Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምን ያስፈራናል?

ከሜክሲኮ ወደ ካዛንቺስ ጉዞ ሊጀመር ነው። ኑሮ እንደ ትናንቱ ናት። ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ነዋሪዎች ወደ ጉዳያቸው ይጣደፋሉ። አዲስ የመንፈስ ፀዳል የሚያጎናፅፈው ማለዳ የተለማጅነት ፀባይ ያመጣ ይመስላል። የዛሬዋ ፀሐይ በመውጣቷ ማንም ቁብ አይሰጠውም። ሁሉም የትናንት ውጥኑ ላይ ካስማውን የተከለ ይመስላል። አዲስ አበባ በፍቅርና በጥላቻ፣ በውሸትና በእውነት፣ በመኖርና ባለመኖር መሀል የተዘጋጀች ግጥም መስላለች። ጨለማ አጥልቶበት ባደረው አውራ ጎዳና ላይ የትናንት ዱካዎች እንጂ አዳዲስ ፈላጊዎች የሉም። እያንዳንዱ ሰው ለመኖር የሚያስገድደውን ኃይል ሳያውቀው ዓላማዬ ብሎ ለሚኖርለት ነገር ሊተናነቅ እነሆ ነግቷል። የጎዳናው መንፈስ ትርምስ ይባላል። መንገድ ከሰው ልጆች ህላዌ ይህን ይቀምራል። ይህም ለልመና በተዘረጉ እጆች በኩል ጎልቶ ይታያል። ለማለቅ የሚጣደፉቱ ደግሞ በእርጅና አዙሪት ውስጥ ይርመሰመሳሉ። ጅምሮቹና ለጋዎቹ ግን በትኩስነት ኃይል ውስጥ ገና ፅንስ ናቸው። ትኩሳት ይሉታል ይህን የዕድሜ ፌርማታ። በትኩስነት ውስጥ ሁሉም ነገር በግልጽና በቀላሉ ሊነበብ ይችላል። አዎ የትናንት ዱካዎችን ሽረው አዲስ የተረከዝ ማኅተም አስቀምጦ ለማለፍ፣ በትውልድ ሰንሰለት ውስጥ ውር ውር የሚሉ ወጣቶች ጎዳናው ላይ በርከት ያሉ ናቸው። እዚህ ያደረሰን መንገድ ነገ ደግሞ በእነዚህ አፍላዎች ትከሻ አሳፍሮን የት እንደሚያደርሰን ማን ያውቃል? አሮጌን አዲስ መተካቱ የግድ ነውና!

የታክሲ ሠልፍ ቦታ በሳቅና በተረብ አሸብርቋል። ቀርበው ሲያዩት ግን የምሬት ጎርፍ ነው። ‹‹እውነትም እየሰነበተ ሲሄድ የማይለመድ ነገር የለም …›› ትላለች አንዲት ልጅ እግር ቆንጆ። ‹‹ችግር ወዳጅ ሲሆን የታየባት በአፍሪካ ብሎም በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ኢትዮጵያ መሆኗ ነው። አቤት ለክፉውም ለደጉም አንደኝነት ስንወድ?›› ይላል አንዱ ከኋላ። እንቅልፍ ያልጠገበ ዓይኑን እንዳይሆን አድርጎ እያሻሸ። ‹‹አሁንማ ቅሬታ ብናሰማም የሚሰጠንን መልስ በህልማቸን ስለፈታነው ተናገርን አልተናገርን ምንም ለውጥ አይኖረውም…›› ይላል አንድ ረዘም ያለ ጎልማሳ ዙሪያውን እየቃኘ። ‹‹ሚዲያዎቻችን ላይ ሐሳብን በነፃነት ከማንሸራሸር ይልቅ እዚህ የሠልፍ ሥነ ሥርዓት ላይ መናገር ተሽሎ አረፈው …›› እያለ ከኋላ አንድ ወጣት ለወዳጁ የፕሬስ ነፃነት መኮላሸትን ያማል። ጎልማሳው በበኩሉ የጀመረውን ለመጨረስ ይወራጫል። ‹‹… ለምሳሌ ‘የታክሲ ችግር እንዲህ የተባባሰው ለምንድነው? ብለን መንግሥትን ብንጠይቅ ከዚህ በፊት ታክሲ የማይጠቀመው የኅብረተሰብ ክፍል ታክሲ ተጠቃሚ መሆን በመጀመሩ ነው። ይህም የኢኮኖሚ ዕድገታችን ምን ያህል በትክክለኛ መስመር እየተጓዘ መሆኑን ያሳያል ብሎ እንደሚመልስልን እናውቃለን …›› ብሎ ትንሽ የምፀት ፈገግ ካለ በኋላ፣ ‹‹ይኼ እኮ ማለት ሐኪም ጋ ሄደን ሐኪም ሆይ አመመኝ ብለን ስንነግረው፣ ከዚህ በፊት ጤነኛ ስለነበርክ ነው የሚል ምላሽ መስጠት ማለት እኮ ነው …›› እያለ ዙሪያውን እውነት ነው ብለው የሚወግኑለት ሰዎችን ይፈልግ ጀመር። ፖለቲካ ያለ ውሸት፣ ሥጋ ያለ ነፍስ ማለት መሆኑ አንዳንዶቻችን የሚገባን አንመስልም፡፡ ወዲያው ‹እውነት ተረጋግቶ ሲቆም ውሸት ግን ይጣደፋል›› የሚል የታክሲ ጥቅስ ትዝ አለን። እህም ያሰኛል!

 አሁን መሳፈር ጀመርን። የተሳፋሪ ብዛት እየጨመረ መሄዱን ላስተዋለ ከመጓጓዝ ውጪ ጊዜ ተርፎ ሥራ መሠራቱን ይጠራጠራል። መጠራጠር ሳይሆን ያምናል ቢባል ይቀል ይሆን? ‹‹ረገጥከኝ እኮ ቀስብለህ አታልፍም እንዴ?›› ያምባርቃል አንድ ጎልማሳ። ‹‹ይቅርታ!›› ይላል የጎልማሳው ግልምጫና ቁጣ ያስደነገጠው ወጣት። ጎልማሳው፣ ‹‹ጫማዬን አስጠርጌ ያበላሽብኛል? ምን ያደናብረዋል?›› ሲል ይቀጥላል። ወጣቱ መልስ አይሰጥም። ፈገግ ብሎ እያየው በዓይኖቹ ይቀልድበታል። ታክሲዋ ሞልታለች። ድፍን የታክሲው ተሳፋሪዎች ‹ታላቅን ማክበር› የሚባለው የማኅበረሰብ እሴት መፈራረሱን እየታዘበ ራሱን በአሉታ ይወዘውዛል። ‹‹ይኼም ኑሮ ተብሎ በማንም ጎረምሳ እየተንጓጠጥን ልንኖር? ኧረ አምላኬ እባክህ በጊዜ ሰብስበኝ?›› ይላሉ የጎልማሳው እንዲያ መሆን ያንገፈገፋቸው አንዲት አዛውንት። ‹‹ታላቅና ታናሽ ያለው ሥጋ ቤት ብቻ ነው ሲል ያደገ ትውልድ፣ እሱን ለሚመቸውና ለሚጠቅመው ወገን ብቻ በማይረባ መማለጃ ስለሚገዛ ምን እንጠብቅ ታዲያ?›› ይላል ጎልማሳው አዛውንቷን አተኩሮ እያስተዋለ። በአዎንታ ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ ‹‹እሱስ እውነት ነው፣ በእኛ ጊዜ ሰው ቀና ብለን እናይ መሰለህ? ዛሬ የሚያውቁትንም የማያውቁትንም ይዘው እኛን ካልሰማችሁ፣ እኛ ካላስተማርናችሁ ሲሉን ይውላሉ። ፈረንጅ ሊጠቀምበት በሠራው ቴክኖሎጂ ሥራ ሲፈቱ እየዋሉ እንዲህ ካሉን፣ ነገ አንድ የረባ ነገር ቢሠሩ ማንን ያስቀምጣሉ ብለህ ነው? ቀደም ቀደም ማለት የዕውቀት መለያ መስሏቸዋል …›› እያሉ አዛውንቷ ሌሎች ነገሮችን ጭምር እያጣቀሱ ብዙ ተናገሩ። ‹‹እኔምለው እንዲህ ዓይን አውጣነት የበዛው በፎርጅድ ዲግሪ ተመራቂው ስለበዛ ነው እንዴ?›› ሲል ከፊት የቀመጠ ጎልማሳ አጠገቡ ያለችን ተሳፋሪ ቢጠይቃት፣ ‹‹ማለት?›› ብላ መልሳ ጠየቀችው። ‹‹ማለትማ ከሰውነት ደረጃ የወረደ የአስተሳሰብ ዝቅጠት በዛ ለማለት ነው …›› ብሏት ለመሳቅ ቃጣ። ወዲያው ግን ሳቁ በመኮሳተር ተተካ፡፡ ወቸ ጉድ!

