Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የጥንቁቅ ቀዶ ሕክምና ፕሮጀክት

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መንግሥት ፖሊሲዎችን ቀርፆ ወደ ሥራ ቢገባም፣ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ግን አሁንም ቢሆን ክፍተቱ የጎላ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይም አብዛኛዎቹ የሕክምና ተቋማት ላይ የመድኃኒት አቅርቦትና ለሕክምና አገልግሎት የሚሆኑ መሣሪያዎች እጥረት መኖሩ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ ሕሙማን ተገቢ የሆነ የሕክምና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ለሌላ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ‹‹እስማኤል ትሬንና ላይፍ ቦክስ›› የተሰኙ ድርጅቶች ቅንጅት በመፍጠር እየሠሩ ይገኛል፡፡ ሁለቱ ተቋማት ለቀዶ ሕክምና (ኦፕሬሽን) የሚሆኑ መሣሪያዎች በመለገስ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል፡፡ ትህትና ንጉሡ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ የሕፃናት ቀዶ ሕክምና ሐኪምና የላይፍ ቦክስ ግሎባል ክሊኒካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የሁለቱ ድርጅቶችን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ላይፍ ቦክስ ድርጅት መቼ ተመሠረተ?

ዶ/ር ትህትና፡- ላይፍ ቦክስ የተመሠረተው የዛሬ አሥር ዓመት አካባቢ ነው፡፡ ድርጅቱም የተመሠረተው የኦክስጅን መለኪያ ወይም ፐልስኮሚትሊ የሚባለውን መሣሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ በማሠራት፣ አቅም ለሌላቸው አገሮች በማሠራጨት ሥራውን ሊጀምር ችሏል፡፡ ድርጅቱም እስካሁን በ110 አገሮች ላይ በመዘዋወር የሠራ ሲሆን፣ 40 ሺሕ ፐልስኮሚትሊን ለእነዚህ አገሮች ማሠራጨት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ለሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን በማከናወን ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ ተቋሙ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮችን ድጋፍ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግም ከእስማኤል ትሬን ድርጅት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በጤና ዘርፉ ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለከንፈርና ለመንጋጋ መሰንጠቅ ችግር የተጋለጡ ሕሙማንን ለመታደግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበከረቱ ይገኛሉ፡፡ ላይፍ ቦክስ በዓለም ላይ የሚሠሩ ኦፕሬሽኖች ጥንቁቅ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ሥልጠናዎችን፣ እንዲሁም ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት በዕርዳታ መልክ ለሕክምና ባለሙያዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይም እስማኤል ትሬን በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችሏል፡፡ ተቋሙም አሁንም ይህንኑ አገልግሎት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ድርጅቶች እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ቅንጅት በመፍጠር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የኦክስጅን መቆጣጠሪያ ግብዓት ለሌላቸው አገሮች በማሠራጨት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮም እስማኤል ትሬን ላይፍ ቦክስ ሴፍ ሰርጀሪ አንስቴዥያ ኢንሼቲቨ ወይም የላይፍ ቦክስና የእስማኤል ትሬን የጥንቁቅ ሰርጀሪና የጥንቁቅ ኢንስቴዥያ ሕክምና መስጠት የሚችል ፕሮጀክት ቀርፀን በጋራ እየሠራን ይገኛል፡፡   

ሪፖርተር፡- ላይፍ ቦክስና እስማኤል ትሬን ቅንጅት ፈጥረው የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛል፡፡ በሕክምና ዘርፍ ላይ ምን ያህል ተደራሽ ሆነዋል?

ዶ/ር ትህትና፡- ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ድርጅቶች ቅንጅት በመፍጠር በሕክምና ዘርፍ ላይ ተደራሽ እየሆኑ ይገኛል፡፡ በተለይም የሕክምና መሣሪያዎችን ለተለያዩ አገሮች በማሠራጨት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል፡፡ በቅርቡም እስማኤል ትሬንና ላይፍ ቦክስ ካፕኖግራፊ የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የሕክምና ተቋማት  ተደራሽ ማድረግ ችለናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕክምና ባለሙያዎች የሙያ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በፅኑ ሕክምና ክፍል የተኙ ሕሙማንን ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚያስፈልጉ የሕክምና መሣሪያዎች መካከል የካፕኖግራፊ መሣሪያ ይጠቀሳል፡፡ ነገር ግን ይህ መሣሪያ ባደጉ አገሮች ላይ ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ፣ ያላደጉ አገሮች እንደ ልብ መሣሪያውን ማግኘት አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ ለረዥም ጊዜ እንደ ልብ ላላደጉ አገሮች መሣሪያው እየደረሰ ባለመሆኑ ሁለቱ ተቋማት ችግሩን ተረድተው መሣሪያውን ወደ ተለያዩ አገሮች ተደራሽ ማድረግ ችለዋል፡፡ የሕክምና መሣሪያውንም ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ሆስፒታሎች በዕርዳታ መልክ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ አንድም የሕክምና ዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ከመቅረፍ ባለፈ በመሣሪያ እጥረት ምክንያት የተለያዩ መስተጓጎል የደረሰባቸው ሕሙማንን መታደግ ተችሏል፡፡

ሌላው ደግሞ የኦክስጅን መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ለተለያዩ አገሮች ተደራሽ እያደረጉ ይገኛል፡፡ በዓለም ላይ የሚከናወኑ ቀዶ ሕክምናዎች በጥንቃቄ እንዲፈጸሙ እስማኤል ትሬንና ላይፍ ቦክስ ድርጅቶች ለተለያዩ አገሮች መሣሪያዎችን እየለገሱ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ስድስት ካፕኖግራፊ መሣሪያዎች ለየካቲት 12፣ ለካዲስኮና ለዘንባባ ሆስፒታሎች መለገስ ተችሏል፡፡ በተለያዩ አገሮች እየቀረበ ያለው ካፕኖግራፊ የተሰኘው መሣሪያ ዋና ጥቅሙ ትቦ ገብቶላቸው የሰመመን መድኃኒት የተሰጣቸው ሕሙማን ወይም ደግሞ የሰመመን መድኃኒት ወስደው ሊታከሙ ያሰቡ ሕሙማንን የራሳቸውን አየር መቆጣጠር ስለማይችሉ ከመጀመርያ ጀምሮ የሕክምና ሁኔታቸውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም ከሆነ በርካታ ሕሙማንን መታደግ ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- እስማኤል ትሬን የከንፈርና የመንጋጋ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ሕሙማን ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ዶ/ር ትህትና፡- እስማኤል ትሬን በዓለም ላይ የከንፈርና የመንጋጋ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን ሕሙማንን በመደገፍ እንዲሁም ተገቢውን የሆነ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ከፍተኛ ሚና መጫወት ችሏል፡፡ እስካሁን 170 ሺሕ የሚሆኑ የከንፈርና የመንጋጋ መሰንጠቅ ችግር የገጠማቸውን ሕሙማንን ተገቢ የሆነ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በርካታ ሕሙማንን ለመታደግ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከንፈርና ላንቃቸው ለተሰነጠቀ ሕፃናት ወጥ የሆነ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህንንም አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ዶ/ር ትህትና፡- በቀጣይ የጤና ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ሁለቱም ተቋማት በጋራ የሚሠሩ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሎች ላይም ይህንን አሠራር በመዘርጋት በርካታ የሕክምና ተቋሞች ላይ ተደራሽ ለመሆን ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ሥልጠና ለመስጠት ዕቅድ ተይዟል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሕክምና መሣሪያ በተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በርካታ ሕሙማንን መታደግ ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...