በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮ ከነበረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ፣ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት፣ ከሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመመሳጠር የተፈጠረውን አለመግባባት ወደ ሌላ አጀንዳ በመቀየር ተጠርጥረው የታሰሩት ፓስተር ቢኒያም ሽታዬ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ከፌዴራል መጀመርያ ደረጃ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር ተደርጎ ዋስትና ቢፈቅዱላቸውም ሊፈቱ አልቻሉም፡፡
የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ፓስተሩ በ5000 ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ውሳኔ የሰጠ ቢሆንም፣ መርማሪ ፖሊሲ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ ሳይፈቱ ቀርተዋል፡፡ ክርክሩ ቀጥሎ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፓስተር ዳንኤል የቀረቡ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማጽናት ከእስር እንዲፈቱ ወስኗል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ግን ተጠርጣሪውን ሳይለቅ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል የይግባኝ አቤቱታውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም፣ ችሎቱ ‹‹የሕግ ስህተት አልተፈጠረም›› በማለትና የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በማጽናት፣ ፓስተር ቢኒያም ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን መርማሪ ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበር ሳይለቃቸው በመቅረቱ፣ ለፓስተሩ የቆሙላቸው ጠበቃ ብሩክ ደረጀን ጨምሮ 33 ጠበቆች ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት (መጀመርያ ዋስትና ለፈቀደው) አቤቱታ በማቅረባቸው፣ ፖሊስ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹እኛ ለቀነዋል›› በማለት ምላሽ መስጠቱን ጠበቃ ብሩክ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ፓስተር ቢኒያም በእስር ላይ መሆናቸውን፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ መታሰራቸውንና በክፍለ ከተማው ከተማ ነክ ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም አቶ ብሩክ ገልጸዋል፡፡
ከተማ ነክ ፍርድ ቤቱም የፖሊስን አቤቱታና ቀደምት ውሳኔዎችን ተመልክቶ፣ ፓስተሩ በ2000 ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ጠበቃ ብሩክ አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ ግን ይግባኝ ማለቱንና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም የዋስትናውን ትዕዛዝ በማጽናት አቤቱታውን ውድቅ ቢያደርግም፣ ፖሊስ ለሰበር ችሎት ይግባኝ በማለቱ እስካሁን ድረስ (ማተሚያ ቤት እስከገባንበት የካቲት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ድረስ) በእስር ላይ መሆናቸውን ጠበቃ ብሩክ ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ፓስተር ቢኒያምን በ11ዱም ክፍላተ ከተማ ባሉ ከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች ቢወስዳቸው ከማንገላታትና ገንዘባቸውን ዋስትና በማስያዝ ከማስጨረስ ሌላ ምንም ጥቅም እንደሌለው ጠበቃ ብሩክ ተናግረዋል፡፡
ፓስተር ቢኒያም ላይ እየተደረገ ያለው እንግልት ሌላው ኅብረተሰብ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዳያድርበት ስለሚያደርግ፣ መንግሥት ሁኔታውን ተመልክቶ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያስፈልገው ከሆነ እንዲወስን ጠይቀዋል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ የዋስትና መብት የተነፈገ ሰው ይግባኝ ከሚል በስተቀር፣ ፖሊስ ዋስትና ለማስከልከል ይግባኝ የሚልበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ ፖሊስ ይግባኝ ይጠይቅ ቢባል እንኳን፣ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ የሚሽር የበላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ወይም ጊዜያዊ ዕግድ ሳይቀርብ፣ ዋስትና የተፈቀደለትን ሰው ማሰር አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ የተጠረጠረን ሰው ከቦታ ቦታ እየቀያየሩ በማሰርና የተለያዩ ፍርድ ቤቶች በማቅረብ፣ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጥስና ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ ለሕዝብም ሆነ ለአገር እንደማይጠቅም ጠበቃ ብሩክ ደረጀ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