Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየትግል ዝቅጠት ለሕዝብ ልሰዋ ከማለት የሕዝብን ጉርስና ደም ወደ መዝረፍ

የትግል ዝቅጠት ለሕዝብ ልሰዋ ከማለት የሕዝብን ጉርስና ደም ወደ መዝረፍ

ቀን:

በቀለ ሹሜ

በ1960ዎች በከተማ አፍላዎች አካባቢ የልሽቀት፣ የሱስ፣ የጩቤ ቡድን ገጽታቸው የነበሩ ቢሆንም፣ ወጣቱን በሰፊው የማንከት ደረጃ ላይ የደረሱ አልነበሩም፡፡ ለተስፋ መቁረጥ እጅ ባልሰጠ አኳኋን በትምህርት ውጤታማ ለመሆን መፍጨርጨር፣ አጠቃላይ የአገሪቱ ወጣቶች ትርታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚያን ዘመን ይቅርና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ ምክንያታዊ ክርክር በማድረግ ለብዙዎቹ ተማሪዎች ምሳሌና መነቃቂያ የነበሩ ትንታጎች እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ የያኔ ትንታግነት ዝም ብሎ የመጣ አልነበረም፡፡ የማወቅ፣ የማንበብና ወቅታዊ ጉዳዮችን የመከታተል ጥረት በወጣቱ ዘንድ ስለነበር ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ፣ በውጭ ፋሽን መሽቀርቀር የሚቀናበት ነገር ሳይሆን፣ የባህል ወራራ አሻንጉሊት መሆን ተደርጎ የሚናቅ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ጥቂቶች ብቻ አልፈው ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያልፉበት ጠባብ ቱቦ ነበር፡፡ በዚያ ጠባብ ቱቦ ካለፉት ውስጥም በማዕረግ እያለፉ ወደ ሕክምናና ምህንድስና፣ ወዘተ የሚገቡና ትምህርቱ የሚሳካላቸው ተማሪዎች ከሌላው ተማሪ ይልቅ ራሳቸውን ምርጦች አድርገው የሚያዩ ነበሩ፡፡ ቢያዩም የሚገርም አልነበረም፡፡ ውጤታቸው በኩረጃና በማጭበርበር ሳይሆን በልፋት የሚገኝ ስለነበር፡፡

በኢሕአዴግ ጊዜ የመማር ዕድል እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ መስፋቱ እሰየው የሚባል ቢሆንም፣ የትምህርት አሰጣጥ ጥራቱ፣ የአመዛዘንና የአስተላለፍ ሥርዓቱ መዝቀጥ ለብዙዎች የተከፈተውን የመማር ዕድል ሰባራ አድርጎት ቆይቷል፡፡ በቤተ ዘመዴና በባልንጀራዬ ቤተሰብ ውስጥ ካጋጠሙኝ በ‹‹ጥሩ›› ውጤት የተመረቁ የምህንድስና ተማሪዎች ውስጥ ከቀለም ትምህርቱ ውጪ የረባ አጠቃላይ የሌለው፣ ‹‹እዚህ ዕቃ ላይ ያለው ምልክት እኮ 666 ነው እንዳትጠቀሙበት›› የሚል ቅራቅንቦ የሚያንቃጭል አግኝቻለሁ፡፡ ተወዳድሮ በመጀመርያ ዲግሪ አቅም በኮሌጅ አስተማሪነት የተቀጠረ ተማሪ፣ የማስተማር ሥራው በአግባቡ አለመማሩን አስገንዝቦት እንደገና ራሱን በራሱ ማስተማር ውስጥ እንደከተተው ስለመናዘዙ፣ በኋላም ብቃቱን ለማሻሻል የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በተከታተለበት ጊዜ ‹‹ምህንድስናን ተማርኩ ማለት ያለብኝ ገና አሁን ነው›› ስለማለቱ አውቃለሁ፡፡

