Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር

ሆድና የሆድ ነገር

ቀን:

(ክፍል ሦስት)

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

ሲበሉ አድርሰን…”…

ደሴ ከተማ ዳውዶ ከሚባለው ሠፈራችን፣ በልጅነት ዕድሜዬ አንድ ዕለት ረፋድ ላይ አያ ጅቦ ከች አለ፡፡ የሠፈሩ ሰውም ከምኔው ፍጥነት ከች፡፡ እጁ የገባለትን ነገር እየያዘ ድንጋዩን፣ ዱላውን፣ አንካሴውን፣ ማጭዱን፣ መጥረቢያውን…

“በለው! በለው! ድገመው!”…

“እንዳያመልጥ! ቅደመው!”…

“ውጋው! እንዳለቀው!”…

“በለው! በለው!”…

ሌሊቱን ሙሉ ደሴ ከተማን ነግሠውባት ሲያስሷትና የወዳደቀ ጥንባጥንቧን ሲያፀዱላት የሚያድሩት ጅቦች፣ ከጦሳ የገጠር አካባቢ ነው የሚመጡት፡፡ ጎህ ከመቅደዱ በፊት የጦሳ ተራራን በመውጣት ከማደሪያቸው ይወሸቃሉ…

ይሄ የነጋበት ጅብ፣ የጦሳ ተራራን አቅጣጫ ይዞ መንገድ ጀመረ (“የቀን ጅብ” አላልኩም ወደ ማደሪያው ሳይመለስ ነግቶበት እንጂ፣ በቀን የሚበላ ፍለጋ አልመጣምና)… ሆኖም አልቻለም፡፡ ልክ የለሹ ድብደባ አቅም አሳጣው… መጨረሻ ላይ “ግሜ ቅጠል” ከሚባል ቁጥቋጦ ውስጥ እንደማንም ብሎ ገባ፡፡ ሆኖም ከአንካሴው፣ ከመጥረቢያው፣ ከዱላው… ድብደባ ትንሽ ፋታ ቢያገኝም፣ ከድንጋዩ የድብደባ ናዳ ማምለጥ ግን አልቻለም… በመጨረሻም ሞተ… ሬሳውን ወደ ጎዳናው ጎትተው አወጡት (እየጎተቱት እያለ፣ በደረቅ ሌሊት ቤት በመስረቅ በሌብነት የሚታወቅ አንድ የሠፈራችን ሰውዬ የጅቡን አናት በአካፋ ደጋግሞ መታው በአካባቢው የነበሩት ሰዎች እስከ ሚገረሙ፣ ከእነ ተረቱ “የሞተ ጅብ ገዳይ” ይባላል፡፡ ምናልባትም አያ ጅቦ ሰውዬው “በሥምሪት” ላይ እያለ መስመር ላይ ተጋጭተው ይሆናል፡፡ አያ ጅቦስ በሰዎች የሥምሪት ሰዓት በመምጣቱ አይደል ለሞት የተዳረገው?)፡፡

ከዚያስ? አንዳንዶቹ ከምኔው ቢላዋ እንዳመጡ አላውቅም፣ የጅቡን የተለያዩ የአካል ክፍሎች ሽሚያ በመሰለ መንገድ መቆራረጥ፣ መበጣጠቅ ያዙ… “ሻንኮ” እያልን የምንጠራት ድመታችን ትዝ አለችኝ… እየሮጥኩ ወደ ቤቴ፡፡ ቢላዋ ይዤ ተመለስኩ… ከወደ ታፋው አካባቢ ቆርጬ ወደ ቤቴ እየሮጥኩ ሄድኩኝ ሻንኮን ላስደስታት…

ሻንኮን ጠራኋት፡፡ እየሮጠች መጣች፡፡ ሥጋውን እጄ ላይ ስታይ በድመት “ስታይል” ፈነደቀች፣ ዘላ ለመንጠቅ ሁሉ ሞከረች፡፡ ቶሎ ብዬ ጣል አደረኩላት… በልጅነቴ ተዓምር አየሁ፡፡ ሻንኮ የጅቡን ሥጋ አሽትታው ተመለሰች፡፡ ብለምናት፣ ባባብላት ልትበላው ቀርቶ ልትነካው አልሞከረችም…

የጅቡ ሥጋ ትንሽ ይቆየንና አሁን መግቢያው ላይ ስላለው ምሳሌያዊ አባባል (“ሲበሉ አድርሰን…” ስለሚለው) ትንሽ እንነጋገር…

“ሲበሉ አድርሰን…” የሚለው ብሂል (ፀሎት)፣ ለራስ መልካም መመኘት ነውና ክፋት የለውም፡፡ ምናልባት አባባሉ (ፀሎቱ) ትዝብት ላይ ሊወድቅ የሚችለው፣ “ሲበሉ አድረሰን” እንደተባለው ሁሉ፣ “ስንበላ አድርሳቸው” የሚል ቀርቶ፣ “ሲበሉ አድርሳቸው” የሚል አነጋገር የሌለ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ ወይም ደግሞ፣ መልካም ምኞትን የሚጠላ የለምና “ሲስቁ አድርሰን፣ ሲጫወቱ አድርሰን፣ ሰላም ሆነው አድርሰን” መሰል አባባል እንኳን ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ ግን የለም፣ ወይም ቢኖርም እንኳን፣ ሲበሉ ለመድረስ ካለ የሆድ ፍቅር የመነጨውን ፀሎት ያህል የገነነ አይደለም፡፡ የሆድ ነገር ሆድን ስለሚቆርጥ ይሆን፣ “ሲበሉ አድርሰን…” ይህን ያህል የገነነው?

 “ሲበሉ አድርሰን…” ትልቅ ቦታ ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ከልክ በላይ ሆድ ተኮር መሆኑን በውል የምንረዳው፣ ከአባባሉ ተቆርጦ የቀረውን አሟልተን ስናየው ነው፡፡ “ሲበሉ አድርሰን፣ ሲሠሩ መልሰን” የሚለውን፡፡ አባባሉ የሆድን አጀንዳ በግምባር ቀደምትነት በማራመድ፣ ሌሎች ሰዎች ለራሳቸው ያዘጋጁትን ምግብ ተጋርቶ የመብላት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ምግቡ ካልተገኘ ሰዎቹን በሥራ ለመርዳት ቅንጣት ታህል ዝግጁነት የሌለ መሆኑን  የሚያሳይ ጭምር ነው፡፡

ምሳሌያዊ አነጋገሩ (“ሲበሉ አድርሰን፣ ሲሠሩ መልሰን”) ሁለት ተቃራኒ ፀሎቶችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ ለራስ ሆድ የምግብን ፀጋ የመፈለግን፣ ለሌሎች ደግሞ ጉልበት የመንፈግን፡፡ አንድ ሰው ሁለቱም ፀሎቶች ከከሸፉበት ምን ያደርጋል? የመጀመርያው ማለትም ሆድ የመሙላት ፀሎቱ በመክሸፉ ሲበሉ አልደረሰም፡፡ ሁለተኛውም ማለትም እየበሉ ካልሆነ ከመንገድ የየመለስ ፀሎቱ ስለከሸፈ አልተመለሰም፣ ይልቁንም ወደ ሰዎቹ ቤት ሄዷል፡፡ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ያለው አማራጭ የግዱን እየለገመም ቢሆን በሥራ ማገዝ ነው (“ሲሮጥ የመጣን አህያ አጥብቀህ ጫነው” የሚለው አነጋገር ትዝ ሊለውም ይችላል)፡፡

ደስ የሚለው ታዲያ ለዚህ ዓይነቱ፣ ሆድን ቁጥር አንድ አድርጎ “ለተሠለፈ” እና ሁለቱም ፀሎቶቹ ለከሸፉበት ሰው የሚያገለግል ሌላ የማስተዛዘኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ያለ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ የሚል፣ “ልፋ ያለው ተበቅቶ፣ ብላ ያለው ተፈትፍቶ”፡፡ (“ተበቅቶ” ማለት “እህሉ በእጅ (ባህላዊ ወፍጮ) ገና ሊፈጭ እንደተዘጋጀ” ማለት ነው)፡፡

እርግጥ ነው ይህ አባባል (“ልፋ ያለው ተበቅቶ፣ ብላ ያለው ተፈትፍቶ” የሚለው) ለሁለቱም አጋጣሚዎች የሚያገለግል ነው፡፡ ሲሠሩም ሆነ ሲበሉ ለደረሰ ሰው፡፡ የየዓውዱን ትርጓሜ በመያዝ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ከፍ ሲል ካየነው የሆድ ፀሎት ውስጥ  “ሲበሉ አድርሰን” ሲሰምር፣ ተረትና ምሳሌው እንዳለ ይነገርና “ብላ ያለው ተፈትፍቶ” የሚለውን ትርጓሜ በመያዝ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ዓውዱ የሚሰጠው ትርጓሜ እሱን ነውና፡፡ “ሲሠሩ መልሰን” የሚለው ፀሎተ ስንፍና ወይም ንፍግና ከከሸፈ “ልፋ ያለው ተበቅቶ፣ ብላ ያለው ተፈትፍቶ” ተብሎ ይነገራል፡፡ የሚፈለገው ዓውዳዊ ትርጓሜ ግን “ልፋ ያለው ተበቅቶ” የሚለውን ይሆናል፡፡ 

