡

እንደማሳያም ‹‹ዘ ዌዲንግ ሪንግ›› በሚል የጻፈችውንና እ.ኤ.አ. በ2016 የለቀቀችውን ‹‹የጋብቻ ቀለበቱ›› የተሰኘውን ረዥም የፍቅር ፊልሟን ርዕስ በፊልሙ መጀመርያና መጨረሻ ላይ በአማርኛ ቋንቋ እንዲጻፍ ማድረጓን ተናግራለች፡፡

‹‹ጅማሮው ለጥረቴ መሳካት በግል የማደርገው አንዱ አካል ነው›› ያለችው ራማቶ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ በመሳተፍ ለአማርኛ ቋንቋ መስፋፋት አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን ገልጻለች፡፡

ጅምሯ ይሳካ ዘንድ የረዥም ጊዜ ጥረት በማድረግ ላይ ያለችው የፊልም ዳይሬክተሯ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያሉ የተለያዩ ባለሥልጣናትን እንዳነጋገረችና እስካሁን ጥረቷን እንደቀጠለች ትናገራለች፡፡

አቶ መለስም በወቅቱ ‹ራማቶ ትክክል ነሽ፣ ነገር ግን ሰነዱ ውስጥ የለም ብለው እንደመለሱላት እሷም ‹‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሑፍን የምናዘጋጀው እኛ ነን›› ብላቸው እንደነበር አስታውሳለች፡፡

አፍሪካ ውስጥ በፓን አፍሪካ ፊልም ሥራዎች ፌዴሬሽን አባልነትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት በሚኖሩ ስብሰባዎችና በተለያዩ ቦታዎች በምንትቀሳቀስበት ሁሉ አማርኛን ይፋዊ የመግባቢያ ቋንቋቸው አድርገው እንዲጨምሩ ውትወታ እንደምታደርግ የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግራለች፡፡

 ‹‹የጋብቻ ቀለበቱ›› የተሰኘው ፊልሟን ስትሠራ እንደ ኃይሌ ገሪማ (ፕሮፌሰር) እና አቶ ሰለሞን በቀለ ከመሳሰሉ አንጋፋና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የፊልም ሰዎች ጋር በመነጋገር ፊልሟ ውስጥ እንደ መነሻ ሐሳብ በጽሑፍ ማስገባቷን ተናግራ፣ ወደፊት ተባባሪ ካገኘች የፊልሙን ሙሉ ታሪክ በአማርኛ ቋንቋ በማስተርጎም ለኢትዮጵያውያን እንደምታበረክት ተናግራለች፡፡

‹‹አማርኛን በአፍሪካ ብሎም በዓለም ደረጃ ማንበብና መጻፍን፣ መስማትና መግባባትን ለማስተዋወቅ የብዙዎችን ጥረትና የረዥም ጊዜ ሥራን የሚጠይቅ ነው›› ያለችው ራማቶ ይሁን እንጂ ሙያዋን ተጠቅማ በዓለም ዙሪያ በሚታዩ ሲኒማዎች በምትገኝበት ወቅት ለማስተዋወቅ እንደምትችል አብራርታለች፡፡

‹‹እኛ ቋንቋውን ለአንድ ብሔር ብቻ የተሰጠ አድርገንና የተሳሳተ ትርክትን በመውሰድ የምንጣላበትን አማርኛ ብዙ ርቀትን ተጉዛ በመምጣት ስለ አማርኛ ቋንቋ ዘብ በመቆም መታገሏ የሚበረታታ ተግባር ነው›› ያሉት ደግሞ መምህር ታዬ ቦጋለ ናቸው፡፡

አማርኛ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን በብዛት እንደሚነገር አንስተው፣ በቀጣይም ከራማቱ ጎን በመቆም ቋንቋውን የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹አማርኛ ቋንቋን በአፍሪካ ዘንድ ማስተዋወቅና በሥራ ላይ ማዋል ከአዕምሮአዊ የቅኝ ግዛት መላቀቅን የሚያመለክት ነው›› ያሉት ደግሞ ፍቅሬ ቶሎሳ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...