Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትርጉም አልባ ሕይወት!

ሰላም! ሰላም! ሳምንት ሞልቶን እንደገና ስንገናኝ ብዙ ሐሳቦችን ይዘን እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የሐሳብ ጥራት እንጂ ብዛት ያን ያህል አላሳስብ ማለቱ ሊገርም አይገባም፡፡ በዚህም ምክንያት ይኼው እንደምታዩት የዘመናችን ሰው ሐሳቡ ሰፍቷል። ለእኛ በሚመቸንና በምናውቅበት ብሂል ለጨዋታ ስናመቻቸው፣ የእኛን ሰው ሐሳብ መስፋት ተከትሎ ወሬው በሁለት ተከፍሏል አሉ። ምንና ምን? ማለት ጥሩ። አሉን መቼም ማን ነገረህ ብሎ ጥያቄ የለም። ዕድሜ ለአሉዋውያን። ምድቡ ይኼን ይመስላል። ከፊሉ ማለት ዓለም ከአገር ይሰፋል ባዩ፣ ሲሉ ሰምቶ ወይም መሠልጠን እንዲህ ያስቀባጥራል በሚል እምነት ብቻ የሚመራው፣ ደግሞም የምር የገባው፣ በፈረንጅም በአገርኛውም መቁጠሪያም እየቆጠረ ዘመን መለወጫን፣ ገናንና ፋሲካን ሁለቴ የሚያከብረው ዘመናዊ ሲባል ወጌ፣ ሥርዓቴና ሃይማኖቴ አንድና አንድ ብቻ ነው ባዩ ደግሞ ኋላቀር መባሉን ሰማሁ። እንግዲህ ይታያችሁ ‹‹ሆድ ከአገር ይሰፋል›› እየተባልን አድገን፣ የራስንና የሌላውን መለየት አለመቻል መሰለኝ ግራ አጋብቶ ከወጪ ወራጁ ጋር የሚያላትመን፡፡ አንዱ በቀደም ዕለት ድንገት ሳላስበው ከአቋራጭ መንገድ ውስጥ ብቅ ብሎ፣ ‹‹አንበርብር ሚናህን ለይተሃል ወይስ አሁንም መሀል ሰፋሪ ነህ…›› ሲለኝ፣ በቀትር ምን ዓይነቱ ጋኔን ገጠመኝ ብዬ ሳማትብ ከአጠገቤ ጭልጥ ብሎ ጠፋ፡፡ ምነው እንደ እሱ ችግሮቻችንና ፈጣሪዎቻቸው ጭልጥ ብለው በጠፉልን ያሰኛል እኮ፡፡ አይደል እንዴ!

ከዘመናዊ እስከ ኋላቀር ያለውን ትርክትና ርቀት መቼም የተጓዘ ያውቀዋል። እናም እኛ ደግሞ ጥሎብን ከዕውቀቱ ጭቅጭቁ ይቀድምብናል። እንዴት ማለት ጥሩ። መቼ ዕለት አዛውንቱ ባሻዬን ከዘመናውያን ምድብ አንዱ ያገኛቸውና የኩዳዴን ፆም አስመልክቶ፣ ‹‹እንኳን ለፆመ ልጓሙ አደረሰዎ ባሻዬ…›› ይላቸዋል። ባሻዬ እንኳን እርጅና ይዟቸው ገና ያኔ በብላቴናነታቸው በዱር በገደሉ አርበኛ ያደረጋቸው የአበው ልማድና ባህል እንከን ስለሌለው፣ ‹‹አንተ እንዴት ሆኖ ነው ለፆም እንኳን አደረሳችሁ የሚባለው?›› ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡለት፣ ‹‹እኔ እኮ ፆም ሲያዝም ሆነ ሲፈታ የአገር ወግ ነው ብዬ ነው…›› እያለ ሊያስረዳቸው ሞከረ፡፡ ‹‹ማን ነህ አንተ፣ እንዲህ ዓይነቱን ግብዝነት ማን እንዳስተማረህ ባላውቅም፣ አንተም ሆንክ እኔ ስንፆም እንደ ግብዞች ፆማችንን እያስተጋባን መሆን የለበትም፡፡ ፆም ማለት የመንፈስ ምግብ ስለሆነ በዝምታና በአርምሞ ነው የምንፆመው እንጂ፣ እንደ ፈሪሳውያን በየአደባባዩ እየደሰኮርንለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ልክ ለኮረና ቫይረስ አፋችን ላይ ጣል እንዳደረግነው ማስክ፣ ፆምም በዚህ ወቅት አፋችንን እፍን አድርገን የምንይዝበት መሸፈኛችን ነው…›› ብለውት አሰናበቱት፡፡ እንዲህ ነው እንጂ!

ባሻዬ ይህንን የመሰለ ማሳሰቢያቸውን ከተናገሩ በኋላ፣ ‹‹እንዲያው ከዚህ ሁሉ ከቤቴ ባልወጣስ ብለው…›› ቤታቸው ገብተው ተቀመጡ። መቼም የቤት ጥያቄ ባይኖርብን በዚህ ነገር ሁሉ ግራ ግራ በሚጫወትበት ዘመን ከቤት ባንወጣ የምንወድ ብዙ ነን። እና ባሻዬም ቤት ተቀምጠው ሲዲያቸውን ከፍተው የበገና መዝሙር እያዳመጡ ይህንን ዓለም የረሱ መሰሉ። እሳቸው በወጣትነታቸው ከቢጤዎቻቸው ጋር ያለፉበትን ውጣ ውረድ ሲነግሩኝ የነበረው ትዝ እያለኝ የእርጅናቸው ዘመን ሲታወሰኝ ቅር አለኝ። ባሻዬ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሃይማኖታዊ ምግባር ተኮትኩተው ማደጋቸውን፣ በድቁና ጭምር ማገልገላቸውን፣ በውትድርና ደግሞ ለበርካታ ዓመታት በቆላውና በደጋው ተሰማርተው የሚፈለግባቸውን መወጣታቸውን ፊት ለፊት ሳይሆን በገደምዳሜ ሲናገሩ፣ ለሌሎች መልካምነትን ለማስተማር እንጂ በጀብደኝነት ለመገበዝ እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ አንድ ጊዜ አንዱ በቴሌቪዥን ቀርቦ፣ ‹‹እኔ አገሬን ለማገልገል ያልወጣሁበት ጋራ ያልወረድኩበት ቁልቁለት የለም…›› እያለ ሲናገር፣ ‹‹ልጅ አንበርብር፣ ድሮ እኛ የምናውቀው አንድ ሰው ሲፎክር እነ እከሌ ስለእኔ ይናገሩ እንጂ እኔ አልናገርም ነበር የሚለው፡፡ ዛሬ የእኛ ሰው ምን ነክቶት ነው አገር አይብቃኝ እያለ የሚንጣጣብን…›› ያሉት አይረሳኝም፡፡ ወቸ ጉድ!

