Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሊዝ ፋይናንስ አዋጁን የማይረዱ አስፈጻሚ አካላት መኖራቸው ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ የሊዝ ፋይናንስ ተቋማትን በመደገፍ ረገድ ለውጦች ቢኖሩም፣ ነገር ግን የሊዝ ፋይናንስ አዋጁን በትክክል የማይረዱ የመንግሥት አስፈጻሚዎች መኖራቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የሊዝ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ሰብሳቢና የአዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሳይ እንሴኔ፣ በሊዝ ፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ የሚገኘውን አዋጅ በትክክል የማይረዱ ፈጻሚ አካላት መኖራቸውን ገልጸው፣ መመርያዎችና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን ብቻ ሳይሆን ዋናውን አዋጅ በደንብ ያልተረዱ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አሉ ብለዋል፡፡

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አዋጁን በደንብ ካለመረዳት በሚፈጥሩት ክፍተት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ኢንተርፕራይዞች ተጎጂ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሊዝ ፋይናንስ ሥርዓቱ አንድ ማሽነሪ ከውጭ ሲመጣ ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ነፃ ነው የሚባል ሲሆን፣ ይህንን የሚተገብሩና የሚከታተሉ የመንግሥት ተቋማት ብዙ እንደሆኑና እነዚህ ተቋማት ተናበው በማይሠሩበት ወቅት፣ የኢንተርፕራይዞች ጊዜና ሌሎች ብክነቶች እንደሚያጋጥሙ አቶ መሳይ ተናግረዋል፡፡ ይኼ ጉዳይ በቀጣይ በሥርዓቱ እየተቀረፀ የሚስተካከልበትና ሁሉም ተቋማት ተናበው (የመንግሥት አካላት በተለይ) የሚሠሩበት ሁኔታ ከተፈጠረ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው የተሻለ እንደሚሆን ሰብሳቢው አክለዋል፡፡

 በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ የሚሉት አቶ መሳይ፣ ከተቋማት ተቋማት የቅንጅት ሥራው ላይ ራሱን የቻለ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የፖሊሲ አይደለም፡፡ ችግሩ ተናቦ የመፈጸም (Implementation)፣ እንዲሁም በቅንነት የመተግበር ችግር ነው፤›› ብለው፣ በአንዳንዶቹ ፖሊሲዎች ላይ ክፍተት ሊኖር ቢችልም ዋና ገዥ ምክንያት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ባለው ፖሊሲ መሥራት አለመቻል ትልቁ በአገሪቱ ያጋጠመ ችግር መሆኑን፣ ፖሊሲውን ከመተግበር አኳያ በተለይ ቅንጅታዊ ሥራው ላይ በሚገባ መታሰብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሊዝ ፋይናንስ ተቋማት የአምራች ዘርፉ ድጋፍ አጥቷል በሚል የተቋቋሙ ሲሆኑ፣ ተቋማቱ በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ፍላጎት፣ ዕውቀትና ሙያ ኖሯቸው በካፒታል እጥረት ምክንያት መሥራት ላልቻሉ፣ ኢንተርፕራይዞች የተወሰነ የጊዜ ገደብና ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠው፣ የካፒታል ዕቃን በማቅረብ የፋይናንስ እጥረታቸውን የሚቀርፉ ናቸው። 

 በአብዛኛው የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ አገሮች እንዲያድጉ ትልቅ ሚና የተጫወተው የሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከ20 እና 30 ዓመታት በፊት ወደ ተግባር ያልተገባበት የሊዝ ፋይናንስ ሥርዓት ከስድስት ዓመታት ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ የተገባበት እንደሆነ፣ ይህንን በማጠናከር ችግሩን ፈትቶ መሄድ ከተቻለ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የማትተናነስበት ዕድል እንደሚፈጠር  ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል በሊዝ ፋይናንስ ተቋማት በኩል እየተከናወነ ያለው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ እንደመጣበት ይስተዋላል የተባለ ሲሆን፣ አሁን የንግድ ባንኮችም ሆኑ ማይክሮ ፋይናንሶች ደፍረው በዘርፉ ሊሳተፉ የሚችሉበት አቅም እየተፈጠረ ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡

አቶ መሳይ እንዳስታወቁት፣ ከፋይናንስ ተቋማት በኩል ብቻ ሳይሆን ከአምራቹ ወይም ከኢንተርፕራይዞች በኩል የሚጠበቁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ አምራቾች አገልግሎቱን የማወቅ፣ የሚጠበቅባቸውን ሁኔታ የመረዳትና አውቀው ወደ ሥራ መግባትና ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማኅበር እስካሁን በአዲስ አበባ ከአራት ሺሕ በላይ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ለሚያወጡ ማሽነሪዎች የብድር አገልግሎት መስጠቱን የተናገሩት አቶ መሳይ፣ በተያዘው ዓመት ደግሞ 373 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ማሽነሪዎችን ለ578 ኢንተርፕራይዞች ተላልፈው ወደ ሥራ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች