በኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለል የሚረዳ የሥልጠና ማዕከል መገንቢያ ቦታ እንዲሰጠው የኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማኅበር ጠየቀ።
ማኅበሩ ጥያቄውን ያቀረበው ለአራተኛ ዙር የተሰጠውን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን የፊያታ ዲፕሎማ የአሠልጠኞች ሥልጠና (FIATA Diploma in Freight Forwarding) ወስደው ያጠናቀቁ ባለሙያዎችን ትናንት የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ባስመረቀበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ኤልሳቤት ጌታሁን እንደገለጹት፣ ማኅበሩ በሥልጠና ማዕከል ችግር ምክንያት የሚፈልገውንና የሚያስፈልገውን ያህል የሰው ኃይል ለማፍራት ውስንነት አለበት ብለዋል።
በመሆኑም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም መንግሥት ለማኅበሩ የሥልጠና ማዕከል መገንቢያ ቦታ በመስጠት ዕገዛ እንዲያደርግ ወ/ሮ ኤልሳቤት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ማኅበሩ የኢንተርናሽናል ዲፕሎማ ፕሮግራምን ፊያታ ከሚባል (Federation of International Freight Forwarders – FIATA) በመታገዝ እንደሚሰጥና ይህን ዲፕሎማ ዓለም አቀፍ ይዘቱን የጠበቀና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በካሪኩለም ውስጥ አጠቃሎ የሚሰጥ በመሆኑ ሠልጣኞች በቀጥታ ወደ ሥራ ለመግባት በሚችል ሁኔታ የሚያዘጋጀው መሆኑ ተገልጿል።
ወ/ሮ ኤልሳቤት ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ማኅበሩ የተከራየው የሥልጠና ተቋም አነስተኛ ሲሆን፣ የራሱን ሥልጠና ተቋም እንዲገነባ የቦታ ድጋፍ ቢያገኝ ከፍተኛ የሥራ ፈጠራ ዘርፍ የሆነውን ሎጂስቲክስ ለመደገፍና ለማጠናከር የሚያስችል ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የኋላሸት ጀመረ (ኢንጂነር) በሎጂስቲክስ ስትራቴጂው ላይ ከተለዩ ዋና ዋና የዘርፉ ፈተናዎች፣ የሎጂስቲክ አገልግሎት ሰጪዎች ብቃትና አቅም ዝቅተኛ መሆን አንዱ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ የዘርፉን የሰው ኃይል ብቃትና ክህሎት በማሳደግና የአገልግሎት ጥራቱን በማሻሻል ዘርፉ በዕውቀት እንዲመራ ማድረግ ከሚጠበቁብን ዋና ተግባራት መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
አራተኛው ዙር የፊያታ ዲፕሎማ የአሠልጣኞች ሥልጠና የፊያታ ዲፕሎማ አሠልጣኞችን የማሠልጠን ፈቃድ ያላቸውና ይህንኑ ሥልጠና በፊያታ አባል አገሮች ውስጥ በመስጠት የሚታወቁት ሚስተር ቶማስ ሲም መሰጠቱ ታውቋል፡፡
ባለሙያው በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፉ የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን (ፊያታ) ውስጥ ካሉት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች መካከል ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት (Senior Vice President) በመሆን እያገለገሉ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ባላቸው የካበተ የሥራ ልምድ ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ማኅበራትን የሥልጠና ፕሮግራሞች የሚከታተለውንና የሚቆጣጠረውን የፊያታ የሥልጠና ተቋም በኃላፊነት የመሩ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ሰፊ የሆነውን የሎጂስቲክስ ዓለም በደንብ ለማወቅ የሚፈልጉም ሆኑ በሙያው ላይ ተሰማርተው ያላቸውን ዕውቀት ለማዳበርና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም የሚሹ ሁሉ ይመርጡታል የተባለውን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን የፊያታ ዲፕሎማ ሥልጠና በሎጂስቲክስ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ 28 ባለሙያዎች ተሳትፈው ማጠናቃቸው ተገልጿል።