ታክሲያችን መጣደፏን ከጀመረች ቆየት አለች። ሾፌራችን በእርጋታ ነው የሚያሽከረክራት። ለስላሳ የክራር ሙዚቃ ከወደ ‘ስፒከሩ’ እየተሰማ አንጀት ያላውሳል። የአንዳንዱ ቀልብ ጭልጥ ብሏል፡፡ ‹‹የትዝታ ኑሮ ማብቂያ ፌርማታው የት ይሆን?›› ይላል ከወደኋላ መቀመጫ በስተግራ የተቀመጠ ወጣት። በስተቀኝ ያለችው ደግሞ፣ ‹‹ወደፊት እየተጓዙ የኑሮን ንረት ባሰቡ ቁጥር ትናንትን እንደ መናፈቅ የመሰለ ሕመም አለ ብዬ አላምንም …›› ትላለች አንገቷን ደፋ አድርጋ። የቁጭት ይመስልባት ነበር። ምንጩ ብዙ የሆነ ቁጭት። ‹‹ወራጅ አለ!›› አለ ትውልዱን ያስነቀፈው ጎረምሳ። ወያላው ፈጥኖ ታክሲዋን አስቁሞ ሸኘው። ሲወርድ በትንሹም ቢሆን ኃፍረት ድሯን አድርታበት አየነው። ‹‹ሳበው!›› ብሎ ወያላው መንቀሳቀስ ልንጀምር ስንል ሦስት ወጣቶች ‹‹ታክሲ!›› ብለው ጮኹ። ወያላው ሳይግደረደር ትርፍ ለመጫን እየቋመጠ ኑ አላቸው፣ መጡ። ‹‹ጠጋ … ጠጋ … በሉላቸው። አንተ እዚህ ጋ ወሸቅ በል …›› እያለ ቦታ መስጠት ጀመረ። ‹‹አልጠጋም!›› አለ አንድ የተማረረ ድምፅ። ወያላው ተንጠራርቶ አየው። ‹‹ማን ስለሆንክ ነው የማትጠጋው?›› አለው ንዴት እንደ ትኩሳት ደም ሥሩን እየገታተረው። ‹‹አልጠጋም …›› ባዩ ተሳፋሪ ሳቅ ብሎ፣ ‹‹ለመጠጋትና ላለመጠጋት ማንነት መጠየቅ ተጀመረ?›› አለ። ወያላው፣ ‹‹ተጠጋ እባክህ ጊዜ አትግደል። እንኳን አንተ ላይ ያሉትም እየተጠጋጉ አይደል፣ ጠጋ በልላቸው…›› አለ ፈርጠም ብሎ። አልጠጋም ባዩ ተሳፋሪ ለሰዎቹ ሲል ለመሸነፍ ወሰነ። አንዱ ነገር አራጋቢ ግን የወያላውን አቃቂር ተከትሎ፣ ‹‹ከላይ ያሉትማ በየቀኑ አጀንዳ እየፈጠረ ሕይወታችንን እንደ ካርታ ይፐውዙታል …›› እያለ ይሳሳቃል። ወግቶ ይማር መሆኑ ነው!

ብሔራዊ ቴአትርን ስናልፍ ዛሬ በስመ ሕንፃ ከቆሙ ሳጥን መሰል ግንባታዎች ይልቅ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተሠሩ የግድግዳ ግርፎችን እያደነቅን፣ በብዙኃኑ መጠቀሚያ ፍልውኃ በኩል ስናልፍ መልክ የሌለውና ውሉ የጠፋው የቤትና የውኃ ችግር ውልብ እያለብን፣ በታላቁ ቤተ መንግሥት ደጃፍ ስንደርስ ደግሞ ባለሥልጣኖቻችንን በሕዝብ ለሕዝብ ተወክለው እንደሚያገለግሉ ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ እያዳመጡ ራሳቸውን እንደሚያገለግሉ ኃያላን ቆጥረን እንደ ደጀ ሰላም በራፍ ለመሳለም እየቃጣን ተጓዝን። ይህ ሁሉ በሐሳብ መንሸራሸር ውስጥ የተገለጠ ሳይሆን፣ በአንድ አገር ውስጥ በምንኖር የጋራ ችግር ተቋዳሽ ሕዝቦች መንፈስ ውስጥ የተገለጠ እውነት ሆኖ ለማንም የሚታይ ነበር። ለማንም የሚታይ፡፡ ከመጻሕፍቱ መንደር ያሳፈርናቸው ወጣቶች በእጆቻቸው በያዙዋቸው ሦስት የተለያዩ መጻሕፍት ዙሪያ ማራኪ ጨዋታ ጀምረዋል። የማንበብ ጥማቱን የእንጀራ ጉዳይ አላዳርስ ብሎ እንዳያረካ የተከለከለው በቅናት አስተያየት ሲያያቸው፣ እስከ እነ መፈጠሩም ባህሉ የሌለው አብዛኛው ተሳፋሪ ግን በቁንፅል ሐሳቦች የራሱን ጨዋታ ጀመረ። ምን ያድርግ ታዲያ!

‹‹አንተ ወንድሜ …›› ይለዋል ጎልማሳው አጠገቡ የተቀመጠውን ተሳፋሪ። ‹‹… ለማንበብ እኮ ብዙ ነገር ያስፈልጋል። ለምሳሌ ቢቻል የግል ቤት፣ ጭቅጭቅ የሌለበት ትዳር፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ጥሩ ደመወዝ …›› እያለ ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹አንተ እሱን ትላለህ፣ ሁሉም ነገር በገንዘብና በብሔር እንጂ በዕውቀትና በቀና መንገድ በማይፈጸምበት አገር ለምን ብለን እናነባለን? ዋነው ነገር እንዴትም ብሎ ቆጥሮ ወይም ተቋጥሮ መገኘት ነው …›› ይለዋል አጠገቡ የተቀመጠው። በቀኝ በኩል ያሉት አዛውንቷና ወጣቷ ተሳፋሪ ደግሞ የሚከተለውን ሲባባሉ ነበር። አዛውንቷ፣ ‹‹አንቺ ልጅ …›› ወጣቷ፣ ‹‹አቤቴ እማማ?›› ስትላቸው ድምፃቸውን ቀስ አድርገው፣ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከሽፋለች ብለው የጻፉትን ሰውዬ መጽሐፍ አንብበሽዋል?›› ማለት፡፡ ወጣቷ ደግሞ፣ ‹‹አዎ!›› አለች ጥያቄያቸው እያስገረማት። ‹‹እውነት ነው?›› ሲሏት፣ ‹‹በአብዛኛው እውነት ነው …›› ብላ መለሰች። ‹‹ታዲያ ምኑን ኖርነው?›› ብለው እንደ መተከዝ አሉ። ይኼኔ ታክሲዋ ቆማ ነበርና ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› አለ። ሁሉም ተሳፋሪዎች ከወረዱ በኋላ ያ ወጣት፣ ‹‹ምን ጻፍ ጻፍ እንዳለኝ ልንገራችሁ?›› አለ እየሳቀ፣ ‹‹ሰውን እንዴት እንዴት እያደረገው እንደሆነ መጻፍ አማረኝ፡፡ ሁሉም ቦታ የምትሰማው አንድ ዓይነት ነገር ብቻ ነው …›› ብሎ መንገዱን ቀጠለ። ከኋላው ይከተለው የነበረ አንድ ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹ሰው ምነው እንዲህ መዳፈር አበዛ? ለነገሩ ምንም የሌለው ምንም አይፈራም አይደል የሚባለው?›› ሁሉም ወደ ጉዳያቸው እያመሩ ነበር። ግን ምንም ከሌለን ምን ያስፈራናል? መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት