Wednesday, March 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መተማመን ሳይኖር የጋራ አጀንዳ ሊኖር አይችልም!

ዝነኛው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔና ጸሐፊ ተውኔት ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ‹‹አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ… የእንቧይ ካብ…›› ያሉት የእርስ በርስ መከባበርን፣ መተማመንና መተባበርን አስፈላጊነት ለማስታወስ ነበር፡፡ እሳቸው ከዚህም በተጨማሪ፣ ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› በሚለው ዘመን አይሽሬ ግጥማቸውም ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚገጥማትን ችግር በብልኃት እንድትሻገር የወተወቱ በርካታ ልሂቅ ኢትዮጵያውያን የነበሩ ቢሆንም፣ አዳማጭ ባለማግኘታቸው ከአንዱ ችግር ወደ ሌላው እየተወረወረች እዚህ ደርሳለች፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከተዘፈቀበት አስመራሪ ድህነት ውስጥ መንጭቆ ለማውጣትና ሰብዓዊ ክብሩን ጠብቆ ለማኖር የሚያስችል አንዳችም ፍላጎት የሌላቸው፣ ነገር ግን በስሙ እየነገዱ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ብቻ ቀውስ የሚቀፈቅፉ የፖለቲካ ልሂቃን እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ እነሱ ሕዝብ ቢራብ፣ ቢጠማ፣ ቢጎሳቆል፣ ቢፈናቀል ወይም ሕይወቱን ቢያጣ ደንታቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህንን አስመራሪ ጉስቁልና ለፖለቲካ ቁማራቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ሁሌም ነገር የሚቆፍሩት መተማመን ጠፍቶ አገር እንድትቃወስ ነው፡፡

ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ለአገርና ለሕዝብ የሚበጅ ፕሮግራም ወይም አጀንዳ ሳይቀርፁ፣ አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አለን በሚሉት ርዕዮተ ዓለም ሳያነቁና ሳያደራጁ፣ ሊንቀሳቀሱበት የሚገባው ምኅዳር ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖረው እንደሚገባ ሳያመላክቱና ከሌሎች ተፎካካሪዎች እነሱ በምን እንደሚሻሉ አሳማኝ መረጃ ሳያቀርቡ በሕዝብ ስም ይነግዳሉ፡፡ ከሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው ጋር በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መሥራት እንደሚቻል እንኳ የተረዱ አይመስሉም፣ ቢረዱም ለተግባራዊነቱ ዳተኛ ናቸው፡፡ የብሔር ሰሌዳ ለጥፈው የሚንቀሳቀሱት ጭምር ከብሶት በስተቀር ተስፋ ሰጪ ነገሮች ላይ ሲያተኩሩ አይታዩም፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ራሱ በውስጡ ያለውን ችግር ሳያጠራ፣ የሐሳብና የተግባር አንድነቱን በተጨባጭ ማሳየት አቅቶት እርስ በርሱ ሲናጀስ ይስተዋላል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲም ሆነ በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ታሪክና ፍላጎት የሚመጥን ቁመና ለማሳየት እየተቸገሩ የሚቀናቸው ግን ሽኩቻ ነው፡፡ በእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ስለማይተማመኑ ወጥ የሆነ የጋራ አቋም ለማሳየት ይቸገራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ችግራቸውን ከመፍታት ይልቅ አገር ያምሳሉ፡፡

አገር የምትፀናው ሕዝብና መንግሥት በበርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ሲስማሙ ነው፡፡ ሁለቱ ሆድና ጀርባ ሲሆኑ ለአገር ህልውና ጠንቅ የሚሆኑ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ መንግሥት ዋነኛ ኃላፊነቱ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ሲሆን፣ መብቶቹና ነፃነቱ እንዲከበሩ ደግሞ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩበት ሥርዓት ማነፅ የመንግሥት ኃላፊነትም ግዴታም ነው፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት ብቁና ንቁ ሆነው እንዲጠናከሩ ብቁ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ያስፈልጓቸዋል፡፡ ተቋማት በጥንካሬ ሲገነቡና በብቁ ሰዎች ሲያዙ አድልኦና ማግለል አይኖሩም፡፡ ሌብነትና ዘረፋ አይታሰቡም፡፡ ብልሹ አሠራሮች ተረት ይሆናሉ፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ተቋማት ባለመኖራቸውና ብቁ ዜጎች ገለል በመደረጋቸው፣ ሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት እያገኘ አይደለም፡፡ በየቦታው ከአንድነት ይልቅ ከፋፋይ አጀንዳዎች እየበዙ ነው፡፡ የፍትሕ ፈላጊዎች ምሬት ከመጠን በላይ ሆኗል፡፡ ላባቸውን ጠብ አድርገው የሚለፉ እየተራቡ በአቋራጭ የሚከብሩ በርክተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹና መሰል አክሳሪ ድርጊቶች በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዳይኖር እያደረጉ ናቸው፡፡

በሕዝብና በመንግሥት መካከል አለመተማመን የሚፈጥር አንድ ችግር ሲያጋጥም፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ባህሪ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት የሚያሰማራቸው የፀጥታ አካላት በገለልተኝነት ስሜት ኃላፊነታቸውን መወጣት ካልቻሉ፣ የሚወስዱት ዕርምጃ ከመጠን በላይ ኃይል በመጠቀም ስለሚከናወን ከፍ ያለ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚችሉትን ከመጠን በላይ ኃይል ሲጠቀሙ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይከሰታሉ፡፡ መንግሥት የዜጎችን ሕይወትና አካል ከማናቸውም ጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን መወጣት ትቶ፣ አላስፈላጊ የኃይል ዕርምጃ ወስዶ ጉዳት ሲደርስ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድምፃቸውን ያሰማሉ፡፡ ከአገር አልፎ እስከ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድረስ ድርጊቱ ይወገዛል፡፡ በዜጎች ዘንድ ደግሞ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ሰሞኑን በዓድዋ ድል በዓል አከባበር ምክንያት የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀማቸው ለደረሰው ጉዳት፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ዜጎችም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ድርጊቱን እያወገዙ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት በብሔር፣ በሃይማኖትና በተለያዩ ሰበቦች አፍራሽ አጀንዳዎች እየተፈበረኩ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዲጋጩና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማካሄድ ተገደዋል፡፡ ከቡራዩ እስከ ወለጋ በተደጋጋሚ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጀምሮ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዕልቂትና ውድመት ድረስ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የተከናወኑ አሳዛኝ ድርጊቶች መነሻቸው ለአገርና ለሕዝብ የማይጠቅሙ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያና ኢራቅ ለመበተንና ለማፍረስ የተቀነቀኑት አፍራሽ አጀንዳዎች አልበቃ ብለው፣ አሁን ደግሞ ታላቁን የዓድዋ ድል የእርስ በርስ መተላለቂያ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት ያስፈራል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› ከሚለው መፈክር ጋር ጨርሶ ሊገጥሙ የማይችሉ አደገኛ ትርክቶች አየሩን ተቆጣጥረውታል፡፡ በዚህም ምክንያት ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አለኝታቸው የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል ሳይቀር፣ የኢትዮጵያውያን መጠፋፊያ ሊሆን ሲቃረብ ከማየት በላይ የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡ እንዲህና መሰል ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች ጭምር አፍራሽ እንዲሆኑ ሲደረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል የሚፈጥሩት ቅራኔ ያሳስባል፡፡ ተቃርኖው እየሰፋ ሲሄድ ደግሞ ለታሪካዊ ጠላቶች ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ሰላምና መረጋጋት አስፍነው፣ በፍጥነት እየተለወጠ ካለው ዓለም ጋር ለመራመድ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡ በየጊዜው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሚስተዋልባቸው ውስን አገሮች በስተቀር፣ ብዙዎቹ ከድህነት ውስጥ በፍጥነት የሚያስወጣቸውን አዋጭ ሥልት እየተከተሉ ነው፡፡ በቀድሞ ቅኝ ገዥዎች የተተከለባቸውን የከፋፍለህ ግዛ ውጤት የሆነውን የጎሳ ልዩነት ወደ ጎን በማለት፣ የጋራ የሆኑ ብሔራዊ ጉዳዮቻቸው ላይ በማተኮር ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ እያዳበሩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እየጣሩም ነው፡፡ ዘመናዊውን ሥልጣኔ ከአገር በቀል ዕውቀት ጋር በማዋሀድ ወጣቶቻቸውን ለማነፅ በሚያደርጉት ጥረት፣ እግረ መንገዳቸውን ያለፉትን ስህተቶች የሚያርሙ መልካም ተግባራትን እያከናወኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኸሪያ ሆና፣ ልጆቿ በተቃርኖ ፖለቲካ ተወጥረው መተማመን ጠፍቶ የጋራ አጀንዳ አልባ ሆናለች፡፡ በገዥው ፓርቲ ብልፅግና ውስጥ በአማራና በኦሮሚያ ቅርንጫፎች ውስጥ እያደር የሚያገረሸው ተቃርኖ፣ ወትሮም በቋፍ ያለውን አንፃራዊ ሰላም የሥጋት ጭጋግ እያለበሰው ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ አካላት የሐሳብና የተግባር አንድነት አጥተው መተማመን ሲጠፋ ያስፈራል፡፡ መተማመን ሳይኖር ደግሞ የጋራ አጀንዳ ሊኖር አይችልም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...

የተዘነጋው የከተሞች ሥራ የመፍጠር ተልዕኮ

በንጉሥ ወዳጅነው አሁን አሁን የአገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ አንገብጋቢና...

ሆድና የሆድ ነገር

(ክፍል ስድስት) በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር) አቶ ባል - "ለዛሬ ገንፎ"   ...

የረቂቅ ሙዚቃ ፈር ቀዳጇ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ (1916-2015)

‹‹...የሙዚቃ ሥራዎቼን ለአድማጭ የማድረስ ፍላጎቴን እኔ ከመረጥኩት መንገድ በተለየ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...