የኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1970ዎቹ ካስተላለፋቸው ተከታታይ የልብ ወለድ ትረካዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ልብ ወለዱ ልብ አንጠልጣይና ተወዳጅ በመሆኑ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል፡፡
በመጻሕፍት ዓለም ሳምንታዊ ፕሮግራም በወጋየሁ ንጋቱ ይተረክ የነበረው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› በሐዲስ ዓለማየሁ የተደረሰው ልብ ወለድ ሲሆን፣ ሰብለ ወንጌልና በዛብህ የሚባሉ የሁለት ገፀ ባህርያትን ፍቅር በስፋት ይተርካል፡፡ ልብ ወለዱ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጪ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ቀርቧል፡፡
የወጋየሁ ንጋቱ የአተራረክ ሥልት የተዋጣለት ስለነበር የብዙ ሰዎች ጆሮ ላይ በቀላሉ ሊገባ ችሏል፡፡
በሬዲዮ ይቀርብ የነበረው፣ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› በአሁኑ ወቅት በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለተመልካቾች ለማቅረብ ብሔራዊ ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) ‹ሰው መሆን ፊልም ፕሮዳክሽን› የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የሥራ ውል ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱም የመጽሐፉን ታሪካዊ ይዘት በጠበቀ መልኩ ወደ ቴሌቪዥን ድራማ ለመቀየርና ለተመልካች ለማቅረብ ያለመ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ኢቢሲ ወደ ፊልም/ድራማ የመቀየር መብት ባለቤት የሆነለትን የፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድን፣ ሰው መሆን ፊልም /ፕሮዳክሽን ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በመቀየር በአራት ምዕራፍ በ48 ክፍሎች ፕሮዳክሽን ሠርቶ እንዲያቀርብለት ተስማምቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍሥሐ ይታገሱ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ በሐዲስ ዓለማየሁ የተደረሰውና ዘመን ተሻጋሪው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የልብ ወለድ መጽሐፍ በዘመኑ የነበሩትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ገጽታዎች በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
በወቅቱም የነበረው የማኅበረሰቡን አኗኗር፣ ወግና ባህል ከማሳወቁም በላይ፣ በጊዜው የነበረውን ሥርዓት በጥልቀት የሚፈትሽ እንዲሁም ተራማጅ ዕሳቤዎችን የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
መጽሐፉም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሬዲዮ በታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰው ወጋየሁ ንጋቱ ተተርኮ፣ በብዙ ኢትዮጵያውያን ጆሮና ልብ ውስጥ መድረስ መቻሉን ገልጸው፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ኢቢሲ ድንቅ መጽሐፉን በድምፅ ከመተረክ ባሻገር፣ የሕዝቡን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ስምምነቱን መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
የሰው መሆን ይስማው ፊልም ፕሮዳክሸን ዳይሬክተር ሰው መሆን ይስማው (ሶሚክ) በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ድንቅ መጽሐፍ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በቴሌቪዥን ድራማ ፕሮዳክሽን ለማዘጋጀት ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡
መጽሐፍ ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ሲቀየርም የዚህ ዘመን ትውልድ፣ ካለፈው ትውልድ በማገናኘት ትምህርት የሚቀስምበትን ዕድል ይዞ መምጣቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
በቴሌቪዥን የሚቀርበው ድራማው በአማካይ 45 ደቂቃ ርዝማኔ ሲኖረው፣ ለእያንዳንዱ የድራማ ክፍል (ኢፒሶድ) ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ 863,075 ብር ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ የድራማውን የመጀመርያ ምዕራፍ ማለትም ከክፍል አንድ እስከ አሥራ ሁለት ድረስ የተጠናቀቁ ሥራዎችን፣ እንዲሁም በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ (48 ክፍሎች) አጠናቆ ለማስረከብ ስምምነት ላይ መደረሱ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
በስምምነቱ መሠረትም መጽሐፉ ታሪካዊ ይዘት ያለው እንደመሆኑ መጠን ወደ ተከታታይ ቴሌቪዥን ድራማ እንዲለወጥ በማድረግ የዋናውን መጽሐፍ ታሪከ በማያፋልስና በማይበርዝ መልኩ እንደሚከናወን ተናግሯል፡፡
‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ለመጀመርያ ጊዜ የታተመው ከ57 ዓመታት በፊት በ1958 ዓ.ም. ሲሆን፣ በወቅቱ የመጽሐፉ የሽፋን ዋጋ 2.45 ብር ብቻ ነበር፡፡ መጽሐፉም በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለአማርኛ ትምህርት ማጣቀሻ አገልግሎት ላይ ይውል ስለነበር ለረዥም ዓመታት በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት በዚህ ዋጋ እየታተመ ለቤተ መጻሕፍትና ለትምህርት ቤቶች ሲከፋፈል ቆይቷል፡፡