በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ አገሮች የጎዳና ውድድሮች ተከናውነዋል፡፡ በውድድሮቹ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መሳተፍ የቻሉ ሲሆን፣ ድል መቀዳጀት ችለዋል፡፡ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. የቶኪዮ ማራቶን፣ የጣሊያን ሮም ግማሽ ማራቶን፣ እንዲሁም የፈረንሣይ ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡
በቶኪዮ ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያውያኑ ደሱ ገልሜሳ 2፡05፡22 አንደኛ፣ መሐመድ ኢሳ 2፡05፡22 ሁለተኛ፣ እንዲሁም ፀጋዬ ጌታቸው 2፡05፡25 ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ በበላይነት አጠናቀዋል፡፡
በውድድሩ መጀመርያ ተያይዘው የሮጡት አትሌቶቹ 5 ኪሎ ሜትር ርቀቱን 14፡45 ሲያጋምሱ፣ 10 ኪሎ ሜትሩን 29፡21 እንዲሁም 15 ኪሎ ሜትሩን 44፡03 መሮጥ ችለዋል፡፡
በአንፃሩ 30 አትሌቶች እግር በእግር እየተከታተሉ በአምስት ሰከንድ ልዩነት 20 ኪሎ ሜትር 58፡04 ማጋመስ ችለዋል፡፡ በዚህም መሠረት 25 ኪሎ ሜትር 1፡13፡45 እንዲሁም 30 ኪሎ ሜትር በ1፡28፡39 ሮጠዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶችን ጨምሮ ስድስት ኬንያውያን የመጨረሻውን 37 ኪሎ ሜትር ብቻቸውን ሲመሩት ቆይተዋል፡፡
ከፍተኛ ፉክክር የታየበት የወንዶቹ ውድድር በኢትዮጵያ የበላይነት ሊጠናቀቅ ደሜ ታዱ 2፡05፡38 በሆነ ሰዓት ስድስኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡
ኬንያዊው ቲታስ ኪፕሩቶ 2፡05፡32 አራተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ ሌላው ኬንያዊ ኬንያ ሶኖቶ 2፡05፡59 ስምንተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
በቶኪዮ ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ደምቀው ያሳለፉ ሲሆን፣ ፀሐይ ገመቹ 2፡16፡56 ሁለተኛ ስትወጣ፣ እሸቴ በከሬ 2፡19፡11 ሦስተኛ ደረጃን፣ ወርቅነሽ ኢዴሳ 2፡20፡13 አራተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡
ኬንያዊቷ ሮስመርይ ዋንጂሩ 2፡16፡28 ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለች አትሌት ናት፡፡ በፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው የቶኪዮ ማራቶን ውድድር አሸናፊዋ ሮስመሪያ የዓለም ምርጥ ስድስተኛዋ ሴት የማራቶን አትሌት መሆን የቻለችበት አጋጣሚ ሆኗል፡፡
የሴቶች ውድድር የመጀመርያው አምስት ኪሎ ሜትር 19፡19 የሮጠች ሲሆን፣ 10 ኪሎ ሜትር 32፡34 በሆነ ሰዓት ማጋመስ ችለዋል፡፡ አራት አትሌቶች ብቻ እግር በእግር እየተከታተሉ 20 ኪሎ ሜትር 1፡04፡41 መሮጥ ችለዋል፡፡
በዚህም 25 ኪሎ ሜትር 1፡21፡07፣ 30 ኪሎ ሜትር 1፡37፡25፣ 39 ኪሎ ሜትሩን 2፡16፡20 አጋምሰው 40 ኪሎ ሜትሩን 2፡08፡14 ሲያጋምሱ ፀሐይ ከአሸናፊዋ በ19 ሰኮንድ ዘግይታ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
በሌላ በኩል በጣሊያን የጎዳና ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን፣ በሮም ኦስቲያ ግማሽ ማራቶን ታደሰ ታከለ 59፡56 ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ በፈረንሣይ ፓሪስ የሴቶች ግማሽ ማራቶን ቤተልሔም ይመር 1፡06፡46 በሆነ ጊዜ ሦስተኛ ወጥታለች፡፡
በፈረንሣይ ካኔስ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ልቅና አምባው 32፡22 አንደኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
በየሳምንቱ በተለያዩ አገሮች ላይ በሚከናወኑ የጎዳና ውድድሮች ላይ የማይጠፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አብዛኛዎቹን ውድድሮች በድል ማጠናቀቁን ተያይዘውታል፡፡
የጎዳና ውድድሮች በተበራከተበት በዚህ ወቅት በየውድድሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መመልከት የተለመደ ነው፡፡
በተለይ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለመም አመቺና በቂ የልምምድ ሥፍራ ባለመኖሩ ፊታቸውን ወደ ጎዳና ውድድር እንዲያዞሩ አስገድዷቸዋል፡፡
ከዚያም ባሻገር የጎዳና ውድድሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱና አቋራጭ የገቢ ምንጭ መሆኑ ነው፡፡ በመም ውድድሮች ጊዜ ከመፍጀት ይልቅ በረዥም እንዲሁም በጎዳና ውድድሮች ላይ ማተኮር አዋጭ አማራጭ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ኢትዮጵያን በመካከለኛው ርቀት በመወክል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚታወቁ አትሌቶች ወደ ረዥም ርቀቱ መግባት ጀምረዋል፡፡
አትሌቶች ወደ ረዥም ረቀት ትኩረት ማድረግ በአትሌቶች ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የአሠልጣኞችና የማናጀሮች ጫና ጭምር እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ይህም አሠልጣኞች አትሌቶችን አሠልጥነው ለውድድር ብቁ በማድረግ ማናጀሮች ደግሞ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማመቻቸት የጥቅም ተጋሪ በመሆናቸው ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱ አሠልጣኝ በጥቂቱ ከ20 ያላነሱ የማራቶን አትሌቶች ይዞ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከአሠልጣኞና ማናጀሮች ባሻገር አትሌቶችን በካምፕ አስቀምጦ ማሠልጠን ሌላው ልምድ ሆኗል፡፡
በተለይ ምርጥ የግል ሰዓት ያላቸውን አትሌቶች መልምሎ ወደ ማኅበሩ ወይም ማዕከሉ በማስገባት አትሌቶች ዘመናዊ መንገድ እንዲከተሉ ማድረግ የዘመኑ መለያ ነው፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ይህንን ቡድን በመቀላቀል ዘመናዊ መንገድ እየተከተሉ ይገኛሉ፡፡
በአንፃሩ አብዛኛውን ጊዜ አትሌቶች በግላቸውና በብሔራዊ ቡድን ተሠልፈው ሲወዳደሩ በግል የሚያመጡት ሚዛን ሲደፋ መስተዋሉ ሁሌም የሚያከራክር ጉዳይ ነው፡፡