Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የባሰ አይምጣ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ሜክሲኮ። ሕይወት በተለያየ ገጽታዋ እየተፈራረቀችብን እንራመድ ዘንድ ግድ ብሎን ልንጓዝ ነው። መጓዝ! መጓዝ! መጓዝ! መጨረሻው የማይታወቅ ዝብርቅርቅ የሕይወት ጉዞ። ሕይወትን አስተውሎ ዓይቶ ረቂቁን የሰውን ልጅ መስተጋብር ላጠና የመፈጠር እንቆቅልሽ ይባስ መወሳሰቡ አይቀሬ ነው። አኅጉር ለይታ፣ ፍጥረት መርጣ፣ ለአንዱ ብቻ ወግናና ሌላውን ረስታ፣ ብርሃኗን የማትሸሽገው ፀሐይ በደማቅ ሰማያዊው ሰማይ ላይ በርታለች። ሁሌም እንደነበረችው ዛሬም አለች። ለውጥ ለሰው ልጅ ብቻ የተቸረው የመከራው ጫፍ ጣፋጭ ፍሬ ይመስል ተፈጥሮ እንደ ትናንቱ ሲቀጥል ሰው ግን ይለዋወጣል። ይህ ነውና ዓላማው። ተፈጥሮ በበኩሉ የመኖር ጥያቄ እያሰቃየን ስንወራጭ እንደኛ የአመፃ ሐሳብ ሳይነበብበት እንደነበረው ገና ወደፊት የሚቀጥል እንደሆነ ያስታውቃል። ማንም ሰው በለውጥ ውስጥ ወደደም ጠላም ይጓዛል። የግድ ነው!

ገሚሱ የጠላውን ሊወድ ገሚሱ የወደደውን አጥብቆ ሊያፈቅር በዕድልና በመከራ ኃይል አሳሩን ያያል። የመኖር አሊያም ያለመኖር ጥያቄ ነው ጎዳናው ላይ የሚታየው። ዝብርቅርቅ ሩጫ። ጊዜ ያለፈበት ጊዜን መቅደም በቻለው ይቀናል። ከራሱ እየተጣላና እየተራበሸ ራሱን ይቀጣል። ጊዜን ቀደምኩ ባዩም እንዲሁ በጥድፊያ ባለው ላይ ሊጨምር ኃይሉን ያድሳል። ዕረፍት የለም። ቢኖርም ለደከሙትና ለታከቱ እንጂ በብርቱዎች ደጃፍ አይደለም። በብሩህ ሰማያዊው ሰማይ ላይ ካለንበት ምድርና ከቆምንበት ጎዳና እጅግ ተቃርኖ ታላቅ የተስፋ ዘመን የተጻፈ ይመስላል። ከወደቁት በቀር ሁሉም ወደዚህ ሰማይ እያማተረ ይራመዳል፣ ይጣደፋል፣ ይሮጣል። ሕይወት፣ ሩጫ፣ ጥድፊያ። ትግል፣ ትንቅንቅ፣ ጦርነት። ጥያቄው የመኖር አሊያም ያለመኖር ነው። ዝብርቅርቅ ጎዳና!

ፈጠን ፈጠን እያሉ ሰዎች ታክሲው ላይ ይሳፈራሉ። ወያላው አይጠራም። “እንዲህ ብዙ ሳይጮሁ ከአቅም በላይ መብላት ሥቃይ በሆነበት ዘመን ሳይታትሩ ሠርቶ መለወጥ ቢቻል?” ይላል አንዱ ወያላውን እየታዘበ። ከጎኑ ያለ ወዳጁ፣ “ገና ከአሁኑ ሰለቸህ? ምኑ ተያዘ ብለህ ነው?” ይለዋል የሚሠሩትን ሥራ እያነሳ። ያን ያህል ሥራ የተቃለለለት የሚመስለው ወያላ ግን እጅግ ተመስጦ የሚመለከተው ነገር ነበረው። እጃችን ሥራ ቢፈታ፣ አፋችን ቢለጎም ዓይናችን የሚያየው የማያጣበት አገር ነውና። በሚያይበት አቅጣጫ ዞር አልን። ከመንገዱ ጠርዝ አንድ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ በቁስል የሚማቅ ጎልማሳ ይታያል። ሰውነቱ በሙሉ በዝንብ ተወሯል። ይኼኔ ነው የረሳነው የሕይወት እንቆቅልሽ በእዝነ ልቡናችን የሚተራመሰው። እንደኛ መቼም ነግ በእኔ የሚል ሕዝብ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም በየተራ እጅግ ማዘኑን ለማሳወቅ፣ ‘ውይ!’፣ ‘ምስኪን!’፣ ‘አበስኩ ገበርኩ!’ ሲል ይደመጣል። በዚህ መሀል ታማሚ የሚመስልን ጎልማሳ አንዲት ሴት ጠጋ ብላ ዝንቦቹን ስታባርርለት ጎልማሳው ተቆጣ። ያለ ነው!