ያለ ምንም ጥርጥር ሁለቱም ብሂሎች፣ ስለሥራ አሉታዊ አስተሳሰብን የሚያሰርፁ ናቸው፡፡ ሆኖም ሁለቱን በንፅፅር ስናይ፣ “…ሲሠሩ መልሰን” ከሚለው ይልቅ “ልፋ ያለው ተበቅቶ…” የአሉታዊነት ደረጃው ቀለል ይላል፡፡ አንደኛ፣ የመጀመርያው በፀሎት ነው የተገለጸው፡፡ በፀሎት (አምላካዊ ተማፅኖ ላይ ተመሥርተው) የሚገለጹ ጉዳዮች ለየት ያለ ትኩረትና አፅንኦት ያገኙ ናቸው፡፡ ሁለተኛ፣ ግን በፀሎት ስላልቀረበ፣ አፅንኦቱ የመጀመርያውን ያህል አይደለም፡፡ ሁለተኛ የመጀመርያው የተነገረው በራሱ በባለቤቱ (በምግብ ፈላጊው) ነው፡፡ ያልጠሩት እንግዳ ሆኖ ምግብ ለማግኘትም ሆነ ከሥራ ለመሸሽ የፀለየው ራሱ ሰውዬው ነው፡፡ ሁለተኛው ግን በማንኛውም ሰው፣ ምናልባት በታዛቢ የተነገረ ከመሆኑም በላይ፣ “ከታሪኩ” ላይ ያለው ሰው የምግብ ፍላጎት ኖሮት ወደ ሰው ቤት ስለመሄዱ የተገለጸ/የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሦስተኛ፣ የመጀርሪያው ሲሠሩ ማየትም አይፈልግም፡፡ ፀሎቱ ሥራ ላይ ከሆኑ፣ ከቤታቸው ከመድረሱ በፊት ከመንገድ የመመለስን ፅኑ ፍላጎት የያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ቢያንስ ከቦታው ተገኝቷል፡፡ አራተኛ፣ የመጀመርያው ሲበሉ ቢደርስ ኖሮ አብሯቸው ይበላ የነበረውን ሰዎች፣ በሚሠሩበት ሰዓት ደርሶ በይሉኝታም ቢሆን ለማገዝ ዕድሉ የለውም፡፡ ፀሎቱ ሥራ ላይ ከሆኑ በእነሱ አካባቢ ዝር እንዳያደርገው ነውና፡፡ ሁለተኛው ላይ ያለው ሰው ግን፣ በሌላ ጊዜ ሲበሉ ቢደርስ ኖሮ (ተፈተፈተም አልተፈተፈተ) አብሯቸው ይበላ የነበሩትን ሰዎች፣ ሲሠሩ በመድረሱ በበጎ ፈቃድም ይሁን በይሉኝታ በሥራ (በመፍጨትም ባይሆን) የሚያግዝበት ሰፊ ዕደል አለው፣ “ተበቅቶ” ደርሷልና፡፡

አስገራሚው ነገር፣ የመጀመርያው ምሳሌያዊ አነጋገር በራሱ “በታሪኩ ባለቤት”፣ ለዚያውም በፀሎት ተጠናክሮ የቀረበ ሆኖ እያለ፣ አሉታዊነቱም የከፋ የመሆኑ ጉዳይ ነው…. የሥራ ፍቅር የት ነው ያለው? (“የዓመት ረፍት ወስጄ ትንሽ ልተኛ” የሚሉ አንዳንድ የእኔ ብጤ መንግሥት ሠራተኞች ትዝ አሉኝ፡፡ “ትዝ አትበለኝ” አይባል ነገር!)…

ለጉዳዩ ያለን ዕይታ ከዚህ በላይ ትንሽ ጥልቀት ይጨምር ዘንድ፣ እስቲ ነገሩን ገልብጠን እንየው… “ሲበሉ አድርሰን፣ ሲሠሩ መልሰን” ባዩ፣ በተለይ የመጀመርያው ፀሎቱ (ማለትም “ሲበሉ አድርሰን” የሚለው) ደግሞ ደጋግሞ ቢሰምርለት የሚፈጠረው ነገር ምንድነው? በሌላ አነጋገር አንድ ሰው ፀለየም አልፀለየ፣ ሰዎች ቤት በሄደ ቁጥር ተደጋጋሚ በሆነ መንገድ ምግብ ሲበሉ ቢደርስ፣ የሐበሻ ባህል እንዴት ነው የሚያስተናግደው? በአድናቆት ወይስ በውግዘት? “እሱ’ኮ የጅብ አፍንጫ ይዟል” ተብሎ በአበሉት ወይም በታዘቡት ሰዎች ይወራበታል፣ ውግዘት መሆኑ ነው፡፡

