Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ችግሮችን በማለባበስ ጊዜያዊ መፍትሔ እየሰጠን ሳይሆን በሳይንሳዊ ጥናት ምላሽ እንዲያገኙ ከመሠረቱ እየሠራን ነው›› ወ/ሮ ጽዋዬ ሙሉነህ፣ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ   

ወ/ሮ ጽዋዬ ሙሉነህ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክስ ኤንድ ሒዩማንራይት ሕግ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪ ሲመረቁ ለሦስት ዓመታት ያህል በዓቃቢተ ሕግነት በኋላም በፌዴራል ፍርድ ቤት ለ14 ዓመታት በዳኝነት አገልግለዋል፡፡ በራሳቸው ፈቃድ ከዳኝነት ሥራ ለቀው በግላቸው ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በአማካሪነት ሠርተዋል፡፡ ዳግም ወደ መንግሥት ሥራ ያስገባቸው ጉዳይ ደግሞ የራሳቸው ገጠመኝ ነው፡፡ ገጠመኛቸው በፍርድ ቤት ያለውን ውጣ ውረድና የሰዎች እንግልት ከውጭ ሆነው እንዲያዩ ዕድል የፈጠረ ነበር፡፡ በመሆኑም ለውጡን ተከትለው ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ ይዘው የችግሩ ፈቺ አካል ሆነው ለመሥራት በሚል ወደ መንግሥት ሥራ ገብተዋል፡፡ መንግሥት መሥሪያ ቤት ዳግም ከተመለሱ በኋላ አንድ ዓመት ያህል የፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ካለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ ወዲህ ደግሞ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ ቢሮው በሚሠራቸው፣ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ከምሕረት ሞገስ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ሥልጣንና ተግባር ምንድነው?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- የአዲስ አባባ ፍትሕ ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊዎች የሚመሩ ሁለት ዘርፎች አሉት፡፡ አንዱ የክርክሩ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የፍትሐ ብሔር ክርክሮችን፣ ማለትም በአዲስ አበባ መስተዳድር ሥር ያሉ ቢሮዎች በሚከሱበትም፣ በሚከሰሱበትም ጉዳይ ቀርበን የምንከራከረው እኛ ነን፡፡ ከሌሎች ዓቃብያነ ሕግ ቢሮዎችና ከፍትሕ ቢሮዎች ለየት የሚያደርገን የፍትሐ ብሔር ክርክሮች ላይ በጣም መሥራታችን ነው፡፡ እዚሁ ዘርፍ ውስጥ የክርክር ምክትል ቢሮ ኃላፊ በሚመራው ዘርፍ የወንጀል ጉዳዮችን እንይዛለን፡፡ አብዛኛው ሥልጣናችን ከግል ተበዳይ አቤቱታ አቅራቢ የሚመጡ ጉዳዮችን ማለትም ስድብ፣ ዛቻና ሌሎችን ማየት ነው፡፡ ሁለተኛው ዘርፍ የሕግ ሥርፀትና ምክር ዳይሬክቶሬት ነው፡፡ በዚህ ትልቁ ሥራችን በከተማው የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎችን ማርቀቅና እንዲፀድቁ ለካቢኔው ወይም ለምክር ቤቱ ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ለአዲስ አበባ ሕዝብ የሕግ ማስረፅ ሥራ ወይም ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ከሕግ ሥርፀቱ ጎን ለጎን የመንግሥት ቢሮዎች ለሚፈልጓቸው ፕሮጀክቶች ውል ሲዋዋሉ፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ እንዲሆን ምክር እንሰጣለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት አለን፡፡ ይህ በከተማው ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚከላከልና የሚቆጣጠር ነው፡፡ ለዚህም በየመሥሪያ ቤቱ ተጠሪዎች አሉን፡፡ በሰብዓዊ መብት ዘርፍም ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለፉት ስድስት ወራት ለ6,000 ያህል የደንብ ሠራተኞች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ አዲስ አበባ መነሻ፣ መድረሻና መተላለፊያ በመሆንዋም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ቢሮዎችን በማስተባበር አብረን የምንሠራበት ጽሕፈት ቤት አለን፡፡ ይህን በተመለከተ እኛ ከመጣን በኋላ ምክር ቤት አቋቁመን እየሠራንና ሥልጠና እየሰጠንም እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡ቢሮው እነዚህን ሥልጣንና ተግባራት ይዞ ሪፎርም ውስጥ ገብቷል፡፡ የክርክር ዘርፍ አለ፣ የሰብዓዊ መብት አለ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አለ፡፡ ወደ ሪፎርሙ  የሳቧችሁ ዋነኛ ችግሮች ምንድናቸው?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- ኅብረተሰቡ የፍትሕ አካላት ላይ የሚያነሳው ችግር ግልጽና ግልጽ ስለሆነ ሪፎርሙ ያስፈለገው ለዚሁ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ፌዴራል ከተማና ዋና ከተማ ችግሩ የበለጠ የጎላ ይሆናል፡፡ የፍትሕ ቢሮ ሪፎርሙን ብቻውን የሚያደርገው አይደለም፡፡ የፍትሕ ሥራና ሪፎርም ከሌሎች ጋር አብሮ የሚሠራ ነው፡፡ ከሕግ አውጪው፣ ከዳኝነት አካሉ፣ ከሌሎች ሥራ አስፈጻሚ አካላት ጋር አብሮ መሠራት አለበት፡፡ በመሆኑም በመንግሥት በፌዴራል ደረጃ የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ፣ ጥናቶች እየተጠኑና ሥልጠናዎች እየተሠጡ ነው፡፡ በቅርቡ የተጠቃለለ ነገር እንጠብቃለን፡፡ ወደ አዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ስንመጣ ቢሮው የበለጠ ሥራውን አሳልጦ ባለው ሥልጣንና ኃላፊነት ውስጥ አዘምኖ መሄድ፣ ሕዝቡን ከሮሮ ማውጣትና ተገቢ አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡ ይህ ሁሌም የኃላፊዎች ሥራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው በቢሮው የሪፎርም ሥራ መሥራት፣ በለውጥ ዕይታ ውስጥ መግባት፣ ሕዝቡን የበለጠ ማገልገል፣ አለ የምንለውን ችግር መቅረፍ፣ የከተማ አስተዳደሩ ያሉበትን የሕግ ችግሮች በጥናት እያየንና እየለየን መለወጥና ከላይ ከላይ ሳይሆን ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት አለብን ብለን የተነሳነው፡፡

ሪፖርተር፡የሪፎርሙ መነሻ የሕዝብ እሮሮ ነው፡፡ ሕዝቡ እሮሮ ከሚያሰማባቸው ጉዳዮች አንዱ ከቦታችን ተፈናቅለን የሚለው ይገኝበታል፡፡ ለልማት የሚባለው እንዳለ ሆኖ በሕገወጥ ሠፍረዋል ከሚባሉትም ቅሬታ ይነሳል፡፡ ዕግድ ራሱ የችግሩ አካል ሆኗል፡፡ ችግሩን እንዴት እየፈታችሁት ነው?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- ከቦታ የሚነሱ ሰዎችን በተመለከተ መመርያ አለ፡፡ የምትክ ቦታ አሰጣጥና የካሳ አከፋፈሉን ጨምሮ በካቢኔ የፀደቀ ነው፡፡ በአጠቃላይ መታየት ያለበት አዲስ አበባ እያደገች መሆኗን ነው፡፡ ስታድግና አንድ መሠረተ ልማት ሲሠራ በግድ ከአንድ ቦታ የሚፈናቀሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን የቱ ያመዝናል? ለመንግሥትና ለሕዝብ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው የቱ ነው? የሚለው ይታያል፡፡ ይህም ሆኖ ተገቢ ካርታ ኖሮት ከቦታው ላይ የሚነሳ ካለ ደግሞ የካሳ አከፋፈልና የምትክ ቦታ አሰጣጥ ዝርዝር መመርያ ወጥቶ በካቢኔ ፀድቋል፡፡ ፍትሕ ማለት የሁሉም ነች፣ ለሁሉም ነች፡፡ ለአንዱ ፍትሕ ሰጥተሽ ለሌላው ማጓደል ፍትሕ አይደለም፡፡ ሕዝብ ሲጠቀም አንድ ግለሰብም ይጠቀማል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ሲነሳ በተገቢው መንገድ እንዴት ነው የሚነሳው? የሚለው ይታያል፡፡ ለመንግሥትና ለሕዝብ የሚጠቅም ትልቅ የልማት ቦታ ሆኖ ከሆነ ቦታው የተፈለገው ሁላችንም መነሳት አለብን፡፡ ከዚህ ውጪ አግባብ ባልሆነ መንገድ ከሆነ የተነሳው ይህ ፍትሕ አይደለም፣ ልክ አይደለም፡፡ በተገቢው መንገድ ከሆነ የሚነሳው መብቱ ተጠብቆለታል ወይ? ተብሎም በተገቢ መታየት አለበት፡፡ ሲነሳ ምትክ ቦታና ካሳ ተሰጥቶታል ወይ የሚለው መታየት አለበት፡፡ የምትክ ቦታና የካሳ መመርያው ከአንድ ቦታ ተነስቶ ሌላ ቦታ በሚኬድበት ጊዜ የሚታጣውን ማኅበረሰባዊ እሴት ሁሉ ያካተተ ነው፡፡ በቂ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ግን የሕግ የበላይነትን ከላይ ይዘን በሕግ መሠረት ከተሠራ ፍትሕ የሁሉም ይሆናል፡፡

ሰብዓዊ መብት አይጣስም፣ የግለሰብ መብት አይጣስም፣ መንግሥትም በተገቢው መንገድ ሥራውን ይሠራል፡፡ መንግሥትም ደግሞ ከሕግ ሥር ነው፡፡ ከሕግ ውጪ ሰዎችን አያስነሳም፡፡ ለዚህ ሕግ ደንግጓል፡፡ እኛ ደግሞ በየክፍለ ከተማው ያሉ ሥራ አስፈጻሚዎቻችን በሕጉና በመመርያው መሠረት በአግባቡ ተነሺዎችን እያስነሱ ቦታውን ለልማት በተገቢው ማዘጋጀት አለባቸው በሚለው ላይ የሕግ ማስረፅ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ  ከሁሉም አቅጣጫ እኩል በሆነ መንገድ መሥራት አለብን፡፡ እኛ ይህንን ሥራ ተወጥተናል ወይ ሲባል ገና እንወጣዋለን፡፡ ሕዝቡን በደንብ አስተምረናል ወይ ሲባል እናስተምራለን፡፡ ሥራ አስፈጻሚዎች በተገቢ በሕጉና በኃላፊነታቸው የሚጠበቅባቸውን መወጣት ያለባቸውን እየሠሩ ነው ወይ ሲባል፣ ማስተማርና ማሠልጠን የእኛ ሥራ ሆኖ መሥራት አለብን፡፡ ለዚህ ነው የፍትሕ ሪፎርም የሚያስፈልገው፡፡ አሁን አስፈጻሚዎችን ለማሠልጠን ብዙ ጊዜ ስለሌላቸው በዙም (በበይነ መረብ) ሥልጠና መስጠት እየጀመርን ነው፡፡ አልሠራንም አንልም፣ ነገር ግን ሠርተን ሕዝቡን ማርካት ይጠበቅብናል፡፡

ሪፖርተር፡በመልማቱ ሳይሆን በልማት አካሄድ በኩል ሰዎች ቅሬታ ውስጥ በመግባታቸው ሳቢያ ዕግድ ያመጣሉ፡፡ በርካታ የልማት ሥራዎችም ከበፊት ጀምሮ በእግድ ሲስተጓጎሉ ተስተውሏል፡፡ ይህን እንዴት እየፈታችሁት ነው?

ወ/ሮ ፅዋዬ፡- ዕግድ በሕግ መርህ ደረጃ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ሰው እስኪያስፈርድ ድረስ ተከራካሪው ሌላ ዕርምጃ ውስጥ እንዳይገባ ክርክሩ እስኪያልቅ ታግዶ መቆየቱ ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ዕግድን እንዴት ነው የምንጠቀመው? አፈጻጸሙ እንዴት ነው? የሚለው ላይ ነው በአብዛኛው ችግሮች የሚነሱት፡፡ ስለዚህ ዓምና ታኅሳስ አካባቢ እዚህ ቢሮ እንደመጣን ከፍርድ ቤቶች ጋር መነጋገር ጀመርን፡፡ ችግሩ ምንድነው ለሚለው መልስ ሊሰጠን የሚችለው ማነው ብለን ተወያየን፡፡ ዓቃቢያነ ሕጎች ብናጠናው ልክ አይሆንም፡፡ ዳኞችም ቢያጠኑት ልክ አይሆንም፡፡ በመሆኑም የሁላችን አስተማሪ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጥናው በሚል ተስማምተንና የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ተነሳሽነቱን ወስዶ ጥናቱ እንዲጠና ተደረገ፡፡ የልማት ሥራ ተጠንቶ እስኪያልቅ ጊዜ ይወስድበታል፡፡ በመሆኑም ይህ እስኪያልቅ በፍትሕ አካላት በኩል ግንዛቤ ለመፍጠር የከተማ አስተዳደሩ ገንዘብ ወጪ አድርጎ፣ በአዲስ አበባ ያሉ የፌዴራልና የአዲስ አበባ መስተዳድር ዳኞች ዕግድ በልማት ሥራዎች ችግር እየሆነ መምጣቱንና በራሳቸው መካከል ምን መደረግ እንዳለበት ተወያይተዋል፡፡ ተጠንቶም አልቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግ፣ ጠበቆችና ግለሰቦች የተሳተፉበት ሰፊ ጥናት ነው ያጠናልን፡፡ በጥናቱ አንኳር የሆኑ ችግሮች ወጥተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያለበት ችግር ምንድነው? በዳኝነቱ አካላት ዕግድ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ አግባብ ነው? አይደለም? ምን መሆን አለበት? ሕጋችን ከሌሎች አገሮች ሲነፃፀር የቆየ ነውና ምን መደረግ አለበት? የሚሉት ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ የኬንያን ብናይ የሕዝብ ፍላጎት ባለባቸውና መንግሥት ለልማት በሚያውላቸው ቦታዎች ዕግድ አይመጣም፡፡ እንዲህ ያለውን ባገናዘበና በዘመናዊ መንገድ ሕጉ መሻሻል አለበት በሚል ሕግ አውጪው የሚወስደው ኃላፊነት ታይቶ የተገቢነት ግምገማ ሠርተናል፡፡ አጥኚው በተሰጡት ግብዓቶች መነሻ ጥናቱን አጠቃሎ በተለይ ዋነኛ የምንባለው የፍትሕ አካላት የምንሠራውን ሥራ ዘርዝሮ ኃላፊነት እንድንወስድ ሰጥቶናል፡፡ በእኛ በኩል ትልቅ ችግር የነበረው ዓቃቢያነ ሕጎቻችን ዕግድ ይነሳልን ሲሉ ምላሽ የማይሰጥበት አንዳንድ ሁኔታዎች ስለነበሩ ክትትል አይደረግም ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን ዕግድ ያለበት መዝገብ በሙሉ ተቆጥሮ ዳታ ላይ ተቀምጦ ክትትል እንድናደርግበት ነው በጥናቱ የተመለከተው፡፡ ጥናቱን አስጠንተን ዳኞቻችንና ሕግ አውጪው ይህንን ዓይነት ዕርምጃ እንዲወስዱ ከጥናቱ ጋር ደብዳቤ ጽፈን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገብተናል፡፡ ወደ ላይ ማዘዝ ባንችልም የራሳችንን ችግር ለመቅረፍ ጥናቱ ላይ የተገኘውን አስፈላጊውን ነገር አድርገናል፡፡ እያደረግንም እንገኛለን፡፡   

ሪፖርተር፡በጥናቱ መሠረት ምን ችግር ተገኘባችሁ?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- በእኛ ላይ የነበረው ችግር አለመከታተል ነው፡፡ ዕግድ ያለባቸውን መዝገቦች በቁጥር ይዞ ተከታትሎ ዕግዱን ከፍርድ ቤት የማስነሳት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መዝገቦቻችን የት እንዳሉ አናውቅም ነበር፡፡ አሁን ምን ያህል ክርክር እንዳለ፣ ምን ያህል ዕግድ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱ ዓቃቤ ሕግም ያሉትን ጉዳዮችና የደረሰበትን ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ክትትልም ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡– በውል አስተዳዳር ላይ ችግሮች አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የልማት ሥራዎች ሲስተጓጎሉ ይስተዋላል፡፡ ቢሮው ይህንን ለመቅረፍ የሄደበትን ርቀት ቢገልጹልን?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- በአጠቃላይ ከ60 እስከ 65 በመቶ የመንግሥት በጀት ግዥ ላይ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ግዥ ውስጥ በምሠራበት ጊዜ የተጠና ጥናት ነው፡፡ ውሎች በሚበላሹበት ጊዜ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ነው አንድን መሥሪያ ቤት ወክሎ ክርክር የሚያደርገው፡፡ ከመነሻው እነዚህን ውሎች እንዴት ነው መዋዋል ያለብን? ከተዋዋልን በኋላ እንዴት ማስተዳደር አለብን? ውሎች የአንድ ቀን ወይም የሦስት ዓመታት ወይም የአምስት ዓመታት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ግዴታዎችና መብቶች በተገቢው እየተፈጸሙ መሄዳቸውን የሚያስተዳድር ሰው ሊኖር ይገባል፡፡ አለበለዚያ አንዱ ጋ የተበላሸ ነገር ካለ ሁልጊዜ ውሎች ወደ ክርክር ይሄዳሉ፡፡  ውል ብዙ ገንዘብ ይይዛል፡፡ ገንዘቡ ደግሞ የሕዝብና የመንግሥት ነው፡፡ ለዚህ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ ለማድረግ ከየት ወዴት እንሂድ በሚል ነው ለማስጠናት የፈለግነው፡፡ ለዚህም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናቱን እንዲያጠና ጠየቅን፡፡ የውል ዓይነቶች በጣም በርካታ ስለሆኑ ዩኒቨርሲቲው አንድ የውል ዓይነት እንድንመርጥ ጠየቀን፡፡ ተመካክረን የኮንስትራክሽን ውል መረጥን፡፡

ሪፖርተር፡ለምን የኮንስትራክሽን ውል ተመረጠ?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- አዲስ አበባ በርካታ የኮንስትራክሽን ሥራዎች እየተካሄዱባት ነው፡፡ አንድ የኮንስትራክሽን ውል ደግሞ በርካታ ብር ይይዛል፡፡ ሲበላሽም በርካታ ገንዘብ ይዞ ይሄዳል፡፡ የኮንስትራክሽን ውል በዩኒቨርሲቲው ቢሠራም ውል በባህሪው የሚያመሳስለው፣ የሚለይበትም ስላለው ጥናቱ ብዙ ነገር ይፈታልናል ብለን ጠብቀናል፡፡ የኮንስትራክሽኑን ዘርፍም ጥሩ ነገር ላይ ያደርስልናል፡፡ ሌሎች ውሎችን እንዴት አድርገን እንሥራ የሚለውንም ይመልስልናል፡፡ እዚህ ላይ ከአዲስ አበባ ኦዲት ቢሮ ጋርም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ እነሱ በየቢሮው እየሄዱ ሥራቸውን ሲሠሩ ውሎች መጀመሪያውኑ በዓቃቤ ሕግ መመርመራቸውን እያረጋገጡ እንዲሄዱ ከስምምነት ደርሰናል፡፡ ለኦዲት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠትም መርሐ ግብር ይዘን እየጠበቅን ነው፡፡ አንዳንድ ችግሮችን አለባብሰን ወይም ጊዜያዊ መፍትሔ ሰጥተን ሳይሆን፣ ከመሠረቱ በሳይንሳዊ ጥናት ምላሽ እንዲያገኙ እየሠራን ነው፡፡  የኮንስትራክሽን ውል ጥናቱን አስጨርሰን በዓቃቢያነ ሕግና በመሐንዲሶች አስተችተናል፡፡ የኮንስትራክሽን ቢሮም የዚህ አካል እንዲሆን አድርገናል፡፡ ምክንያቱም የኮንስትራክሽን ውሎች የተለየ ባህሪ አላቸው፡፡ ማወቅ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ዓቃቤ ሕግም እንደ መሐንዲስም መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህን ጥናት ለሁሉም አካላት በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡ የጥናቱ ውጤት ኮንስትራክሽን ላይ ደረጃውን የጠበቀ ውል እንዲኖረን ያስችለናል፡፡

ሪፖርተር፡ውል ላይ ችግር መኖሩና በልማት ሥራዎች ላይ ያስከተለው መስተጓጎል ምን ያህል ከተማ አስተዳደሩን ጎድቶታል? ከፍትሕ አንፃር ያደረሰው ጉዳትስ?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- ጥናቱ ይህንን አላካተተልንም፡፡ ችግሩን አጥንቷል፣ ችግር መኖሩን አውጥቷል፡፡ ችግሩን እንዴት እንፍታው የሚለው ነው የታየው፡፡

ሪፖርተር፡ኮንስትራክሽን ሲነሳ አንዱ ችግር በተባለው ጊዜ አለመጠናቀቁ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ውል ሲደረግ የተቀመጠ ጊዜ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ኮንስትራክሽኑ በሚከናወንበት አካባቢ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦች መነሳት፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ዕግድ፣ ኋላ ላይ ደግሞ ወጪው በውሉ ከሰፈረው ገንዘብ ልቆ መገኘት፣ በአጠቃላይም ተያያዥ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ ችግሮች ነው የሚስተዋሉበት፡፡ ለውሉ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ አለማየት፣ አለመገመትና መፍትሔ ሳያበጁ መሄድም ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ እንዳይፈጠር ቢሯችሁ ምን መክሯል? የቄራ መንገድ ለአብነት ቢነሳ ቀድሞ ሕዝቡን የማወያየት ሥራ ስለተሠራ ብዙ ችግር ሳይገጥም ተጠናቋል፡፡

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት ቦታው ፅዱ መሆን አለበት፡፡ ፕሮጀክት ሲጀመር መሣሪያ ይገባል፣ የሰው ኃይል ይመጣል፡፡ ሥራው ከተጀመረ በኋላ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ማሽኖችም የሰው ኃይልም ባሉበት ይቆማሉ፡፡ የምትክ ቦታና ካሳ አከፋፈል መመርያ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችና ሒደቱን በሙሉ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ የልማት ተነሺዎች ቀድሞ መወያየት አለባቸው የሚሉና ሌሎች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ ይህንን የሚሠራ አስፈጻሚው አካል አለ፡፡ የእኛ የአዲስ አበባ አደረጃጀት ደግሞ ለዚህ አመቺ ነው፡፡ በማዕከል፣ በከፍለ ከተማና በወረዳ አደረጃጀት አለ፡፡ ይህ ልማት የሚደረስበትን ቦታ እስከ ጫፍ ይነካል፡፡ ስለዚህ ሁሉም አስፈጻሚ በየደረጃው መሥራት ያለበትን ሠርቶ ቦታው ፀድቶ የልማቱ ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡ የኮንስትራክራሽን ሥራዎች ከመጀመራቸው በፊት ይህ ባለመደረጉ ችግሩ ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም ይህንን አተኩረን መሥራት አለብን፡፡ ውል ውስጥ ከመገባቱ በፊት ቦታው ለልማት ዝግጁ ስለመሆኑ ሥራ አስፈጻሚው አካል እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ እርግጥ ይህ መሆን አለበት ብለንም ዝግት አናደርግም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያልታሰቡ ነገሮች በሥራ መሀል ያጋጥማሉ፡፡ ፕላን ይከለሳል፣ ያልታሰበ የልማት ተነሺ ሊመጣም ይችላል፡፡ በመሆኑም ከሥራው ጎን ለጎን ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አሠራርን ታሳቢ አድርጎ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ኅብረተሰቡም መረዳት አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በአዲስ አበባም የሚፈጸም ቢሆንም ከክልሎች ጭምር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን  ሴቶችና ሕፃናት ጭምር ለሕገወጥ ዝውውር እየተዳረጉ መሆኑንም የዓለም የፍልሰት ድርጅት አስታውቋል፡፡ እዚህ ላይ ያላችሁ ሚና ምንድነው?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- እዚህ ላይ በፌዴራል ደረጃ በ2012 ዓ.ም. የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አለ፡፡ ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ክልሎች ለማጠቃለል ብሔራዊ ምክር ቤት አቋቁሟል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ደግሞ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተቋቁሟል፡፡ የአዲስ አበባው በምክትል ከንቲባ ይመራል፡፡ አደረጃጀቱ እስከ ወረዳ መውረድ ያለበት ሲሆን፣ በክፍላተ ከተሞች ያለውን አዋቅረን ጨርሰን ወደ ወረዳ እየወረድን ነው፡፡ በከተማ ደረጃ አስፈጻሚ አካላት ያላቸውን ሥራ በጋራ የሚሠሩበት ነው፡፡ የሥራ ዕድልና ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የጤና ቢሮ የተጎዱትን ያክማል፡፡ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ተሃድሶ ላይ ይሠራል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ እኛ የማስተባበር ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ በጽሕፈት ቤታችን የጥሪ ማዕከልም እያቋቋምን ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ኮሚሽን ለማዕከሉ የ1.5 ሚሊዮን ብር ያህል ዕቃ ሰጥቶን ማዕከሉ በቁሳቁስ ተሟልቷል፡፡ ሠራተኛ ለመቅጠር በሒደት ላይ ነን፡፡ ይህ ተቋም በተጓዳኝ ሥልጠናም ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡የአዘዋዋሪዎችን ወንጀል በተመለከተስ?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- ወንጀሉን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር እየሠራን ነው፡፡ በመሠረቱ ግን ወንጀልን በተመለከተ ያለን ሥልጣን ትንሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ቢሯችሁ ያለው ድርሻ እስከ ምን ድረስ ነው?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- አዲስ አበባ ውስጥ ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እኛ ተወካይ ነን፡፡ ጥሰት የተፈጸመበትን ሰው ይዘን የወንጀል ምርመራና አስፈላጊው የሕግ ምርመራ እንዲደረግ ወደ ፌዴራሉ እንሄዳለን፡፡ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ አንዳንድ ጥሰቶች ይፈጸማሉ፡፡ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድም አለበት፡፡ ለዚህ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ አስፈላጊውን እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ለደንብ ሠራዊታችን በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በዕግድ ዙሪያም ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ሥልጠና በየጊዜው መደጋገም አለበት፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የምንችለውን ያህል እየሠራን ነው፣ እንሠራለን፡፡ በየቢሮው ለተጠሪ አካላት ሰብዓዊ መብት ላይ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ከተፈጸመ ደግሞ ቢሯችን ሁልጊዜም ክፍት ነው፡፡ ሰዎችም ይመጣሉ፡፡ የወንጀል ዳይሬክቶሬት ጉዳዩን በባለቤትነት ይዞ ይከታተለዋል፡፡

ሪፖርተር፡ቢሯችሁ ተጠያቂና ግልጽ እንዲሆን ያከናወናችሁት ተግባር ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ አገልጋይነትና ታማኝነትን ለማስፈን በመጀመሪያ ያደረግነው የዓቃቢያነ ሕግ የሥነ ምግባር ደንብ በካቢኔ ማፀደቅ ነበር፡፡ ዓቃቢያነ ሕግ የሚፈጽሙትን የሥነ ምግባር ግድፈቶች ታይቶ በምን መንገድ እንደሚወሰንባቸው የሚገልጽ ደንብ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ጉባዔ ተቋቁሟል፡፡ ዓቃቢያነ ሕግ ችግር ካለባቸው ታይቶ ይወሰንባቸዋል፡፡ የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬትም ተቋቁሟል፡፡ ይህ ዓቃቢያነ ሕግ የሚከራከሩባቸውን መዝገቦች በተገቢና በሕግ አግባብ ክርክር ማድረጋቸውን ይመረምራል፡፡ ይህንን በ2015 ዓ.ም. አጠናክረነዋል፣ በሰው ኃይል አደራጅተነዋል፡፡ ዓቃብያነ ሕጎቻችን በአደረጃጀት ክፍለ ከተማ ነው ያሉት፡፡ ተጠሪነታቸው ለክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ነው፡፡ ከ2014 ዓ.ም. እስከ 2015 ዓ.ም. በሰባት ክፍላተ ከተሞች ያሉትን ዓቃቢያነ ሕግና መንግሥት ላይ የተወሰኑ መዝገቦችን በሙሉ መርምረናል፡፡ ለምንድነው የተወሰነብን? የሚለውን ዓይተናል፡፡ በዚህ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው እንዲጠየቁ ግብረ መልስ እየሰጠን ነው፡፡ ሕዝቡም አመኔታውን ወደ እኛ እንዲመልስ አስፈላጊውን የቁጥጥር ሥርዓቶችና ተቋማዊ አደረጃጀቶች በመፍጠር እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡በፍርድ ቤት ያሉ የአሠራር መጓተቶች እንዲቀሩ በእናንተ በኩል የተሠራ ሥራ ካለ?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- የፍርድ ቤት መጓተትን በተመለከተ ዓቃቤ ሕግ በአብዛኛው ተከሳሽ ሆኖ ነው ፍርድ ቤት የሚቀርበው፡፡ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ የሕግ አካላት ስለሆኑ ይህንን በራሳቸው የሚያዩት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡ሁላችሁም የአዲስ አበባ፣ የፌደራልም ሆነ የክልል ፍትሕ አካላት አገር ውስጥ ፍትሕ ለማምጣት ነው የምትሠሩት፡፡ አሠራሮች እንዲሻሻሉና መጓተቶች እንዲቀንሱ አልተወያያችሁም?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- በፍትሕ ሚኒስቴር አማካይነት ሁሉም የክልልና የከተማ ፍትሕ ቢሮዎች ያሉበት የጥምረት ፎረም አለ፡፡ ይህ የፍትሕ ቢሮዎች የምንገናኝበትና የምንመክርበት ነው፡፡ በፊት ዳኞችና ዓቃቤ ሕጎች አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ከለውጡ ጋር የዳኝነትን ነፃነት ይጋፋል በሚል በአብዛኛው ቀርቷል፡፡ በክልሎች የተፈጠረ አሠራር አለ፡፡ በአዲስ አበባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሚሰበስቡት አለ፡፡ እዚህ አባል ለመሆን ለቀድሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ሆኖም የተሰጠኝ ምላሽ የወንጀል ሥልጣን ስለሌላችሁ አባል መሆን አትችሉም የሚል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡አሠራራችሁን አውቶሜትድ አድርጋችኋል፣ ችግሩን ይቀርፋል?

ወ/ሮ ጽዋዬ፡- መሥሪያ ቤታችንን ለማዘመን የሶፍትዌር ሥራ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በራሳቸው ወጪ ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡ ይህ ሶፍትዌር የክስ ሒደቶችን ከክፍለ ከተማ ጀምሮ እስከ ማዕከል ድረስ ለመከታተል ዕለት ከዕለት ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ በፓናል የዓቃቢያነ ሕግ ውይይት መዛግብት እንዲዘጉ ሲወሰን፣ የመረጃ ደኅንነቱ ተጠብቆ በተሟላ ሁኔታ እንዲመዘገብ ያስችላል፡፡ መረጃዎችን በሙሉ በሶፍት ኮፒ ያጠናክራል፡፡ ሲስተሙ የሚበዙ ፋይሎችን የሚያስቀርና ሥራዎችን የሚያቀላጥፍ በመሆኑ ከአሠራር ጋር የተያያዙ ችግሮችን የሚያቃልል ይሆናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...