Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ባለመውጣቱ በኤሌክትሪክ ዘርፍ ብቻ 534 ሚሊዮን ብር መባከኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ2006 ዓ.ም. የፀደቀን አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ባለመውጣቱ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ በሚካሄድበት ወቅት በተቋማት ቅንጅት ማነስ በሚፈጠር የመረጃ ዕጦትና በውስጣቸው በሚታይ የአሠራር ጉድለት የተነሳ፣ በኤሌክትሪክ ዘርፍ ላይ ቢያንስ 534 ሚሊዮን ብር መባከኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ጋር በ2012 እና በ2013 ዓ.ም. በተጀመሩና በተመረጡ 242 የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ አካሄድኩት ባለው ጥናት፣ በመሠረተ ልማት ቅንጅት አለመጣጣም ምክንያት በርካታ የአገር ሀብት መባከኑን በሚኒስቴሩ የአገራዊ የተቀናጀ መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ተገኝ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በኤሌክትሪክ ዘርፍ የደረሰው የሀብት ብክነት ለአዲስ ማስፋፊያ ሥራ ቢውል ኖሮ 1,100 መካከለኛ መስመር መዘርጋት የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች መግዛት ይችል እንደነበር አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሰብስቴሽን በ40 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ርቀት ውስጥ በሚገኙ አምስት ከተሞች፣ በየአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት የ23 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ ማካሄድ ያስችል እንደነበርም አክለዋል፡፡

በጥናቱ የተዳሰሱት 242 የመንገድ ፕሮጅክቶች በአማካይ መጠናቀቅ ከነበረባቸው ጊዜ በ25 ወራት የዘገዩ ሆነው መገኘታቸውን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሌላ በኩል የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከተመደበላቸው አጠቃላይ በጀት እስከ 200 ፐርሰንት ድረስ ተጨማሪ ጠይቀዋል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ጥናቱ እንደሚያሳየው የቅንጅታዊ አሠራር ጉድለት የተነሳ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ከአገልግሎት ሽያጭ ያገኝ የነበረውን 11 ሚሊዮን ብር በየወሩ ያሳጣው መሆኑን፣ በውኃ ብክነት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በዚህ የመረጃ ክፍተትና ቅንጅታዊ አሠራር ጉድለት፣ ከአጠቃላይ የውኃ አቅርቦት ውስጥ ከ37 እስከ 41 በመቶ እንደሚባክን አስረድተዋል፡፡

የአስፈጻሚ አካላት ሥራን በኃላፊነት ወስዶ የማስፈጸም ድክመት መኖሩን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በ2006 ዓ.ም. ለፀደቀው የፌዴራል መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ባለመውጣቱ፣ ተቋሙን ጥርስ እንዳይኖረው ስለማድረጉ ተናግረዋል፡፡ ይህም ሊከሰት የቻለው በመሠረተ ልማት ቅንጅት አዋጁ መሠረት የማይሠሩ ተቋማት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ቢገለጽም፣ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወሰድ ግን ስለማያብራራ ነው ብለዋል፡፡ ለአዋጁ ማስፈጸሚያ የሚሆነው ደንብና መመርያ በዚህ ዓመት ተጠናቆ እንደሚፀድቅ አቶ ቴዎደሮስ ተናግረዋል፡፡

ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች ጋር በተገናኘ ክልሎች በፌደራል መንግሥት ለራሳቸው መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚሰጠውን ገንዘብ መንግሥታዊ ካልሆነ የዕርዳታ ድርጅት የሚመጣ እንደሚያስመስሉት፣ አጠቃቀማቸውም ከመጠን ያለፈ መሆኑን በመግለጽ በርካታ ገንዘብ በካሳ እየተከፈለ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ልክ ያልሆነ የካሳ አጠቃቀም ሊያስተካክል ይችላል የተባለለት አዲስ የካሳ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ በዝግጅት ላይ ባለው ረቂቅ አዋጅ የካሳ ልኬት ኃላፊነቱን ለክልሎች የሚሰጥ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታያውን ወጥ ያልሆነና በተለይም በአንዳንድ አካባቢ ብቻ በሚገኙ ቀበሌዎቸ መካከል አንዱ ከሌላው በአንድ ድንበር ላይ ያሉ ቦታዎች የሚቀርብን የተለያየ ዓይነት የካሳ ክፍያ ጥያቄ ለማስተካከል፣ በቀጣይ የሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶቸ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በሚኒስቴሩ በተቋቋመ ራሱን የቻለ የሀብት ግመታ ሥራ አስፈጻሚ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱ ተጠቁሟል፡፡

ይህ የሀብት ግመታ ሥራ አስፈጻሚ በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የእርሻ መሬት ምን ያህል የሰብል ምርት እንደሚያመርት በማጥናት፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከክልል ግብርና ቢሮዎች መረጃ በማሰባሰብ ለሚኒስቴሩ ያቀርባል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች