Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከአንድ ሺሕ በላይ የፊስቱላ ኬዞች መገኘታቸውን አስታወቀ

ሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከአንድ ሺሕ በላይ የፊስቱላ ኬዞች መገኘታቸውን አስታወቀ

ቀን:

ከአንድ ሺሕ በላይ የፊስቱላ በሽታ ኬዞች መገኘታቸውንና በተለይ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ነዋሪዎች፣ በበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቁ መሆኑን፣ ሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡

የፊስቱላ በሽታ መንስዔዎችን በተመለከተ እየተደረገ ነው በተባለ ዳሰሳ ከ1,000 በላይ ኬዞች በመገኘታቸው፣ የፊስቱላ በሽታ በወሊድ ምክንያት ብቻ እየመጣ አለመሆኑን ማወቅ እንደተቻለ፣ የሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ማሞ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ባስረዱት መሠረት፣ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ነዋሪዎች ‹‹በሽታውን ደብቀው ስለሚቀመጡ›› የፊስቱላ ሕሙማን በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ ፊስቱላን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋትም ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ገለጻው ከሆነ፣ ለፊስቱላ በሽታ ምክንያት የሆኑ የተለያዩ ኬዞች እየተገኙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ እስከ ዛሬ የፊስቱላ በሽታ የሚከሰተው በይበልጥ ከወሊድ መራዘም ጋር በተየያዘ ነው ተብሎ ሲታመን የነበረ ቢሆንም፣ እየተደረጉ ባሉ ዳሰሳዎች ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ (ለአብነትም ያለ ዕድሜ ጋብቻ) ሌላው ሰፊ መንስዔ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እየቀነሰ መጥቷል ቢባልም፣ ሙሉ በሙሉ መቆም ባለመቻሉ ለፊስቱላ በሽታ መስፋፋት መንስዔ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

የተለያዩ የፊስቱላ በሽታ ኬዞች እንደተገኙ፣ እያንዳንዱ ኬዝ በጥልቀት እየታየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ ዳሰሳው ሲጠናቀቅ ሁሉንም ኬዞች በተመለከተ ማብራሪያ እንደሚሰጥ፣ የፊስቱላ በሽታንም ይበልጥ መከላከል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ጤና ተቋም ስለማይሄዱ፣ የጤና ተቋማትም የመድኃኒትና ቁሳቁስ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው በርካታ የፊስቱላ ሕሙማን እየተገኙ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት ወቅት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሀምሊን ፊስቱላ ቅርንጫፍ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ባለመቆየቱ፣ የታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በጦርነቱ ወቅት ሕክምና እንዳላገኙ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ጦርነቱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው የፊስቱላ ሕሙማን ሁኔታ ተከታትለው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ጦርነቱ መቆሙን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚገኘው የሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ወደ ሕክምና ያልመጡ የፊስቱላ ሕሙማን መረጃ እንደደረሳቸው አክለዋል፡፡

በፊስቱላ የተጠቁ ሕሙማንን ቁጥር ለማወቅና ወደ ጤና ጣቢያ እንዲያቀኑ ለማድረግም ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የፊስቱላ በሽታን ለማጥፋት በኢትዮጵያ በሚገኙ ከ800 በላይ ወረዳዎች የፊስቱላ ቁራኛ ሆነው ወደ ጤና ጣቢያ ያላቀኑ እናቶችን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ተቋሙ ዕቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ከ60 ዓመታት በፊት በአውስትራሊያዊቷ ካትሪን ሀምሊን (ዶ/ር) እና የቀዶ ጥገና ባለሙያዋ ሬግ ሀምሊን (ዶ/ር) የተመሠረተው ሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ቦታዎች የፊስቱላ ሕሙማንን እያፈላለገ ሕክምና የሚሰጥ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. ከ2,500 በላይ የፊስቱላ ሕሙማንን እንዳከመ፣ በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ከ3,000 በላይ ሕሙማንን ለማከም ዕቅድ ይዞ እያፈላለገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...