Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የተጠራቀሙ ችግሮች ገደባቸውን እያለፉ ሥጋት እየደቀኑ ነው!

የአገርን ህልውና አደገኛ አዘቅት ውስጥ የሚከቱ ችግሮች እየበዙ ነው፡፡ ዜጎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው በሰላም ተንቀሳቅሰው ጉዳያቸውን ለመፈጸም እያዳገታቸው ነው፡፡ ከቦታ ቦታ መዘዋወር ብቻ ሳይሆን አንድ ቦታ በሰላም ተረጋግቶ መኖርም እያቃተ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ከኖሩበት ቀዬ መጤ እየተባሉ የሚገደሉና የሚሳደዱ ከመብዛታቸውም በላይ፣ በሕገወጥ ግንባታ ሰበብ ለዓመታት የኖሩበት ጎጆ እየፈረሰ ሜዳ ላይ የሚጣሉ ወገኖች እሪታ በስፋት እየተሰማ ነው፡፡ ውኃ ጠማን ብለው ሠልፍ የወጡ አቤቱታ አቅራቢዎች በጥይት መቆላታቸው በምሬት እያነጋገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋና በመኸር እርሻ ከፍተኛ የሚባል ስንዴ አልምታ ኤክስፖርት ማድረግ ጀመረች እየተባለ፣ የዱቄት ፋብሪካዎች ምርቱን ማግኘት አቅቷቸው ተቸግረዋል ተብሎ አቤቱታ እየቀረበ ነው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ የቦረና አስደንጋጭ ድርቅ የመንግሥት ያለህ እያስባለ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ገዝቶ ባስገባቸው አውቶቡሶች የተጋነነ ዋጋ ምክንያት የግልጽነት ጥያቄ በየአቅጣጫው እየተስተጋባ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ትርምስ ለምን ተፈጠረ ሲባል በአግባቡ መልስ የሚሰጥ የለም፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የአፍሪካ ሞዴል መሆን ሲገባትና በእርግጥም ማድረግ እየቻለች፣ በተልካሻ ምክንያቶች እያደር ቁልቁል ስትሄድ ማየት ያንገበግባል፡፡ በአብዛኛው ወጣት በሆነው የሰው ኃይሏና በተፈጥሮ ፀጋዎቿ በመታገዝ እንኳንስ አሁን የሚፈጠሩትን የቀድሞዎቹን ችግሮች መፍታት እየተቻለ፣ ዘወትር አገርን ምስቅልቅል ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶች ተራ እየጠበቁ ሲፈጸሙ ለምን አለማለት ያስተዛዝባል፡፡ አገር መምራት ከባድ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ግን ተቋማትን የማጠናከርና የአመራር ጥራት ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አገርን የምታህል የጋራ ቤት ማልማትም ሆነ ማሳደግ የሚቻለው፣ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አሠራር ማስፈን የሚያስችል ተሳትፎ በማረጋገጥ ነው፡፡ የአገር ህልውና የሚመሠረተው በዜጎች እርካታ ላይ ሲሆን፣ አድሎአዊና አግላይ ድርጊቶችን ማስወገድ የግድ ይላል፡፡ ዜጎች በአገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ሲነፈጉና የአስከፊ ዕርምጃዎች ሰለባ ሲሆኑ፣ ለአገር ሰላምም ሆነ ደኅንነት ጥሩ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማውሳት እንደተሞከረው፣ ዜጎች በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት አገር ታስፈልጋቸዋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት አስፈላጊ ናቸው፡፡

የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕጉ ዜጎችን ካልታደገ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሕዝቡን በታማኝነትና በቅንነት ካላገለገሉ፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች ሕዝቡን በሥርዓት ካላስተዳደሩ፣ የገበያውን ጤናማነት እየተቆጣጠሩ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት እንዲያሰፍኑ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግዴታቸውን ካልተወጡ፣ የሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ካጓደሉ፣ ግዴለሽነትና ሕገወጥነትን የሚያስፋፉ አካላት እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ ከተደረገ መንግሥት አገር እያስተዳደርኩ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም፡፡ ይልቁንም አሉታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እየቦረቦሩት ነው ማለት ይቀላል፡፡ ምንም እንኳን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ‹‹ገበያ መር›› ነው ተብሎ ቢነገርም፣ በእርግጥ በኢኮኖሚ ሕግጋት ነው የሚመራው? ወይስ የጥቂት አድመኞች መፈንጫ ነው? እነዚህ ገበያውን ሥርዓተ አልባ ያደረጉ ኃይሎችስ ማንን ተማምነው ነው ሕዝብ የሚያስለቅሱት? የሸቀጦችንና የአገልግሎቶችን ዋጋ እንደፈለጉት ሲሰቅሉት ማን ነው የሚጠይቃቸው? በሕዝቡ ውስጥ ማኅበራዊ እኩልነት ሰፍኖ ዜጎች በአገራቸው ልማት ተሳታፊና የውጤቱ የጋራ ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው፣ ይህ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሚሆኑ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡

የመንግሥት ሥልጣን የሚገኘው ከሕዝብ በሚገኝ ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የሕዝብ ነፃ ፍላጎት ነው፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችለው በእኩልነት ለመኖር ፈቃደኝነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክርና የሕግ የበላይነት መኖር ናቸው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ትግል ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ጉዳይ ብዙ ጊዜ ብዙ የተባለበት ቢሆንም፣ አሁንም ከአሳሳቢነት በላይ የዘለቀ ነው፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ምን ያህል አመኔታ አላቸው? ከክልሎች እስከ ፌዴራል መንግሥቱ ድረስ ለዜጎች አቤቱታ የሚሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል? ያለ ምንም ተጨባጭ ምክንያት ዜጎች ለምን ከጎጆአቸው ይፈናቀላሉ? መብቶቻቸውን የሚጠይቁ ለምን ይንገላታሉ? ችግሮች መቃለል ሲገባቸው ለምን ይብስባቸዋል? መልስ የለም፡፡

በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ዋና ተጠሪነቱ ለሕዝብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መንግሥት ዜጎች መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን ተረድተው በሥርዓት እንዲተዳደሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥታዊ ተቋማት አወቃቀርና የሹማምንቱ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወሰን ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ዜጎች የግብር ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ በተለያዩ ብሔራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑና ለአገራቸው ባላቸው አቅምና ዕውቀት እንዲያገለግሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን የሚያስፈጽሙ የመንግሥት ተሿሚዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት አሠራር ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሲጎድለውና የሹማምንቱ የተጠያቂነት ወሰን በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሕዝብን በሀቅና በትጋት ከማገልገል ይልቅ ሌብነት ላይ መረባረብ ልማድ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ሙስናን እንታገላለን›› እየተባለ በስፋት እየተነገረ ሌብነቱ ግን ክብረ ወሰኖችን እየሰበረ ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ግዴታውን እየተወጣ፣ ተሿሚው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ማከናወን ሲያቅተው እንዴት ነው የሚጠየቀው? የት ነው የሚከሰሰው? የት ነው የሚዳኘው? ይህ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡

የሕዝብ አደራ አለብኝ የሚል መንግሥት የአገር ኢኮኖሚን ከማሳደግና መሠረተ ልማቶችን ከማስፋፋት በተጨማሪ፣ ለሕዝቡ ሕይወት ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህም መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ፣ የኑሮ ውድነትን በማርገብ፣ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት በማስፈን፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን በማስፋት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት በማስከበርና በመሳሰሉት ጉዳዮች ይገለጻል፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚኖረው ደግሞ መንግሥት አሠራሩ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት በተግባር ሲታይበት ነው፡፡ ባለሥልጣናቱም በዚህ መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲደረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመንግሥት ሹማምንት የኃላፊነትና የተጠያቂነት ወሰን በግልጽ ይታወቅ የሚባለው፡፡ ዜጎች ፍትሕ አጣን፣ ያላግባብ ከቀዬአችን ተፈናቀልን፣ ሙስና አላንቀሳቅስ አለን፣ ደኅንነታችን ያሳስበናልና የመሳሰሉ አቤቱታዎችን ሲያቀርቡ እንዳላዩ ወይም እንዳልሰሙ ማለፍ አይቻልም፡፡ ችግሮች እየተጠራቀሙ ገደባቸውን እያለፉ ሥጋት እየደቀኑ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

አስተዳደሩ ይዞታን ለማረጋገጥ ከመረጣቸው ይዞታዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ብቁ አለመሆናቸው ተገለጸ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ይዞታን...

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...