Saturday, June 15, 2024

አገር አጥፊ አዝማሚያዎች ካልተወገዱ ፈተናው ይቀጥላል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያስማሙ የጋራ ጉዳዮች ይልቅ ለጠብ የሚያንደረድሩ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ ነው፡፡ በዓለም ፊት የሚያኮራውን ታላቁን የዓድዋ ድል በዓል ሳይቀር በአንድነት ማክበር እያቃተ ነው፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት መዋል ያለበት የሰው ኃይል፣ ገንዘብ፣ ጊዜና ኢነርጂ ለተቃርኖ ብቻ እየዋለ ትልቅ ኪሳራ እየደረሰ ነው፡፡ ይህ ኪሳራ አገርን ለመበታተን የሚችል ዕምቅ ኃይል እያጠራቀመ ነው፡፡ በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ ብልፅግና አመራሮች መካከል የተከሰተው ችግርና የተድበሰበሰው መግለጫቸው፣ ኢትዮጵያ አሁንም ከፊቷ የተጋረጠ ብርቱ ፈተና እንዳለ አመላካች ነው፡፡  ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ መሆን ሲገባው ነጋ ጠባ የቅራኔ አጀንዳ መፈብረክ ያሳዝናል፡፡ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ድህነትን  አሽቀንጥሮ ለመጣልና ኢትዮጵያን እንደ ታላቁ ዓድዋ ድል የዘመኑ አብሪ ኮከብ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ሲገባ፣ እርስ በርስ መዳማትና መቋሰል ለታሪካዊ ጠላቶች እንጂ ለማንም አይበጅም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በጠላት ፊት የተንበረከከበት ጊዜ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ስትወረር እንጂ የሰው አገር ስትወር አትታወቅም፡፡ ለወረራ የመጡ ኮሎኒያሎስቶችና የተለያዩ ዓላማ የነበራቸው ጠላቶች አፍረውና ተዋርደው ተመለሱ እንጂ፣ በቅኝ ገዥነት አልቆዩባትም፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ አገሩን አንዴም አስደፍሮ አያውቅም፡፡ በታሪክም አልተመዘገበም፡፡ ሕዝባችን በተለያዩ ዘመናት በተነሱ ጨቋኝ ገዥዎች አፈና ውስጥ ሆኖ እንኳን አገሩን ለባዕዳን አሳልፎ አልሰጠም፡፡ ይልቁንም በደሉንና መከራውን ችሎ አገሩን ከጠላት ሲከላከል ኖሯል፡፡ አሁንም ይህ ዓይነቱ አኩሪ ገድል በዚህ ትውልድ መቀጠል ሲገባው፣ ኢትዮጵያዊነት በጠላት ፊት የሚያንበረክኩ ድርጊቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ግዙፉን የኢትዮጵያዊነት ምሥል የሚገዳደሩ ጥፋቶች እየበረከቱ ነው፡፡ ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ይበልጥ ያስተሳስረናል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዘመን ልዩነት ከመነጋገርና ከመደማመጥ በላይ እየሆነ ክፍተት እየፈጠረ ነው፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ ሕዝባችን የሚታወቅበትን የአትንኩኝ ባይነትና አገርን በጋራ የመጠበቅ አኩሪ ባህል እየተጋፋ ነው፡፡

ዜጎች መብቶቻቸውን ሲጠይቁ መነፈግ የለባቸውም፡፡ የፖለቲካም ሆነ የሌላ ልዩነት መከበር አለበት፡፡ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተናገድ ቀርቶ የጥላቻ የሚመስሉ ዕርምጃዎች መውሰድ ተመርጧል፡፡ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ፍላጎት የሚወክሉ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ በተዛባ የታሪክ ትርክት ላይ ተጥዶ አገር ማመሳቀል ተመርጧል፡፡ ይኼ ፀንቶ ለኖረው ለኢትዮጵያ አንድነት አይስማማውም፡፡ አገር በመርህ የምትመራው ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል፡፡ የሕግ የበላይነት አለ ሲባል ዜጎች በነፃነት የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሕገወጦችና ግብረ አበሮቻቸው ደግሞ አደብ ይገዛሉ ማለት ነው፡፡ በሕግ ፊት ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው ማለት ከሕግ በላይ ማንም የለም ማለት ነው፡፡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ራሳቸው ሕግ መሆን ሲጀምሩ ግን አደጋ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አዝማሚያ ሲኖር በሕግ ማለት ተገቢ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲከበር የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ዜጎች ቢሆንም፣ ከማንም በበለጠ ግን መንግሥትን ይመለከተዋል፡፡ ሕግ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡

በኢትዮጵያ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ምክንያት ዜጎች ቅሬታ ሲያቀርቡ አፋጣኝ ምላሽ ስለማያገኙ በደሉ የተደራረበ ይሆንባቸዋል፡፡ ፍትሕ ሲፈልጉ በተቃራኒው ሲገጥማቸው ብሶት ይበረታባቸዋል፡፡ በሴረኞች ምክንያት ሥራቸው ሲጓተትባቸውና አላስፈላጊ ለሆኑ እንግልቶች ሲዳረጉ ምሬቱ ጣሪያ ይነካል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ የዜግነት ደረጃዎች ሲስተዋሉ ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ለአገር ዘላቂ ጥቅምና ህልውና ደንታ የሌላቸው እንደፈለጉ ሲፈነጩና ዜጎች ሲያበሳጩ ዝም ማለት ተባባሪነት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለው ችግር ይህንን በስፋት ያሳያል፡፡ ለዜጎች ምሬት ምክንያት የሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች እንደፈለጉ ሲፈነጩ ጠያቂ እያጡ ነው፡፡ በበርካታ መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ዘረፋ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ በየደረሰበት የሚያጋጥመው አምጣ የሚል ብቻ ሆኗል፡፡ ሌብነቱ እየከፋ ከመምጣቱ የተነሳ ሕጋዊውን ከሕገወጡ ለመለየት አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ በየተቋማቱ የተገልጋዩን ሕዝብ ቅሬታ የሚሰማ ባለመኖሩ ዜጎች ሳይወዱ በግድ የሕገወጦች ተባባሪ እንዲሆኑ ይገደዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው አገርን ነው፡፡

ዜጎች የሕግ የበላይነት አለ ብለው እንዲተማመኑ ከሚያደርጋቸው መካከል አንዱ፣ የመንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ነው፡፡ መንግሥት ዜጎችን ከተለያዩ አጥቂዎች የመጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለምሳሌ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብታቸው ሲገፈፍ ከማንም በላይ መንግሥት ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ ያለ ምንም አድልኦ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማግኘታቸውን መከታተልና ማስፈጸም ያለበት መንግሥት ነው፡፡ በዓላትን ሲያከብሩ፣ ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ ሠልፍ ሲወጡ፣ በመኖሪያቸውም ሆነ በሥራ ቦታቸው ደኅንነታቸውን ማስከበር ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ ምኅዳር ሊፈጠር የሚችለው ዜጎች መብቶቻቸው ተከብረው ግዴታቸውን መወጣት ሲችሉ ነው፡፡ ሕግን አክብሮ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት አደራውን ካልተወጣ ሕገወጥነት ይንሰራፋል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲከበር ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ተቋማትና የመንግሥት መዋቅሮች በሙሉ ሥራቸውን በአግባቡ ይሠራሉ፡፡ ሕገወጦች የሕግ የበላይነትን ሲጋፉ ዝም ከተባለ ግን ሰላም ተናግቶ ለአገር መከራ ያስከትላል፡፡ አንዱ ሌላውን በሸፍጥ ሲሸፍንና ሲከላከል ለጊዜው ሕግ የተከበረ ቢመስልም፣ እየቆየ ግን ሥሩ የማይነቀል ደዌ ይተክላል፡፡ ሕጋዊና ሕገወጡ እየተጣቀሱ መቀጠል ስለማይቻል፣ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ፡፡

በዚህ ዘመን ሕግ በአግባቡ ስለማይከበር ድንገት ሳይታሰብ ሚሊየነር የሆኑ ሰዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ድርጊት በጊዜ ለምን ካልተባለ የሚወቀሱት ሰዎቹ ሳይሆኑ መንግሥት ነው የሚሆነው፡፡ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢምፖርት ኤክስፖርትና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች ሳይሳተፉ፣ ወይም የረባ ሥራ ሳይኖራቸው በጉዳይ አስፈጻሚነት ወይም በደላላነት የሚከብሩ ሰዎች እየበዙ ነው፡፡ የአየር በአየር ሥራ አገርን እንደማያሳድግ፣ ይልቁንም መቀመቅ እንደሚከት መታወቅ አለበት፡፡ በሌብነት እየተቀባበሉ መክበር ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን አገርንም ያሳፍራል፡፡ ሕግ ይከበር ሲባል የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ ማለት ነው፡፡ ማንም ሰው በነፃነት አመለካከቱን የማራመድ፣ የመሰለውን የመምረጥ፣ የመደራጀትና ዓላማውን የማስተዋወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ይህንን መብት መጋፋት ማለት የሕግ የበላይነትን መጋፋት ነው፡፡ በአመለካከቱ ምክንያቱ መሠረታዊ መብቶቹን ለመጋፋት የሚሞክሩ ኃይሎች ሕገወጥ ናቸው፡፡ ሕግ ጥሰው የሰው መብት ሲጋፉ ዝም ሲባል መንግሥት አለ ወይ ነው የሚባለው፡፡ አገር አጥፊ አዝማሚያዎች በትብብር ካልተወገዱ ፈተናው ይቀጥላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...