“የጅብ አፍንጫ ይዟል” ትርክት ምግብ ከሚሰጠው ክፍል (ከሚያበላው) አንፃር (“አንግል”) የተነገረ የመሆኑም ጉዳይ ሹክ የሚለን ሚስጥር አለ፡፡ ከሰው ቤት ሄዶ የመብላት ፍላጎት ያለው ሰው፣ ፍላጎቱን የገለጸው በፀሎት ነው፣ በጨዋ አቀራረብ፡፡ ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ቤት በተከታታይ ሲበላ (ሲቀናው) “የታዘቡት” ግን፣ ፀሎቱን ቢያውቁም ባያውቁም፣ ከሰው ቤት ምግብ የማግኘቱን ጉዳይ የፀሎቱ መሳካት ወይም የዕድለኝነት ጉዳይ አድርገው አይዙለትም፡፡ ወይም “ልፋ ያለው ተበቅቶ፣ ብላ ያለው ተፈትፍቶ” ብለው ብቻ ሊያልፉት አይፈለጉም፡፡ ዝም ብለውም አይተውትም፡፡ ይልቁንም፣ “እሱ የጅብ አፍንጫ ይዟል” በማለት፣ ከአጉል እምነት (Superstition) ጋር አያይዘውለት ዕርፍ ነው! እንዴት በእያንዳንዳቸው ይሆን?…

ወደ እነዚያ የጅቡን አካል ሲቆራርጡ ወደ ነበሩት የመንደሬ ሰዎች ታሪክ እንመለስ… በወቅቱ የሰው ዝርያ ከሆኑት ከወገኖቼ ዓላማ ይልቅ፣ የሻንኮ የእንስሳዋ መልዕክት ለእ’ኔ ግልጽ ነበር፡፡ ሻንኮ የጅቡን ሥጋ “አልነካም” ብላ ስትተወው፣ “የዝርያዬን ሥጋ አልበላም” ማለቷ እንደሆነ ወዲያው ነበር የገባኝ፡፡ የጅቡን ሥጋ በመቁረጥ የተሻማኋቸው የሠፈሬ ሰዎች ዓላማ የገባኝ ግን በጣም ዘግይቶ፣ ትልቅ ከሆንኩ በኋላ ነበር፡፡ ለካስ ለድመታቸው ወይም ለውሻቸው አልነበረም የጅቡን አካል በመሻማት እየቆራረጡ የወሰዱት፡፡ የጅብን የአፍንጫ፣ የጆሮ፣ የሸሆና… ቁራጭ መያዝ “ሲሳይ ያመጣል ወይም ያስገኛል” የሚል አጉል ዕምነት (Superstition) ስላላቸው ነው፡፡

ለራሱ ሲሳይ ፍለጋ ከጦሳ ደሴ ከተማ ድረስ በመምጣት የሚንከራተት፣ ሲነጋበት ደግሞ በእነሱው እጅ ተቀጥቅጦ የሚገደል፣ በሸተተና ከዚያም በደረቀ ብጣቂ ቁርበቱ ለእነሱ ሲሳይ ሊያመጣላቸው? አይ ሞኛሞኝነት! ካመጣስ ከየት ነው የሚያመጣላቸው ከሰው ሰርቆ? ወይስ ነጥቆ? ወይስ ሰልቦ?… የደረቀ የጅብ የአፍንጫ ቁራጭ፣ ቁርበት፣ ሸሆና… በቁራጭ ጨርቅ ጠቅልለው በኪሳቸው ይዘው ወይም በክንዳቸው ላይ አስረው፣ “ሲበሉ አድርሰን፣ ሲሠሩ መልሰን”ን እያቀነቀኑ፣ ከሥራ ፍቅር “ተፋተው”፣ በቂላቂልነት ሕይወታቸውን የሚገፉ ሰዎችን በዓይነ ህሊናችሁ ተመልከቱ…

ጣሊያን ከወጋንና ከወጋነው በላይ ወይም ከዚያ ባልተናነሰ፣ የወጉንና እየወጉን ያሉ የዕድገታችንና የልማታችን ፀር የሆኑ ብዙ ጉዶች ከውስጣችን አሉ፡፡ ከመሰል ጉዶች መላቀቃችንን ማረጋገጥ ግድ ነው፡፡ ኋላቀርነት ስላወገዙትና ስለሰደቡት ብቻ ወደኋላ አይቀርም፡፡ ከመሰል ጉዶች ተላቀን በሥራ ካላሸነፍነው በስተቀር፣ ከፊታችን እየቀደመ እኛን ኋላ ቀር ከማድረግ አይመለስም…

(በክፍል አራት እንገናኝ)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...