“የዘንድሮ ሰው እኮ ሲያዝኑለት አይገባውም…” ይል ጀመር ያ ሁሉ አዛኝ ቅቤ አንጓች። ወያላው አሁንም ሁለመናው እዚያው ነው። ታክሲዋ ሞልታለች። መንገዱ እንኳ ሳይቀር እንቅስቃሴው በዚያ ምስኪን ጎልማሳ ድራማ ተገትቷል። “ምን አደረግኩህ ዝምቦችን አባረርኩልህ እንጂ…” አለችው ሴትዮዋ በጣም ደንግጣ። ‘እፀድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች’ ዓይነት ሆኖባት ግራ እንደገባት ታስታውቃለች። ይህን ተመልክቶ ከፊት ለፊታችን የተቀመጠ ወጣት፣ “ዘንድሮ ማን ግራ ያልገባው አለ እህቴ ፈርዶብሽ?” እያለ ሁኔታዋን ዓይቶ ለእሷ ማዘን ጀመረ። ታማሚው፣ “ምን መሆንሽ ነው? ደህና የጠገቡትን ዝንቦች አባረሽ አዳዲስ ዝንቦች ትጠሪብኝ?” ሲላት የተቆጣበት ሚስጥር ለሚመለከተው ሁሉ ተገለጸለት። በተለይ ለታክሲያችን የነገር መጀመሪያ ሆኖ አረፈው። ሾፌሩ ታክሲውን አስነስቶ ቀልቡ የተሰረቀውን ወያላ በግድ አስገባው። እናም መንቀሳቀስ ጀመርን። ሳብ እንዲል ወያላ!

“ወይ ጉድ የለመዱት ይሻሉኛል አዲሶቹን አትጥሪብኝ? ሰው ግን እንዲህ ታሞ ከፖለቲካ ራስ ላይ በቃ አይወርድም?” ትላለች ከኋላ መቀመጫ ተጣባ የተቀመጠች ሴት። ታክሲ ውስጥ አንድ አንድ ለመባባል ሰበብ ብቻ ስለሚፈለግ ምን ለማለት እንደፈለገች ሁሉም ገብቶታል። ወያላው ገና የተሳፈርንበትን አካባቢ ሳንሰናበት ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። ጨዋታው በሙስና በኩል አፈትልኳል። “ለመሆኑ የሌብነቱ ከመጠን በላይ መግዘፍ መንግሥትን እንደ እኛ አስቦበታል? ካልሆነ ሰውዬው እንዳለው ያልጠገቡት ዝንቦች ገና እስኪጠግቡ ያው ነው…” ስትል፣ “ባያድለንና ባይልልን እንጂ ይኼን ሁሉ ዘመን የጠገበ አለማግኘት ምን ይባላል?” ትላታለች አጠገቧ የተቀመጠች ሰውነቷ ምንምን ብሎ ያለቀ ጎስቋላ ወይዘሮ። ሳያስቡት ተግባብተው ሁለቱ ብቻ ጨዋታውን አደሩት። “ቢሆንማ ምድረ ሌባ ሁሉ ይኼኔ የሚገቡበት በጠፋቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል የዘንድሮ ሌባ ሕግ አይፈራ፣ ፈጣሪን አይፈራ…” አለቻት የመጀመሪያዋ። ተጀመረ!

“መንግሥትማ ስሙም አይጠቀስ፡፡ ለምን ብትሉ አንድ ላይ ተደራጅተው ከጉያው በቅለው፣ በጉያው አድገው፣ ከራሱ በልጠው እየኖሩ ለምን ብለው ደግሞ መንግሥት ይጠቀስ?” ትላለች የወዲያኛዋ። ሁላችንም እነሱን ነው የምናዳምጠው። የሚያወሩት በታላቅ ምሬት ነበረና። ከእነሱ በስተግራ የተቀመጡ ሁለት ወንዶች በመስኮት ይከፈት ይዘጋ ዱላ ቀረሽ ጭቅጭቅ ሲያነሱ ግን ወደ እነሱ ዞርን። አይዘጋም ባዩ፣ “አንተ ስላልክ ነው? ዴሞክራት ከሆንክ በድምፅ ብልጫ እናስወስን…” ሲለው መዘጋት አለበት ባዩ ከት ብሎ ስቆ ሳይጨርስ፣ “ይህቺን ዓይነት ጥቃቅንና አነስተኛ ዴሞክራሲ እንዲያው የት አባቴ ብሄድ ነው የማልሰማና የማላየው? ዴሞክራሲን የሚያህል ነገር ሌብነት ክብር የሆነበት አገር ውስጥ ስሙን ማንሳት ይደብራል…” አለው። ወዲያው፣ “እውነት ሌብነትን በቆራጥነት መዋጋት አቅቶን ነው የምንንሾካሾከው?” ብሎ አንዱ ዙሩን ማክረር ጀመረ፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!

“ኧረ እባካችሁ መስኮቴን እንዳትሰብሩት። እንዴ ምን አለበት ቢከፈት? ስለመስኮት መከፈት ስንት ትምህርት እየተሰጠ ይዘጋ ማለት ምን ይባላል?” ብሎ ወያላው በሁለቱ ጭቅጭቅ መሀል ገባ። ሒሳብ መሰብሰቡን ጨርሶ ትርፍ ሰዎች ሊጭን ሲሞክር ነው ይኼ ንትርክ የተነሳው። “ታዲያ ንፋሱን አንድ በለዋ፣ እኔ ብርዱን አልቻልኩትም…” አለ ካልተዘጋ ባዩ ተሳፋሪ። “ኤድያ! እኛን እንኳን ብርድ ይኼው አገሩን የሞላው ሌብነትም አልገደለን። ይኼ ቆዳ ለስሙ ነው እንጂ ሥጋ ሸፈነ የምንለው እንደኛ ውስጠ ብረት የለም እሺ…” አለው አይዘጋም ባዩ ተሳፋሪ ተናገረ። ይኼኔ ከሾፌሩ ጋር ጋቢና የተቀመጡ አዛውንት፣ “ኧረ እውነት ነው፣ ስንቱን ችለን ንፋስ ካጠቃንማ እውነት እግዜሩም ጨክኗል…” ይላሉ። የመስኮቱ መከፈት ከንክኖት ክርክር የገጠመው ተሳፋሪ ነገሩ ግራ ገብቶታል። ይኼን ሲያስተውል ቆይቶ፣ “ይህ ሰው የታክሲ ውስጥ ጨዋታና ወሬ እንዲህ ውስጠ ወይራ መሆኑን ገና በደንብ የተረዳው አይመስልም…” ሲል የምንሰማው ከመሀል ወንበር ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ ነው። አጠገቡ የተቀመጠች ምጥጥ ያለች ሴት በበኩሏ፣ “እኛም ባንደርስበት እንጂ ኑሯችን ራሱ ውስጠ ወይራ ከሆነ ዘመን የለውም። ስንታይ ያለን እንመስላለን እንጂ የለንም እኮ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ስላቅ አለ? ግን ዘለዓለም ዕድገትና ልማት ለችግሮቻችን መድረስ ካልቻሉ ምን ይፈይዳሉ? ስትል ነገሩን መረር አደረገችው። ምሬት በየፈርጁ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጎልማሳው ‘እንዴት?’ ብሎ አልጠየቃትም። ከአቅም በታች በሚጫወተው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ ነገሩ መረር ብሎ ውሎ ማደሩን ያውቃል። “በጣም የሚያሳዝነው የእኛን ሊረዳው ካልቻለው መሀል ዋናው ተወክያለሁ የሚለው ሹምና ባለሥልጣን ብዛት ነው። ኧረ ኑሮ አይደለም…” ትላለች ይህችው ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠች ተሳፋሪ። ዝርዝር ውስጥ ሳትገባ በደፈናው ለገባው ይግባው ብላ የመሰላትን ትናገራለች። ጆሮ ያለው ጠፋ እንጂ። ግን ጥቂት ይቀረናል። “የዘንድሮ ሰው ብልጥ ነው ሲባል ይገርመኛል። ከሕዝብ ላይ ሰርቆ መክበር እንዴት ያለው የብልጥነት ምልክት ይሆን?” ይላል አንዱ። የጨነቀ ነገር፡፡

“እኛ እኮ ላያችን ላይ አምባገነንና ሌባ ማንሰራፋትን ያስለመደንን ከንቱዎችን ነው” ይላል አንዱ ከኋላ። “ኧረ እሱስ እውነት ነው…” አለ ሌላው መልሶ። “እኔ የምፈራው የእኛ አገር ዕድገት እንደ ህንድና ብራዚል ሆኖ እንዳያርፍ ነው…” ትላለች መሀል ወንበር የተቀመጠች ወጣት፣ በሀብታምና በደሃ መካከል የሚፈጠረው የሰማይና የምድር ዓይነት ልዩነት ስታስበው እያንገፈገፋት። “የት ይቀራል? የጠሉት ይወርሳል የፈሩት ይደርሳል አይደል የሚለው? በዚያ ላይ ሌብነቱ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ፣ የብሔር አድሎኦና ኢፍትሐዊነት፣ ኧረ ስንቱ ገና ይከተለን ይሆን?” ይላሉ አዛውንቱ ከጋቢና። “ታዲያ ይህንን ጊዜ ምን እንበለው?” ብሎ ሲጠይቅ ጎልማሳው አዛውንቱ ዞር ብለው፣ “ምን እንድንል ትጠብቃለህ? የባሰ አታምጣ ነው እንጂ…” ብለው ሜክሲኮ ደርሰን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት