Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፋይናንስ ተቋማትና በሜትር ታክሲ አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ...

በፋይናንስ ተቋማትና በሜትር ታክሲ አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ይፋ ሆነ

ቀን:

  • ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ባላቸው ላይም ቫት ይጣላል

ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚሰጧቸው ከፊል የፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ እንዲሁም እንደ ራይድ ያሉ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ይፋ ሆነ።

በሥራ ላይ ያለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በአዲስ ለመተካት የተረቀቀው አዋጅ ቫት ተፈጻሚ ሳይሆንባቸው የቆዩ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች በርካታ የንግድ ዘርፎችን አካቶ የቀረበ ከመሆኑ ባሻገር በርካታ ማሻሻያዎችንና አዳዲስ ድንጋጌዎችንም የያዘ ነው።

በረቂቁ በግልጽ ባይቀመጥም ከተወሰነ የኤሌክትሪክ ፍጆታ በላይ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይም ቫት እንዲጣልባቸው ይደነግጋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ከማከሰኞ የተካቲት 19 ቀን ጀምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ የጀመረ ሲሆን ፣ ማክሰኞ ዕለት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው ከዚህ ቀደም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ ወይም ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ ተደርገው የነበሩ እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ያሉ ተቋማት ቫት የመሰብሰብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

በረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዋስይሁን አባተ እንዳመለከቱት እነዚህ ተቋማት ከቫት ውጪ ሆነው የቆዩበት የተለያዩ ምክንያቶች እንደነበሩ አስረድተው አሁን ግን ከሚሰጡት አገልግሎት የሚያገኙት ገቢ ላይ 15 በመቶ ተጨማሪ ታክስ መሰብሰብ እንዳለባቸው ታምኖበታል፡፡ 

ረቂቁ እንዲሻሻል ከተፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ የታክስ ገቢን ማስፋት ሲሆን በተለይ ተጨማሪ ታክስ ሊሰበስብባቸው ሲገባ ሳይሰበሰብባቸው የቆዩ የአገልግሎት ዓይነቶች በመለየት እንዲካተቱ ለማድረግ ነው፡፡ 

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የባንክ ሥራንና ከባንክ ውጪ ያሉ አገልግሎቶችን በመለየት የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊሰበስብባቸው ይገባል የተባሉትን የባንክ አገልግሎቶች ለይቶ አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህም መካከል ገንዘብ በማዘዋወር የሚያገኙት ኮሚሽን፣ ለውጭ ንግድ ከሚከፍቱት ኤልሲ ላይ የሚያገኙት ገቢና መሰል የባንክ አገልግሎቶች ላይ ቫት መሰብሰብ እንደሚጠበቅባቸው ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

እስካሁን ባንኮች ከተለያዩ አገልግሎቶቻቸው የሚያገኙት ኮሚሽንና ገቢ ላይ ቫት (የተጨማሪ እሴት ታክስ) የማይታሰብበት ሲሆን ከዚህ በኋላ ግን እንዲመለከታቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡ መሠረታዊ የባንክ አገልግሎቶች የሚባሉት እንደ የገንዘብ ቁጠባ ፣ ብድር ላይ የሚገኝ ወለድ ግን ከተጨማሪ እሴት ታክክ ውጪ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ 

በተመሳሳይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹም በአስገዳጅነት ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበስቡ የሚስገደድ ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ 

በተለይ ማንኛውም የኢንሹራንስ ኩባንያ የዋስትና ሽፋን ለሰጠው ግለሰብ ወይም ኩባንያ የካሳ ክፍያ ሲፈጽም ከኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የካሳ ክፍያውን ከሚቀበለው ደንበኛ 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተቀናሽ በማድረግ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

ኩባንያዎቹ ከካሳ ተከፋዮች 15 በመቶ ቀንሰው የሚሰበስቡትን ተጨማሪ እሴት ታክስ በአዋጁ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ማስገባትም ይኖርባቸዋል፡፡ 

ይህ በረቂቅ አዋጁ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የተመለከተው አንቀጽ ተፈጻሚ የሚሆነው ለጠቅላላ የኢንሹራን ሽፋን ሲሆን የሕይወት መድን ሽፋንን የሚመለከት እንዳልሆነም አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡ 

የፋይናንስ ተቋማትን በሚመለከት በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ድንጋጌዎች ዙሪያ ለመወያየት ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ሦስት ብቻ ቢሆኑም የተገኙት ባለሙያዎች ይህ ረቂቅ አዋጅ ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አደጋ ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ 

በመድረኩ የተገኙት የአንበሳ የኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም መርሻ ረቂቅ የቫት አዋጁ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል።

