Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከፋይናንስ ተቋማት እስከ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ድረስ ቫት እንዲጣል የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ20 ዓመታት በላይ ሥራ ላይ የቆየውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ለማሻሻል የወጣው አዲስ ረቂቅ አዋጅ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየበት ነው፡፡ 

የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በየቢዝነስ ዘርፋቸው በመከፋፈል ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ውይይቱ የተጀመረ ቢሆንም፣ በየመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነበር፡፡ ሪፖርተር መታዘብ እንደቻለውም በሁለቱ ቀናት በተካሄዱ አራት መድረኮች በአጠቃላይ ተሳታፊ የነበሩ ከ205 የማይበልጡ ነበሩ፡፡ በአንድ መድረክም አምስት ሰው ብቻ ተገኝተው ታይተዋል።

ረቂቁን ያዘጋጀውና የውይይት መድረኩን የፈጠረው የገንዘብ ሚኒስቴር የተሳታፊዎች ቁጥር ከጠበቀው በታች ቢሆንበትም፣ ለተገኙት ተሳታፊዎች የረቂቅ አዋጁን ይዘት የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ማብራሪያውን የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር የታክስ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዋስይሁን አባተ፣ ረቂቁ በርካታ ማሻሻያዎች የተደረገበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለማሳያ ከተጠቀሱት ውስጥ ታክስ ሳይመለከታቸው የቆዩ እንደ ፋይናንስ ተቋማትና የትራንስፖርት ዘርፍ ጭምር ታክሱ እንዲመለከታቸው ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በተለያዩ ምክንያቶች ከታክሱ ነፃ (ታክስ ኤዘምት) ተደርገው የነበሩ ዘርፎችም በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

በማብራሪያቸው ከ20 ዓመታት በላይ ብዙ መሻሻል ሳይደረግበት የቆየውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንፃር አጣጥሞ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ከተደረጉ ዋና ዋና ማሻሻያዎች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው ከዚህ ቀደም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጪ የነበሩ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶች በረቂቅ አዋጁ ተካተው መቅረባቸው ነው። 

ፋይናንስ ዘርፉ በጥቅል በፋይናንስ ስም ከታክስ ነፃ ሆነው የቆዩበት ምክንያት ኢንቨስትመንትና ቁጠባን ለማበረታታት እንደነበርም፣ ከዚያ ውጪ ግን ፋይናንስ በሚባል ብቻ በስመ ባንክ ጠቅላላ ከታክስ መረብ ውጪ መሆናቸው ተገቢ ስላልሆነ ታክሱ እንዲመለከታቸው መደረጉ ተገልጿል፡፡ እስካሁን የፋይናንስ ተቋማት የባንክ አገልግሎት ብለው ሲሠሩበት የነበረውን መሠረታዊ የባንክ ሥራ የሚባሉት የቁጠባና የብድር አገልግሎቶችን በመለየት በሌሎች የባንክ አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል ወይም እንዲሰበሰብ በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል። በዚህም መሠረት ባንኮች ከገንዘብ በማስተላለፍ በሚያገኙት ኮሚሽን ላይ እንዲሁም ለውጭ ንግድ ክፍያ ከሚከፍቱት የኤልሲ (Letter of Credit) አገልግሎት በሚያገኙት ገቢና መሰል አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚጣል የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ፡፡  

ሌላው ትልልቅ ኩባንያዎችና ባንኮች ሶፍትዌሮችን በከፍተኛ ዋጋ ሲገዙና ሲከራዩ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበሰብ በረቂቅ አዋጁ የተካተተ ሲሆን፣ አሁን ባለው አዋጅ ግን እንዲህ ዓይነት ግዥዎች ከቫት ውጪ ናቸው። አሁን ይህ እንዲካተት ተደርጓል።

