Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊማቆሚያ ያጣው ጎዳና ተዳዳሪነት

ማቆሚያ ያጣው ጎዳና ተዳዳሪነት

ቀን:

በየጢሻው ሥር ቁጭ ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አላፊ አግዳሚውን አባት ምሣ ግዛልኝ እናት የቁርስ ስጪኝ እያሉ ልመናቸውን አጧጡፈውታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቁራጭ የፕላስቲክ ጠርሙስ ውስጥ ያስቀመጡትን ማስቲሽ በመማጋቸው ሙሉ ሰውነታቸው የደነዘዘ ይታያሉ፡፡

ባዕድ ነገሮችን የሚወስዱበት ምክንያት አንድም ብርድ ለመከላከል በሌላ በኩል ረሃባቸውን ለማስታገስ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚናገሩት ልጆችና ታዳጊ ወጣት ጎዳና ተዳዳሪዎች ፊታቸውን ዓይቶ መጎሳቆላቸውንና ከሰውነት ተራ መውጣታቸውን መረዳት አይከብድም፡፡

በጎዳና ላይ ኑሮና አዳራቸውን ያደረጉት አብዛኛዎቹ ሕፃናት ልጆችና ሴቶች መሆናቸው ችግሩን ያጎላዋል፡፡ ገና በልጅነታቸው ጎዳና መውጣታቸው ችግሩን ይበልጥ ከማጉላቱም ባለፈ ጫት፣ ሲጋራ፣ ማስቲሽና ሌሎች መሰል ባዕድ ነገሮችን መጠቀማቸው የሰውነታቸውን ቀለም ከመቀየር ባለፈም ጤናቸው ላይ ችግር ስለመከሰቱ በጉልህ ይታያል፡፡

የሚያስላቸው፣ ዓይናቸው የቀላ፣ ከንፈራቸው የተሰነጣጠቀ፣ ከአፍና አፍንጫቸው የሚወጣ ፈሳሽ መቆጣጠር የማይችሉ ሲያወሩ ንግግራቸው የሚቀራረጥና ሐሳብ የሚጠፋባቸው እንዲሁም እጃቸው የሚንቀጠቀጥ ማየቱም የተለመደ ነው፡፡

 እነዚህ ዜጎች በፒያሳ፣ በቦሌ፣ በቦሌ ሚካኤል፣ በመገናኛ፣ በእስታዲየም፣ በብሔራዊ ቴአትርና በሌሎች ቦታዎች ላይ ካመት ዓመት የሚታዩና የሚተካኩ ናቸው፡፡

ጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማንሳትና ጤናቸውንና ስብዕናቸውን ጠብቆ ራሳቸውን ለማስቻል በመንግሥትም ሆነ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኩል ከሁለት አሠርታት ላላነሰ ጊዜ በሥራው ሲጠመዱ ቢስተዋልም እነሱም እየሠራን ነው ቢሉም ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም፡፡ በተለይም በመንግሥት በኩል የሚጀመሩ ሥራዎች ዳር ሳይደርሱ ሲስተጓጎሉ ወየም ከጎዳና የተነሱ አብዛኞቹ በታሰበው ልክ ውጤታማ ሳይሆኑ ይስተዋላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጎዳና በማንሳት በመጠለያ ማስቀመጡን፣ ወላጅና ዘመድ ያላቸውን ማገናኘቱን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ ችግሩ ግን አልተቀረፈም፡፡ አሁንም ከገጠር ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት በተለይ ምንም በማያውቁ ሕፃናት ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡

የጎዳና ልጆች ከትምህርት ተስተጓጉለዋል፡፡ ከወላጅ ዘመድ ተለይተዋል፡፡ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ለሰብዓዊ መብት ጥሰትም ተጋላጭ ናቸው፡፡

ሰሞኑን ደግሞ፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመታደግና ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡

የቢሮው የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ቅጣው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና አረጋውያን ከጎዳና ለማንሳት ቢሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሠራ ነው፡፡