በዚህ ዓመት ጠበቅ ባለ አኳኋን የ12ኛ ክፍል የመውጫ ፈተናን ወስደው፣ ከሃምሳ በላይ ማምጣት የቻሉ ከመቶ 3.3 ብቻ መሆናቸውም ሥር የሰደደ ገመናችንን ያንፀባርቃል፡፡ አያሌ ዘበናይ ወጣቶቻችን በምዕራባዊ ልሽቀት እየተወረሩ መሆናቸው፣ ፊልሞቻችንና የዘበናዮቻችን ንግግራዊ የዘፈን ቪዲዮዎች ውኒጥ ውኒጥ በሚሉ ኮረዶች ታፋ ላይ ብር የመነስነስን ዝቅጠትና ፆታዊ ዘለፋ ሥልጣኔ ብለው እስከ መቅዳት መድረሳቸው፣ ብዙ ወጣቶች በጫትና በሺሻ ልምድ መጠመዳቸው፣ የጫት ላይ ተረብ በስልክ በኩል ሶሻል ሚዲያ ላይ መውጣቱ፣ ሌላው ቀርቶ በቴሌቪዥን ዝግጅቶች ላይ ‹‹አገር በቀል ባህሎቻችንን እንንከባከብ/እንወቅ›› እያሉ የሚሰብኩ ወጣቶች የስብከታቸው አዝማች ‹‹ዋው!… ኡፕስ›› መሆኑ ወጣቶቻችን በጥቅሉ ምን ያህል አዙሪታዊ እንቆቅልሽ ውስጥ እንደወደቁ ይነግረናል፡፡

እዚህ ላይ ምን አደረሰን? ወደ 1960ዎች ትውልድ መለስ ሳንል ይህንን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ አንችልም፡፡ በ1960ዎች ውስጥ የታየው የለውጠኝነት ቡቃያ የተከታታይ ትውልዶች መለምለሚያ ዘር ለመሆን ስለምን ሳይበቃ ቀረ? መልሱ ብዙም አወዛጋቢነትና አደናጋሪነት የለውም፤ ተደጋግሞ እንደተባለው የ1960ዎች ውድ የአገሪቱ ልጆች በትግል ልምድ አፍላነትና ባለመስከን ምክንያት እርስ በርስ ስለተበላሉና ጮርቃ ሠልፈኞቻቸውን ስላስበሉ ነው፡፡ በሌላ አባባል የአገሪቱ ኅብረ ብሔራዊ ትግል ከመሸነፍም በላይ ተመትቶ ስለነበር ነበር፡፡ ከ1970 እስከ 1971 አንስቶ እስከ 2009 ዓ.ም. አካባቢ ያለው ረዥም ጊዜ ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ትግል የተራዘመ የሽንፈት ዘመን (ኅብረ ብሔራዊ ትግል በጠባብና በተከፋፈሉ ዕይታዎች ተገዝግዞ የቆየበት ዘመን) ነበር ሊባል የሚችል ነው፡፡ በተነሸነፈው ኅብረ ብሔራዊ ትግል እግር የተተካው የተበታተነ ብሔርተኛ ትግል የሽንፈትን (የመንገድ መሳትን) ተራዝሞ መቀጠል የሚያሳይ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. ግንቦት 20 ደርግ ወድቆ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መምጣትም የተራዘመውን የሽንፈት ዘመን መቋረጥ የሚወክል ሳይሆን፣ የባሰ ዕዳ ባጠራቀመ መልክ ሽንፈት ድል መስሎ (መፍትሔ ያገኘ መስሎ) የቀጠለበት ዘመን ነበር፡፡

ነገሩን ከመንግሥት ሥርዓት አኳያ ብናየው የ1966 ዓ.ም. ለውጥ የሕዝብ አስተዳደር እንብርታዊ ጥያቄ መንገድ ስቶ ፊት ለፊቱ የዝግታ ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ ሲካሄድ አልታወቀውም ነበር፡፡ ግልበጣው ‹‹በለውጥ›› እየተኳኳለ ለውጠኞቹን ከፋፍሎ አንድ ሰው ወደ ‹‹አነገሠ››፡፡ ሙሉ ጥፍነጋ የመሸጋገር ጉዞ ሲያደርግም እየተጣፉ ይቃለሉ የነበሩት ለውጠኞች በአያሌው አልታወቃቸውም ነበር፡፡ ከ1969 – 1970 ዓ.ም. አንስቶ እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ድረስ የነበረው አገዛዝ የመልክና የቅርፅ ለውጥ ከማድረጉ በቀር በባህርይው ሙሉ የጥፍነጋ ሥርዓት ነበር፡፡ በአበሳዎች ደፋ ቀና እያለ እዚህ በደረሰው የለውጥ ጊዜ እየሆነ ያለው ሁሉ፣ ያ የተራዘመ የሽንፈት ጊዜ አጠራቅሞ ያቆየውን ነባራዊና ህሊናዊ ዕዳ (በአገረ መንግሥት ስብራት፣ በዕይታ ብልሽት፣ በዕውቀት መራገፍ፣ በትግል አቅም የደረሰውን ድቀት) ሒሳብ የማወራረድ ጉዳይ ነው፡፡ ሒሳብ የማወራረዱም ተግባር ከእነ ምጡና ሥቃዩ ገና አላለቀም፡፡ እስካሁን ካሳለፍነው ዕዳ እያወራረዱ አዲስ ሥርዓት የመገንባት አምስት የሰበር ሰካ ዓመታት ጊዜ መሀል፣ የ2013 ዓ.ም. ምጡ እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ግብግብ እስከ ማድረግ ድረስ የሞት ሽረት ጣሪያን የነካበትም ጊዜ ነበር፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ኅዳር ወዲህ ያለው ጊዜ የትግላችን ሥቃይና ቃስታ የሞት ሽረቱን ጣርያ ነክቶ እያቆለቆለ የመጣበት (ዴሞክራሲያዊና የምትገስግስ አገር የመገንባት ዕድላችን መለምለም የጀመረበት) ምዕራፍ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ የተጠራቀመብን ዕዳ ገና ምኑ ተነክቶ!!

ለማነፃፀር እንዲመቸኝ ወደኋላ ትንሽ መለስ ብዬ ወደ ድቀት የተላለፍንበትን ታሪክ ዳበስ ላድርገው፡፡ የአሲምባ ፍቅር የሚባል መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ በሚዲያ ሲሞጋገስ መጽሐፉን ለማንበብም ሆነ ለመግዛት ፍላጎቱ አልነበረኝም፣ በሁለት ምክንያቶች፡፡ በግራም በቀኝ በኩል ስለነበሩት የጊዜው ትግሎች ታሪክ፣ ስለድክመትና ጥንካሬያቸው የሚበቃኝን ያህል አንብቤያለሁ/ግንዛቤም ጨብጫለሁ የሚል ዕሳቤ ነበረኝ፡፡ የአሲምባ ፍቅር የሚለው ርዕስም በአዕምሮዬ እንዲያቃጭል ያደረገው ግምት፣ ያንኑ ወደ አምልኮ የተጠጋ የኢሕአፓ ፍቅር የሚያወሳ ሳይሆን አይቀርም የሚል ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት በጨዋታ ላይ ስለዚህ መጽሐፍ ወዳጄ አንስቶብኝ ለመግዛትም ለማንበብም ያልጓጓሁለት መጽሐፍ ስለመሆኑ ስነግረው፣ ‹‹እንዴት እንዴት!›› እያለ ተገረመ፡፡ በመገረምም አላቆመም መጽሐፉን ገዝቶ በል አንብብ ብሎ ሰጠኝ፡፡

 መጽሐፉን እስከ ተወሰነ ደረጃ ያነብብኩትም የወዳጄን ግፊት በማክበር ስሜት ውስጥ ሆኜ እያዛጋሁና እያቋረጥኩ ነበር፡፡ መጽሐፉ የድርጅት ጭፍን ፍቅርን የማያባዝት፣ በጠንካራ የሕዝብና የለውጥ ፍቅር የተሞላ የትግል ቁርጠኝነት ስለነበራቸው ወጣቶች የዕውን ሕይወት የሚተርክ መሆኑን ካወቅሁ በኋላ ግን፣ ስለእንቅልፍ ሰዓት ለማሰብ እንኳ አቅሙ አልነበረኝም፡፡ እንኳን አነበብኩት አልኩ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ያገኘሁት የወጣቶች ቁርጠኝነትና የለውጥ ጥማት፣ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ወደ እዚህ የነበረውን አፍላ የትግል ጊዜ እንደ ትኩስ ትዝታ ፊቴ ደቀነብኝ፡፡ ስደት የሚባል ነገር የማያማልላቸው የዚያ ጊዜ ወጣቶችና ከወጣት አጥፊነት ወደ ትግሉ ሠፈር እየተሳቡ ሕይወታቸውን ለትግሉ ያሉ አፍላዎች ሁሉ ትውስታዬን ተሻሙ፡፡ እነዚህ ወጣቶች በግራም ሆነ በቀኝ በነበሩት ትግሎች ውስጥ ሁሉ ነበሩ፡፡

የትግራይ ልጆች የትግል ታሪክም ሕወሓቶች ሲሉቱ እንደነበሩት ከሕወሓትነት ጋር የተጣበቀ አልነበረም፡፡ በግራም በቀኝም በነበሩት ድርጅቶች ውስጥ ከመሪነት እስከ ተራ ታጋይነት ድረስ የትግራይ ልጆች ተሳትፎ ነበር፡፡ ትግራይ፣ ጠመንጃ ይዘው ለረዥም የትጥቅ ትግል የገቡ ኅብረ ብሔራዊና ብሔርተኛ ቡድኖችን በጉያዋ አቅፋ አቆይታለች፡፡ የትግራይ እናቶች ለሁለቱም ቡድኖች ማዕዳቸውን አቋድሰዋል፡፡ በሁሉቱም ቡድኖች ላይ ተስፋቸውን አሳርፈው ‹‹ለምን ተለያያችሁ? ለምን አንድ ላይ አትሆኑም?›› እስከ ማለት ድረስ በውዝግባቸው ተብከንክነዋል፡፡ ለሁለቱም ጉስቁልና ተንሰፍስፈዋል፡፡

በአሲምባ ፍቅር ውስጥ የብዙ ቆራጥ ወጣቶች ታሪክ የሚወሳ ቢሆንም፣ ዋናዎቹ ባለታሪኮች ካህሳይና ድላይ (ስመኝ) ናቸው፡፡ ሁለቱም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቅጡ ያልገፉ አፍላዎች ነበሩ፡፡ አንድ የትግራይ እናት የድላይን ፆታ ሴት መሆን አላምን ብለው ጡቷን ካሳየቻቸው በኋላ፣ አንድ ፍሪት ልጅ ከእናቷ ጉያ ወጥታ በረሃ ለበረሃ ሽቅብ ቁልቁል ለማለት በመምረጧ አልቅሰዋል፡፡ ‹‹ለዛሬ ማታ እናት ልሁንሽ›› ብለው ተብሰክስከዋል፡፡ ከጊዜ በኋላ በአግባቡ ያስተዋልኩትን ‹‹የከተማ ትጥቅ ትግልም›› ሆነ ‹‹የገጠር ረዥም ትጥቅ ትግል›› የነበረውን ስህተተኝነት በዛሬ ህሊናዬ ይዤ እኔም፣ ያኔ ትግል ተብሎ በከተማ ጥይት እየተኮሱ ለተጋደሉ ወጣቶች እንደ አዲስ በተቀሰቀሰ ሐዘን አልቅሻለሁ፡፡ ከአጠገቤ ላጣኋቸው ብዙ ጓደኞቼና አንዳንድ ፍሪት ታናናሾቼ እንደ አዲስ ተንገብገቤያሁ፡፡

በአሥራዎች ዕድሜ ውስጥ የነበረው ካህሳይ (የትግል ስሙ አማኑኤል) እና አፍላዋ ስመኝ (የትግል ስሟ ድላይ) በዚያ ዕድሜያቸው ከቁርና ንዳድ ጋር መጋተር፣ በረሃብና በረዥም ጉዞ መፈተን፣ ከተባይ ጋር መታገል ሁሉ ባለበት ኑሯቸው የትግል ቁርጠኝነታቸው አለመዛሉ፣ በዚያ ዕድሜያቸው የትግል ጓደኞቻቸውን በተኩስ ልውውጥ ውስጥ ከማጣትም በላይ ለመቅበር ያለመታደልን ሬት እያጣጣሙና ዕንባቸውን እየዋጡ ግዴታቸውን ለመውጣት ብርታት ማግኘታቸው፣ ከአንተ/ከአንቺ በፊት እኔን ያስቀድመኝ እስከ ማለት የነበራቸው የመስዋዕትነት ጥንካሬ፣ ካህሳይና ድላይ ክንፍ ያደረጋቸውን ፍቅር በዚያ አፍላ ዕድሜቸው ቁንጥጥ አድርገውና ለትግሉ ያለባቸውን አደራ አብልጠው ሳይደራረሱ ለመቆየት ጥንካሬ ማግኘታቸው ዕፁብ ያሰኛል፡፡ እነሱ ጋርና በብዙ ሥፍራዎች ውስጥ በጊዜው የነበረው የወጣቶች የሕዝብና የለውጥ ፍቅር ከእነትግል ቁርጠኝነቱ በእየእስር ቤት፣ በየጎዳናና በየዱር በገደሉ ከመባከን ፈንታ በትክክለኛ የፖለቲካ አመራር ፍሬ በሚያስገኝ የለውጥ ዥረት ውስጥ እንዲፈስ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያ የት በደረሰች ተብሎ ሲታሰብ ደግሞ አሥር እጥፍ ያስለቅሳል፡፡

ፍቅራቸውንና የትግል ሕይወታቸውን ለሕዝብ በሰጡት ወጣቶችና በሕዝብ መካከል ያለው ቁርኝት የሚገባውን ያህል ባልጎለመሰበት/በተሰነጣጠቀበት ሁኔታ ውስጥ ሕይወታቸውን ለለውጥና ለሕዝብ ያሉ ወጣቶች በገበሬ የታደኑበትን (የተገደሉበትንና የተማረኩበትን) ውድቀት ማስተዋል ደግሞ የሚያስከትለው ለቅሶና ሕመም ሌላ ዓይነት ነው፡፡ እንደዚያ ባለው የሞት ላንቃ ውስጥ በገቡ ጊዜ እንኳ፣ በወጣቶቹ ታጋይነት ውስጥ የነበረው የሕዝብ ፍቅር አልተሰለባቸውም ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ታጋይነታቸውን እየተናገሩ ተጠቁ፣ አንዳንዶቹ ሽሽትና ተኩስን እያደባለቁ ተደፉ፣ ተማረኩ፡፡ ካህሳይም ገበሬን ከመግደል በገበሬ መገደልን መርጦ ተማረከ፡፡ የማረከው ገበሬም ካህሳይን ደብቆ አትርፎና ሸኝቶ ከትግል ባልንጀሮቹ ጋር ለመቀላቀል ዕድል ሰጠው፡፡ ካህሳይም አሲምባ ተመልሶ ‹‹ትግሉን›› ቀጠለ፡፡

ከልምድና ከስህተት መማር ያልቻለው የትግል ሥልት ግን የረባ ዕርማት ማሳየት አልቻለም፡፡ የካህሳይና የድላይ ቃል የተገባባ ፍቅርም በትግል ሥፍራ ምደባ መለያየት ተራራቀ፡፡ በኢሕአፓ ውስጥ ቀውሱ የተባባሰበት፣ ከሕወሓትም ጋር የነበረው ግንኙነት የከፋበት፣ የደርግ ጥቃትም የበረታበት ጊዜ መጣ፡፡ በኢሕአፓ/ኢሕአሠ ውስጥ የታየ መግደልና መገዳደል የትግልን ቅስም እየሰበረ ከትግል መሸሽ ሲመጣ፣ ካህሳይም ወኔው ተጎድቶ ኤርትራ ተሰደደ፡፡ ከኤርትራም ወደ ሱዳን ገባ፡፡ እዚያ ሆኖም፣ እንዴት ሆና ይሆን እያለ ይናፍቃት የነበረችው ድላይ ቆስሳ ስለመሞቷ ይረዳል፡፡ በሐዘንና በዕንባ እንደተቆራመደ አሜሪካ ገብቶ ተምሮ ሥራ ይዞ ቤተሰብ ካፈራ በኋላም ባለውለታውን ይመር ንጉሤን ባያገኘውም ባለቤቲቱንና ቀሪ ቤተሰቧን አግኝቶ ያሰበውን አደረገ፡፡ በታጋይነቷ የጀግንነት ዝና ያተረፈችውን ድላይን አማሟትም አጣርቶ በጉዞ ላይ ሳለች ባደባ የሚሊሻ ጥይት እንደተደፋች አወቀ፡፡ አውቆም ሁለቱ ወጣቶችና ሌሎች የትግል ባልደረቦቹ ያለፉበትን የትግል ታሪክ ለአደባባይ በማጋራት፣ የድላይ ቤተሰቦችም ተመሥገን እንኳን አኩሪ ገድሏን በመጨረሻ ለማወቅ በቃን ብለው እንዲደሰቱ አበቃቸው፡፡

ከልዩ ልዩ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች ከመጡ የትግል ባልንጀሮች ጋር በትግል ተሠልፎ የነበረው የትግራዩ ልጅ ካህሳይ አብረሃ ለዓመታት ከትግል ባልንጀሮቹ ትውስታ ጋር ኖሮ ኖሮ ተጋድሏቸውን በመጽሐፍ እየዘከረ ብርታታቸውን/ገድላቸውን ሲያደንቅ፣ ስቅየታቸውን ሲሰቃይ ናፍቆቱንና ፍቅሩን በትዝታ እያስተመመ ዕንባውን ሲረጭ አስተዋልን፡፡ የካህሳይ አብረሃ መጽሐፍ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትስስር በለውጥ ትግልና መስዋዕትነት የታነፀ መሆኑን የሚያሳይ/የሚዘክር የታሪክ ሐውልት ነው፡፡

የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞና የደቡብ ልጆች አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ የተባባሉበትን ኅብራዊ የትግል ታሪክ ትናንትና ባየንበት ዓይን፣ ዛሬ ደግሞ አውሬው የወጣ ‹‹ብሔርተኝነት›› አንዳንድ ፍሪት ወጣቶችንና ታዳጊዎችን በጥላቻና በበቀል ህሊናና ስሜታቸውን እየሞላ ጨካኝ ግፍ ሲያሠራ አስተዋልን፡፡ የትግራዩ ካህሳይና የቆቦይቱ ልጅ ድላይ በትግልና በፍቅር ቁርኝት ያነፁት ሐውልት፣ እንዲሁም የወሎውን ገበሬ ይመር ንጉሤንና ካህሳይን ያቆራኘው የታሪክ ሰንሰለት ዛሬ በጥላቻ ፋስ ሲቀጠቀጥ አስተዋልን፡፡ በአይበገሬነት ለሕዝብና ለለውጥ አፍላ ነፍሳቸውን ለሰጡት ለእነ ካህሳይ ያለቀሰ ዓይናችን፣ ዛሬ ደግሞ ድርብ ለቅሶ አለቀሰ፡፡ በጥላቻ ተዘርፈው የጥፋትና የአራጅነት ተግባር መጫወቻ ለሆኑ፣ መጫወቻ ሆነውም ሕዝብን እያረገፉ ለረገፉ ወጣቶቻችን አለቀስን፡፡ እየረገፉ ላረገፋቸው ንፁኃን ሕፃናትና አባት እናቶች አለቀስን፡፡ ሕዝብና አገርን በመታደግ ፈንታ እንዳይሆኑ ለማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ እስከ ማፋጀት የሚሄድ ማንኛውንም ጭካኔና ግፍ ማካሄድ አንድምን በኢትዮጵያ ውስጥ ትግል ነኝ ብሎ ሊያመሳቅለን ቻለ? በቀልና ጥላቻ ታዳጊዎችንንና ወጣቶቻችንን እየዘረፈ ምንም ያልበደሉ ሕፃናትንና እናቶችን፣ አዛውንት ገበሬዎችን የሚገድሉ፣ የሚዘርፉ፣ የሚደፍሩ፣ የሚያፈናቅሉ ግፍ ሠሪዎች ሊያደረግብን እንደምን ቻለ? ግልጽ ነው፡፡ የእነ ካህሳይና የእነ ድላይ ኅብራዊ መተሳሰብ ኅብራዊ የሕዝብ ፍቅር እየተኮተኮተና እጎለመሰ ወደ ዛሬው ጊዜ በአግባቡ ሊሸጋገር ያልቻለበት የታሪክ ክፍተት ስለተፈጠረ ነበር፡፡

ክፍተቱ የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ውዳሴ፣ የንግግር መክፈቻና መዝጊያ መሆን የጀመረበት ሙሉ የጥርነፉ አገዛዝ ብቅ ካለበት ከ1969 ዓ.ም. ማክተሚያ አንስቶ እስከ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ያለውን ዘመን ያጠቃለለ ነው፡፡ ከአርባ ዓመታት የዘለለ ጊዜን የሚሸፍን፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ትግሉ በከተማም በገጠርም በኩል ስብርብሩ ከወጣ አንስቶ ከድቆሳ የተረፉ ብዙ ወጣቶችና የተማሩ ሰዎች በረሃ እያቆራረጡ በስደት ነጎዱ፡፡ በቦሌ በኩል ወደ ውጭ ለመሄድ የሥራና የትምህርት አጋጣሚ ሲያገኙም በሄዱበት ቀልጦ መቅረት ሌላው የስደት መልክ ነበር፡፡ አገሪቱ በዚህ መልክ ከድቆሳ የተረፉ ብዙ ውድ ልጆቿን አጥታለች፡፡ በመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አፄነት ጊዜ የጋሸበው ስደት እዚህ ጊዜ ላይ ረገበ የሚባል አይደለም፡፡ ወደ ምዕራብ አገር ለመሄድ አጋጣሚ አግኝቶ ተመልሶ የሚመጣ ሰው (ያልከፋው የገዥው ክፍል አካል ካልሆነ በቀር) ጤና ያጣ ያህል ነበር የሚቆጠረው፡፡

በስደት ሰው ከመራገፉ ጎን ለጎን ከገጠር እስከ ከተማ ያለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየተበተበ የሄደው አገዛዝ በልሽቀትና በንቅዘት ሰደድ ተሰለቀጠ፡፡ ጨዋነት፣ በሀቅ መሥራት፣ በወዝ ማደር፣ በሥራ ማደግ በየትኛውም ኑሮ መስክ ነውርና ጅልነት መሰለ፡፡ መዝረፍ እያስቦጠቦጡ መቦጥቦጥ፣ ስለሀቀኝነት ስለቁጥጥር ስለልማት ስለአዲስ ባህልና ሥርዓት ከላይ እያወሩ ከሥር ተቃራኒውን መሥራት ሁሉንም የኑሮ መስክ አነከተ፡፡ ይህ የዝቅጠት ጉዞ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ከተተከለም በኋላ (ለተወሰነ አጭር ጊዜ ደንቀፍቀፍ ከማለቱ በቀር) የቀጠለ ነው፡፡ ሕወሓታዊ አገዛዝ ይዞት የመጣው የአዕምሮ ሙሽት ዕይታን፣ ተቆርቋሪነትንና መተሳሰብን በየብሔር በየጎጥና በየጎሳ ሁሉ እየበጣጠሰ ስለሄደ ንቅዘቱና የዘረፋ ሽሚያው ያንኑ ያህል ተባዝቶ ነበር፡፡ ከሽሚያው ጋርም ተጠቃሁ፣ ተበለጥኩ፣ ተገፈፍኩ ባይነቱ የሚያመነጨው መብከንከን ሠፈር ለሠፈርና አደባባይ ለአደባባይ ከሚናፈሰው የዱሮና የዘንድሮ የበደል ትርክት ጋር ይወፍራል፡፡ የበደል ግንዛቤ ሲወፍር ደግሞ፣ በአዕምሮና በስሜት ውስጥ ቁጭት፣ ጥላቻና በቀል የሚኖራቸው ይዞታ እየደረጀ ይሄዳል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ፣ ሌሎች የሰብዕና ጅማቶች እየተበጣጠሱ የማመዛዘንና ሚዛናዊ ግንዛቤ የመፍጠር አቅም እየሰለለ፣ የርኅራኄና ከእኔ ይቅር የማለት አቅሞች በጥላቻና በበቀል ስሜት እየተሰለቀጡ የሰብዕና እልቀት ያድጋል፡፡ በሰሜንም በታች በኩልም ያየነው ፈሪኃ ፈጣሪ፣ አዛውንት አካባሪነት፣ ርኅራኄና መሰቀቅ ድራሹ የጠፋበት (ጭካኔ ጭንቅላት ላይ የወጣበት) ነውረኛ ጥቃት የዚህ የሰብዕና እልቀት ውጤት ነው፡፡

በፌዴራል መንግሥት ከለውጡ ወዲህ እየተገነባ ያለውና በጭካኔ የተሞላውን የጥፋት ወረራ ተዋግቶ በማምከን ተግባር የተፈተነው መከላከያ ሠራዊታችን የአዲስ ሕዝባዊ ሥርዓት ምልክት ነው፡፡ ሕዝባዊ ፍቅር ወደ አገረ መንግሥታዊ የታጠቀ ሠራዊት ሲያሸቅብ አውሬነት ወደ ትግል ሠፈር መውረዱ የምፀት ምፀት ነው፡፡ የሰብዕና እልቀት የተንሰራፋበት ረዥም ክፍተት ገና በልምላሜ አልተሞላም፡፡ የዘቀጠውን የትምህርትና የምዘና ሥርዓት የማንሳት መርሐ ግብር እንደተያያዘን ሁሉ፣ የጨለምተኝነትና የጥፋት መጫወቻ ሆነው ሕዝብን ማመስና ኑሮውን ማወዳደም ትግላቸውና ዕርካታቸው አድርገው የያዙ ወጣቶችን ከአዘቅት ለማውጣት ልዩ መርሐ ግብር መቀየስም ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ ይህንን ጉድ አጠውልገን ወጣቶቻችንን ቢያንስ በአዲስ ሕይወት የተሰፋ ችቦ ሥር ለማሰባሰብ ሳንችል የነገው የየካቲት አብዮት ሃምሳኛ ዓመት ቢደርስብን ምን ይውጠናል? ነጠላ ዘቅዝቀንና ተሸማቀን ልናከብረው ነው?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...