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠቅላላ የመድን ሽፋን አገልግሎት ለገዙ ደንበኞቻቸው የጉዳት ካሳ በሚከፍሉበት ወቅት 15 በመቶ ቫት እንዲሰበስቡ የሚያስገድደው የሪቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ደንበኞችን እንደሚያሸሽና ዘርፉን እንደሚጎዳ ባቀረቡት ማብራራያ ገልጸዋል።

አቶ አብርሃም መርሻ እንደገለጹት ደንበኞች ከገቡት የመድን ሽፋን ውጪ 15 በመቶ እንደሚቀነስባቸው ከተረዱ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎት ሊርቁ እንደሚችሉና ይህም ዘርፉን እንደሚጎዳ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ አንድ ደንበኛ ለንብረቱ የመድን ሽፋን የሚገባው ጉዳት ቢደርስበት ንብረቱን መልሶ ለመተካት በሚል እሳቤ መሆኑን ጠቅሰው በረቂቅ አዋጁ ግን ለዚህ ዓይነት ጉዳት የሚከፈለው ካሳ 15 በመቶ ታክስ ተቀናሽ በማድረግ ነው መባሉ የኢንሹራንስ አገልግሎት መርህን እንደሚፋልስ አቶ አብርሃም ገልጸዋል።

በተለይ እጅግ ዝቅተኛ የኢንሹራንስ ተገልጋይ ያለበት አገር ውስጥ እንዲህ የለው ሕግ ዘርፉን የበለጠ ሊያቀጭጨው ይችላል በማለት የሞገቱት አቶ አብርሃም ፤ አጠቃላይ ኢንሹራንስ ኩባንያውን የተመለከቱና በረቂቁ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ድጋሚ ሊጤኑ ይገባል ብለዋል፡፡ 

በዚህ ሥጋት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ዋሲሁን በበኩላቸው ረቂቁ ሲዘጋጅ ተጨማሪ እሴት ታክስ ከዓረቦን ይሰብሰብ የሚል እንደነበር አስታውሰው ይህንን ማድረግ ግን ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ይጎዳል በሚል ታክሱ የካሳው ክፍያ ሲፈጸም ይሰብሰብ ወደሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ 

ነገር ግን ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ደንበኛው በውሉ መሠረት የካሳ ክፍያውን እንዲያገኝ ለማድረግ ውሉ ሲፈጸም 15 በመቶውን ታክስ አካቶ በመዋዋል ሥጋቱን ማስቀረት እንደሚችሉ ጠቁመዋል። 

ሆኖም በረቂቁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ችግር የሚያስከትል ሆኖ ከተገኘ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ስለሁኔታው በዝርዝር ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማቅረብ በድጋሚ ሊታይ የሚችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የተሻለ ነው የተባለ አማራጭ ከቀረበም ማሻሻያ ማድረግ እንደሚቻል የታክስ ፖሊሲ አማካሪው አቶ ዋሲሁን አመልክተዋል፡፡ ለፋይናንስ ዘርፉ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በረቂቁ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሐሳባቸውን እንዲያቀርቡ እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ዕድሉ መሰጠቱን ፣ በዕለቱ በውይይት መድረኩ ላይ ያልተገኙ ባንኮችም ሆኑ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በረቂቁ ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ 

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ ከ20 ዓመታት በላይ ማሻሻያ ሳይደረግለት በመቆየቱና በአሁኑ ወቅት ካለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር ለማጣጣም ሲባል እስካሁን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ የተደረጉ ንግዶች ከሞላ ጎደል በሙሉ እንዲገቡ የተደረገበት ነው ተብሏል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይት የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይም ቫት እንዲሰበስቡ በረቁቅ አዋጁ የተካተቱ ሲሆን ፣ እነዚህ ተቋማት ቫት የሚሰበስቡባቸው አገልግሎቶች የትኞቹ እንደሆኑና ታክሱን እንዴት እንደሚሰበስቡ በአዋጁና አዋጁን ተከትለው በሚወጡ መመርያዎች ይመላከታሉ ተብሏል፡፡ 

ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች አንፃር እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪኮም ያሉ ተቋማት ከዚህ በኋላ ከሚሸጡት ከእያንዳንዱ የአየር ሰዓት (ካርዶች) ከወኪሎቻቸው 15 በመቶን ታክስ ማሰባሰብ የሚጠበቅባቸው ስለመሆኑም በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውይይት ላይ ተመልክቷል፡፡ 

ተጨማሪ እሴት ታክስ እስካሁን የትራንስፖርት ዘርፉን የማይመለከት ሆኖ የቆየ ሲሆን አሁን ግን ብዙኃን የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች ውጪ ያሉ የሜትር ታክሲ አገልግሎቶች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚሰበስቡ በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል። በዚህ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ተከታታይ ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...