Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአገራዊው የኪነ ጥበብ ነፃነት እምን ላይ ይገኛል?

አገራዊው የኪነ ጥበብ ነፃነት እምን ላይ ይገኛል?

ቀን:

በአበበ ፍቅር

የሰው ልጅ ሐሳቡን ለሌላው መግለጽ መጀመሩ ሰዎች የጋራ  ባህሪያትን ይዘው ወደ አዲስ ለውጥ እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡ ነገር ግን የዚህ ትስስር ድንበር የለሽ መሆን ጉዳት አለው በማለት በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ ምክንያቶች መረጃን የመለዋወጡ ሒደት ገደብ እንዲኖረው ይደረጋል፡፡

ለኪነ ጥበብ ነፃነት እስከ ፈለገው ድረስ ዕድገትን እንዲያመጣ በጥብቅ ከሚቆጣጠሩትና በአስገዳጅነት ገደብን ከሚጥሉበት ተቋማት መካከል ቤተሰብ፣ የእምነት ተቋማትና መንግሥት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህን ተቋማት ከመጠበቅ አንፃር የተለያዩ አገሮች የተለያዩ የሕግ ማዕቀፍን ያዘጋጃሉ፡፡

ነገር ግን ሊገደብ የሚገባው መብት የትኛው መሆን አለበት የሚለው ሐሳብ ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

መንግሥት ራሱን እንደጠባቂና ሁሉን አድራጊ በማድረግ ይህ የተፈቀደ ነው፣ ይህ ደግሞ የተከለከለ ነው የሚል ከሆነ፣ የዜጎችን የመናገርና የመጻፍ ሐሳባቸውን በነፃነት በጽሑፍም ሆነ በሥዕል የመግለጽ መብታቸውን የሚያቀጭጭ ነው ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ይሞግታሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የኅብረተሰቡ ወካይ አለመሆኑ ኅብረተሰቡ የማይቀበላቸውንና በኅብረተሰቡ ዘንድ የተከለከሉ የሚላቸውን ነገሮች በሕግ መገደብ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

ሐሳብን የመግለጽ ገደብ መኖር የለበትም፣ ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ገደብ ማድረግ ይገባል ወደሚለው ድምዳሜም ደርሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በ1935 ዓ.ም. ‹‹የቴአትርና የሲኒማ አደራረግን ስለመመርመር›› ተብሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 37/1935 ቀዳሚው ገደብ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ለሳንሱር መሠረት የሆነው የሕግ ማዕቀፍ የተዘረጋው ከጣሊያን ወረራ መቀልበስ በኋላ በወጣው አዋጅ ነበር፡፡ በዚህ ‹‹ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን ለመመርመር በወጣ አዋጅ አንቀጽ አራት መሠረት››፣ ‹‹ማንኛውም ፊልም ቴአትር፣ ሪቪውና የተለያዩ ጨዋታዎች የጨዋታ መርማሪ ሳይመረምራቸው ለሕዝብ እንዲታዩ ማድረግ አይቻልም፤›› በማለት ይደነግግ ነበር፡፡

በመቀጠል አንቀጽ ሰባት ላይ ‹‹የጨዋታ መርማሪው›› ማንኛውም ፊልም፣ ቴአትርና ሪቪው ይህንንም የመሰል የልዩ ልዩ ጨዋታ ሕዝብ ይየው ወይም አይየው ብሎ የሚወሰን የሕዝብን ፀጥታና ንፅህና በመጠበቅ እንደሆነ ቢነገርም ሥርዓቱን የሚሸነቁጡ ማናቸውም ድምፆች ለመገደብ እንደ መሣሪያ ተደርጎ ይሠራበት እንደነበር ይነገራል፡፡

ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅትም በመጀመሪያዎቹ የሽኩቻ ዓመታት ላልተው የነበሩ ቢሆንም፣ ሥልጣኑን ማደላደሉን ተከተሎ ግን ጠንካራ ሕግና ደንቦችን በማውጣት ‹‹ሐሳብ የሚታሰብ እንጂ የሚነገር አይደለም›› በሚል ብሒል ሳንሱርን (ቅድመ ምርመራ) አክርሮ ይሠራበት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ሐሳባቸውን በጽሑፍ በንግግር በሥዕልም ሆነ በማንኛውም የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተጠቅመው ያስተላለፉ ባለሙያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንግሥትን ተችታችኋል፣ አሽሟጣችኋል ተብለው የተገደሉ፣ የታሰሩና የተንገላቱ ሰዎች በርካታ እንደሆኑ ይነገራል፡፡

ለአብነትም አቤ ጉበኛ፣ በዓሉ ግርማና ሌሎች በርካታ ደራሲዎች ዘፋኖችና ጋዜጠኞች ሐሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ የሥርዓቱ ሰለባ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን በንጉሡና በወታደራዊ መንግሥት ሥርዓቶች ወቅት በርካታ ሥራዎቹ ለሕዝብ ዕይታ ሳይበቁ እንደቀሩ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡ ከጻፏቸው 41 ቴአትሮች ውስጥ አሥራ ሁለቱ ሙሉ በሙሉ እንደታገዱባቸው፣ 21 የሚሆኑት ደግሞ ተቆራርጠው ተጥለዋል፣ ሦስቱ ግማሽ በግማሽ ወድቅ ተደርገዋል፣ ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

የደርግ ሥርዓት መገርሱ ካስገኛቸው መሠረታዊ ለውጦች አንዱ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መከበሩና የሳንሱር ቢሮ መዘጋቱ ነው፡፡ ለዚህ መብት የመጀመሪያ የሆነው በ1983 ዓ.ም. የወጣው የሽግግር ወቅት ቻርተር ነው፡፡

በዓለም አቀፉ የሰላም መብት ድንጋጌ አንቀጽ አንድ በኢትዮጵያ ያለ ምንም ገደብ ተግባራዊ የሚደረግ ሰነድ መሆኑን ከደነገገ በኋላ በተለይም እያንዳንዱ ግለሰብ የእምነትና ሐሳብን የመግለጽ እንዲሁም የመደራጀት መብት አለው በማለት አስቀምጧል፡፡

በዚህ የኪነ ጥበብ ነፃነትን ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ለመስጠት በማሰብ በ1987 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፤›› ሲል በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ላይ ደግሞ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፣ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው ማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል ብሏል፡፡ መብቱን በማስፋትም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሦስት ላይ ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከተለ ነው፤›› በማለት ተገልጿል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ነፃነት ግምገማ›› በተሰኘውና በ2010 ዓ.ም. በቀረበው ጥናት እንደተገለጸው፣ ከተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ በኋላ ለአራት ዓመታት በርካታ አርቲስቶች ያለምንም ሳንሱር ሊባል በሚችል ሁኔታ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን በምናባቸው የማሰብ፣ የመፍጠር እንዲሁም የማሠራጨት በርካታ ነፃነት ነበራቸው፡፡

ነገር ግን ሌሎች የኪነ ጥበብ ነፃነት አመለካከቶች ለምሳሌ የቅጂ መብትና የሕግ ማዕቀፍ ከለላ የመስጠት (ጥበቃ የማድረግ) ሚና፣ እንዲሁም ኪነ ጥበቡ ካለው የሕዝብ ተደራሽነት የሚገኙ የኢኮኖሚ ጥቅሞች በዝቅተኛ ደረጃ እንደሚገኝ ጥናቱ ያብራራል፡፡

የኪነ ጥበብ ነፃነት በኢትዮጵያ በመካከለኛ ደረጃ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፣ የገንዘብ ውስንነት፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ የተቋማትና የቁሳቁስ እጥረት፣ ከመንግሥት ዕውቅና አለማግኘት እንዲሁም የሰላምና ደኅንነት አለመረጋገጥ ለኪነ ጥበብ ነፃነት ዕድገት ትልቅ ማነቆ ናቸው ሲል ጥናቱ አስቀምጧል፡፡

‹‹ሰላም ኢትዮጵያ›› የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በቅርቡ በኢትዮጵያ ያለውን የኪነ ጥበብ ነፃነት በጥልቀት ለመረዳት በሚል ባስደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ ባለፉት አራት ዓመታት የታዩትን መልካም ጅምሮችና ተግዳሮቶች አሳይቷል፡፡

ጥናቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማኅበራት ኅብረትና የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮውዲሰሮች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አሁን ላይ ያለውን የኪነ ጥበብ ነፃነት በስዊድን ኤምባሲ ቅጥር ግቢ የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ገምግመዋል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች በሥራቸው ላይ ከፍተኛ አፈናና ሐሳባቸውም ሐሳብ ብቻ ሆኖ እንዲቀር እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሥራቸውም በተለይ በሚዲያው ዙሪያ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ሚዲያውን እንደፈለጉ የማድረግ አዝማሚያ እየታየባቸው ነው ብለዋል፡፡

በማስታወቂያ ሥራ ላይ የተሰማራች አንዲት ባለሙያ ‹‹በምሠራበት ሥራ ላይ የኢትዮጵያ ስም እንዳይነሳና አገሪቱን የሚገልጹ አንዳንድ ነገሮች በሥራችን ውስጥ እንዳይገቡ በመባል እየተከለከልን ነው፤›› ስትል ተናግራለች፡፡

የኪነ ጥበብ ነፃነትን ተግባራዊ ለማድረግ የተቀመጠው ሕግ ወደ መሬት ቢወርድ ኖሮ፣ ችግሮችን በወቅቱ መፍታት ይቻል ነበር ያለው የፊልም ፕሮውዲሰርና ዳይሬክተር የሆነው ዳዊት ተስፋዬ ነው፡፡

ወደፊት ምን ያመጡብኛል በማለትና በሥጋት ብዙ አስተማሪና አዝናኝ የሆኑ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ወደ ሕዝብ ሳይደርሱ ስቱዲዮ ውስጥ ተደብቀውና ቀጭጨው የሚቀሩ ሐሳቦች በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሥራ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከሕግ አስከባሪዎች ጀምሮ በሚደረገው ክልከላና መሰል እንቅፋቶች ለኪነ ጥበብ ዕድገት ማነቆ ናቸው ሲል ተናግሯል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ጠበቃ የሆኑት መሰንበት አሰፋ (ዶ/ር)፣ በኪነ ጥበብ ነፃነት ዙሪያ የወጡ ሕጎችና ደንቦችን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ሕግ ብቻውን ዋጋቢስ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥትም የኪነ ጥበብ ነፃነትን የማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ግዴታ እንዳለበት መሰንበት (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...