‹‹የቦረና ውኃ ኔትወርክ ፕሮጀክት›› የተሰኘው ከተጀመረ በትንሹ 16 ዓመታት ያለፈው ሥራ አስካሁን የመጀመሪያ ምዕራፍ አለመጠናቀቁ ታወቀ፡፡ የፕሮጀክቱ መዘግየት ለቦረና ዞን በድርቅ ክፉኛ መጎዳት ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ በአምስት ወረዳዎች ውስጥ በአምስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ እያንዳንዱ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ከከርሰ ምድር ውኃ አውጥቶ በግዙፍ ታንከሮች በማከማቸት ለመጠጥ፣ ለከብቶችና ለግብርና በትልልቅ ቱቦዎች ውኃ ያቀርባል ተብሎለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን የመጀመሪያው ምዕራፍ ራሱ ሳይጠናቀቅ 65 ከመቶ ላይ ቆሟል፡፡
አምስት ውኃ ጉድጉድና ትልልቅ ማከፋፈያዎች እያንዳንዱ በስሙ አሬሮ፣ ድቡሉቅ፣ ወይብ፣ ጎበሌና ኤሎዬ ወረዳዎች ታስቦ ነበር፡፡ በእነዚህ የቦረና ወረዳዎች በአሁኑ ሰዓት ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በዘለቀው ድርቅ ከብቶችና እንስሳት በብዛት የሞቱበትና ሰዎች የተጎዱበት ወረዳዎች ናቸው፡፡
እያንዳንዱ ፕሮጀክት አንድ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ሲሆን፣ በጥቅሉ አምስት ቢሊዮን ብር ያወጣል ተብሎ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ወጪው ከዚያ ከፍ ማለቱ ተነግሯል፡፡ እስካሁን የተጀመው የአንድ ወረዳ ውኃ ጉድጓድ ሲሆን ይህም 66 ከመቶ ገንዘቡ ተከፍሏል፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያ ምዕራፍ ፕሮጀክት በመጠኑ ለውጥ ያሳየው ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲሆን አሁን 65 ከመቶ ደርሷል፡፡
የቦረና ዞን ውኃና ኢነርጂ ኃላፊ አቶ ዲዳ ጨርቆሌ ግንባታውን እያከናወነ ያለው የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው፡፡ አማካሪው ደግሞ የኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ሥራዎች ነው፡፡ ‹‹በፕሮጀክቱ መጀመሪያ የዲዛይን ችግር አለበት ተብሎ እንደገና ዲዛይን ተሠራ፡፡ ከዚያ ደግሞ በተደጋሟ የሚቀርበው ምክንያት የትቦ ምርትና አቅርቦት የለም የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡
የመጀመሪያ ፕሮጀክት 82 ኪሎ ሜትር ቱቦ ዝርጋታ የሚጠይቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት 50 ኪሎ ሜትር ቱቦ ብቻ ተገንብቷል፡፡
ለፕሮጀክቱ ቱቦዎችን ያቀርባል ተብሎ የነበረው የኦሮሚያ ቱቦዎች ማምረቻ ፋብሪካ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አልቻለም ቢባልም፣ ምንጮቹ የፕሮጀክቱ ገንዘብ ባለፉት 15 ዓመታት በክልሉ በተፈራረቁ መሪዎች መበላቱን ይገልጻሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ገንዘብ በየዓመቱ ሲለቀቅ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
‹‹ፕሮጀክቱ አንዴ በኦሮሚያ ክልል ሌላ ጊዜ በፌዴራል መንግሥት ሥር እየገባ ሳያልቅ ቆይቷል፤›› የሚሉት ደግሞ አቶ ጃርሶ ቆንጮሮ የቦረና ዞን ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡ እስካሁን 3.3 ሚሊዮን ከብቶች የሞቱ ሲሆን እስካሁን አስቸኳይ ዕርዳታ ያልደረሳቸው 263 ሺሕ ሰዎች አሉ ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ሰሞኑን 14 ሚሊዮን ዶላር ለቋል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሥር ይቀጥላል የሚል ውሳኔ መኖሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በእርግጥ አቶ ዲዳና አቶ ጃርሶ ኮርፖሬሽኑ ይቀጥል ወይስ ሌላ ኮንትራክተር ይመረጥ የሚለው አልተወሰነም ይላሉ፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ (ዶ/ር) ሀብታሙ ኢተፋ ለሪፖርተር እንደለገጹት፣ ከኮንትራክተር መረጣው በፊት ጥልቅ ግምገማ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ ‹‹በዛሬው ዕለት (ረቡዕ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም.) ወደ ቦረና ዞን እናቀናለን፡ የፕሮጀክቱን መዘግየት በጥልቅ ገምግመን ውሳኔ እናሳልፋለን፤›› በማለት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