Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአገር በቀል የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ለአደጋ የሚሰጡት የድጋፍ ምላሽ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ...

አገር በቀል የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ለአደጋ የሚሰጡት የድጋፍ ምላሽ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

አገር በቀል የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚገኝን ፈንድ የማድረስ አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ፣ ለአደጋ የሚሰጡት ምላሽ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ ተገለጸ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ከሚገኘው ፈንድ ቢያንስ 25 በመቶ የሚሆነው በአገር በቀል ድርጅቶች በኩል ለተጎጂዎች እንዲዳረስ የሚል ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም፣ በአገር በቀል ድርጅቶች በኩል በቀጥታ የሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ ቃል ከተገባው 25 በመቶ ያነሰ ነው ተብሏል፡፡

የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ዕርዳታ በአገር ውስጥ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የማዳረስ አፈጻጸሙ እጅግ ደካማ እንዲሆን ካደረጉት እንቅፋቶች ውስጥ፣ የአገር አቀፍና አገር በቀል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በሀብት ክፍፍል ላይ ያላቸው አነስተኛ ተሳትፎ ቀዳሚው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን ቀጥተኛና ተገቢ ፈንድ ማግኘት አለመቻል የሰብዓዊ ዕርዳታ አድራሽ ተቋማቱን በጊዜና በተገቢ መንገድ ምላሽ እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም የአገር በቀል የዕርዳታ ድርጅቶቹ የሚያገኙት ፈንድ አቅርቦት ውስንነት ለአደጋ ምላሽ መስጠት ላይ እንጂ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ላይ እንዳይሠሩ እንዳደረጋቸው፣ የድርጅቶቹ ተቋማዊ ዘላቂነት እንዳይጠናከር በዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚታዩ ቸልተኝነቶችም እንቅፋት መሆናቸው በውይይት መድረክ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የጀርመን አግሮ አክሽንና ቱጌዘር ፕሮጀክት የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል ‹‹ሰብዓዊ ዕርዳታ በአገር በቀል ተቋማት›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የውይይት መድረክ ያዘጋጀ ሲሆን፣ በመድረኩ ወቅታዊው የአገር በቀል ድርጅቶች ለተጎጂዎች ድጋፍ የማድረስ ሁኔታ ተዳሷል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ተመዝግበው ከሚገኙ በሺሕ የሚቆጠሩ አገር በቀል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች መካከል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ በቀጥታ ማግኘት የቻሉት ከ14 አይበልጡም ተብሏል።

በኢትዮጵያ በአገር በቀል ድርጅቶች በኩል በቀጥታ የሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ ከግብ እንዲደርስ ከተፈለገ፣ አገር አቀፍና አገር በቀል የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በውሳኔ አሰጣጥ እንዲሳተፉ፣ በሀብት ማዳረስና በአጀንዳ መረጣ ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር የድርጅቶቹ አቅም ግንባታም በድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊከናወን የሚገባ ተግባር ሊሆን እንደሚገባው በውይይት መድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡

የአሶሴሽን ፎር ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት ኦልተርኔቲቭስ (ASDA) አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታከለ ተሾመ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ አገር በቀል ሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የአገሬውን ቋንቋ፣ ባህል ስለሚያውቁ ከማኅበረሰቡ ጋር አብረው የሚኖሩ በመሆናቸው የተሻለ አረዳድ አላቸው፡፡ ስለሆነም የሰብዓዊ ዕርዳታ ምላሾችን ለመስጠት አሁን እየተመሠረቱ ያሉ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪዎችና አገር በቀል ሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪዎች ጥምረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አገር በቀል ድርጅቶች አነስተኛ የሰው ኃይል ቁጥር ያላቸውና ዓመታዊ በጀታቸው አነስተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን የሚገልጹት አቶ ታከለ፣ ትልቅ የሀብት ክፍተት እንዳለባቸውና ይህንን ክፍተት ማጥበብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ያለባቸውን የልምድ ችግር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመጣመር የሁለትዮሽ ልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ በኢትዮጵያ መልካም የሚባለውን ጅማሬ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገው አክለዋል።

በስብሰባ መድረኩ ላይ ከጀርመን አግሮ አክሽንና ቱጌዘር ፕሮጀክት በተጨማሪ፣ አምስት አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅቶችን ማለትም አፍሮ ኢትዮጵያ ኢንተግሬትድ ዴቭሎፕመንት አሶስዬሽን (AEID)፣ አክሽን ፎር ኢንተግሬትድ ሰስትኔብል ዴቭሎኘመንት አሶሴሽን (AISDA)፣ አፋር የአርብቶ አደር ልማት ማኅበር (APDA)፣ ኮሙዩኒቲ ፋሲሊቴሽን ኤንድ አሲስታንስ (CIFA- Ethiopia)፣ እንዲሁም ዋቆ ጉቱ ፋውንዴሽን (WGF) ተሳትፈዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...