Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዲሱ ረቂቅ የቫት አዋጅ ለማኅበረሰቡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው!

የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ተግባራዊ ከሚደረግባቸው ከ151 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ይህንን የታክስ በኢትዮጵያ ዓይነት መተግበር ከጀመረ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኗታል፡፡ በአፈጻጸም ረገድ ብዙ ክፍተቶች እየታዩበትም ቢሆን እየተሠራበት ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት የተጨማሪ እሴት ታክስን ሥራ ላይ ለማዋል ተዘጋጅቶ በነበረው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ሲደረግ እጅግ በርካታ አለመግባባቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስን በዚያን ወቅት በነበረው ኢኮኖሚያዊ አቅም ተግባራዊ ማድረጉ ሊሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ በተለይ በወቅቱ የነበሩ የንግድ ምክር ቤት መሪዎች በብርቱ ሲሞግቱበትም ነበር፡፡ 

በዚያን ወቅት አዋጁን መተግበር ያስከትላሉ ተብለው በዝርዝር ከቀረቡ በርካታ ጉዳዮች መካከል ለዋጋ ንረት መንስዔ ይሆናል የሚለው አንዱ ነበር፡፡ ሌላው የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔው በዝቷል የሚል ሐሳብ የተለያዩ ማሳያዎችን በማቅረብ አስረድተዋል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክሱ 15 በመቶ መሆኑ ተጠቃሚውን ይጎዳል በሚልም ሰፊ ክርክር ቢደረግበትም ተቀባይነት የሚያገኝ የተጨማሪ እሴታ ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል ሊታወጅ ችሏል፡፡ 

ከሰሞኑ ይህንን አዋጅ እንደ አዲስ አሻሽሎ ሥራ ላይ ለማዋል አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ምክር እየተደረገበት ነው ሲባልም ያስታወሰኝ ይህ ከ20 ዓመታት በፊት የነበረውን ሙግት ነው፡፡ 

የተጨማሪ እሴት ታክስ ሄዶ ሄዶ ጫና የሚፈጥረው ታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ወይም ተገልጋዩን ነው የሚለው ሥጋት አሁንም በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የተመለከቱ አንቀጾችና ታክሱ የሚመለከታቸው አገልግሎቶች በ15 በመቶ መጨመራቸውን ታች ያለው ተጠቃሚን የሚጫን ይሆናል፡፡ 

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ በርካታ ማሻሻያዎች ከነበሩ አዋጅ ጠንከር ያሉ አንቀጾችን የያዘ ብቻ ሳይሆን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚመለከታቸው የቢዝነስ ዘርፎችና አገልግሎቶችን በስፋት ያጠቃለለበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ታክሱ የማይመለከታቸው ዘርፎች ሁሉ እንዲመለከታቸው ተደርጓል፡፡ 

ይህ ማለት ቀድሞም ታክሱ የሚመለከታቸው የቢዝነስ ዘርፎች እንዳሉ ሆነው፣ ሌሎች አዳዲስ ቢዝነሶች ተጨማሪ ታክስ እንዲመለከታቸው ሆኖ ባዘጋጁት ተገልጋዩ 15 በመቶ ታክስ የሚከፈልባቸው አገልግሎቶች መጨመራቸውን ያሳያል፡፡ 

ስለዚህ እስካሁን ተጨማሪ እሴት ታክስ በተለይ የመጨረሻ ተጠቃሚ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ በርካታ አገልግሎቶች ላይ ተገልጋዩ ተጨማሪ 15 በመቶ ክፍያ የሚያስከትሉ አዳዲስ አገልግሎቶች ተፈጥረዋል፡፡ የዋስትና ውርስና የመድን ሽፍን ካሳ ሁሉ ታክሱ እንዲመለከታቸው ያደርጋል፡፡ ያገለገሉ ዕቃዎች ሽያጭ በአዲሱ ረቂቅ ላይ የተመለከቱ ናቸው፡፡ ሌላ ቀርቶ የሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲመለከተው ተደርጓል፡፡ ሌሎች በርካታ አዳዲስ አንቀጾች ተካተዋል፡፡  

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚመለከታቸው ቢዝነሶች ብቻ ሳይሆን ስጦታ፣ ዕርዳታ፣ የሠራተኞች ጥቅማ ጥቅሞች፣ ሽልማቶችና የመሳሰሉ ሁሉ ታክስ እንዲመለከታቸው ተደርገዋል፡፡ 

በጥቅል ሲታይ አዲስ ተጨማሪ እሴት ታክስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያርፈው ኅብረተሰቡ ላይ የመሆኑ ጉዳይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት ለዋጋ ንረት ምክንያት ይሆናል የሚለውን ጥያቄ አሁንም ጠንከር አድርገን የምናነሳው የዋጋ ንረቱ ባየለበት ሰዓት ይህንን ረቂቅ አዋጅ መተግበሩ ጫናውን ስለሚያብሰው ነው፡፡  

መንግሥት እንዲህ ያለ ታክስ መሰብሰብ የሚገባው ቢሆንም፣ በሁሉም የገንዘብ እንቅስቃሴ ውስጥ የተጨማሪ እሴት ተፈጻሚ ይሁን መባሉ፣ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ከፍ ከማድረጉም በላይ ገቢው ባለበት የቆመውን አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍልን እንዳይጎዳን ሊያስብበት ይገባል፡፡ 

ዛሬ ኅብረተሰቡ ያለበትን ሁኔታም ከግምት ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ላይ አሁን በሥራ ላይ ያለው ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ምን ያህል በአግባቡ መተግበር ተችሏል? የሚለውም ጉዳይ መታየት አለበት፡፡ አዋጁ አሁንም ቢሆን በተገቢው መንገድ እየተተገበረ አለመሆኑን መንግሥት ጭምር የሚያምነው ጉዳይ በመሆኑ፣ መጀመርያ ሥራ ላይ ያለው አዋጅ በአግባቡ ማስፈጸም አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከመተግበሩ በፊት በቂ አቅም መፍጠርም መልካም ሆናል፡፡ 

አሁን ላይ የታክስ አስተዳደሩ መሰብሰብ ከሚኖርበት ተጨማሪ እሴት ታክስ ምን ያህል እየሰበሰበ እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ያለውንም አዋጅ በአግባቡ ለማስተግበር ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ባልተቻለበት ሁኔታ፣ በርከት ያሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚመለከታቸውን ለማኅበረሰባችን አዲስ ነገር መምጣቱ ብዥታ ይፈጥራል፡፡

በተለይ ደግሞ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ባህሪ አንፃር የመጨረሻው ተጠቃሚ ላይ የሚያርፍ በመሆኑ፣ በዚህ ኅብረተሰብ ላይ የሚፈጥረውን ተጨማሪ ጫና መንግሥት እንዴት አስቦት እንደሆነም ግልጽ አይደለም፡፡

ረቂቅ አዋጁ ይተግበር ቢባል እንኳን የታክስ ምጣኔውን ማወረድ አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የመጀመርያ ረቂቅ ላይ ውይይት ሲደረግ በብርቱ ሲሞገትበት ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንፃር የተጨማሪ እሴት ታክስ 15 በመቶ ይሁን ማለት ተገቢ ያለመሆኑን፣ ነበርና ዛሬም ይህንን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንቱም በእያንዳንዱ ቢዝነስ ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይሁኑ ከተባለ፣ ግን የታክስ ምጣኔውን መቀነስ ተፅዕኖውን ማውረድ ይቻል ይሆናል፡፡ አሁን ባልንት ወቅት አዲሱን ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ መተግበር ግን ከባድ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ታች ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በቀጥታ የሚመለከቱ አገልግሎቶች በተበራከቱ ቁጥር የተጨማሪ እሴት ታክስ የሸማቹን ወጪ ከፍ እያደረጉት መሄዳቸው  ስለማይቀር ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህንን ረቂቅ አዋጅ ለመተግበር እንደ ምክንያት ከተጠቅሱት ውስጥ አንዱ የመንግሥት ታክስ የሚሰበሰብባቸውን ዘርፎች ማስፋት የሚል ነውና የታክስ ሽፋኑን ለማሳደግ ሲባል ኅብረተሰቡ ላይ ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ድንጋጌዎችን መጫን ተገቢ አይሆንም። በነገራችን ላይ ይህ ረቂቅ እጅግ ሰፊ የሆኑ ድንጋጌዎችን የያዘና አተገባበሩን በተመለከተ የተቀመጡ የረቂቅ ድንጋጌዎች ውስብስብነት የሚታይባቸው በመሆኑ፣ ረቂቁ ወደ መፅደቅ ከመሄዱ በፊት አሁንም ተጨማሪ የምክክር መድረኮች ይሻሉ፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉ ረቂቅ አዋጁን አይተው ሐሳብ እንዲሰጡበት ማድረግ በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ይቀንሳል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት