Wednesday, May 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበሕግ አምላክ እዩልኝ ስሙልኝ!

በሕግ አምላክ እዩልኝ ስሙልኝ!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የምን በሕግ አምላክ!? ለምን ‹‹እዩልኝ ስሙልኝ!›› ይህ የልብ አድርጉልኝ ጥያቄ ነው! ግራ ቀኙን ሁሉ፣ የሁሉንም ድምፅ በሙሉ የእዩልኝ ስልሙኝ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን የበሕግ አምላክና የእዩልኝ ስሙልኝ ጥያቄዬን፣ አቤቱታዬን፣ ማመልከቻዬን ለማገዝ፣ እግዜሩ ራሱ እንዲያሳያችሁና እንዲያመላክታችሁ ለማገዝ ከሰሞኑ ብቻ መሰንበቻችንን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣቸውን አንድና ሁለት መግለጫዎች መንደርደሪያ/መንደርደሪያችሁ አድርጌ ላቅርብ፡፡

አንደኛው፣

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከየካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተፈጸሙ እስሮችን በተመለከተ የአዲስ አበባን፣ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስና የፀጥታ አካላት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን፣ ምስክሮችንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በማነጋገር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የተለያዩ ማቆያ ቦታዎችን በመጎብኘት ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የተወሰኑ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች በፍርድ ቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ ዋስትና እየተለቀቁ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ያረጋጠ ቢሆንም፣ አሁንም ብዙ ሰዎች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ጋር ለተያያዘ በተለያየ ዓይነት ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ዋስትናም ተከልክለው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ተያይዞ የዚህ ዓይነቱ እስር የዘፈቀደ እስር ሊሆን ስለሚችል የመንግሥት የፍትሕ አስተዳደር አካላት በሙሉ በበቂ ምክያት በወንጀል የተጠረጠረን ሰው በሕጉ መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ፣ በተለይም በቅድመ ምርመራ ወቅት የዋስትና መብት አጠባበቅ ሥርዓትን ባከበረ መንገድ ምርመራ ከማድረግ ውጪ ተገቢ ያልሆነ እስር እንዲያስወግዱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አሳስበዋል›› ሲል፣

ሌላኛው፣

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች፣ የቧንቧ ውኃ አቅርቦት ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ ላጋጠማቸው የውኃ ችግር መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ለማቅረብ ሠልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በፖሊስ በተወሰደ የኃይል ዕርምጃ በነዋሪዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ኢሰመኮ የዓይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችንና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር ባሰባሰበው መረጃና ማስረጃ መሠረት ሦስት ሰዎች ጭንቅላቸውና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመትተው የተገደሉ ሲሆን፣ ቢያንስ በ30 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት መድረሱን አረጋግጧል፡፡

የአካባቢ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ለደረሰው ጉዳት ምክንያት የሆነው ከሠልፈኞቹ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች የከተማው የውኃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ላይ ድንጋይ መወርወራቸውንና የመኪና መንገድ መዝጋታቸውን ተከትሎ፣ በክልሉ ፖሊስ በተወሰደ የኃይል ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር የተወሰደው የኃይል ዕርምጃ ከነገሩ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ተመጣጣኝ ያልሆነ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹አንገብጋቢ በሆነ የውኃ አቅርቦት ጥያቄ ሠልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ ሕይወት የሚያጠፋ መሣሪያ ተጠቅሞና ጥይት ተተኮሱ ነዋሪዎች መገደላቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ዕርምጃ በመሆኑ፣ የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ሊያረጋግጥና የተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፣ ለወደፊቱም ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለፀጥታ ኃይሎች ግልጽ አመራር እንዲተላለፍ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል›› ይላል፡፡

ልብ አድርጉልኝ! ለማስታወስ ያህል ልብ አድርግልኝ ማለት በመዝገብ ቃላት ‹‹ለዛ ቢስ›› ትርጉሙ እንኳን እማኝ ወይም ምስክር ትሆናለህና ሁኔታውን ተመልከት ማለት ነው፡፡ በተጨባጭ የጭንቅ የጥብ ጊዜ ውስጥ፣ ያንዣበበ ጥቃትን ለመከላከል፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይቻል እንደሆነ ለመሞከር በሚደረግ የተማፅኖ ጥረትና ልመና ውስጥ ደግሞ ልብ አድርጉልኝ የሚያጎናፀፈውን ፍቺና ትርጉም ልብ ማድረግ የሚገድ አይመስለኝም፡፡ ሰው መሆን ማለት ከሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ይዘትና ትርጉም አኳያ የገዛ ራስንና የወዳጅ የዘመድን ጥቃት መታመምና መሰቅየት ማለት አይደለም፡፡ የሌላው ሰው፣ ዘመድ ያልሆነው፣ የባዳውና የእንግዳው ጥቃት ራሱ ጥቃታችን ‹‹ሞታችን›› ሆኖ ካልተሰማን፣ ስለሰብዓዊ መብት እናውቃለን ማለት ይቸግራናል፣ አይቻልምም፡፡ ከዚህ አንፃር ነው የልብ አደርጉልኝን ትርጉም ልብ ማድረግ አይገድም የምለው፡፡

