የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ለመስጠት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የመጨረሻ ፈቃድ እየጠበቀ ያለው ሳፋሪኮም፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በሳፋሪኮም መካከል በጋራ ለመሥራት ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት ለማሳደግ ሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸው ነው፡፡
የኢትየጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎትን እያሰፋ ሲሆን፣ ይህንን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና አማራጭ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለመስጠት በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት አጋዥ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገልጸዋል፡፡
‹‹ስምምነቱን ውጤታማ ለማድረግም ባንኩ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሁለቱ ተቋማት በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በመሥራት በጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ስምምነት የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል፤›› ያሉት አቶ አቤ፣ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው ሥልታዊ ትብብር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በለውጥ ጉዳና ላይ የሚገኘው ባንካቸው ከተያዙት የለወጥ ውጥኖች መካከል ደግሞ ዲጂታል ባንክ አገልግሎትና የማይቆራረጥ የቴሌኮም ኔትዎርክ ሥራ ላይ ማዋል ነው፡፡ በመሆኑም ሳፋሪኮም በዚህ ረገድ ያለው ልምድ የባንኩን የዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ ችግር መቅረፍና አቅሙንም የሚያሳደግ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሳፋሪኮምን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አኑዋር ሱሳ፣ ‹‹አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ኩባንያቸው አብሮ መሥራቱ ትልቅ ዕድል ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሳፋሪኮም በአፍሪካ ደረጃ እያሳየ ያለው ለውጥ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ተንፀባርቆ በጋራ ለማደግ የሚረዳ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት እንዲህ ያለውን ስምምነት መፈጸማቸው፣ ሳፋሪኮም ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡ ኩባንያው ያለውን ልምድ በመጠቀም ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሳፋሪኮም በቴሌኮም ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሥራ የገባ የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ ሲሆን፣ በገንዘብ ማስተላለፍና በዲጂታል ባንኪንግ ሥራ ውስጥ ለመሰማራትም ብሔራዊ ባንክ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠው ሲሆን፣ ወደ ሥራ ለመግባትም የባንኩን የመጨረሻ ፈቃድ እየተጠባበቀ ነው፡፡
በዚህም የሚታወቅበትን የኤም ፔሳ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ገበያ ለማስተዋወቅ ያቀደ ሲሆን፣ ኤም ፔሳ ሥራ ሲጀምርም ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረው የቴሌ ብር አገልግሎት ዋነኛ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ80 ዓመታት በላይ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ1.2 ትሪሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ ባንኩ የደንበኞችን ቁጥር 38.1 ሚሊዮን መድረሱን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ ከ1880 ቅርንጨፎችም አሉት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንትናው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ ድሬ ጁቲ ቀበሌ በክቡር ዶ/ር አርቲስት ዓሊ ቢራ ስም 1,881 ቅርንጫፍ ‹‹ዓሊ ቢራ ቅርንጫፍ›› በሚል መጠሪያ ሥራ አስጀምሯል፡፡