በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የከተሰተው ድርቅ ከቀጠለ፣ በቂ ዕርዳታና የቀጣይ ወቅት ዝናብ ካልዘነበ 1.7 ሚሊዮን ዜጎች ለምግብ እጥረት እንደሚጋለጡ የዞኑ የጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ለተከታታይ አምስት ዓመታት በሁሉም የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለማግኘቱ ሦስት ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን፣ 1.7 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚኖርባት የሚገመተው ቦረና 800,000 በላይ ዜጎች ዕርዳታ እንደሚሹ የዞኑ የጤና ቢሮ የእናቶችና ሕፃናት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጃርሶ ሳራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 21,637 ሕፃናት ለምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን አቶ ጃርሶ አስረድተው፣ ከእነኚህ ውስጥ 1,018 የሚሆኑት የከፋ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ ፕሮግራሙ አስተባባሪው ገለጻ፣ በዞኑ 54,457 ነፍሰ ጡር እናቶች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን፣ የከፋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ደግሞ 25,338 መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዞኑ በጤና ተቋማት የተመዘገበ የሰው ሞት ባይኖርም፣ በቤታቸው በምግብና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የሞቱ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የቦረና ዞን የግብርና ቢሮ እንስሳት ዘርፍ ኃላፊ ቃሲም ጉዩ (ዶ/ር)፣ በዞኑ የተከሰተውን ድርቅ በመገናኛ ብዙኃንና በመንግሥት ትኩረት እንዳላገኘ ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ዜጎችና ከብቶች የሕይወት አድን ሥራ ቢሠራም፣ ካለው ሰፊ ፍላጎት አንፃር በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
ግብርና ቢሮው ባለው መረጃ መሠረት ዜጎች በቂ ዕርዳታና፣ የቀጣይ ወቅት ዝናብ አካባቢው ካላገኘ እጃቸውን የሚዘረጉ ቁጥራቸው ከፍ እንሚል አስረድተዋል፡፡
የቦረና ዞን የግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፍፁም ዳገሙ፣ የቀጣይ ወይም በየካቲት መጨረሻ የሚጠበቀው የዝናብ ወቅት ትንበያ፣ ዞኑ በቂ ዝናብ እንደሚያገኝ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በድርቁ ምክንያት 3.3 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን፣ 300,000 ዜጎች ወይም 68,000 አባወራዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው፣ በከተማ ዙሪያ መስፈራቸውን አስረድተዋል፡፡ የተቀሩት ከ800,000 የሚልቁ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል፡፡
በዞኑ ለሁሉም ዜጋ የውኃ አቅርቦት ለማሰራጨት 115 ቦቴዎች እንደሚያስፈልግ፣ ከዚህ ውስጥ በአሁን ወቅት በ20 ቦቴዎች ብቻ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አቶ ፍፁም ተናግረዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አኳያ በፍጥነት አልሚ ምግብ ለዜጎች ካልቀረበ፣ ከአሁን በኋላ የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር ከፍ ይላል ብለዋል፡፡
በቦረና ዞን በያቤሎ ከተማ እንስሳት ፕሮግራም ኦፊሰር፣ በዞኑ እስከ የካቲት መጨረሻዎቹ ዝናብ ካላገኙ መላው ነዋሪ ለከፋ ችግር ይጋለጣል ብለዋል፡፡ እንደ አዲሱ ገለጻ፣ አሁን ባለው ሁኔታ በቂ የምግብ ዕርዳታና ዝናብ በወቅቱ ካልዘነበ ዜጎች የሕይወት አደጋ ተጋርጧባቸዋል፡፡
የቦረና ዞን የኑሮ መሠረት የሆነው የእንስሳት ሀብት የሚመገቡት በማጣታቸው ባዕድ ነገሮችን ወደመመገብ ተሸጋግረዋል ብለዋል፡፡ በዞኑ ከከብቶች ሞት በተጨማሪ የሰዎች ሞት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሞት የተረፉት የቀንድ ከብቶች ግማሹ በሰው ጉልበት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን፣ በከብት ገበያው ከ2,000 በላይ የሚያወጣ የቀንድ ከብት የለም ብለዋል፡፡
በዞኑ 807,000 ሰዎች ዕርዳታ እንደሚፈልጉ ከእነዚህ ውስጥ 167,000 የሚሆኑት አስቸኳይና ተከታታይ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውንና ከቀንድ ከብቶች ውስጥ አሥር በመቶውን ለመታደግ 4.4 ሚሊዮን እስር ሳር እንደሚያስፈልግ ተነግሯል፡፡