እነዚህን ልብ አድርጉልኝ ያልኳቸውን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫዎች ያቀረብኳቸው አወዳድሬና መርጬ አይደለም፡፡ በያዝነው ወር፣ በራሱ በምንኖርበት ወቅት ራሱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ካወጣቸው ውስጥ ፊት ለፊት ያገኘኋቸውን ሁለቱን የየካቲት ወር የመጀመርያ ሳምንት መግለጫዎችን ነው፡፡

እነዚህ መግለጫዎች ብቻቸውን የኮሚሽኑ መግለጫ ውስጥ የተጠቀሱ ተደጋግመው የሚታወቁ ቃላትና ሐረጎች እንደሚጠቁሙት፣ የአገራችን የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት (ይህ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶችና እስር ቤቶች የሚሠሩት ሥራና የሚሰጡት አገልግሎት የሙያ ስምና ስያሜ ነው) የምርመራ ሪፖርት የምርመራ ውጤት ነው፡፡ ይህ የሰብዓዊ መብቶች ሐኪም ጊዜያዊ ወይም የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት ደጋግሞ ስለእስር፣ ስለእስራት፣ በቁጥጥር ስለመዋል፣ እነዚህ ሁሉ እንዴት እንደሚፈጸሙ፣ የዘፈቀደ እስር የሚባል ነገር እንዳለ፣ በወንጀል መጠርጠር ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ በበቂ ምክንያት በወንጀል መጠርጠር ብሎ የሙያ ዕውቀትና አስፈላጊነት እንዳለ፣ በሌላ አነጋገር በጥርጣሬ ለማሰር ራሱ የአሳሪውን፣ የማሰር ሥልጣን የተሰጠውን መጠርጠር ብቻ ሳይሆን፣ ጥርጣሬውን ራሱን አሳማኝ የማያደርግ ማስረጃ/መረጃ ማግኘትን በቅድመ ሁኔታነት እንደሚጠይቅ፣ ከዚህ ቢያልፍ በፖሊስ የሥልጣን ግቢ ውስጥ በራሱ ጭምር ዋስትና (በዋስ መልቀቅ) የሚባል ሥርዓት እንዳለ፣ ‹‹የዋስትና መብት አጠባበቅ ሥርዓትን ባከበረ መልኩ›› የማይካሄዱ እስራቶች፣ ‹‹በቁጥጥር ሥር›› ማዋሎች እንዳሉ ሪፖርቱ ይፋ ያደርጋል፡፡

ሪፖርቱ ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃውሞን፣ ማለትም ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ የተሰጠውን የአንቀጽ 30 መብት የጣሰ የሰላማዊ ሠልፈኛ ሞት (ቢያንስ ቢያንስ ሦስት ሰው) የፖሊስን ግድያ ያስከተለ ጥፋት መፈጸሙን ገልጾ፣ ከዚያም ከፍ ብሎ ለዚያውም ‹‹አንገብጋቢ በሆነ የውኃ አቅርቦት ጥያቄ ላይ ሠልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ›› ከመጠን ያለፈ የኃይል ዕርምጃ መውሰዱና መግደል፣ አካል ማጉደል ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፣ የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት ሊያደርግ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ ይገባል በማለት ጭምር የአገራችንን የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት የ‹‹ዕለት ሁኔታ›› ይናገራል፡፡

እነዚህ የጠቀስኳቸው ሁለት ድንገትና በአጋጣሚ ተመዝዘው የወጡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት ውስጥ፣ ብዙዎቻችን ምናልባትም ሁሉም ሰው የሚያየው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በጭራሽ አለመሻሻሉን፣ የተሻለ ነገር አለመኖሩን፣ የኢትዮጵያ የሕገ መንግሥቱ የምዕራፍ ሦስት መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ነገር ከድጡ ወደ ማጡ እየዘቀጠ መሄዱን ሊሆን ይችላል፡፡ ሙሉ በሙሉ ውሽት ነው፣ ጨርሶ ሐሰት ነው ብለው ምላሽ የማይሰጡበት፣ የማይወራረዱበት፣ ተወራርደውም ዕዳ የማይገቡበት ሀቅነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር፣ ከመንግሥት የሥልጣን አካላት ጋር፣ ከሕግ አስከባሪዎች ጋርና ከተጠቁ ሰዎች ጋር ያለንን እያንዳንዷን ግጥምጥምና ግንኙነት መመርመር ሳያስፈልግ ዝም ብሎ መታዘብ ብቻ በቂ ነው፡፡ አገርና ዓለም መላው አካሉን ዓይንና ጆሮ አድርጎ ይመለከተው በነበረው በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ እንኳን ፖሊስ ቄሱን ‹‹በጥፊ ሲያጮለው›› አይተናል፡፡ የካቢኔ ሚኒስትር በሚመራው ዓውራ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሌለ አለ ቢባልና ቢኖር እኮ ባልተነገረን የልብስ ደንብ (ድሬሲንግ ኮድ) አስፈጽማለሁ ሲባል መስክረናል፡፡ ሕግና ደንብ እነዚህን መሠረት ያደረገ መመርያ ሳይሆን የራሳቸው የሕግ አስከባሪዎች ፈቃድና ፍላጎት ሕግ ሆኖ ሲፈጽም፣ የዕለት ተዕለት ኑሯችንና ውሏችን በየቀኑ የሚመዘግበው ሪፖርት ነው፡፡ እኛም መብት ማስከበርን በመፆም መንግሥታዊና የባለሥልጣናት ሕገወጥነትን አድራጊ ፈጣሪነትን እሽሩሩ እያልን እንኮተኩታለን፣ እናለመልማለን፡፡ ይህ ለሰብዓዊ መብቶች ከመቆም ጋር አብሮ አይሄድም፡፡

ሰብዓዊ መብቶች ተፈጥሯዊ ናቸው፡፡ ማንም የሚሰጣቸው፣ ማንም የሚነጥቃቸው አይደለም ማለት እኮ ሁልጊዜም የምንማማልበት መፈክር ነው፡፡ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችንን ከእርጥባን በዘለለና ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ላይ ግን አልደረስንም፡፡ የአገራችን የሕዝብ አገልግሎት ሠራተኛ ሁሉ፣ ከሲቪል እስከ መለዮ ለባሽ ድረስ ያለው ሁሉ ሕዝብን መፍራት ሳይጀምሩ፣ በሕዝብ ዓይን ውስጥ መሆናቸውን የማይዘነጉበት፣ መጋለጥና መጠየቅን የሚፈሩበት ሁኔታ ሳይፈጠር፣ ስለሰብዓዊ መብቶች ተፈጥሯዊነት መናገር ይከብዳል፡፡ አገራችን ይህ ሁሉ ጉዞ፣ ይህን የመሰለ ዕዳና ግዳጅ አለባት፡፡ የእነዚህ ከባድና አስቸጋሪ ጉዞና መንገድ መጀመርያ የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ አድርጎ መገንባት ነው፡፡ ይህ ማለት ፖለቲከኛ ያልሆኑ፣ ከየትኛውም ወገንተኛ ፖለቲካ ያልወገኑ ነፃ ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥታዊ የፀጥታ፣ የመከላከያ፣ የሕግ ማስከበር፣ እንዲሁም መላውን የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት አካላት በሙሉ የሙያ ስላታቸውንና ብቃታቸውን የሚፈታተኑ ብልሽቶቻቸውን ማራገፍ አለባቸው ማለት ጭምር ነው፡፡ በሕዝብ ዘንድ የሚገባቸውን ያህል አመኔታ የሚያገኙት ይህ ሲሆን ነው፡፡

ከሰባራ ጎናችን መካከል አንዱ ለምሳሌ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ህልውና ቆርቁዞ መኖር ነው፡፡ ነበሩ፣ ወይም አሉ የሚባሉትም በአድሏዊ ዘገባቸው፣ በሥርጭት ስፋታቸው፣ በተደማጭነታቸው፣ በድክመታቸው ሲብስም ጭልጥ ባለ ወገንተኛነታቸውና ዓይን ያወጣ አስመሳይነታቸው የሌሉ ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ፣ የአፈናውና የጥርነፋው መዋቅር አንድ አካልና አምሳል ነበሩ፡፡

ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት ሒደት ውስጥ የፈለገውን ያህል ውስን ቢሆንም፣ የሒደቱ ጉዞም ጦርነት ውስጥ ቢገባም የለውጡ ዴሞክራሲን የማደላደል ሥራና አደራ ቢያንስ ቢንያስ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን እንደገና ማቋቋም፣ ነፃነቱንና ገለልተኛነቱን ማረጋገጥ የሚያስችል ጉዞ ጀምሯል፡፡ በብዙ ዘርፍ እኩልና አቻ ዕርምጃ ማስመዝገብ ባቃተበት አገር፣ ኢሰመኮ ‹‹ለስም መጠሪያ የተስፋ ቁና››ነቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ዛሬ በዚህ አድሏዊ ዓለምና አደባባይ የማይናቅ ድምፅ፣ በአገርም በውጭ አገርም በምንጭነት የሚጠቀስና የሚጠራ ተቋም መሆን ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በመደበኛው የሥራ አፈጻጸም ሒደቱ ውስጥ ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን፣ ነፃነትንና ገለልተኛነት በሚፈታተኑና በሚጠይቁ የቁርጥ ጊዜ ግዳጆች አማካይነት እውነቱን፣ እርግጡንና ሕጉን ሳይፈራ ለሥልጣንና ለባለሥልጣን መናገርን ለመጀመርያ ጊዜ ያስመዘገበ ተቋም ሆኗል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ‹‹መልኬ በቃኝ›› የምትለው ‹‹ድል›› አይደለም፡፡ ገና ብዙ ይቀረዋል፣ በርታ ግፋ ገና ነው በሚባል አንድ የተሳካለት (እየተሳካለት ያለ) ኢሰመኮ ላይ ብቻ የሚንጠለጠል ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር የመንግሥት አውታራትን የመገንባት፣ የዴሞክራሲን መሠረት የማደላደል ሥራም የለም፡፡

ሁለት የዚህ የካቲት ወር የመጀመርያ ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን መግለጫዎች ይዘት ዓይተናል፡፡ እነሱንም ዓይተን፣ በእነሱም ላይ ተመሥርተን የአገራችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በተለይም የወንጀል ፍትሕ ሥርዓታችንን የሚያኩራራ አይደለም ብቻ ሳይሆን አሳፋሪማፈሪያ አያያዞች ልብ አድርገናል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን ኮሚሽንን ‹‹ብይን›› ወይም ‹‹ፍርድ›› ሰምተናል፡፡ ‹‹የመንግሥት የፍትሕ አስተዳደር አካላት ተገቢ ካልሆነ እስር ‹‹እንዲከለከሉ››፣ ‹‹የዋስትና መብት አጠባበቅ ሥርዓትን›› እንዲያከብሩ ‹‹ብይን›› ሰጥቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፖለቲካዊ ንቃታችንና ግንዛቤያችን (በተለይም ከመንግሥት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን በሚያስደንቅና በሚያስደነግጥ አኳኃን መሠረታዊ የውኃ አቅርቦት ጥያቄ ለማቅረብ ሠልፍ የወጡ ሰዎች ላይ ድንጋይ ወረወሩና መንገድ ዘጉ ብሎ ጥይት ተኩሶ ሰው መግደል ተቀባይነት የለውም ማለትን የመሰለ የገዛ ራስ የውስጥ አሠራር ‹‹ፍርድ›› ወይም ብይን መስማት በገዛ ራሱ ምክንያት እውነት መስማት ነው፣ ፍትሕ ሲበየን ማየት ነው፡፡ ልብ አድርጉልኝ የምለው ይህንን ሁሉ ነው፡፡

በአገራችን ውስጥ ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት የተዘረዘሩትና ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ የተሰጣቸው የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች የእርስ በርሳቸውን መኗኗሪያ እንዲሆኑ፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላት የራሳቸው መረማመጃ መሆናቸው እንዲረጋገጥ ደግሞ ተቋማት፣ የመንግሥት አውታራት፣ ዓውደ መንግሥታት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓይነት (ከእሱም የተማረና የበለጠ) ፈርሶ መሠራት፣ እንደገና መገንባት አለባቸው፡፡ ይህን ‹‹አፍርሶ የመሥራት›› እንደገና የመገንባት፣ ገለልተኛ አድርጎ የማዋቀር ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት አፅድቶ መልሶ የማደራጃት ሥራ ሁሉም ቦታና ሁሉም ተቋማት ላይ የሙሉ ጊዜ ሥራችን አልሆነም፡፡ የተሳካውና የሚያኮራ ያልነው፣ የምንለው ኢሰመኮ ያስመዘገበው ድል እንኳን ገና ሥርዓታዊ መተማመኛ አላገኘም፡፡ ይህንን አጀንዳ የሙሉ ጊዜ የአገር አደራ ከማድረግ የከለከለን ዋነኛው ጉዳይ የታወቀው ጦርነቱ ነው፡፡ ጦርነቱን በፕሪቶሪያው ስምምነት አማካይነት በድል ብንገላገለውም፣ ‹‹ግጭት በማቆም አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገ››ውን ስምምነት ተከትሎ የተገኘው ፋታና ዕፎይታ፣ እንዲሁም እስካሁን ድረስ አፈጻጸሙ የፀናው የስምምነቱና የአፈጻጸም ሒደት ግን ከስምምነቱ በኋላ ባሉ ሦስት/አራት ወራት ብቻ ሁለት ጊዜ የአገር የደኅንነት ሥጋት የሆኑ አደጋዎች አጋጥመውናል፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ክልል ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የክልል መዝሙርንና ሰንደቅ ዓላማን አስመልክቶ የተነሳው ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ የተፈጠረው ችግር አገር ላጋጠማት አደጋ ሰበብ፣ መነሻ ወይም አጋጣሚ ሆነው ያገለገሉ ሁነቶች ነበሩ፡፡ ሁለቱም አደጋ የደገሱልን አጋጣሚዎች ያስተማሩን፣ መከራ እያሳዩን ጭምር የመከሩን ሁሉም ጉዳይ በዋናው ጉዳይ ውስጥ በዚያ ግቢ ማዕቀፍ ውስጥ መታየት ያለበት መሆኑን ነው፡፡

ለዘላቂ ሰላም የተደረገውና ግጭት በማቆም በኩል ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው ስምምነት ሒደት ፀንቶ እንደቀጠለ ነው፡፡ አካሄዱም እስካሁን ያለ አንዳች አቤቱታ፣ ተቃውሞ እየተራመደ ነው፡፡ እኔ ይህንን ስል የሚደነቅ ካለ በሕወሓት ወገን ስምምነቱን የፈረሙት ወገኖች ምን እንደሚሉ ለአብነት ልጥቀስ፣ ‹‹የተጀመረው የሰላም ስምምነት ሒደት የማይቀለበስበት ደረጃ ደርሷል፤›› ያሉት ታደሰ ወረደ ናቸው (የካቲት 8 ቀን 2015)፡፡

የሰላም ስምምነቱ እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ፣ ስለዚህም ጦርነቱን ከሞላ ጎደል ተገላገልን ማለት፣ ከሌሎች መካከል ከጦርነቱ ጋር ደርበን፣ የአገርን ህልውና ከማዳን የአገር አደራ ጋር አዳብለን፣ ምናልባትም ሁለተኛ ደረጃ የተቀጥላ ቦታ ሰጥተን ሳንሠራው ወይም ‹‹ረስተነው›› ወደ ነበረው የለውጥና የሽግግር ሥራ ገባን፣ እሱንም ዋናው ግዳጃችን አደረግን ማለት ነበር፡፡ የለውጥና ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ የሽግግር ሥራ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ሥራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሽርሽር ነገር አይደለም፡፡ ደጋግመን የምናነበንባቸው መብቶችንና ነፃነቶችን መኗኗሪያ ለማድረግ የአኗኗር ለውጥ ማምጣት አለብን፡፡ በሕዝብ ድምፅ በግልጽ አሠራር፣ የሚዲያ፣  በጋዜጠኛና በሕዝብ ንቁ ተመልካችነት ውስጥ መኖር የሚጠይቅ ለውጥ ነው፡፡ ይህንን የጉዞ ፈር አድርገን ይዘነዋል ወይ? እዚያ ፈር እዚያ መንገድ ውስጥ መግባት ደፍረናል ወይ? መንገዱን ይዘነዋል ይቅርና ስለመንገዱ የሚናገሩትን መስማትና ማዳመጥ ችለናል ወይ? ዋናው ጥያቄ ነው፡፡

የአኗኗር ለውጥ ለማምጣት በሕዝብ ድምፅ እንገዛለን ለማለት ዝም ብሎና ዘው ብሎ የሚገባበት፣ ወደ እዚያ የሚወስድ ‹‹መንኮራኩር›› የለም፡፡ ስለሕገ መንግሥት አንቀጽ 8 ለማውራት (እሱ ነው ስለሕዝብ ሉዓላዊነት የሚደነግገው) ሁሉንም አስተሳሰብና ፍላጎት (የሥልጣን ፍላጎት ጭምር) በውድድር የሚያስተናብር አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ ሐሳብን የመግለጽና የሚዲያ ነፃነት የመደራጀት መብት የሚባሉ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተደነገጉና ‹‹ተበታትነው›› የምናገኛቸው የመብትና የነፃነት ድንጋጌዎች ደግሞ፣ የዚህ ዴሞክራሲ/ሥርዓት የምንለው ሥራ የግንባታ ዕቃዎችንና መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ምርጫዎች ትርጉም የሚኖራቸው፣ የምክር ቤቶችን በምርጫ መደራጀት የሚወሰነው፣ የእነዚህ ምክር ቤቶች ሿሚነትና ተቆጣጣሪነት ከላንቲካነትና ጌጥነት ከስም ይልቅ እውነት የሚያደርገው መጀመርያ የመንግሥት አውታር ፓርቲያዊነት ሲፀዳ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላይ የተሠራው ዓይነት ሥራ በየቦታውና በእያንዳንዱ አውታረ መንግሥት ውስጥ በጥልቀትና በሰፊው ሲሠራ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜ የተካሄደውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ትግል ሲቀለብስና ሲያከሽፍ የቆየው መጀመርያና ከሁሉ አስቀድሞ ገልተኛ ተቋም ላይ የመዋደቅና የመሥራት የጋራ መግባባት ጥረት አለመኖሩ ነው፡፡ አምባገነንነትንና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀናበሩ አውታራት፣ ለሕግና ሕጉ በሚያዘው መሠረት ለሕዝብ ታምነው ሊያገለግሉ አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት የትኛውም የመንግሥት አውታር ለሕግና ለሕዝብ ሥልጣን በቀር ለማንም ቡድን የብቻ መጠቀሚያ የማይሆንበት ባህርይ እስኪጎናፀፍ (ሥልጣን ላይ ያለው ገዥ መንግሥት ከወግ ባለፈ ደረጃ በሕግና በሕዝብ ሥልጣን ሥር ማደሩ ዕውን እስኪሆን) ድረስ ገልተኛነትን የማጥለቅ ሒደት መቀጠል፣ ወደ የማይቀለበስ ውጤት መድረስም አለበት፡፡ ዋናው ሥራችን ይህ መሆን አለበት፡፡ ባልተገባና ባልተሠራበት መዋቅር ላይ ዴሞክራሲ አይቋቋምም፣ የአኗኗር ለውጥ አይመጣም፡፡ ዋናው የዴሞክራሲ ግንባታ ሥራ ይህ ነው፡፡

በዚህ ዋና ማዕቀፍና ዴሞክራሲን የመገንባት ግዳጅና አደራ ውስጥ፣ የሕዝብና የልዩ ልዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የመብት ጥያቄዎችና ትግሎች የመንግሥት አካል ሕግና የሕዝብ ድኅንነት የመጠበቅ ሥራ አልጣጣም እንዳይሉ ሁሉም ኃላፊነት አለበት፡፡ ዋናው ግብ የመንግሥት አካል መብትና ነፃነት አክባሪነት፣ ሕግና ሥርዓት አስከባሪነት፣ እንዲሁም የሕዝብ ከመብት ቀናዒ መሆን የተገናኙበት ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን ማቋቋምና ሥር ማስያዝ ነውና፡፡

ደጋግመን የምንለፈልፍለት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ይህ ለውጥና ሽግግር ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ዓይነት ብሔራዊ/አገራዊ የደኅንነት ሥጋቶችና ዱብ ዕዳዎች አስቀድሞ ሳይከሰቱ ማምከን ጭምር የሚችለው፣ መጀመርያ የለውጡ ጉዞ የሽግግሩ ሒደት የሚከፋፍሉ ጉዳዮችን የሚሸሽ፣ የለውጡን የራሱን ቅድሚያ መጠናከር የሚፈልጉ ጥያቄዎችን በቀጠሮ የሚያሳድር፣ ቅደም ተከተል የሚያበጅ መግባባት እስከፈጠረ ድረስ ብቻ ነው፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...