- ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም። ልታወሪኝ የፈለግሽው ነገር ያለ ይመስላል?
- አዎ። እንዲያው ነገሩ ግርም ቢለኝ ልጠይቅዎ አስቤ ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ምንድነው?
- ሰሞኑን አባቶችን አስማምታችሁ አልነበርም እንዴ?
- ልክ ነው። ቤተ መንግሥት ጠርተን እንዲወያዩ አድርገን አስማምተናቸዋል።
- እንዲያውም የጠፉትን በጎች ይዘን መጥተናል ብላችሁ ስትወስዷቸው በቴሌቪዥን ሁሉ ተላልፎ ነበር።
- ልክ ነው።
- ታዲያ ለምን ተመልሰው ወጡ።
- ወጡ ማለት?
- ስምምነቱን አፈረሱት።
- አያደርጉትም?
- አድርገውታል። እንዲያውም መግለጫ ሁሉ ሰጥተዋል።
- ቤተ መንግሥት ድረስ ጠርተን አስማምተናቸው? አያደርጉትም!
- የቤተ መንግሥቱ ካልሆነ ሌላ ቦታ ውሰዷቸው?
- የት?
- ፕሪቶሪያ!
[ፓርቲው ያፀደቃቸውን አገር አሻጋሪ መርሆች እንዲያሰርጹ ሁሉም የፓርቲው አባላት በታዘዙት መሠረት ክቡር ሚኒስትሩ ከቤታቸው ቢጀምሩም ባለቤታቸው የዋዛ ሆነው አልተገኙም]
- የፓርቲያችን መርሆች እንደ አገር ለማሳካት ለምንፈልጋቸው ትልሞችና ለጀመርነው የለውጥ ሒደቶች ከፍተኛ አቅም እንደሚሆኑ ጥርጥር የለኝም።
- ምኖች ነው ያልከው?
- መርሆች።
- ምንድናቸው?
- አራት ናቸው።
- ምን ምን?
- አንደኛው መርህ፣ የዜጎች ክብር ነው!
- ሁለተኛውስ?
- ሁለንተናዊ ብልፅግና ለዜጎች!
- እህ … ቀጣዩስ?
- ነፃነትና እኩልነት!
- እሺ … አራተኛውስ?
- ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት
- ምን እማማችነት?
- ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት።
- እሱ ብቻ ነው የሚቻለው?
- የሚቻለው ማለት?
- ማለቴ ከወንድማማችነትና እህትማማችነት ውጪ ሌላ ነገር አይኖርም።
- ሌላ ነገር ማለት?
- ኅብረ ብሔራዊ ጋብቻ?
- ለምን ታፌዣለሽ?
- እህ … እኔስ ከማን አንሳለሁ?
- ከማን አንሳለሁ ማለት?
- እናንተ ስታፌዙ ማለቴ ነው።
- ወደ ብልፅግና የሚያስፈነጥሩን መርሆች ናቸው አልን እንጂ መቼ አፌዝን?
- ተው … ተው …
- ለምን?
- የምትሉትና የምትተገብሩት ነገር አይገናኝማ? የተለያየ ነው።
- የቱ ጋ ተለያየ?
- ከምታደርጉት አንዱን ወስደህ ብትፈትሽ ታገኘዋለህ።
- ምኑን ልፈትሽ?
- ሰሞኑን በወልቂጤ ከተማ የተፈጸመውን ድርጊት ብትፈትሽ ልዩነቱን ታየዋለህ።
- የምኑን ልዩነት?
- ያስፈነጥሩናል በምትሏቸው መርሆችና በምትተገብሩት መካከል ያለውን ልዩነት።
- ጥሩ፣ እንፈትሽ። ግን በወልቂጤ ምንድነው የተፈጠረው?
- የገጠማቸው የመጠጥ ውኃ ችግር እንዲታወቅላቸው ሠልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጥይት ተኩሰው ሦስቱን ገደሉ።
- አልሰማሁም።
- ሰላማዊ ሠልፍ የወጡት እንኳን እንዳንተ አልሸሹም።
- እኔ እየሸሸሁ አይደለም። አልሰማሁም።
- ባትሰማውም ይኸው አሁን ሰምተሃል።
- እሺ … በወልቂጤ የተፈጸመውን በማነጻጸር መርሆቹን እንድፈትሽ ነው ያልሽው አይደል?
- አዎ።
- እሺ ቀጥይ … እንፈትሽ።
- መርህ አንድ የዜጎች ክብር ነው አይደል?
- አዎ።
- ከዚህ መርህ አንፃር የመጠጥ ውኃ የጠየቁ ነዋሪዎች ላይ ጥይት ተኩሶ መግደል የዜጎች ክብር መገለጫ ነው? ተገቢ ነው?
- አይደለም።
- መርህ ሁለት ሁለንተናዊ ብልፅግና ነው አይደል?
- አዎ።
- የመጠጥ ውኃ ማግኘት መሠረታዊ የዜጎች መብት አንጂ የብልፅግና ጥያቄ አይደለም።
- እውነት ነው።
- ይህንን መሠረታዊ መብት ጥያቄ ሳይመልሱ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ይቻላል?
- አይቻልም።
- መርህ ሦስት። ነፃነትና እኩልነት ነው። የወልቂጤ ነዋሪዎች ከሌሎች ከተሞች ነዋሪዎች ዕኩል የመጠጥ ውኃ ሊቀርብላቸው አይገባም?
- ይገባል! ግን..
- ቆይ ቆይ። የወልቂጤ ነዋሪ የገጠመውን ችግር የመግለጽና ተቃውሞ የማሰማት ነፃነት የለውም።
- ነፃነትማ አለው፣ ነገር ግን …?
- ግን ምን?
- ሠልፉ የተፈቀደ መሆን አለበት?
- መርህ አራት። ሕዝብን ቅራኔ ውስጥ እየከተትክ የሚፈጠር ወንድማማችነትም በለው እህትማማችነት አይኖርም። አራት ነጥብ።
- በእርግጥ ስለ መርሆቹ አተገባበር ያነሳሽው በሙሉ ትክልል ነው። ጉድለት አለበት። ነገር ግን …
- ‹‹ነገር ግን›› ካላችሁ ማምለጫ እየፈለጋችሁ እንደሆነ ይታወቃል።
- በፍፁም አይደለም።
- እሺ … ግን ምን?
- የመርሆቹ አተገባበር ላይ ያነሳሽው ትክክል ነው። ግን መረዳት ያለብሽ እኛም አንቺ ያልሽውን ነው ያልነው።
- እናንተ ምንድነው ያላችሁት?
- ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማስፈንጠር የምንችለው በእነዚህ መርሆች ብቻ አይደለም ብለናል።
- ታዲያ ሌላ በምንድነው?
- መርሆቹን በአግባቡ መተግበር ስንችል ነው!
- ለምን ትደረድራላችሁ ታዲያ?
- ምን?
- መርህ!
– |
– |
|