በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይ፣ አርበኛ፣ የዓለም አቀፉ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ/ማዲባ የዓድዋ ድል በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በአገራቸው በደቡብ አፍሪካና በመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ የመላው ጥቁር ሕዝቦች አንጠባራቂ ድል መሆኑን በትልቁ ያሰምሩበታል፡፡
ማንዴላ የአገራችን ኢትዮጵያ ሺሕ ዘመናት የነፃነት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ እንዲሁም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አውሮፓውያንን የኃፍረት ሸማ እንዲከናነቡ ያደረገውና በባርነት፣ በቅኝ ግዛትና በጭቆና ቀንበር ሥር ለነበሩ መላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ብስራትን ያበሰረው ታላቁ የዓድዋ ድል በእሳቸውና በደቡብ አፍሪካውያን የፀረ ባርነትና የፀረ አፓርታይድ ትግል ውስጥ መቼም የማያረጅ፣ ህያውና ደማቅ አሻራ እንዳለው ይስማማሉ፡፡
ማንዴላ ከዓድዋው ድል በኋላ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነፃይቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስምና ጥላ ሥር የተቀጣጠሉ የፀረ ቅኝ ግዛትና የፀረ አፓርታይድ የነፃነት እንቅስቃሴዎችን በማስመልከት በአንድ ወቅት ታሪክ አጣቅሰው ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡-
Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. …The Adwa victory provided practical expression to Ethiopianism: self worth, dignity, unity, confidence, self reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.
(Nelson Mandela, Speech to the Free Ethiopian Church of South Africa)
ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ፣ ነፃነትና አንድነት፣ ኪነ ጥበብና ኪነ ሕንፃ፣ ሕግና ፍትሕ፣ ሥነ ጽሑፍና ፍልስፍና…፣ ወዘተ ዕድገት ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነፃነትና አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ተቋም ናት፡፡
ከዚህም የተነሳ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምዕመኖቿ ስለአገር ክብር፣ ስለእውነት፣ ስለፍትሕ፣ ስለነፃነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው፡፡ እናም ይህች ጠንካራ ሃይማኖታዊ ተቋም ማዳከምና ብሎም መምታት ለብዙዎቹ የኢትዮጵያን የነፃነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነፃነቱና ሰብዓዊ ክብሩ ቀናዒ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች መሆኗ በበርካታ የታሪክ ድርሳናት የተመዘገበ ነው፡፡ እስኪ ከላይ ያነሳሁትን እውነታ የሚያጠናክርልኝና የሚያስረግጥ ጥቂት ምስክርነቶችን ከታሪክ መዛግብት ላጣቅስ፡፡
ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው የጎበኙ አያሌ የውጭ አገሮች ተጓዦች፣ አሳሾችና የታሪክ ተመራማሪዎች ስለኢትዮጵያና ስለሕዝቦቿ በጋራ የሚመሰክሩትና የሚስማሙበት አንድ እውነት አለ፡፡ ይኼውም፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፡፡›› የሚል ነው፡፡
በአንድ ወቅትም ፈረንሣዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ እ.ኤ.አ. 1963 ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል በፓሪስ ከተማ ለሚታተም ጋዜጣ፡- ‹‹የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታውቃላችሁን?›› በሚል ርዕስ ባሠፈረው ሐተታ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-
‹‹…ኢትዮጵያ ወራሪዎች ምድሯን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፡፡ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሣሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነፃነቷን መልሳ አግኝታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍፁም ልብ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባህርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባህር ዓሳም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ሥፍራዋን ይዛ በነፃነቷና በልዑላዊነቷ ቆይታለች…፡፡›› በማለት ጽፏል፡፡
ይህችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በዓድዋው ጦርነት ወቅትም ለጦርነቱ ዘመቻ የክተት ጥሪ ከማስተላለፍ ጀምሮ በተለያዩ የጦርነት ዓውድ ግንባሮች ሁሉ ላይ ሳይቀር በመሳተፍ ጭምር ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ አደራዋን ተወጥታለች፡፡ በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ይዞ ነው በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በሚሊተሪ ሳይንስ ከሠለጠነ አውሮፓዊ ጦር ጋር ለመጋጠም ‹‹ስንቁን በአህያ ዓመሉን በጉያው›› አድርጎና የኢትዮጵያን አምላክ ተስፋ አድርጎ ወደ ጦርነቱ የተመመው፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሠራዊታቸውን ክተት ብለው ወደ ዓድዋ የዘመቱትም የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት፣ ሊቀ ጳጳሱን ግብፃዊውን አቡነ ማቴዎስን፣ በርካታ ካህናትንና መነኮሳትን ጭምር አስከትለው ነበር፡፡ የዓድዋን ጦርነት በሰፊው የዘገቡ የውጭ አገሮችና የአገር ውስጥ ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች እንደጻፉትም፡-
በጦርነቱ ቀን ብዙ መነኮሳት የሰሌን ቆባቸውን እንደደፉ፣ ወይባ ካባቸውን እንደደረቡ የቆዳ ቀሚስ ለብሰው ግማሹ ከንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ፣ ግማሹ ከእቴጌ ጣይቱ ዘንድ የቀሩትም በተዋጊው መኳንንትና ወታደር ዘንድ ሆነው ወዲያና ወዲህ እየተላለፉ ሊዋጋ ወደ ጦርነቱ የሚገባውን እያናዘዙና ከጦርነቱ ሊሸሽ ያለውንም እየገዘቱ፣ ሲያበራቱና ሲያዋጉ መዋላቸውን ጽፈዋል፡፡
የአፄ ምኒልክ ጸሐፌ ትዕዛዝ የሆኑት አለቃ ገብረ ሥላሴ በዓድዋ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ ስለ ‹ዐፄ ምኒልክ ታሪክ› በጻፉት መጽሐፋቸው እንዲህ በሥዕላዊ መንገድ አስቀምጠውታል፡፡
ንጉሡ ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲደርሱ አቡነ ማቴዎስና የማርያም ታቦት የያዙት ካህናት በኋላቸው ነበሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱም ከዘበኞቻቸውና ከሠራዊቱ ጋር ሆነው በአቡነ ማቴዎስና በታቦቷ ጎን ነበሩ፡፡ የአክሱም ካህናት ቅዳሜ ማታ እንደ ጥንቱ አስተዳድሩን ብለው ለንጉሡ ለማመልከት መጥተው አድረው የነበሩት፣ በዚህን ጊዜ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕልና ሰንደቅ ዓላማ ይዘው በእቴጌ ጣይቱ ግንባር ተሠልፈው ነበር፡፡
የጽዮን እምቢልተኞችም መለከታቸውንና እምቢልታቸውን እየነፉ በእቴጌይቱ ፊትና በሠራዊቱ ፊት ይጫወቱ ነበር፡፡
…ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ ይላሉ አለቃ ገብረ ሥላሴ ከሌሊቱ ፲፩ ጀምሮ እስከ ፬ ሰዓት ድረስ ተኩስ ሳያቋርጥ ከሁለቱም ወገን ሲተኮስ ድምፁ እንደ ሐምሌ ነጎድጓድ፣ ከተኩስም የሚወጣውም ጢስ የተቃጠለ ቤት ይመስል ነበር፡፡ በዚህ ቀን በዓድዋ በዓይናችን ያየነውንና በጆሯችን የሰማነውን ለመጻፍ ችግር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው በጋለ ጸሎት ወደ ኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር፡፡ በማለት ጽፈዋል፡፡
በሌላ በኩል ታዋቂው ታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ ‹አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፡-
እቴጌ ጣይቱ በተፋፋመው የዓድዋው ጦርነት ውስጥ ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮች ታጅበው በጦርነቱ መካከል መገኘታቸውን ጽፈዋል፡፡ አቡነ ማቴዎስም የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ በፊት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን ጽፈዋል፡፡
ኢጣሊያዊው ጸሐፊና የታሪክ ምሁር ኮንቲ ሩሲኒም ስለዓድዋው ጦርነት ውሎ ሲመሰክርም፡-
ከልዩ ልዩ ምንጭ እንዳገኘሁት፣ ከሐበሾችም ጽሑፍ እንደተረዳሁት፣ ጦርነቱ ሲጀመር አፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ሌሎችም የጦር ሹማምንትና መሳፍንቱ ሁሉ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ጀምሮ በዓድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያስቀድሱና በጸሎት ሲማጸኑ ነበር…፡፡ ሲል ስለዓድዋ ጦርነት በተወው ማስታወሻው ላይ አስፍሮታል፡፡
ዓድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለዩ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወታደር፣ ገበሬ፣ ካህን፣ መነኩሴ… ሳይባል ሁሉም ለነፃነቱ ቀናዒ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተሳተፉበት ነው፡፡ የድሉ መንስዔም ይኼው የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ አንድነትና ልዩ ኅብረት ነው፡፡
ከዓድዋው ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ለውጭ አገሮች ወዳጆቻቸውና መንግሥታት በጻፉትም ደብዳቤያቸውም፣ ድሉ ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከመግለጻቸውም በላይ ሳይወዱ በግድ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ነፃነት ሲሉ በገቡበት ጦርነት ምክንያት የእነዚያ ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ ስለመፍሰሱ የተሰማቸውን ሐዘኔታም በመጋቢት ፳፫ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ለፈረንሣዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-
…ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ ዕርቅ ይሻላል ብላቸው እንቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡
አፄ ምኒልክ በተመሳሳይም ለሞስኮብ ንጉሥ ለዛር ኒቆላዎስም በላኩት ደብዳቤያቸውም፡-
እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ፀብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወንበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግንባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአህዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…፡፡ በማለት ድሉ ከኢትዮጵያ አምላክ ዘንድ የተገኘ መሆኑን ጽፈውላቸዋል፡፡
የዓድዋ ድል አውሮፓውያን፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ፣ አረመኔ ሕዝቦች ናቸው፡፡›› የሚለውን ከንቱ የሆነ መረዳታቸውንና ግብዝነታቸውን በዓለም ፊት ዕርቃኑን ያሳየና ያጋለጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የሰብዓዊ መብቶችና የጦር ምርኮኞች አያያዝ ሕግ ሳይፀድቅ፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮንቬሽንና ድንጋጌዎች ከመውጣታቸው በፊት ለወረራ በግፍ የመጣውን የኢጣሊያ ምርኮኛ ሠራዊት የሚገባውን ክብርና እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረግ በዓለም ፊት የሞራል ልዕልናቸውን፣ የበላይነታቸውንና ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅርና ክብር አሳይተውበታል፡፡
ስለሆነም የዓድዋው አንፀባራቂ ድል ኢትዮጵያውያን በጦር ግንባር ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲው መስክም ድል ተጎናፅፋ ለሰው ልጆች ሁሉ ነፃነት፣ አንድነትና ክብር ዘብ የቆመች ልዑላዊት አገር መሆኗን ለዓለም ሁሉ ሕዝብ አስመስክራበታለች፡፡ በዚህ ፈርጀ ብዙ በሆነው ዓድዋው ድል ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵውያንን ሁሉ በማስተባበር የተጫወተችው ሚና፣ በድሉም ወቅት ውስጥ የነበራት ደማቅ አሻራና ትልቅ ድርሻ ሁልጊዜም ታሪክ የሚያስታውሰውና የሚዘክረው ለትውልድ ትውልድ ሁሉ የሚተላለፍ ህያው ቅርስ ነው ማለት ይቻላል፡፡
አውሮፓውያን በአፍሪካ ያደረጉት የቅኝ ግዛት መስፋፋት ዘመቻና እንደ ኢጣሊያ ያሉ አገሮች ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ እግራቸውን የሚዘረጉበት የቅኝ ግዛት አገሮችን ለመማተር አስቀድመው ዓይናቸውን በኢትዮጵያ ላይ መጣላቸውን አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያውያን ቀድመው ተረድተው ነበር፡፡ ይህንን ኢጣሊያን የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ በጥንቃቄ ሲከታተሉ ከነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከል አለቃ ለማ ኃይሉ የተባሉ ሊቅ ከጦርነቱ አምስት ዓመት በፊት፤ ‹‹ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረሯ ነገር አይቀሬ መሆኑንና ግና በጦርነቱ ተሸንፋ የኃፍረት ሸማን ተከናንባ ኢትዮጵያን እንደምትለቅ፤›› የሚከተለውን ትንቢታዊ ቅኔ መቀኘታቸውን ልጃቸው አብዬ መንግሥቱ ለማ፣ ‹‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል፡፡ ቅኔው እነሆ፡-
‹ምኒልክ ግበር ላዕለ ሮምያ/ሮማ መጠነ እዴከ ትክል፣
አምጣነ ለአጺድ በጽሐ ማእረራ ወመዋዕሊሃ ለኃጉል፣
ዓዲ ተዘከር ውስተ ወንጌል፣
ላዕለ ሮምያ በለስ ኢሀሎ አስካል፣
በከመ ይቤ ወልደ ያሬድ ቃል፡፡›
ትርጉም፡- ምኒልክ በሮማ ላይ እጅህ እንደቻለ መጠን አድርግ፣
መከሯ ለመታጨድ፣ ቀኗም ለጥፋት ቀርቧልና፡፡
ዳግመኛ በወንጌል ያለውን አስብ፣
በሮምያ/በበለስ ላይ ፍሬ የለም እንዳለ ወልደ ያሬድ/ቃል (ወልድ)፡፡ ብዬ ፲፰፻፹፫ ተቀኘሁ፡፡ ምኒልክ በቤተስኪያን የሉም ይሄ ሲባል፡፡ ይሄ ጥንቆላ ነው፡፡ የዓድዋ ጦርነት ሳይደረግ ነው፡፡ ኸጣልያን ጋር ስምም ናቸው ያን ጊዜ አጤ ምኒልክ፡፡ አለቃ ወልድ ያሬድ ‹መልካም መልካም!› አሉና፣ እሑድን ዋልነ፡፡ ሰኞ ጉባዔ አለ፡፡ አለቃ ተጠምቆ ናቸው እሚያኼዱ፡፡ አለቃ ወልደ ያሬድ እሳቸው እልፍኝ አጠገብ ቤት ሰጥተውናል፡፡ እርሳቸው መጥተው ይቀመጣሉ ኸጉባዔ ለመስማት፡፡
‹የኔታ ተጠምቆ›
‹አቤት!‘
‹ኸኒያ ክፉዎች ጋር እኮ ጠብ ላይቀርልን ነው› አሉ፡፡
እንግዴህ ትግሬ ናቸው አለቃ ተጠምቆ እነ ራስ አሉላ፣ እነ ራስ መንገሻ አሉ ኸኒያ መስሏቸው፤
‹ኸነማን ጌታዬ? ኸነማን?› አሉ ደንግጠው አለቃ ተጠምቆ፡፡
‹ኸነጮቹ›
‹ምነው፣ ምነው?‘ አሉ፡፡
‹እንዴ! የልጅዎን ቅኔ በቀደም አልሰሙትም?›
‹በለማ ቅኔ ሆነ እንዴ ጦርነት?› አሉ አለቃ ተጠምቆ፡፡
‹አናጋሪው ማን ይመስልዎታል?› አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቅ የነበሩት አለቃ ለማ በዚሁ ቅኔያቸው እንደተነበዩትም ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ ታወቀ፣ ተረጋገጠ፡፡ አለቃ በቅኔያቸው እንደተቀኙትም ሮማ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተጋድሎ አማካይነት ታላቅ ውርደትንና ሽንፈትን ተከናነበች፡፡ ይህም ድልም ለጥቁር ሕዝብ ንቀት የነበራቸውን መላው አውሮፓውያን ያስደነገጠና ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደረገና በተቃራኒው ደግሞ በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ወድቀው የነበሩ አፍሪካውያንን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝቦችን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱና ብሎም ለነፃነቱ፣ ለመብቱና ለሰብዓዊ ክብሩ በአንድነት፣ በኅብረት እንዲነሳ ትልቅ የወኔ መነቃቃት የፈጠረና ለነፃነት ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ዓቢይ ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የቅኝ ገዥውን፣ የሮማ መንግሥትን የግፍ ወረራና የዓድዋ ጦርነትን አይቀሬነት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ከመተንበይ ጀምሮ ለጦርነቱ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በመምከር፣ ሕዝቡን በማዘጋጀት፣ በክተት ዘመቻውና በዓውድ ጦር ግንባር ጭምር በመሳተፍ አገራችን ኢትዮጵያ በነፃነቷ፣ በልዑላዊነቷ ታፍራና ተከብራ እንድትቆይ የበኩሏን መንፈሳዊና ታሪካዊ ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአፍሪካውያን፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና ዓርማ የመሆን ክብርን እንድትጎናፀፍ አስችሏታል፡፡
ይህን እውነታ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ታቦ ምቤኪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2002 ዓ.ም. በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ ባበረከተላቸው ጊዜ በልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው፡- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነፃነት ክብርና ዓርማ የሆነች ለአፍሪካ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ማከማቻ፣ ማዕከል መሆኗን እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት፣
…the Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church..
ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