በሌላ ማዕዘን ደግሞ ከሚታየውና ከሚሰማው ሁሉ ውስጠ ሚስጥሩን መበለት የሚያቅተን በዝተናል። እንዲያው ከሁሉ ከሁሉ የገረመኝ ለሚታየውና ለማይታየው ነገር የሚሰጠው ክብደት እያደር እንደ ኑሮ ኪሎ እየጨመረ መምጣቱ ነው። ማለት ስንቱ በሕይወት ባህር ውስጥ በሥውር የበደል ማዕበል ህልውናውን እየተነጠቀ እንዳለ እያወቅን፣ የምናወራውና የምናስወራው በዓይን የምናየውን ብቻ ነዋ። እውነቴን እኮ ነው። የህሊና ካሳና የሞራል ስብራትን እውነት በአሁን ዘመን ማን ነው አክብዶ የሚያያቸው? አሁን በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ ደንበኛዬ የቶርኖ ማሽን ገዝቶ አስመጥቶ ለመሸጥ ያስባል። ወንድሙ በደህና ጊዜ አንገቱን ያስገባ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ሰው ስለሆነ የማስጫኑን ነገር በእሱ በኩል እጨርሳለሁ ብሎ ሙሉ እምነቱን ጥሎ፣ ከተማው ውስጥ አሉ የሚባሉትን ማሽኖች እየዞርን አብረን አየን። ማስመጣት ስላለበት ማሽን ዓይነትና ሞዴል በቂ መረጃ አሰባስበን ስንጨርስ ገንዘቡ በወንድሙ የባንክ ቁጥር አስገብቶ መጠባበቅ ያዘ። በጣም እኮ ነው የሚገርማችሁ? ወንድምዬው አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ክዶት አያርፍ መሰላችሁ? ቢባል ቢሠራ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ አለ አሉ። ውል የለ ማስረጃ የለ ሕግስ ምን ብሎ መሀል ይግባ? ይኼው የተለመደችዋ መደገፊያዬ ላይ ሆኜ አላፊ አግዳሚውን ሳስተውል መለ መላውን አብዶ ሲሮጥ አየሁት። ወይ ዘንድሮ!

 ‹‹የማይታይ የማይታየውንማ ለፈጣሪ መተው ነው አንበርብር። ወይ ጉድ አስኪ መጀመሪያ ማየት የቻልነውንም በደንብ እናፅዳው…›› ይሉኝ የነበሩት ባሻዬ ናቸው፣ ከአቅም በላይ ለሆነ ነገር ምን ማድረግ ይቻላል ሲሉ። ሳስበው ባሻዬ የተናገሩት በጣም እውነት ነው። አጠገባችን ዓይን ያወጣ ዘረፋ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሕገወጥነት እያስመረረን ችግራችንን አራግፈን ሳንጨርስ ስለማይታዩት የህሊናና የሞራል ወንጀሎች ልናወራ እንደማንችል ገባኝ። አሁን ይኼን ሁሉ ስለታየ አይደል ማንሳታችን? ታዲያ አንድ ወዳጃችን፣ ‹‹ይገርማል ለመጠጥ የሚሆን ውኃ በወጉ በቧንቧ ማግኘት የሚያቅተን በውኃ ዕጦት ስንሞት ምን ይባላል?›› ሲለን ስለእኛ ‹አብስትራክት› የኑሮ ቋጠሮ ማንም ምንም ማለት እንደማይችል ገባኝ፡፡ ጊዜው ቆየት ቢልም አንድ አዛውንት የነገሩኝ አይረሳኝም፡፡ ‹‹አቶ አንበርብር፣ እኔ በዚህ ዕድሜዬ የተረዳሁት ቢኖር ከዛሬ ትናንት፣ ከነገ ደግሞ ዛሬ እንደሚሻል ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ እርጅናዬ ድረስ ሁሌም ነገ ያስፈራኛል፡፡ ትናንት መከባበርና መፋቀር ጠፋ ብለን በቁጭት ስንናገር እንዳልነበረ፣ ዛሬ ደግሞ እሱም ቀርቶብን በሰላም ወጥተን በገባን ማለት ጀመርን፡፡ ነገ ደግሞ የባሰ ይመጣና በገዛ ቤታችን ወይም ደጃችን መቆም ወይም መቀመጥ ያቅተን ይሆናል…›› ነበር ያሉኝ፡፡ ትንቢት ሳይሆን አይቀርም!

ደግሞ አለላችሁ የቱንም ያህል ያሰብነው ቢሳካ የወጠነው ቢሰምር ያለ ጤና ምንም ዋጋ እንደማይኖረው ከተረዳሁ ቆይቻለሁ። ‘እያዩት ከማይበሉት ሰዎች ተርታ አያስቆጥራችሁ’ ነው አሉ የሚባለው ድሮ። አይ እኛ መቼም አሉ ስንወድ እኮ፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ ባለፈው ሰሞን ከዕድር ስብሰባቸው ሲመለሱ፣ ‹‹አቤት፣ እግዚኦ አንተ ፈጣሪ…›› እያሉ ሲራመዱ አገኘኋቸው። እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንስተው ረቂቅ ትዝብታቸውን ለአምላካቸው ይኸው ብለው እንደ ንድፍ የሚያሳዩት ይመስላሉ። ‹‹ምነው ባሻዬ?›› ስል እንደ ልማዴ፣ ‹‹እንዲያው ማን ይሆን ጤነኛ ዘንድሮ አንበርብር? ሰው ሁሉ ጉዱን ከኋላው ደብቆ ነው ለካ የሚኖረው?›› ሲሉኝ ምን ሰምተው እንደሆነ አልጠየቅኳቸውም። ምድረ ሙሰኛ እንደ ቀበሮ ካለበት ጉድጓድ እየታደነ ለሕግ መቅረብ ባለበት ጊዜ የምን ጥያቄ ማብዛት ነው እሱ? ይልቅ የገረመኝ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ነው። በስርቆትና በሕገወጥ መንገድ ዘመናችንን በሙሉ ለምን የተደላደለ ነገር ይዘን ለመኖር እንደምንደክም ሳስበው ብቻዬን ገርሞኝ እስቅ ጀመር። ወደው አይስቁ እኮ ነው፡፡ ስለዚህ አመራማሪ ስለሆነ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ከባሻዬ ጋር ስንጨዋወት፣ ‹‹ይኼ አሁን የምትለኝ ነገር ከጥንትም ከእነ አዳም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለ አመል ነው። ቀናው እያለ ጠማማውን፣ ፊት ለፊቱ እያለ ጓሮውን፣ ብርሃን እያለ ጨለማ ጨለማውን መሄድ ነው የምንወደው። እንዴት ያለ ባህሪ ነው ግን?›› ብለውኝ ባሻዬ ራሳቸው እጅግ ገርሟቸው ሳቁ። በዚህ መሀል ስለሰው ልጅ በሥልጣኔ መገስገስና መራቀቅ ለማሰብ ሞከርኩ። ጨርሶ የሚዋጥልኝ ነገር አልሆነም። ሰው ሰውን የሚጥልበትን ገደል እየማሰ፣ ለሰውነቱም ለአዕምሮውም ጤና የማይሰጠውን የሕዝብ ገንዘብ እየቀማ፣ የአገርን ኢኮኖሚ ለማድማት የማይገባበት ሲገባ ስታዩ እውነት 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ነን ወይስ የጋርዮሽ ዘመን ላይ ትላላችሁ እኮ፡፡ ‹እያወቁ አለቁ› ነው በደፈናው የእኛ ነገር!

የሆነው ሆነና ማምሻም ዕድሜ ነውና የሸቃቀልኳትን ቆንጥጨ ይዤ ከፊሉን ለማንጠግቦሽ የቤት ወጪ አድርጌ፣ ከፊሉን ወደ ‹አካውንቴ› ወርውሬ ወደ ሠፈር አዘገምኩ። ስደርስ ድብልቅልቅ ጠበቀኝ። በሐሳቤ ብዙ ነገር ይመላለሳል። ማን ዓይን በዓይን ተከድቶ ይሆን? እህ ስል የአንድ ወዳጃችን ታናሽ ወንድም ራሱን ሰቅሎ በገዛ ፈቃዱ ከዚህ ዓለም መሰናበቱን ሰማሁ። ደግሞ በቅርብ አውቀዋለሁ። አርጋጅ አሸርጋጁ፣ ‹‹እንዲያው ምናለበት ፆሙን አሳልፎ ከፋሲካ በኋላ ቢሰቀል?›› ሲልም እሰማለሁ። ‹‹አሁን እስኪ ዕለቱን መዋል ያቃተውን ሰው በዓል ውሎ ቢሰቀል ብሎ ነገር’ ብዬ ሳስብ ብሽቀት ይይዘኝ ይጀምራል። ዕንባና ትዝብት በህልውናዬ ሰርጥ እሰጥ አገባ ገጥመው መንፈሴ ደቀቀ። ባሻዬ ገና ያኔ ከቤት መውጣታቸው ነው። ‹‹የት ይደርሳል የተባለው ገና መንገዱን ሳይጀምር እንዲህ ሩብ መንገድ ላይ ሲታጠፍ፣ መንገዱን የጨረሱት ምን ይሉት ይሆን?›› ስል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሰማኝ። ‹‹ሩጫዬን ጨርሻለሁ ነዋ…›› ብሎ ተኮሳትሮ መለሰልኝ። የምይዝ የምጨብጠው ሲጠፋኝ፣ ማንን ማፅናናት ማንን ማረጋጋት እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ፣ እሱን ከለቅሶው መሀል ጎትቼ ይዤው ጠፋሁ። ኑሮአችንም ሕልፈታችንም እንደ ሰው ስሜት እየተለካ አቃቂር ሲወጣለት፣ አንዳንዴ ዞር ብሎ መለስ ማለት ሳይሻል አይቀርም፡፡ እውነት ይመስላል!

በሉ እንሰነባበት። እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግሮሰሪ ደርሰን አንድ አንድ እያልን ተዘጋግተን ተቀምጠናል። ያየኛል አየዋለሁ። ቆይቶ ግን፣ ‹‹ስማ እንጂ አንበርብር?›› ብሎ ጀመረኝ። ‹‹ወይ?›› ስለው፣ ‹‹አይገርምም ግን የዚህ ዓለም ነገር?›› ብሎ አፈጠጠብኝ። ‹ተገራሚ መሆኔን አምነህ ሳለ መልስ እንዳለው ሰው ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?›› ስለው ድምፁን ዝግ አድርጎ፣ ‹‹ተመልከተው እስኪ ሰውን… ይሠራል… ይደክማል… በውጣ ውረዱ ሁሉ ተስፋውን በሚተማመንበት አምላኩ ላይ አድርጎ ይውላል… ያድራል… ነገር ግን ይኼው የአንዱ ውልደት ለሌላው የድሎትና የፈንጠዝያ ኑሮ… የአንዱ የትግልና የፍልሚያ ኑሮ ለሌላው የውለታ ቢሶች መፈንጫና ማደሪያ ሆኖ ይቀራል… አይገርምም?›› ሲለኝ ለማለት የፈለገው ቢገባኝም ምንም እንዳልገባው ዝም አልኩ። ድንገት ተወልዶ ድንገት ከሚሞተው የምስኪኑ ሰው ልጅ ሞት ይልቅ እኔን ያሳስበኝ የነበረው የሕይወት ትርጉም ነበር። ዛሬ ጊዜ ትርጉም አልባ ሕይወት የሚኖረው አላንስ ብሎ ሕይወት ትርጉም እንዳላት የረሳነው በዝተናል። ገንዘብ፣ ዝና መብልና መጠጥ የኑሯችንና የሐሳባችን ጣሪያ ሆነዋል፣ መጥኔ። ግን ደግሞ ሕይወት በዚህ አበቃ ስትሉት ዞሮ ልደት ሆኖ ይመጣል። ከልደት አንስተን እስከ ትንሳዔያችን የምንሸከመው መስቀል ላይቀል በገዛ ራሳችን ላይ በቁምም በአካልም ሞት የምንፈርደው በዝተናል። በበኩሌ ያቅልል ብያለሁ። አንዳንዴ እኮ ከማይጋፈጡት ባላጋራ ጋር ከመታገል ዞር ማለትም ጥበብ ነው፡፡ አለበለዚያ ሕይወት ትርጉም አልባ ሆኖ ብዙ እንከፋለን፡፡ ትርጉም አልባ ሕይወት ደግሞ ደስ አይልም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት