Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ለሚጀምረው የማስተርስ ፈተናዬ ለሳምንታት በትጋት ሳጠና ቆይቼ ነበር፡፡ ወደ ፈተናው አዳራሽ በሰዓቱ ለመድረስ ከታክሲ ይልቅ ባቡር የተሻለ እንደሆነ በማመኔ ሰባተኛ ወደሚገኘው ባቡር ጣቢያ አመራሁ፡፡ በሥፍራው በርካታ ሕዝብ ባቡር እየጠበቀ ደረስኩ፡፡ ይህም ባቡሩ ካለፈ ብዙ ደቂቃ እንዳለፈው ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ባቡሩ በሁለት ደቂቃ እንደሚደርስ በመገመቴ ትኬት ገዝቼ በፍጥነት ከሕዝቡ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡

ሰዓቱ ለሰባት ሃያ ጉዳይ ነበር፡፡ ፈተናዬ ግሎባል ሆቴል አቅራቢያ በመሆኑ ባቡሩ ከሁለት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይደርሳል፣ ለፈተናዬም በአስተማማኝ ያደርሰኛል የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ ይሁንና ሰዓቱ እየነጎደ ሄደ፡፡ ከባቡር ጣቢያው ወጥቼ በታክሲ ልሂድ ብል እንኳን ጊዜውን በባቡር ጥበቃ ያቃጠልኩት በመሆኑ የመድረስ ተስፋ አልነበረኝም፡፡ በመሆኑም ልቤ በፍርኃት መራድ ጀመረ፡፡

ከብዙ እልህ አስጨራሽ ቆይታ በኋላ 7፡20 ሰዓት አካባቢ ከአውቶቡስ ተራ የሚመጣ ባቡር ተመለከትኩ፡፡ ፈተናው ከተጀመረ 20 ደቂቃ እንዳለፈው ሳስብ ፍርኃት ተሰማኝ፡፡ ይሁንና ከባቡሩ የሚፈጥን ትራንስፖርት ባለመኖሩ ዘልዬ ገባሁ፡፡ እንደዚያ ዕለት ባቡር ሲንቀራፈፍ ዓይቼ አላውቅም፡፡ ልቤ በጭንቀት ሊፈነዳ ደረሰ፡፡

ግሎባል አካባቢ እንደደረስኩ ኮቴ እንደ ባንዲራ እየተውለበለበ በሩጫ ወደ ትምህርት ቤቴ አመራሁ፡፡ አራተኛው ፎቅ ላይ የሚገኘው የፈተናው ክፍል ስደርስ 7፡38 ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ ፈታኙ በንዝህላልነቴ በመደነቅ ዓይኖቼን እያየ ኮምጨጭ ባለ ፊት፣ ፈተናው ከተጀመረ ግማሽ ሰዓት ስላለፈ መግባት አትችልም ሲል ቁርጤን አረዳኝ፡፡ 

ከ475 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራስፖርት መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ሥራ ሲጀምር፣ የከተማይቱን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡  በየስድስት ደቂቃ ልዩነት ተሳፋሪዎችን ከየፌርማታው በማንሳት በሰዓት እስከ 15 ሺሕ ተሳፋሪዎችን ያጓጉዛል ተብሎ ነበር፡፡

ከሰባት ዓመታት አገልግሎት በኋላ የድርጅቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ሊሻሻል፣ ሽፋኑ ሊጨምርና በየስድስት ደቂቃው ይደርሳል ተብሎ የነበረው ባቡርም በሒደት በየሁለት ወይም ሦስት ደቂቃ ሊደርስ በተገባው ነበር፡፡ 

ይሁንና ድርጅቱ ገና የሙሽርነት ዘመኑ ሳያበቃ እርጅና ተጭኖታል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱ እያሽቆለቆለ ዋጋው ብቻ ጨምሯል፡፡ የባቡር አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደመሆኔ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያስተዋልኳቸውን አንዳንድ ችግሮች እንደሚከተለው አነሳለሁ፡፡

አገልግሎት ሰዓት መቀነስ፡- የባቡር አገልግሎቱ ከሰባት ዓመት በፊት ሲጀምር ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ የባቡር አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የባቡር አገልግሎቱን ወደ 24 ሰዓት በመጨመር የከተማይቱን እንቅስቃሴ ይበልጥ ያሳልጣል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ከተሟላም የንግድ እንቅስቃሴ ይጨምራል የሚል እምነት ነበር፡፡ ይሁንና ቀስ በቀስ የአገልግሎት ሰዓቱ በሁለት ሰዓት እንዲቀንስ ተደረገ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አብዛኞቹ የምሽት ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በመሆኑ፣ እንዲሁም በርካታ የመሀል ከተማ መደብሮችና መዝናኛ ካፌዎች የሚዘጉት ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ወደ አካባቢያቸው ለመሄድ የባቡር አገልግሎት እንዳያገኙ ከልክሏቸዋል፡፡

ባቡር ብልሽት፡- በበርካታ አገራት አዳዲስ ባቡሮች በአማካይ ለ28 ዓመታት ያለ ብልሽት ያገለግላሉ ተብሎ ይነገራል፡፡ ይሁንና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በተደጋጋሚ ተሳፋሪዎችን እንደያዘ በብልሽት ሳቢያ ይቆማል፡፡ በዚያ የተነሳ ተሳፋሪዎች ብዙ ፌርማታ እየቀራቸው የከፈሉበት ትኬት ሳይመለስ ለመውረድ ይገደዳሉ፡፡ የተበላሸውን ባቡር ድርጅቱ ፈጥኖ የማያነሳው በመሆኑ ቢያንስ አንድ ቀን የባቡር አገልግሎት ይቋረጣል፡፡ ጸሐፊው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ በባቡር ብልሽት ሳቢያ ለትራንስፖርት የማይመች አጉል ቦታ ለመውረድ ተገዶ ያውቃል፡፡

ባቡር ትኬት መሸጫ  ሱቆች መዘጋት፡- የባቡር አገልግሎትን ለማግኘት ደንበኛው ትኬት መግዛቱ ግድ ነው፡፡ ይሁንና ባቡሩ በሥራ ላይ እንዳለ ሠራተኞቹ የቲኬት መሸጫዎቹን በጊዜ ዘጋግተው ወደ ቤት ወይም ወደ ጉዳያቸው የሚሄዱበት ጊዜም አለ፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ቢያንስ ሁለት ቀን ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ባቡሩ እየሠራ ምኒሊክ አደባባይ የሚገኘው የባቡር ትኬት መሸጫ በመዘጋቱ በጥበቃ ላይ የነበሩት መልካም ፖሊሶቹ ተሳፋሪዎች ያለ ክፍያ እንዲገቡ ሲፈቅዱ ተመልክቻለሁ፡፡

አላስፈላጊ የአገልግሎት ማቋረጥ፡- የተቃውሞና የድጋፍ ሠልፎች ሲኖሩ ምናልባት በዚያ ሰዓት የባቡር አገልግሎት ማቋረጡ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ማለዳ የሚካሄዱ ሰልፎች ወይም የሃይማኖት ሥርዓቶችን አስታኮ የሚቋረጠው የባቡር አገልግሎት እስከሚቀጥለው ቀን ማለዳ ሲቀጥል አይስተዋልም፡፡ በእኔ አስተሳሰብ የባቡር መስመሩ ከዋናው መንገድ የተለየ በመሆኑ ምንም ዓይነት ሠልፍ ወይም የሃይማኖት በዓል ቢኖር የባቡር አገልግሎት ሊቋረጥ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ሠልፈኛውም የባቡር አገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናልና፡፡

ባቡሮችን ቀጣጥሎ ያለመጠቀም፡- ተሳፋሪ በሚበዛባቸው ሰዓታት ከተጠቃሚው ብዛት የተነሳ ባቡር ቶሎ ቶሎ ቢመጣ እንኳን በአንድ ፌርማታ ሰው ነው የሚሞላው፡፡ በተለይም ተሳፋሪ በሚበዛባቸው እንደ አውቶቡስ ተራና ስታዲዮም ያሉ የባቡር ጣቢያዎች የሚገባው ተሳፋሪ በራሱ አንድ ባቡር የሚሞላ ነው፡፡ በመሆኑም ቢያንስ ተሳፋሪ በሚበዛባቸው የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት ባቡሮችን ቀጣጥሎ በአንድ ጊዜ በርካታ ተሳፋሪዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይሁንና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አልፎ አልፎ ብቻ የሚስተዋለውን ባቡሮችን ቀጣጥሎ አገልግሎት የመስጠት ሥራ በስፋት አጠናክሮ ሊሄድበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

የባቡሮች ተመሳሳይ ቀለም መቀባት፡- በመላው ዓለም የሚገኙ የከተማ ቀላል ባቡሮች በማያሳስት ሁኔታ ቀለማቸው ይለያያል፡፡ በመሆኑም ተሳስቶ ሌላ አካባቢ የሚሄድ ባቡር ውስጥ መግባት የተለመደ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሲጀመር የባቡሮቹ ቀለም በማያሳስት ደረጃ ከርቀት የሚለይ ነበር፣ አረንጓዴና ሰማያዊ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ባቡሮቹ በላያቸው ላይ ማስታወቂያ ተለጥፎባቸው አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመለየት አዳጋች ሆኗል፡፡ ለአብነትም ከምኒሊክ አደባባይ ወደ ቃሊቲ የሚሄደው ሰማያዊ ባቡር ላይ ከጦር ኃይሎች እስከ አያት ከሚሄደው ባቡር ቀለም ጋር በሚመሳሰል የሳፋሪኮም ማስታወቂያ በመሸፈኑ ለተሳፋሪ አሳሳች ሆኗል፡፡ በተለይም ከልደታ መገንጠያ እስከ እስታዲየም በሚገኙት  ጣቢያዎች የሚሳፈሩ ሰዎች የሚሳፈሩበትን ባቡር በጥንቃቄ ሊመርጡ ይገባል፡፡

የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ፡- የአጭር ርቀት ዋጋ ከፍለው ረዥም መንገድ የሚጓዙ ተሳፋሪዎችን ለመከላከል ሲባል ሁሉም ተሳፋሪ ተመሳሳይ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጎ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የባቡር ትኬት ዋጋ አራት ብር ነበር፡፡ ይሁንና ከቀናት በፊት በተደረገው አዲስ የዋጋ ማሻሻያ የ75 በመቶ ጭማሪ ተደርጎበት ተሳፋሪዎች ሁሉ ሰባት ብር በመክፈል ላይ ይገኛሉ፡፡ ዋጋው በኑሮ ውድነት በተጎዳው ኅብረተሰብ ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡

የቲኬት ቆራጮች ለተሳፋሪ መልስ ያለመስጠት፡- የቲኬት ዋጋ አራት ብር እያለ ዝርዝር ሳንቲም የለንም በሚል ምክንያት በርካታ ሰዎች አንድ ብር ሳይመለስላቸው ቆይተዋል፡፡ ይሁንና ለአንድ ብር ተብሎ ከመነጋገር ብዙ ሰው ዝም ይላል፡፡ ሰሞኑን ዋጋው ሰባት ብር በመግባቱ የሚበዛው ሰው ትኬት ለመቁረጥ ድፍን አሥር ብር ይከፍላል፡፡ ትኬት ቆራጮቹ ዝርዝር ሳንቲም የለንም በሚል ምክንያት ለአንዳንድ ተጓዦች መልስ የማይሰጡ በመሆናቸው በተደጋጋሚ አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ሰሞኑን ይህንን ችግር ከዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ መነሻ ጣቢያ አስተውያለሁ፡፡ ቲኬት ቆራጮቹ ከተጓዦች ጋር የሚያደርጉት ምልልስ የአገልጋይነት መንፈስን ይበልጥ የተላበሰ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የንፅህና ችግር፡- በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለአንዴ እንኳን የተጓዘ ሰው ባቡሮቹ ምን ያህል ንፅህና እንደሚጎድላቸው ማየት ይችላል፡፡ ባቡሮቹን ለማፅዳት የሚሆን ውኃ የሌለ ይመስል ባቡሮቹ በጣም ቆሽሸው ነው የሚታዩት፡፡በመሆኑም ለሕዝብ ጤና ሲባል ድርጅቱ የንፅህናውን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል፡፡

(ጅብሪል ላሞ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...