በ2015 ዓ.ም. እስከ ዓመቱ መጨረሻ አሥር ሺሕ ዜጎችን ከጎዳና ለማንሳት ዕቅድ መያዙን ከዚህ ቀደም ከ17 ሺሕ በላይ ዜጎች በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉና ራሳቸውን ማቋቋም እንዲችሉ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ላይ 77 የሙያ ክህሎት ኖሯቸው መሥራት የሚችሉ ዜጎችን የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ያስረዱት ኃላፊዋ፣ ወደ ሥራ ለማስገባትና ያላቸውን ሙያ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲያውሉት ለማድረግ ክልሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከያዛቸው የሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ ትስስር በመፍጠር ውሎና አዳራቸው ጎዳና ላይ ያደረጉ 400 ዜጎችን የሥራ ዕድል ሊፈጠርላቸው እንደቻለ ወ/ሮ ገነት ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ክልል ሰበቃ አካባቢ የሚገኘው የሚድሮክ ኩባንያ 240 ማምረት የሚችሉ ዜጎችን ከጎዳና በማንሳት ወደ ሥራ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ የጎዳና ዜጎችን የማንሳት ቀጣይነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች ሆኖ በፈቃደኝነት ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የሚፈልጉትን ሕፃናት ከወላይታ ዞን ጋር ርክክብ በማድረግ ሕፃናት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን በቅርቡ 400 ዜጎችን ወደ መጡበት ቀዬ በመመለስ ከቤተሰቦቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን፣ ከእነዚህ ውስጥ 230 የሲዳማ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ማኅበራዊ ቢሮ መረከባቸውን፣ 170ዎቹን ዝዋይና ሻሸመኔ ይኖሩ የነበሩ በመሆኑ ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ከጎዳና የተነሱ ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነና እነዚህን ዜጎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከሱሳቸው አግልለው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በማዕከሉ ላይ የሕክምና፣ የምግብና የሥነ ልቦና አገልግሎቶች እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ትክክለኛ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ቢሮ ከሜቄዶንያና ከሌሎች በጎ አድራጎት ድርጀቶች ጋር እየሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ ከዓለም ባንክ በተገኘው ድጋፍ አማካይነት ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ለማንሳት ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎቹ መፍትሔ ለማበጀት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አብዛኛው የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚፈልሱት ከክልል ቦታዎች ላይ መሆኑን በተለይም በደቡብ ክልል በሕገወጥ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ለሕፃናት ልጆች የተለያዩ ሥራዎች እንዲሠሩ ‹‹ምቹ ሁኔታዎችን እንፈጥርላችኋለን›› በማለት ከቤተሰቦቻቸው እንደሚለዩዋቸው ወ/ሮ ገነት አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቢሮው ከክልሎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር እንደነዚህ ዓይነት አሠራርን ለማስቀረት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ ይኼም አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ከጎዳና ተዳዳሪዎች የፀዳች ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ ለዚህ ጉዳይ የሚሆን 45 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ በጀት መድቦ እንደነበር፣ በጀቱም አሁን ላይ ተጠናቆ እንደ አዲስ ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ብር መበጀቱን ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጎዳና የሚፈልሱት ከወላይታ፣ ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከሲዳማ ክልልና ከሌሎች ቦታዎች ጭምር መሆኑን ከዚህ በፊት ከቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለው የነበሩ ዜጎች እንደ አዲስ ጎዳና መውጣታቸውንና ይኼም ለምን እንደሆነ እንደማይታወቅ አስታውሰዋል፡፡

አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም. ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ላደረጉ 900 ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማድረጉን አሁን ላም ይኼንን አሠራር በመከተል ሌሎች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታዎች እያመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ውሎና አዳራቸው ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችም ማዕከል ውስጥ ሲገቡ አንድም የገቡበት ሱስ ከፍተኛ በመሆኑ ማዕከሉ ላይ ለመቆየት ብዙ እንደሚቸገሩና ችግሩም አሁን ላይ ጭምር እንዳለ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ጀብሎ፣ ሚዛንና ሌሎች ሥራዎችን የሚሠሩ ሕፃናት መጨረሻቸው ጎዳና ላይ መውጣት መሆኑን፣ አዲስ አበባ ላይ ገንዘብ የሚገኝ መስሏቸው የሚመጡ መኖራቸውም ችግሩን እንዳሰፋው አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎች በቂ ሙያዊ ሥልጠና እንደሚሰጣቸውና ሥልጠናውንም ከወሰዱ በኋላ ቢሮው ከተለያዩ ተቋሞች ጋር በመነጋገር የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እያመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...