እስካሁን የባንክ አገልግሎቶች በሙሉ የፋይናንስ አገልግሎት ተብለው ከቫት ነፃ የተደረጉ መሆኑን ያመለከቱት አማካሪው፣ አሁን ግን የባንክ ሥራን ከሌሎች አገልግሎቶቻቸው በመለየት ታክሱ እንዲመለከታቸው ለማድረግ በረቂቁ ውስጥ የታክስ አሰባሰቡን የሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ለምሳሌ የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ የባንክ ሥራ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ዋስይሁን ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ግን ይህንን አገልግሎት የባንክ ሥራ ብሎ ገልጾታል፡፡ እኛ ደግሞ ለእኛ አገልግሎት ይህ የገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎት የባንክ ሥራ አይደለም ብለናል፡፡ ምክንያቱም የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ በሌሎች ተቋማትም ይሠራል። ስለሆነም ታክስ ሊከፈልበት ይገባል በማለት ይህንኑ በረቂቁ እንዲካተት ተደርጓል፤›› ብለዋል።

ከዚህም ሌላ በርካታ ተቋማት የደመወዝ ክፍያዎችን በባንኮች ይፈጽማሉ፡፡ ነገር ግን ይህን አገልግሎት መስጠት የባንክ ሥራ ሊባል እንደማችል አቶ ዋስይሁን ገልጸዋል። ምክንያታቸውን ሲገልጹም፣ ይህንን የደመወዝ ክፍያ ሥራ የፖስታ አገልግሎት ድርጅትም ሆነ ሌሎች የሚያከናውኑት በመሆኑ የባንክ ሥራ ተብሎ ሊመደብ አይችልም።

በመሆኑም ባንኮች ከሚሰጧቸው መሰል የባንክ ሥራ ባልሆነ አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ መደረጋቸውን አስረድተዋል።

የፋይናንስ ተቋማቱ ከታክስ ነፃ የሚሆኑት ቁጠባና ኢንቨስትመንት (ብድር) አገልግሎታቸው ላይ ብቻ መሆኑን በማስረዳት ገንዘብ ማስተላለፍ ከቁጠባና ከኢንቨስትመንት ጋር ግንኙነት ስለሌለው ታክሱ እንዲመለከታቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡

ከፋይናንስ ተቋማቱ ውጪ እስካሁን ታች ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ሲባል ከታክስ ነፃ የተደረጉ አገልግሎቶችና ዕቃዎች ቫት እንዲከፈልባቸው በረቂቅ አዋጁ መካተታቸውን አቶ ዋስይሁን ገልጸዋል፡፡ 

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመጥቀም ሲባል የተወሰኑ ግዥዎች ከቫት ነፃ የተደረጉ ቢሆንም፣ በዚህ የመንግሥት ውሳኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ ከተደረጉት የማኅበረሰብ ክፍሎች ውጪ ሌሎች መንግሥት ሊጠቅማቸው ያልፈለጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጭምር እየተጠቀሙበት በመሆኑ ከታክስ ነፃ የተደረጉ ዕቃዎችና አገልግሎቶች በሙሉ በረቂቅ አዋጁ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣልባቸው መደረጉን አቶ ዋስይሁን አስረድተዋል።

ለምሳሌ እንደ ኤሌክትሪክና የመጠጥ ውኃ ያሉ አቅርቦቶች አሁን ባለው አዋጅ ከተጨማሪ እሴት ታክክ ነፃ የተደረጉት መንግሥት ታሳቢ ያደረጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመጥቀም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዋስይሁን፣ በተግባር ግን ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ በረቂቅ አዋጁ ይህንን ሁኔታ የሚያስቀር ማሻሻያ መቅረቡን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ወደፊት በመመርያ ከሚወሰን ወርኃዊ ፍጆታ በላይ ኤሌክትሪክና የመጠጥ ውኃ በላይ በሚጠቀሙት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል የሚደነግግ ማሻሻያ በረቂቁ ተካቷል።

አቶ ዋስይሁን እንደገለጹት፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ ከቫት ነፃ የተባሉ ዕቃዎችና አገልግቶችን በማንሳት አብዛኛዎቹን ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ በማድረግ የታክስ ሽፋኑን ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ገንዘብ ሚኒስቴር ከታክስ ነፃ የማድረግ ሥልጣን የሚሰጠው ለምግብና ከምግብ ጋር የተያያዙ ነገሮች ላይ ብቻ እንደሚሆን አመልክተዋል። ከዚያ ውጪ ገንዘብ ሚኒስቴር ፓርላማው ታክስ ሰብስብበት ያለውን ገንዘብ ሚኒስቴር ከታክስ ነፃ ይሁን የሚልበት ሁኔታ እንደማይኖርም ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታ የሚታዩና እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ካሉት በስተቀር ቫት እንደሚከፈልባቸው ገልጸዋል፡፡ 

በረቂቅ አዋጅ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣልባቸው ከተለዩት መካከል የትራንስፖርት ዘርፍ ይገኝበታል።

‹‹ትራንስፖርት ዘርፍ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆን የተወሰነው የዋጋ ንረትን እንዳይከሰት ነው። የትራንስፖርት ዋጋ ናረ ማለት ደግሞ የሸቀጦ ዋጋ ያንራል፡፡ ሁለተኛ ለአስተዳደርም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን በስመ ትራንስፖርት ሁሉንም ነፃ ማድረግ አይገባም፡፡ አቅም ያለው ሰው የሚጠቀምባቸው እንደ ራይድ ያሉ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተጨማሪ ዕሴት ታክሱ እንዲመለከታቸው ይደረጋል፤›› ብለዋል።

ኤሌክትሮኒክስ ግብይትን በተመለከተም ረቂቅ አዋጁ የተለያዩ ድንጋጌዎችን ያሠፈረ ሲሆን፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ምን ምን እንደሆነ ትርጓሜ በመስጠት ቫት የሚከፈልበትን ሁኔታ አስቀምጧል።

በዚህም መሠረት የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሲፈጸም ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዴት እንደሚሰበሰብና የትኞቹ የግብይት ዓይነቶች ታክሱ እንደሚሰበስባቸው በረቂቅ አዋጁ የተመለከቱ ሲሆን ማስፈጻሚያ መመርያ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

የኤሌክትሪክ ግብይት ምን ማለት እንደሆነ በረቂቅ ለማብራራት የተሞከረ መሆኑን ያስረዱት አቶ ዋስይሁን፣ ወደፊት የውጭ ምንዛሪ በገበያ መርህ እንዲሸጥ ሊፈቅድ የሚችል መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፣ ከአማዞንና ከመሳሰሉት የውጭ ዲጂታል ገበያዎችም ሆነ ከአገር ውስጥ መሰል ገበያዎች የሚፈጸም ግብይት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣልበት በረቂቅ አዋጁ መካተቱን ገልጸዋል።

እንደ አማዞን ካሉ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ የሚደረገው ግብይት ላይ ታክስ ለመሰብሰብ በረቂቁ በአማራጭነት የተቀመጠው አንዱ ድንጋጌ ኩባንያዎቹ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መመዝገብና ወኪል ኖሯቸው ከእነሱ ታክሱ መሰብሰብ የሚችልበት አማራጭ ተይዟል፡፡ ሌሎች አማራጮችም ተቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች እዚህ ሳይመዘገቡ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ እንደ አማዞን ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች በሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት በኢትዮጵያ ተመዝግበው የግብይት ገንዘቡ በሚተላለፍበት ጊዜ ታክሱን አስቀርተው እንዲከፋፈሉ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

እነዚህ ተቋማት በኢትዮጵያ ባለመመዝገባቸው ወይም ወኪል ባለማቆማቸው ምክንያት መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ታክስ እንዳያጣ፣ ከእነዚህ ተቋማት ግዥ በሚፈጽም ሰው ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚጣል አስረድተዋል። 

ሌላው በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ለውጥ ተደርጎበታል ተብሎ በአማካሪ ማብራሪያ የተሰጠበት ጉዳይ የዕቃና የአገልግሎት ትርጉም ነው፡፡ ለምሳሌ የኤክሌክትሮኒክ ግበይት የሚፈጸምባቸው ዕቃ በሚል ትርጉም የነበረው ሲሆን፣ አሁን ግን አገልግሎት የሚል ትርጉም የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ አንድ ሶፍት ዌር ሲሸጥ አገልግሎት ተሸጠ ነው የሚባለውና በዚሁ አግባብ በአዲሱ ረቂቅ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ 

ኤክስፖርትን በተመለከተ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አዳዲስ አንቀጾች ተካተዋል፡፡ በነባሩ አዋጅ ኤክስፖርት ሲገለጽ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ መላክ ነው፡፡ አሁን ግን ይህ ትርጉም አይሠራም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ድርጅት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ዕቃ ማቅረብ ይችላል፡፡ ወይም አሁን በቅርብ ለተቋቋመው ለድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምርት የሚያቀርብ በመሆኑ ወደ እነዚህ ፓርኮችና የንግድ ዞኖች ምርት ሲሰጥና ግብይት ሲደረግ ወደ ውጭ እንደሚላክ የሚቀጠር ይሆናል ተብሏል፡፡  

የንግድ ዞኑ እንደ ኢትዮጵያ ሕጋዊ ድንበር አይቆጠርም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን አንድ ሰው የንግድ ዞኑ ውስጥ ላለ ማኑፋክቸር ወይም ሌላ ኩባንያ ሰፕላይ ያደረገ ከሆነ ኤክስፖት እያደረገ የሚቆጠር በመሆኑ ከታክስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በዚሁ አግባብ እንዲፈጸሙ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አመላክቷል፡፡ 

በዚህ ረቂቅ ላይ ተካተተ ተብሎ የሚጠቀሰው ሌላው አዲስ አንቀጽ የዱቤ አገልግሎትን የተመለከተው ነው፡፡ እንደ አቶ ዋስይሁን ማብራሪያ በዱቤ የሚሰጥ አገልግሎት ታክሱ መከፈል ያለበት ዱቤው እንደተሰጠ መሆን ይኖርበታል፡፡ 

የዱቤውን የሰጠው ኩባንያ ታክሱን አስልቶ ገቢ ማድረግ አለበት እንጂ፣ መንግሥት ታክሱን ለማግኘት የዱቤ ክፍያ እስኪፈጸም ድረስ አይጠብቅም፡፡ ስለዚህ ዱቤ ሲሰጥ ታክሱ ወዲያው ተሠልቶ ገቢ እንዲደረግ የሚደርግ ድንጋጌ አዲሱ ረቂቅ ሕግ ተካቷል፡፡

 ከዱቤ የታክስ ከፍያ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያ በአዋጁ ስለመካተቱም ታውቋል፡፡ ክፍያው እስኪፈጸም ሊጠበቅበት የሚችል ጉዳይ ካለ ለዚህ ተብሎ በሚዘጋጀው መመርያ ላይ የሚጠቀስ ይሆናል ተብሏል፡፡ 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ፕሮሞሽኖች ተብለው የሚሰጡ ስጦታዎች ታክስ ሊከፈልባቸው እንደሚገባ በዚሁ ረቂቅ ላይ ተመላከቷል፡፡ ሊጠበቅበት የሚችል ጉዳይ ካለ ለዚህ ተብሎ በሚዘጋጀው መመርያ ላይ የሚጠቀስ ይሆናል ተብሏል፡፡ 

ለምሳሌ አንድ የቢራ ፋብሪካ ለፕሮሞሽን ብሎ የሚሰጠው ቢራ ከዚህ በኋላ ታክስ ሊከፈልበት እንደሚገባ አቶ ዋስይሁን ገልጸው፣ ፋብሪካው ስጦታውን መስጠት መብቱ ቢሆንም፣ በዚያ ስጦታ ምክንያት መንግሥት ሊያገኘው የሚገባው ገቢ መቅረት ስለሌለበት ተጨማሪ እሴት ታክሱ ታስቦ ለመንግሥት መግባት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ 

በዚህ ረቂቅ አዋጅ መንግሥት ከፍተኛ ታክስ ሊሰበስብ እችላለሁ ብሎ ካቀዳቸው ዘርፎች መካከል ቴሌኮም ዘርፍ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ከቴክኖሎጂና ከቴሌኮም ሥራዎች ጋር በተያያዘ ቢዝነሶች ላይ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸውም፣ ዘርፉን የሚመለከቱ አዳዲስ ድንጋጌዎች በረቂቅ አዋጁ ተካትተዋል፡፡ 

በዚህ ቢዝነስ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች የትኞቹ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚመለከታቸው በዝርዝር የተቀመጠ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ የአየር ሰዓት ሽያጭን የተመለከተው አንቀጽ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ 

የቴሌኮም ኩባንያዎች የሚሸጡበት ቅድሚያ ክፍያ የአየር ሰዓት (ካርድ) 15 በመቶ ተጨማሪ ታክስ የሚሰበሰብበት ይሆናል፡፡ ይህንን ታክስ ከኩባንያዎቹ አከፋፋዮች ወይም ቸርቻሪዎች መደብር መሰብሰብ ስለማይችል ኩባንያዎቹ ከዚህ የአየር ሰዓት ሽያጭ 15 በመቶውን የተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰብሰብ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ እንደሚኖባቸው አመልክተዋል፡፡ 

ዓለም አቀፍ ጥሪዎች ላይ ታክስ መሰብሰብ እንደሚኖርባቸውም በዕለቱ በተሰጠው ማብራሪያ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎች አገልግሎቶቻቸው ላይም አዋጁ ተፈጻሚ የሚያደርጋቸው ድንጋጌዎች ስለመኖራቸው ታውቋል፡፡ 

በዚሁ ውይይት መድረክ ላይም የሳፋሪኮም ተወካዮችና የአራት ኩባንያዎች ወኪሎች ብቻ የተገኙበት የነበረ ሲሆን፣ በተለይ የሳፋሪኮም ወኪሎች በታክስ ጉዳይ ባለሙያዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በገንዘብ ማስተላለፍ መሰል ሥራዎች ላይ ለመሰማራት እየተዘጋጀ ስለሆነ፣ በዚሁ ሥራው የሚሰማራበት የገንዘብ ማዘዋወር አገልግሎቱ እንደ ባንክ ሥራ የሚቆጠር፣ የማይቆጠር በመሆኑ ገቢው ላይ ታክስ የሚከፍል መሆኑ ተገልጾለታል፡፡ ሌሎች ኩባንያዎችም ቢሆኑ ለኤሌክትሮኒክስ መንገድ የገንዘብ ማዘዋወር ሥራዎቻቸውና ሌሎች ገቢ የሚገኙባቸው አገልግሎቶች እንደ ባንክ ሥራ የማይቆጠሩ በመሆኑ ታክስ ይመለከታቸዋል ተብሏል፡፡               

ኩባንያዎች ለሠራተኞቻች የሚሰጡት ማበረታቻ ሽልማትና መሰል ስጦታዎች በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ታክስ ሊከፈላቸው ይገባል የሚል ይዘት ያለው አንቀጽ ተቀምጧል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳታፊዎች ይህ እንዴ ሊሆን ይችላል የሚል ሙግት የቀረበበት ነባር በረቂቅ ግን በዓይነት ለሠራተኞች ሽልማት ቢሰጥ በሽልማት የተሰጠው ዕቃ ሽልማቱ በተሰጠበት ቀን ባለው የዕቃው ዋጋ ተሠልቶ 15 በመቶውን ታክስ ኩባንያው ሊከፍል እንደሚገባ የሚደነግግ ነው፡፡ ከዕርዳታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በተመሳሳይ የሚታዩ ሲሆን፣ ዕርዳታው ሲሰጥ በዕርዳታ የተሰጠው ዕቃ ታክሱ እንዲመለከተው ይደረጋል፡፡ በመንግሥት በኩል በተደረገ ጥሪ የሚሰጥ ዕርዳታ ግን ከዚህ ውጪ እንደሚሆንም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ ረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል ከተባሉ በርካታ አንቀጾች መካከል አንዱ ተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ምን ያህል ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ነው የሚለው ነው፡፡ በቀድሞ አዋጅ ዓመታዊ የገንዘብ እንቅስቃሴው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ በአስገዳጅነት የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ መሆን ይኖርበታል የሚል ሲሆን ይህ መጠን በአዲሱ ረቂቅ ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡ በፈቃደኝነት የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ መሆን የሚፈልግ ግን በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚንቀሳቀስ ከሆነ መመዘገብ የሚችልበት ዕድል እንዳለውም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በሁለቱ ቀናት የውይይት መድረኮች በአመዛኙ ማብራሪያ የተሰጠው የየቢዝነስ ዘርፎችን የሚመለከቱ አንቀጾችን በመጥቀስ ሲሆን፣ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናትም በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ማብራሪያ የሚሰጥ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም የሚሰጡ ግብረ መልሶችን የሚያሰባሰብ ይሆናል፡፡ በረቂቅ አዋጅ ላይ የሚቀርቡ ማንኛውንም ሐሳቦች በጽሑፍ ጭምር ለመቀበል የሁለት ሳምንታት ጊዜ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች