ቤአ ኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም የሚያስችለውን ስምምነት፣ ከቻይናው ሻክማን የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ከቻይናው ሻክማን የመኪና አምራች ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነትም በሦስት ምዕራፍ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ካሶኒ፣ ሎቤድ፣ ሳይቤድና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ የታለመ መሆኑን፣ ኩባንያው ሐሙስ የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በወዳጅነት ፓርክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ፈተና የሆነውን የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ችግርን ለመቅረፍ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በተወሰነ መጠን ለማስቀረት ይረዳ ዘንድ ተቋሙ ከቻይናው ኩባንያ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
በመጀመርያው ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ በዓመት 1,500 ከባድ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 3,000 ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በሦስተኛው ዙር ፋብሪኬሽንን ጨምሮ የተለያዩ ክፍሎችን በአምስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ የመጀመርያውን የመገጣጠሚያ ምዕራፍ ሁሉንም ሥራዎች አጠናቆ ለመጨረስ 45 ቀናት ብቻ እንደሚፈጅ አክለው ገልጸዋል፡፡
የትራንስፖርት ዘርፍ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከቻይናው ሻክማን የመኪና አምራች ኩባንያ ጋር የተደረገውን ስምምነት፣ መኪናን ገጣጥሞ ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ኃይል ሥልጠናና የዘርፉን የሥራ ባህል ለማሳደግ ይረዳል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከሻክማን የመኪና አምራች ኩባንያ ጋር በተደረገው ስምምነት፣ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ፈሰስ መደረጉን፣ ፕሮጀክቱም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ሻክማን የመኪና አምራች ኩባንያ በአፍሪካ በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከፍ ከማድረግም ባለፈ፣ በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን እየቀረፈ መሆኑን የሻክማን ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ፍሎሪንስ ጄም ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 40 ዓለም አቀፍ ቢሮዎች፣ ከ150 በላይ የገበያ ፍራንቻይዞች፣ 26 ዓለም አቀፍ የመለዋወጫ ማዕከላትና ከ380 በላይ ድኅረ ሽያጭ ትስስር ያለው ግዙፍ የመኪና አምራች ኩባንያ እንደሆነ ጭምር አክለው አስረድተዋል፡፡
ሻክማን ግሩፕ በቻይና ከሚገኙ ስመ ጥር የመኪና ብራንዶች ቀዳሚ የሚባል መሆኑን፣ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በበርካታ የኢንዱስትሪ ሒደቶች ውስጥ በማለፍ ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቶ መላኩ አለበል፣ ‹‹በኢትዮጵያ የትራንስፖርት አቅርቦትን በማጣጣምና ተደራሽነትን በማስፋት ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን አንድ ዕርምጃ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 11 የመኪና መገጣጠሚያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በአገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን በብዛት በመገጣጠም የትራንስፖርት አቅርቦት ችግርን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ ዘርፍ እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስቀረት፣ እንዲህ ዓይነት ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መንገድ ማሳየት እንዳለባቸው አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡
ቤአ ኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለፉት ዓመታት በበርካታ የንግድና የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት ሲሳተፍ የቆየ ግዙፍ አገር በቀል ኩባንያ መሆኑንና በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በእርሻ በኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም በሪል ስቴት የሥራ ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