ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its Neighbors፡ Somalia and Eritrea›› በሚል ርዕስ በደቡብ አፍሪካ ዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ምሁሯ በናምላ ማትሻንዳ የቀረበው ጽሑፍ፣ ስለኢትዮጵያና ጎረቤት አገሮች ዕጣ ፈንታ ብዙ ጉዳዮችን ያወሳል፡፡
‹‹በታሪክ ሚዛን ከመዘነው አሁን ያለው የኢትዮጵያ ጦርነት ከነባር የፖለቲካ መሠረቶች ጋር የሚሰናሰል ነው፡፡ ዘመናዊ ኢትዮጵያ ከተመሠረተች ጊዜ ጀምሮ በመሀል አገር የኢትዮጵያ ግዛቶችና በዳር አገር የኢትዮጵያ ግዛቶች መካከል ግጭትና ውጥረት ሰፍኖ የቆየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዛሬ ማንነቷ የተገነባው በወረራና ወደ ዳር አገሮች ግዛት በማስፋፋት ነው፤›› የሚለው ዘገባው፣ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተመሠረተችው ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎች ግዛት በማስፋፋት ነው ይላል፡፡
ይህን መሰል ሀተታ የሚያቀርቡ ዘገባዎችና ዘጋቢዎች በርካታ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አለፍ ሲልም፣ ‹‹የአማራ ቅኝ ገዥዎች የመስፋፋት ውጤት ነው›› በማለት ከበድ ያለ ጥላቻ አዘል ትርክት የሚያቀርቡም አሉ፡፡
የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሥረታ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን የተሻገረና ጥንታዊ መሠረት ያለው ነው የሚሉ ወገኖች ግን፣ ይህንን ዓይነቱን መላ ምት ፈጽሞ አይቀበሉም፡፡ ከሺሕ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያውያን በበርበራና በዘይላ ወደቦች መነገዳቸውን በማስረጃ በማቅረብ፣ ዛሬ የዳር አገር ወይም ጎረቤት አገር የሚባሉ አካባቢዎች ጭምር የኢትዮጵያ አካል እንደነበሩ ይሞግታሉ፡፡
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ተሻግራ ግዛት የነበራት አገር እንደነበረች በማስታወስ ወደ ዳር አገሮች የተስፋፋች አገረ መንግሥት ሳትሆን፣ በተቃራኒው የግዛት አንድነቷ በየአቅጣጫው እየተሸራረፈና እየተቆራረሰ በዛሬ ቅርፅና ይዘቷ ተወስና እንደቆየች ይከራከራሉ፡፡
ኢትዮጵያ የመሀል አገር ቅኝ ገዥዎች ወይም ደገኞች በኃይል ግዛት እያሰፉ የመሠረቷት ሳትሆን፣ ከጥንት ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ሰፊ ግዛትና ሉዓላዊ ድንበር የነበራት አገር ነበረች የሚሉ ወገኖች ብዙ የታሪክ መከራሪያ ያቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ድንበርም በየታሪክ ምዕራፉ ሲጠብና ሲሰፋ ቆይቶ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አሁን ያለውን ገጽታ አገኘ እንጂ፣ በቅኝ ግዛትና በተስፋፊነት ዓውድ ሊበየን አይገባውም በማለት ጠንካራ ሙግትን ያቀርባሉ፡፡
ይህ ክርክር ደግሞ አሁን አሁን እየተፈጠሩ ካሉ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ችግሮች ጋር ተጋምዶ ሲነሳ ይሰማል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራ ሠራዊት ድንበር የመሻገር ጉዳይ የትግራይ ጦርነት የፈጠረው ብቻ ሳይሆን፣ የድንበር ይገባኛል ጥያቄን ያነገበም መሆኑ ይነገራል፡፡ በሱዳን በኩል የኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬት በወረራ የመያዙም ጉዳይ ታሪካዊ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በደቡብ ሱዳን ድንበር በኩል ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለው የታጠቁ ኃይሎች ወረራና መስፋፋትም የቆየ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው፡፡ የአልሸባብ ሽብር ቡድን ከሶማሊያ የተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ የመዝለቅ ሙከራ፣ እንዲሁም በግጭትና በድርቅ ሥጋት ላይ የወደቀው አገሪቱ ከሶማሊያ፣ ከፑንትላንድና ከሶማሌላንድ ጋር የምትጋራው ሰፊ የድንበር መስመርም ቢሆን ከውጥረት ያልተላቀቀ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉ የጎረቤት አገሮች ጋር በአሁኑ ወቅት የገነባችው ግንኙነት የሰመረ ስለመሆኑ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ሁሌም ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት አገሮችና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ኢጋድ (IGAD) ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ፍሰሐ ሻውል (አምባሳደር)፣ አገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር የገነባችው ግንኙነት እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ስለመሆኑ ከሰሞኑ ለአንድ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተር ጄኔራሉ እንደተናገሩት ከሆነ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላት ግንኙነት ለ50 ዓመታት በሰመረ ሁኔታ የዘለቀ ነው፡፡ ከጂቡቲ ጋር ያላት ግንኙነት ደግሞ አንዳቸው ከሌላቸው መነጣጠል የማይችሉ ጥብቅ ወዳጅ አድርጓቸዋል፡፡
ፍሰሐ (አምባሳር) ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ጋር የገነባችው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በኢኮኖሚ ትስስር መደገም እንዳለበት ነው የሚያሳስቡት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉ ጎረቤቶቿ የምትፈልገውን ዓይነት አጋርነትና ወዳጅነት ታገኛለች፤›› ሲሉ የተናገሩት ዲፕሎማቱ፣ ይህ ደግሞ በኢኮኖሚ ትስስር መደገም እንደሚኖርበት ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ መሆኑንና በዙሪያዋ ያሉ አገሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል ያስረዱት ፍሰሐ (አምባሳደር)፣ የወደብና የንግድ ኮሪደር አማራጮችን ዘርዝረዋል፡፡
የአሰብንና የምፅዋን ወደቦች የመጠቀም አማራጮችን ዳግም ፈጥራለች ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጂቡቲ ወደብን በሰፊው እየተጠቀመች ትቀጥላለች በማለት፣ ደቡብ ሱዳንን በሚያገናኘው በኬንያው የላሙ የወደብና የንግድ ኮሪደርም የመጠቀም አማራጭ አላት ይላሉ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በሰሜን ሱዳን በኩል በፖርት ሱዳን የመጠቀም ዕድልም አላት ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት እየተፋጠነ መሄዱና ኢኮኖሚዋ ትልቅ መሆኑ፣ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ትስስሮች መሠረት እንደሆነ ነው ዲፕሎማቱ ያስረዱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር እንደሚችሉ ደጋግመው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እሳቸው ወደ ሥልጣን እንደመጡ ጂቡቲን በማስቀደም በአካባቢ ወዳሉ አገሮች ተከታታይ ጉዞዎች አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤት አገሮች መሪዎች ጋር የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ቀጣናዎችን የመመሥረት ስምምነቶችን ከመፈራረም ጀምሮ፣ በተለይ ከኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂና ከሶማሊያው መሐመድ ፋርማጆ ጋር የቀጣናዊ አጋርነት ስምምነት እስከ መፈራረም ደርሰው ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ለሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አገሪቱ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ከመናገር ተቆጥበው አያውቁም፡፡ የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿን ኢኮኖሚያዊ ትስስር አስፈላጊነትንም ከማጉላት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ይህን ስታደርግ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ጠብቃ መሆን የለበትም ወይ? የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ጉርብትና ወይም ለቀጣናዊ ትስስር ቅድሚያ የምትሰጥ ናት ሲባል፣ በዙሪያዋ ድንበሯ ሲጣስና ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ ሲወድቅ በዝምታ ማለፍ አለባት ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡
ከደቡብ ሱዳን የተነሱ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም ወደ ጋምቤላ ክልል የመግባታቸው ዜና በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ታጣቂዎቹ እስከ 200 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ መዝለቃቸው፣ የአካባቢ ስም መቀየራቸው፣ በአንድ ማኅበረሰብ ላይ ጭፍጨፋ ማድረሳቸው፣ ጉግል ማፕ ላይ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የድንበር መስመርን ኤዲት ማድረጋቸውና ሌላም ችግር መፍጠራቸው ተደጋግሞ ሲዘገብ ነው የከረመው፡፡ ይህ ችግር መከሰቱን የመከላከያ ባለሥልጣናት ለፓርላማ ሪፖርት ባቀረቡ ወቅት አረጋግጠውታል፡፡
የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መሳተፉ ዓለም አቀፍ ውግዘት ያስከተለ ጉዳይ ነበር፡፡ መንግሥት የኤርትራ ጦር መግባት/አለመግባቱን በይፋ ባያረጋግጥም፣ ከሕወሓት ጋር በተፈራረማቸው የሰላም ስምምነቶች የኤርትራ ሠራዊት መውጣት ጉዳይ የስምምነቱ አካል ሆኖ መቀመጡ የኤርትራ ኃይሎች ድንበር መሻገራቸውን ያረጋገጠ በሚል በማስረጃነት ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
መንግሥት በመሠረታዊነት የኤርትራ ኃይሎችን በጦርነቱ መሳተፍ በይፋ ባይቀበለውም፣ ጉዳዩን የሉዓላዊነት ጥያቄ አድርገው የሚያቀርቡ አሉ፡፡
ከሰሜን ሱዳን ጋር በምትዋሰነው ድንበር የሱዳን ጦር በአልፋሽቃ በኩል ሰፊ ለም መሬትን ተሻግሮ መቆጣጠሩ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ወደቀ ለሚለው ድምዳሜ ለረዥም ጊዜ መነሻ ተደርጎ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
ከሰሞኑ በፓርላማ የመከላከያ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት ሪፖርት ያቀረቡት የመከላከያ ባለሥልጣናት ተቋሙ ከቁልፍ ተልዕኮዎቹ መካከል፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱን፣ ሕዝቡንና አገርን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ ጠላት መከላከል፤›› አንዱ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች አገር ሲወሩና የወርቅ ማውጫ ቦታዎችን ሲቆጣጠሩ መከላከያ ዕርምጃ ለምን አልወሰደም? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ የመከላከያ ባለሥልጣናቱ የአገሪቱ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ለጣሉ ችግሮች ተቋሙ የተከተላቸው የምላሽ አሰጣጥ ሥራዎች ተጠይቀዋል፡፡
የመከላከያ ባለሥልጣናቱ ግን ሠራዊቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሥራዎችን ለይቶ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ አደጋዎችን የመመከት ሥራ እያከናወነ ስለመሆኑ ነው በሰፊው ያብራሩት፡፡ ከኢትዮጵያ ድንበር ስፋት አንፃር የመከላከያን የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችል ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እያካሄደ መሆኑን ነው የተቋሙ ባለሥልጣናት በሰፊው ያስረዱት፡፡
ከመከላከያ መጠናከርና የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ በሚችል ጠንካራ ቁመና ላይ ከመገኘት ባለፈ፣ አገሪቱ ዳር ድንበሯን ለማስከበር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ፣ የደኅንነትና የልማት ሥራዎችን መሥራት እንዳለባት ነው ብዙዎች የሚመክሩት፡፡ በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በቂ መሆናቸውን የሚጠራጠሩ ግን አሉ፡፡
በወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ ተከራካሪ የሆኑትና በሱዳን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ውስጥ ለ30 ዓመታት የሠሩት አቶ ተስፉ የሺወንድም፣ ከሰሞኑ ሱዳኖች በወረሩት የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ሆነ ያሉትን ሁኔታ ይናገራሉ፡፡
‹‹ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግሥት ከሕወሓት ጋር ዕርቀ ሰላም ማውረዱን ተከትሎ ከያዙት ቦታ ለቀው መውጣት ጀምረው ነበር፤›› ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ ወዲያው ግን መውጣታቸውን እንዳቆሙና ባሉበት እንደቆዩ ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹መንግሥት ከፈለገ ከሱዳኖች ጋር በመነጋገር ጥይት ሳይተኩስ የተወረረውን ግዛት ማስለቀቅ ይችላል፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
ለሱዳንና ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ካላቸው ቅርበት አንፃር ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ወደ 200 ኪሎ ሜትር ገብተው የኢትዮጵያን ድንበር ተቆጣጥረዋል ስለተባሉት ታጣቂዎች ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ተስፉ፣ ‹‹የማይመስል ውሸት›› ሲሉ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡
‹‹ያዙት የተባለው 200 ኪሎ ሜትር በጣም ሰፊና የማይታመን ነው፡፡ እንደሚባለው ወረራውን ከውጭ የመጡ ታጣቂዎች ሳይሆኑ እንደ ኦነግ ሸኔና ጋነግ ያሉ ኃይሎች ናቸው ሊፈጽሙት የሚችሉት፤›› በማለት የግል ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ፈተና እየገጠማት ያለው በአገር ውስጥ የራሷን የቤት ሥራ አገሪቱ ባለመሥራቷ ነው የሚል ትንታኔ ይሰማል፡፡ የውጭ ጥቃት የሚጋብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች በመፈጠራቸው የሉዓላዊነት አደጋ እንደሆኑ መንግሥትም በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል፡፡
በቀጣናውና በዙሪያው ለሚፈጠሩ ተለዋዋጭ ጂኦ ፖለቲካዊ ክስተቶች እግር በእግር ተከታትሎ ምላሽ በመስጠት በኩልም፣ በኢትዮጵያ በኩል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ደካማ ስለመሆናቸው የሚተቹ አሉ፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቀው ጋዜጠኛ ኢስማኤል ቡርጋቡ በበኩሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ስለአካባቢያችንና ቀጣናዊ ጉዳዮች ግንዛቤያችን የተገደበ ነው፤›› የሚል ዕይታ ያጋራል፡፡ ከሰሞኑ በሶማሌላንድ፣ በፑትላንድና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ጋዜጠኛው ለዚህ እንደ ምሳሌ ያወሳል፡፡
‹‹ላሳኖድ በሚባለው ፑንትላንድና ሶማሌላንድ በሚዋሰኑበት አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ቀጣናዊ የኃይል አሠላለፍን የፈጠረ ነው፡፡ ሶማሌላንድ አሁን ሶማሊያና ፑንትላንድ በዚያ አካባቢ የሚኖሩትን የዱልባሀንቴ ጎሳዎች በማስታጠቅ በእጅ አዙር እየወጉኝ ነው እያለች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ግጭት ላይ የምታራምደው አቋም ከራሷ ዘላቂ ጥቅም አንፃር አብሮ የሚሄድ እስካልሆነ ዋጋ ትከፍላለች፤›› በማለትም ያስረዳል፡፡
በሶማሊያ፣ በፑንትላንድና በሶማሌላንድ ፖለቲካ ውስጥ የጂቡቲ ተፅዕኖ እየጎላ መምጣቱን የሚናገረው ጋዜጠኛው፣ ከሰሞኑ ግጭት በተጨማሪም ይህን የኃይል አሠላለፍ ለውጥ ኢትዮጵያ በቅርበት መከታተል እንዳለባት ነው ያሳሰበው፡፡