- ሀገረ ስብከቱ ለመንግሥት የ15 ቀናት ጊዜ ገደብ ሰጥቷል
- የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የፀጥታ አካላት በአግባቡ ሥልጠና እንዲወስዱ ጠየቀ
ባለፈው ሐሙስ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የዓድዋ ድልና በዓል እየተከበረ ባለበት ሰዓት በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያ አጥር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው እያከበሩ በነበሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችና የሃይማኖቱ አባቶች ላይ፣ አስለቃሽ ጭስ የተኮሱ የመንግሥት የፀጥታ አካላትና ትዕዛዝ የሰጡ ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጠየቀ፡፡
‹‹መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና በሚዳፈር መልኩ በተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ የፀጥታ አባላትንና ትዕዛዝ ያስተላለፉ የመንግሥት ኃላፊዎችን በ15 ቀናት ውስጥ ለይቶ በሕግ እንዲጠይቅ፤›› ሲል ሀገረ ስብከቱ ባለፈው ዓርብ የካቲት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ጠይቋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሔኖክ እንደጠየቁት፣ ‹‹መንግሥት ዕርምጃውን ለቤተ ክርስቲያንና ለሕዝቡ እንዲያሳውቅ፣ በተጨማሪም በተለመደው የሐሰት ውንጀላ በዓላቸውን በማክበር ላይ እያሉ የመንግሥት የፀጥታ አካላት በፈጸሙት ሕገወጥ ተግባር ምክንያት፣ በተፈጠረው ግርግር መነሻ የታሰሩ ምእመናንን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ፤›› አሳስበዋል።
ሊቀ ጳጳሱ እንደገለጹት፣ መንግሥት በተጠቀሰው ጊዜ ይህንን የማያደርግ ከሆነም፣ ቤተ ክርስቲያኗ ወደ ቀጣይ ዕርምጃዎች እንደምትገባ ያሳወቁ ሲሆን፣ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ አዋቅረው ወደ ሥራ እንደሚገቡም ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜናም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተመሳሳይ ቀን ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘ በምኒልክ አደባባይና በቤተ ክርስቲያኑ አጥር ጊቢ ውስጥ የፀጥታ አካላት ላሳዩት አላስፈላጊና ከልክ ያለፈ ኃይል መንግሥት ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲል ጠይቋል።
‹‹የፀጥታ አካላቱ የአስለቃሽ ጭስ፣ ፕላስቲክና ገዳይ ጥይት ተጠቅመዋል። የአንድ ሰው ሞትና በርካታ የሰውነት ጉዳቶች እስኪያስከትል ድረስም ከልክ ያለፈ ዕርምጃ በሕፃናትና አረጋውያን ላይ ተጠቅሟል፤›› ሲል ዋና ኮሚሽነሩን ጠቅሶ መግለጫ ያወጣው ኮሚሽኑ፣ በዚህም ድርጊት ላይ የተሳተፉት የፀጥታ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም በአግባቡ ሥልጠና እንዲወስዱና ተመሳሳይ ጉዳቶች እንዳይፈጠሩ መረጋገጥ እንዳለበት አሳስቧል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያኑ አጥር ግቢ ውስጥ አስለቃሽ ጭስ ተተኩሶ የተሰበሰቡት አማኞች እንዲጎዱ በመደረጉ፣ መንግሥት ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ ሲገባው፣ ለድርጊቱ ዕውቅና ሰጥቶ አልፏል፤›› በማለት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በዕለቱ የሰጠውን መግለጫ አጣጥለዋል።
‹‹በዚህ ድርጊት መንግሥት በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያሉና መንግሥትንና ሕዝብን፣ እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ ያለመግባባት የሚያባብሱትን ግለሰቦችና አመራሮች ለይቶ ዕርምት ከመውሰድ ይልቅ፣ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ የሚያደርግ ተግባሩን አስፋፍቶ ቀጥሏል፤›› ብለዋል አቡነ ሄኖክ።
ሊቀ ጳጳሱ እንደተናገሩት፣ ሁለት ጊዜ የአስለቃሽ ጭስ ተተኩሶ በተፈጠረ ችግር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ረብሻ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ግለሰብ የሞተና ሌሎች በርካቶች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ 15 የሚሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ባጋጠማቸው ጉዳት ሆስፒታል ተወስደዋል። በተፈጠረው ሁከትና ረብሻ ታቦተ ሕጉም ሥርዓተ ንግሡን ሳይጨርስ ወደ መንበሩ ሊመለስ መገደዱን አክለዋል፡፡