Wednesday, March 29, 2023
Homeስፖንሰር የተደረጉየቱሪዝም ዘርፍ እንዳያንሰራራ የግብር ማነቆ ተደቅኖበታል!

የቱሪዝም ዘርፍ እንዳያንሰራራ የግብር ማነቆ ተደቅኖበታል!

Published on

- Advertisment -

ኢትዮጲያ እንዳላት የታሪክ የባህል እና የተፈጥሮ ጸጋ፤ የቱሪዝም ዘርፉ ተጠናክሮ ለአገሪቱ የሚገባትን ያክል ጥቅም እያስገኘ አይደለም የሚለው ሃሳብ ሲወተወትበት የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እነኳን አገሪቱ እንዳላት አቅም ያክል ባይሆንም እስከ 2019 እ.ኤ.አ. ድረስ የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ እመርታን እያሳየ ነበር፡፡

በ2019 እ.ኤ.አ. ከ800 ሺህ በላይ ጎብኚዎችን አገሪቱ ማስተናገድ ችላ ነበር፡፡ ይህም በ2000 እ.ኤ.አ. ከነበረው ከ136 ሺህ የጎብኚዎች ቁጥር እጅጉን የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዚህም ሳያበቃ ከ2019 እ.ኤ.አ. በፊት ዘርፉ ከአምስት በመቶ በላይ ለኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እያበረከተ ቆይቷል፡፡

ይህ ሁሉ የዘርፉ ተስፋ ከ2019/20 እ.ኤ.አ. በኋላ ጨለመ፡፡ የኮሮና ቫይረስ አለም ላይ ከደቀነው አደጋ የከፋ የሚባለው የቱሪዝም ዘርፉ ላይ የደቀነው አደጋ ሆነ፡፡ ሆቴሎች ተዘጉ፤ ሰራተኞቻቸው ተበተኑ፤ አንዳንድ ሆቴሎች ወደጤና ማዕከልነት እስከመቀየር ደረሱ፤ የአስጎብኚ ድርጅቶች የስራ ዘርፋቸውን እንዲቀይሩ ተገደዱ! ውርጅብኙ በአለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ተብሎም ተመዘገበ፡፡

የኮሮና ቫይረስ የደቀነው ስጋት በአለም ላይ ጋብ እያለ ቢመጣም የኢትዮጲያ የቱሪዝም ዘርፍ ግን ለብቻው ሌላ ተግዳሮት ተጋርጦበት ቆይቷል፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጲያ ከ2013 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በተለያዩ ፖለቲካዊ ውጥንቅጦች ውስጥ ስታልፍ ነው የኖረችው፡፡ ይህ ውጥንቅጥ በአጠቃላይ ለንግድ እንቅስቃሴው በተለይ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉ ጉሮሮ ላይ በመቆም አላላውስ ሲሉት እንደኖሩ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ በተለይ ደግሞ በባለፉት አራት አመታት አይነቱን ቅርጹንና ምክኒያቱን እየቀያየረ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተግዳሮት መሆኑን ቀጥሏል፡፡ አሁንም በ2020 እ.ኤ.አ. በሰሜን ኢትዮጲያ የፈነዳው ጦርነት ደግሞ በአይነቱ ልዩ የሆነና ከባድ ማነቆን በዘርፉ ላይ ጥሎ ከርሟል፡፡ ይህኛው ተግዳሮት የቱሪስት መስህብ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እስከማድረስና በዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት አገልግሎታቸውን አቁመው ሰራተኞቻቸውን እስኪበትኑ ያደረሰ ከባድ ግዜም ነበር፡፡

ምንም እንኳን የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉና እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እስካሁንም እንደቀጠሉ ቢሆንም፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ችግር ለመፍታት የተሄደበት ውሳኔ እንደተቀረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፍል ለቱሪዝም ዘርፉም እፎይታን ማስገኘት ነበረበት፡፡

ያ ግን በቅርቡ የሚሆን አይመስልም!

መንግስት የዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተጠቃሚ ብሎ በአዲስ ረቂቂ አዋጅ ላይ ካስቀመጣቸው ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ የማይገኝበት መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ የፖሊሲ አቅጣጫ ትክክል እንዳልሆነ ብዙ አመክንዮዎችን በማንሳት መሞገት ይቻላል፡፡

በቅድሚያ የአስጎብኚዎችና የሆቴል እንዲሁም መሰል እንቅስቃሴዎች በዘርፉ ውስጥ የተሰማሩትን የንግድ ተቋማት እጅግ ብዙ ወጪ የሚያስወጡ ቢሆንም ሁሉም እነዚህ ወጪዎች ግን በግብር ስርዐቱ አለመሸፈናቸው አንድ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

አንድ ሆቴል የምግብ አገልግሎቱን ለማቅረብ የሚገዛቸው ቁሳቁሶች በሙሉ በማለት በሚያስችል ደረጃ በደረሰኝ ተገዝተው በወጪ መልክ ከገቢዎች ጋር መወራረድ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም አንድ አስጎብኚ ድርጅት አስጎብኚዎችን ይዞ ከአንድ የቱሪዝም ቦታ ወደሌላኛው ሲያዘዋውር የሚያወጣቸው የትራንስፖርት፤ የጉብኝት ቦታዎች ክፍያዎችና መሰል ወጪዎች ሁሉም ደረሰኝ ሊሰበሰብላቸው የሚችሉ ባለመሆናቸው እንደወጪ ተመዝግበው በገቢዎች ደረጃ ሊወራረዱ አይችሉም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ ውስጥ አገራቸውን በአለም ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ለራሳቸውም ገቢ ለማግኘት ከአገር ውጪ የተለያዩ ክፍያዎችን በመፈጸም የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ማሰራት፤ ከአገር ውጪ እይታን የሚጨምሩ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ እና ለነዚህም እንቅስቃሴዎች ክፍያን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ ሆቴል፤ አሊያም የአስጎብኚ ድርጅት ከፍቶ ቁጭ ስለተባለ ብቻ ጎብኚዎች ይመጣሉ ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡

በቅድሚያ የትኞቹም እነዚህ ወጪዎችን እንዲያደርጉ የውጪ ምንዛሬ እንዲያገኙም ሆነ የክፍያ ስርዐቱን በማመቻቸት በኩል ከመንግስት የትኛውንም ድጋፍ ሳያገኙ በግል ጥረት እነዚህን ክፍያዎች በራሳቸው እየከፈሉ ጎብኚዎችን ወደአገር ውስጥ ሲያመጡ ነው የኖሩት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የትኞቹም እነዚህ ወጪዎች በአገር ውስጥ እንደወጪ ተመዝግበው የሚወራረዱበት መንገድ አለመኖሩን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፡፡

አዲሱ የረቂቅ አዋጅ ከግምት ውስጥ ያላስገባቸው እውነታዎች በዚህም የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ኢትዮጲያ ከኮሮና እና ከፖለቲካዊ አለመረጋጋቶቹ በፊት በአመት ከ800 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጎብኚዎችን ያስተናገደችበት ወቅት ነበር፡፡ እነዚህ ጎብኚዎች ወደአገር ቤት መጥተው ኢትዮጲያን እንዲገበኙ በማሳመኑ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የሚጫወቱት እነዚህ አስጎብኚ ድርጅትች ናቸው፡፡

በዚህ ሚናቸው ለራሳቸውና ለቀጠሯቸው ሰራተኞች የገቢ ምንጭ ከመሆን አልፈው ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ የትኛውንም ያክል እያደገ ቢመጣ አንድ ሊቀርፈው ያልቻለው ትልቁ ህልውናውን እየተፈታተነ ያለው ተግዳሮት የውጪ ምንዛሬ እጥረት መሆኑ ይታወቃል፡፡

የውጪ ምንዛሬ እጥረት በአገር ውስጥ ተጠቃሚው ላይ ዋጋን ከማስወደድ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ መካሄድ እንዳይችሉ እንቅፋት ሲሆን ማስተዋል የተለመደ ሆኗል፡፡ ኢትዮጲያ ገፋ ሲልም ለአንድ ሳምንት የሚሆን የውጪ ምንዛሬ ብቻ ሲቀራት የሞት ሽረት ጥረት እየተደረገ የኢኮኖሚውን ህይወት ማራዘም የተለመደ የመንግስት ተግባር ከሆነም ሰነባብቷል፡፡

እንዲች ባለች አገር ውስጥ ለኢኮኖሚው አንድም ተጨማሪ ዶላር ሊያመጣ የሚችል ዘርፍ በምሉዕ አቅምና ፍላጎት መደገፍ እንድምታው በዘርፉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ተቋማት አልፎ አገራዊ እንደሆነ መገመት ብዙም አዋቂ መሆንን አይጠይቅም፡፡

በአለም ላይ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት ላይ ግብር ከምንጥል እነሱ ተበረታተው ከሚያመጡት የንግድ እንቅስቃሴ ብንጠቀም ይሻለናል ብለው በነዚህ ተቋማት ላይ ምንም ግብር ካለመጣል በጣም አናሳ ግብር እስከመጣል የሚደርስ ድጋፍን የሚያደርጉ በርካታ አገራት አሉ፡፡ አጅግ የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህ አገራት እንደኢትዮጲያ እጅግ የከበደ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንኳን ያለባቸው አገራት አለመሆናቸው ነው፡፡

በነዚህና በሌሎች በርካታ ምክኒያቶች የቱሪዝም ዘርፉን የተጨማሪ እሴት ታክስ ዜሮ ሊደረግላቸው ከታሰቡ ዘርፎች ዝርዝር ውስጥ አለማካተት እንድምታው ከዘርፉ አልፎ በአጠቃላይ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ ከኮሮና እና ከጦርነት እና ግጭት ጠባሳዎች እንዲያገግም፤ አርፎ ተርፎም ለአገር በውጪ ምንዛሬ አምጪነት መሪ ሚናውን እንዲጫወት የመንግስትን ከወትሮው የተለየ እርዳታ ይሻል፡፡

ኢትዮጲያ ዘመናዊ በሆነ መልኩ ከዘርፉ ሙሉ አቅሟን የሚመጥን ጥቅም ማግኘት እንድትችልና የቱሪዝም ዘርፉ ያንን ማድረግ ይችል ዘንድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ያሉበትን የግብር መነቆዎች ለመፍታት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ይህ መሆን የማይችል ከሆነ ምናልባትም ለአገሪቱ አለኝታ መሆኑ ቀርቶ ካለፋቸው ከባድ ችግሮች አንጻር የመኖር ህልውናውም አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል፡፡

የቅርብ ጊዜ መጣጥፎች

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣ የእለት ጉርሳቸውን ምፅዋት ለማግኘት ለወጪ...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች...

የተዘነጋው የከተሞች ሥራ የመፍጠር ተልዕኮ

በንጉሥ ወዳጅነው አሁን አሁን የአገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ አንገብጋቢና ሊታሰብበት የሚገባ አጀንዳ እየሆነ ነው፡፡...

ሆድና የሆድ ነገር

(ክፍል ስድስት) በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር) አቶ ባል - "ለዛሬ ገንፎ"    ወ/ሮ ሚስት - "ለልክህ ድፎ" ዜናዎች...

ተመሳሳይ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና ለዳይሬክተሮች ቦርድ ተጠሪ የሆኑ ንዑሳን...

በዚህ የየቅዱስ ፓትሪክ መታሰቢያ ቀን አየርላንድ የታሪኳን ሶስት ወሳኝ ወቅቶች መለስ ብላ ትመለከታለች

አየርላንድ እጅግ ከፍ ባለ ሁኔታ የምታከብረው የቅዱስ ፓትሪክ ቀን በሚውልበት መጋቢት 8 (እ.ኤ.አ. ማርች...

የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና  የታዩ  ለውጦች በኢትዮጰያ ፦ ከተመረጡ የአበባ እርሻዎች የተገኙ ተሞክሮዎች

የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና  የታዩ  ለውጦች በኢትዮጰያ ፦ ከተመረጡ የአበባ እርሻዎች የተገኙ ተሞክሮዎች ፎረም...