Tuesday, June 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቮክስዋገን ኩባንያ በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች እንዲደረግ ይፈልጋል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የቮክስዋገን ተሽከርካሪዎች ለማምረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው የጀርመን ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች እንዲደረግ ይፈልጋል ተባለ፡፡

የቮክስዋገን ኩባንያ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር እ.ኤ.አ በ2019 መጀመሪያ መፈራረሙ የሚታወስ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ግን ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ሳያደርግ ቆይቷል፡፡

በቻይና፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአልጄሪያ፣ በኬንያና በሩዋንዳ መገጣጠሚያዎች የከፈተው ግዙፉ የአውሮፓ መኪና አምራች ኩባንያ ኢትዮጵያ ገብቶ ለመሥራት ከገደቡት ውስጥ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አስመልክቶ የተዘጋጀ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ እንደሚገኝበት፣ በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኦኑር የል ገልጸዋል፡፡

የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ከመኪና አምራች ኩባንያው ተወካዮች ጋር ባደረጉት ንግግር፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ ለመምጣት እንዲያመነታ ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አስመልክቶ ያለው የሕግ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ለአብነትም ID.4 እና ID.6 የተባሉ የኤሌክትሪክ መኪና ሞዴሎች ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡና እነዚህ ለቻይና ገበያ ተብለው የሚመረቱ መኪኖች ኢትዮጵያ ውስጥ የጥገናና የሰርቪስ አገልግሎት ማን ይሰጣቸዋል የሚለው በሕግ ማዕቀፍ ያልተዘጋጀ በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ ካልተስተካከለ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጁ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል ብለዋል፡፡

ኦኑር እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ ኢምፖርትን ጨምሮ በሌላውም ዘርፍ በፍጥነት የሚለዋወጡ የመመርያ ማሻሻያዎች በተለይ ለውጭ ባለሀብቶቹ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም በዚህ ላይ ተቀራርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግና መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እያለው፣ በዚያ ላይ ተደጋጋሚ መመርያዎች የሚወጡ ከሆነ የኢንቨስተሩን እምነት ይሸረሽራሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ቆይታ የነበራቸው በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኦር የጀርመን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሊሻሻል እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከአጋር ተቋማት ጋር በጋራ ያዘጋጀው የአውቶሞቲቭ ፖሊሲ ረቂቅ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ባለፈው ዓመት የገለጸ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ተጠናቆ ወደ ሥራ አለመግባቱ ይታወቃል፡፡

የፖሊሲ ረቂቁ የተዘጋጀው የአውቶሞቲቭ ዘርፍ እየሰፋ በመምጣቱ መሆኑንና በፖሊሲ የተደገፈ አሠራር መዘርጋት በማስፈለጉ እንደነበር ከዚህ ቀደም የተገለጸ ሲሆን፣ የአውቶሞቲቭ ረቂቅ ፖሊሲው የዘርፉን አሠራርና ዕድገት በፖሊሲ የተደገፈ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ መንግሥት በአውቶሞቲቭ ዘርፉ የተሰማራውን የግሉን ዘርፍ የሚደግፍበትን አሠራር ለመፍጠር ያግዛል ተብሎ ነበር፡፡

ቮክስዋገን ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገባ ከተፈለገ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ የሕግ ማዕቀፎች ሊሰናዱ የሚገባ መሆኑን ኦኑር ገልጸው፣ በተጨማሪም በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀቀም ያሉ አሠራሮችም ለኢንቨስተሩ ምቾት በሚሰጥ መንገድ መቃኘት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የጀርመን ኤምባሲም በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲሁም በልማት አጋሮች በኩል ጉዳዮን እየተነጋገረበት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ 

በተያያዘም ‹‹ሜድ ኢን ጀርመኒ – አፍሪካ›› የተሰኘ የጀርመንና የአፍሪካ አገሮችን የንግድ ግንኙነትን ለማሳደግና በንግዱ ዘርፍ ለአፍሪካ ኢንዱስትሪዎች ዕድል ለመስጠት የተዘጋጀ የንግድ መድረክ፣ ከየካቲት 23 ቀን 2015 ጀምሮ እስከ የካቲት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሏል፡፡

ከ2,500 በላይ ጀርመናዊያንና አፍሪካዊያን ባለሙያዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ዲፕሎማቶችና የመንግሥት አካላት በመድረኩ ላይ በመገኘት የንግድ ትስስሮችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ታውቋል፡፡

‹‹ሜድ ኢን ጀርመኒ – አፍሪካ›› የንግድ መድረክ የተዘጋጀው በጀርመን የንግድ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍና በንግድና ባዛር ቡድን እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ አዘጋጅነት ሲሆን፣ የተዘጋጁ ታዋቂ የምርት መለያዎችን፣ ምርቶችንና አገልግሎቶች ከመቅረባቸው በተጨማሪ የጀርመንና የአፍሪካ ባለሙያዎች፣ የአፍሪካ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በጥራት ማደራጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች