በኢትዮጵያ የሞቀና የተመቻቸ ኑሮ ውስጥ የነበረው ቤተሰብ በቅጽበት ነበር ዕጣ ፈንታው ስደት የሆነው፡፡ የታሪኩ ባለቤና የአሁኗ ‹‹የላይፍ ሴንተር›› መሥራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ ደርግን ለመጣል በተደረገው ሕዝባዊ ትግል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ኢሕአዴግ አገር መምራት ሲጀምር ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ የሽግግር መንግሥት (1983 – 1987) ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በመቀጠልም የፌዴራል ሪፐብሊኩ ሲቋቋም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፣ ወ/ሮ ሙሉም በወቅቱ በአዲስ አበባ የድርጅት ጽሕፈት ቤትን በአመራርነት አገልግለዋል፡፡ ሆኖም ባለቤታቸው አቶ ታምራት 1989 ዓ.ም. መታሰራቸውን ተከትሎ፣ የሁለት ሕፃናት ልጆቻቸው ሕይወት አደጋ ላይ በመውደቁ ወደ ኬንያ ስደተኞች በማምራት ሦስት የሥቃይ ዓመታትን ማሳለፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ያለ አባት ሁለት ልጆችን ይዘው በኬንያ ስደተኛ ጣቢያ የከተሙት ወ/ሮ ሙሉ፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ ጉዳያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ አሜሪካ አቀኑ፡፡
ከ12 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2012 ወላጅ እናታቸውን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና እነዚህ በኬንያ ያሳለፏቸው የመከራ ጊዜያት የችግረኛ እናቶች ሕይወትና ያለ አባት የሚያድጉ ሕፃናትን ስቃይ እንዲረዱ በማድረጉ፣ ‹‹ላይፍ ሴንተር›› የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅትን እንዲመሠርቱ ምክንያት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ልጆቻቸውን ታቅፈው ጎዳና ላይ የወጡትን እናቶች ሲመለከቱ፣ በስደት በነበሩበት ወቅት ያለ አባት ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን በማሰብ በኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ በ2005 ዓ.ም. የተቋቋመው ድርጅቱ በአዲስ አበባ በቂርቆስና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች እንዲሁም በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ ዞን፣ ሰቆጣ ከተማ ውስጥ የበጎ አድራጎት ሥራን መሥራት ጀመሩ፡፡ ላይፍ ሴንተር የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት በፕሮግራሙ ለ280 ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ልጆች መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎታቸውን በማሟላት የተረጋጋ ሕይወት ይኖራቸው ዘንድ በትምህርትና በጥሩ ሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመደገፍ እንዲቻል በአሜሪካ ‹‹ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ›› የሚል ሌላ ድርጅት የተመሠረተ ሲሆን፣ ከዚያ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ለሚገኘው ድርጅት እንዲውል መደረጉን ወ/ሮ ሙሉ ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች የኢኮኖሚ አቅም በዓለም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ተርታ ሲሆን፣ ላይፍ ሴንተር ይህንን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
በላይፍ ሴንተር መሠረታዊ የቢዝነስ ሥልጠናና ተዘዋዋሪ ብድር እየተመቻቸ፣ የገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ ተሠማርተው የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ በማሻሻል ላይ የሚገኙ እማወራዎች ቁጥር 300 መድረሱንም ይናገራሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ መሠረታዊ የልብስ ስፌት ሙያ ሥልጠና ወስደው የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት በማሻሻል ላይ የሚገኙ ከመቶ በላይ ሴቶች በድርጅቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ወ/ሮ ሙሉ እንዳሉት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ እናቶች በራሳቸው መተማመንና በጥረታቸው ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ መሠረታዊ የንግድ ክህሎት፣ የልብስ ስፌት ሥልጠናዎች፣ የብድር አገልግሎት የክትትል፣ የድጋፍና የምክር አገልግሎት ያገኛሉ፡፡
ድርጅቱ የልጆች ድጋፍና እንክብካቤ መርሐ ግብር ሲኖረው፣ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ሕፃናት በወርኃዊ የገንዘብ ድጋፍ መሠረታዊ የምግብ አቅርቦት፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎች፣ አስተማሪና አዝናኝ ትምህርታዊ ጉዞዎች፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲሁም የእጅ ሙያ ሥልጠና ያገኛሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር በላይፍ ሴንተር የቤት መጻሕፍት አገልግሎት ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሁም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ልጆች የማበረታቻ ሽልማት በድርጅቱ ውስጥ ከሚያገኙ ድጋፎች ውስጥ በጥቂቱ መሆኑን ዳይሬክተሯ ያብራራሉ፡፡
‹‹ልጆች ቀጣይ አገር ተረካቢዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከልጅነታቸው አንስቶ በጥሩ ሥነ ምግባር ማደግ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም በማዕከላችን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤›› ሲሉም ወ/ሮ ሙሉ ያስረዳሉ፡፡
ልጆችን ከወላጆቻቸው ወይም ከአሳዳጊዎቻቸው ነጥሎ ማሳደግን እንደማያምኑበት የሚያስረዱት ዳይሬክተሯ፣ ይልቁንም ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር ሆነው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ማሳደግ የበለጠ ተመራጭ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ድርጅቱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ልጆች በክፍለ ከተማ ከሚገኙ ቀበሌዎች የሚረከብ ሲሆን፣ የራሱ መቀበያ መሥፈርት አለው፡፡ ቀዳሚው ምንም ወላጅ የሌላቸው ልጆችን መቀበል ሲሆን፣ በቀጣይ አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸው እንዲሁም ወላጆቻቸው የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚ የሆኑ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ወላጅ ያጡ ደግሞ በአካባቢው ከሚገኙ ኅብረተሰብ ውስጥ እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡
ድርጅቱ ከተመሠረተ በኋላ የቢዝነስ ሥልጠና የወሰዱና ብድር ያገኙ 400 እናቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው ራሳቸውን ችለው ቤተሰብ እየደጎሙ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ላይፍ ሴንተር ዕድሜያቸው ከአራት ዓመት ጀምሮ ላሉ ሕፃናት በማዕከሉ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፣ ኮሌጅ እየተማሩ ያሉና በቅርቡም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እየተዘጋጁ የሚገኙ መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ማዕከሉ ከአዲስ አበባ ባሻገር በዋግኸምራ ለ57 ዜጎች ተመሳሳይ ዕርዳታ እያደረገ ሲሆን፣ የውኃ ጉድጓድ በማስቆፈርም ድጋፍ የሚያገኙ የጓሮ የአትክልት ሥራ ላይ ተሰማርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ማስቻሉን ዳይሬከተሯ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ሙሉ ድርጅቱ የተቸገሩ እናቶችንና ሕፃናትን ሕይወት እየታደገ፣ የበጎ አድራጎት ሥራውን በአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫ የማስፋፋት ውጥን ይዞ እየሠራ ቢሀንም፣ የመሥያ ቦታ ለማግኘት የመንግሥትን ደጅ ቢጠኑም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን ላሉበት የሥራ ማስኬጃና መኖሪያ ቤት ከፍተኛ ኪራይ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡
እንደ ወ/ሮ ሙሉ አስተያየት መንግሥት የቦታ አቅርቦት ቢያመቻች፣ በየዓመቱ ለኪራይ በሚወጣው ገንዘብ የበርካታ እናቶችንና ሕፃናትን ሕይወት መታደግ ይቻል ነበር፡፡
ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚያከብር መሆኑንና ከምሥረታው ጀምሮ የተከናወኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለማስተዋወቅ፣ የማይተካ ሚና የተጫወቱ ባለድርሻ አካላትን ለማመሥገንና ዕውቅና ለመስጠት የድርጅቱን የበጎ አድራጎት አገልግሎትና ተደራሽነት ለማስፋት እንዲሁም ተጨማሪ ባለድርሻ አካላትን ለመፍጠር ግብ ያደረገ መርሐ ግብር መሰናዳቱንም ገልጸዋል፡፡