Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የኢንቨስትመንት ችግሮችን የሚያቃልሉ የንግድ ትስስሮች

አፍሪካ ትረስትድ ፓርትነርስ (ኤቲፒ) ለኢትዮጵያ ልማት ተግዳሮት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ16 ዓመታት በፊት የተቋቋመውና ‹‹ለቋሚ ዕድገትና ለውጥ የሚፈለግ ኩባንያ መሆን›› ርዕይን አስቀምጦ እየሠራ የሚገኘው ድርጅቱ፣ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ከዚሁ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ እንዲልኩ ለማስቻል ዝግጅቶችንም ያከናውናል፡፡ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ወደ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች እንዲቀላቀሉ የሚያስችሉ የአገር ውስጥና የውጭ ዓውደ ርዕዮችንም ላለፉት ዓመታት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከመጋቢት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ አገሮች የሚደረጉ ኢንቨስትመንት ነክ ዓውደ ርዕዮችን እንደሚያዘጋጅ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ አቶ አክሊለ በለጠ የአፍሪካ ትረስትድ ፓርትነርስ (ኤቲፒ) መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ በድርጅቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር:- ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንቨስትመንት በኩል ለመሥራት ያቀዳችኋቸውን ዝግጅቶች ቢገልጹልን?

አቶ አክሊለ– በዋነኝነት የምንሠራው የንግድ ዝግጅቶችን ማከናወን ነው፡፡ ከሥራዎቻችን መካከል በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንሠራቸው ዓውደ ርዕዮች ይገኙበታል፡፡ ይህንንም ይፋ አድርገናል፡፡ ዓውደ ርዕዮቹና ሲምፖዚየሞቹ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍና በወጪ ንግድ የተሰማሩ እንዲሁም መንግሥት በዓለም አቀፉ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል የሚከፍቱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር:- የንግድ ትስስሩን ለመፍጠር የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እንድታሰናዱ አብረዋችሁ የሚሠሩት ድርጅቶችና ባለሀብቶች እነማን ናቸው? ድጋፋቸውስ ምን ይመስላል?

አቶ አክሊለ– በሥራው ላይ 16 ዓመታት ያህል ቆይተናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ኔትወርካችንን እያሰፋን በርካታ አጋሮችን መፍጠር ችለናል፡፡ በ18 አገሮች ውስጥ አጋሮች አሉን፡፡ አንዳንዶቹ አጋሮቻችን የመንግሥት ቢሮዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከኔዘርላንድ የንግድ ኮሚሽን ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ከኤምባሲዎችም ጋር እንዲሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ በንግድ ለንግድ ግንኙነት በተመሳሳይ ንግድ የተሰማሩትን አጋር እያደረግን እንሠራለን፡፡ ይህም በሁሉም አቅጣጫ ኢንቨስተሮችን እንድናመጣ እያስቻለን ነው፡፡ ያሉንን ኔትዎርኮች በሙሉ በመጠቀም በተለያየ አቅጣጫ ባለሀብቶች እንዲመጡ ዕድል እየፈጠርን ነው፡፡

ሪፖርተር:- በንግድ ዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ በአጋርነት የሚሠሩ ሥራዎች ቀጣይነት ማጣት ይገኝበታል፡፡ በዚህ ረገድ ድርጅታችሁ ምን ሠርቷል?

አቶ አክሊለ– ሥራው ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ እያደገም መጥቷል፡፡ በአገር ውስጥ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ማስጠቀም መቻላችን ግንኙነቶች እንዲቀጥሉና ዕድገቱ እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል፡፡ ይህ በአገር ውስጥ ላሉት የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

ሪፖርተር:- ፋይዳው ምንድን ነበር?

አቶ አክሊለ– የመጀመርያው የወጪ ንግድን ማበረታታቱ ነው፡፡ ለኩባንያዎች የወጪ ንግድ ዕድልን መክፈት ተችሏል፡፡ እየሠሩበትም ነው፡፡ ሁለተኛው ቴክኖሎጂን ወደ አገር ውስጥ ማምጣት ነው፡፡ እዚህ ላይ ቴክኖሎጂዎችን ከማምጣት ባለፈም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚሠሩበትን ዕድል ፈጥረናል፡፡ አዲስ ይዘን የመጣነው የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ ደግሞ ሌላው መልካም ዕድል ነው፡፡

ሪፖርተር:- የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ አሠራራችሁ እንዴት ነው? የት የት አገሮች ላይ ትሠራላችሁ?

አቶ አክሊለ– የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ አሁን የጀመርነው ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካና ኔዘርላንድ ነው፡፡ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ የሚያደርጉ ባለሀብቶችና የመንግሥት አካላት ለመንግሥትም ሆነ ለግል ፕሮጀክቶች ፋይናንስ የሚያደርጉበት ነው፡፡ ይህ ከአሥር ሚሊዮን ዶላር እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ያሉ ፕሮጀክቶች ፈንድ የሚያገኙበት ወይም የመዋዕለ ንዋይ መዋጮ (ኢኪዩቲ) የተመቻቸበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ አሁን ያለብን መሠረታዊ ችግርና ወደኋላ የጎተተን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የገንዘብ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በተወሰነ ደረጃ ሊያግዝ ስለሚችል እዚያ ላይ ትኩረት አድርገን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር:- የውጭ ፋይናንሱ ለየትኞቹ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚደረግ ነው?

አቶ አክሊለ– የፋይናንስ ድጋፉ ከመሠረተ ልማት ይጀምራል፡፡ ግብርና፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ሪል ስቴት፣ ሆቴልና ቱሪዝምን ይጨምራል፡፡ በልዩ ሁኔታ ደግሞ በግብርና ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ፈንድ ብቻ ሳይሆን ግራንት የሚያገኙበት ነው፡፡

ሪፖርተር:- እንደዚህ ዓይነት ዕድሎችን ባለሀብቶች እንዲያውቋቸው የምታደርጓቸውን ሥራዎች ቢገልጹልን፡-

አቶ አክሊለ– ከውጭ የሚገኙ የፋይናንስ ዕድሎችን፣ የንግድ ልውውጦችንና መረጃዎችን ለባለሀብቶች ይፋ ለማድረግ በተለያዩ አገሮች የማስተዋወቅ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ ዘንድሮ ከመጋቢት 16 እስከ 21 የሚቆይ ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት አፍሪካ የሚል የመጀመርያውን የአፍሪካ ኢንቨስትመንትና ትሬድ ኮንፍረንስ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን እናደርጋለን፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ የንግድ ሚኒስቴር፣ የቆዳ ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩትና ሌሎች በወጪ ንግድ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚሳተፉበት ነው፡፡ የአፍሪካን የንግድ ምኅዳር ለማስፋት የሚያስችሉ የንግድ ሐሳቦችም በኢንዱስትሪ ኤክስፐርቶችና በምሁራን የሚቀርብበት ነው፡፡ ቀጣዩ ዝግጅት በኔዘርላንድ አምስተርዳም ይደረጋል፡፡ ይህ ‹‹ኢንቨስት ኢን አፍሪካ›› ይባላል፡፡ ከኢትዮጵያ 37 ያህል የአፍሪካ አገሮች ተወካዮች ይሳተፋሉ፡፡ ይህ ኩነት ኢንቨስትመንትን ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ የሚሠራበት ነው፡፡ በተለይ ለጀማሪ የንግድ ሰዎችና ለሴት ነጋዴዎች  የተለየ ግራንት ያለበት ፕሮግራም ነው፡፡ ሦስተኛው ካናዳ ንታሪዮ የምናደርገው ፌስቲቫል ነው፡፡ ይኼኛው በተለይ ባህልን፣ ሙዚቃን፣ ጥበብንና አልባሳትን ለማስተዋወቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሰሜን አሜሪካ የንግድ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅና የንግድ ለንግድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ካናዳ ቡና አያበቅልም፡፡ ቡና ከዚህ ብቻ የሚያገኙ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ አራተኛው ፕሮግራም በአሜሪካ የሚደረግ ነው፡፡ ለዚህ አጋራችን አፍሪካን ብሬን ባንክ ይባላል፡፡ አፍሪካን ብሬን ባንክ የአፍሪካውያንን የዕውቀት ክምችት መጠቀም አልቻልንም በሚል መነሻ የተመሠረተና የአፍሪካውያንን የዕውቀት ሀብት አሰባስቦ ለመጠቀም አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ አፍሪካ አሜሪካውያን ቢሊየነሮች የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕድል የሚከፍት ነው፡፡ አምስተኛው ፕሮጀክታችን አዲስ አበባ ላይ የሚዘጋጀው ‹‹ፊንቴክስ አዲስ›› ነው፡፡ ይህ በፈርኒቸር፣ በውስጥ ዲዛይንና በፊኒሽንግ ሥራ ትኩረት ያደገና የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡   

ሪፖርተር:- የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት አዋጭ የሆነ የንግድ ሐሳብ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል ችግሮች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት ተነስተዋል፡፡ በእናንተ በኩል የሚደረግ ዕገዛ ይኖራል?

አቶ አክሊለ– በእኛ በኩል የሠራናቸውና በሒደት ላይ የሚገኙ ወደ አራት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ሒደታቸውም ጥሩ ነው፡፡ ፕሮጀክቶችና የፕሮጀክት ሐሳቦችም አሉ፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የማስተካከል፣ ቅርፅ የማስያዝና ፋይናንስ ለማግኘት በሚያስችል ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም እኛ የኮንሰልታንሲ ድርጅት አለን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የውጭ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ፕሮጀክቱ ከመጣ በኋላ ቅርፅ የማስያዝ፣ ለደጋፊዎች ወይም ፈንድ ለሚያደርጉ አካላት ፕሮጀክቱን ብቁ አድርጎ የማስተካከል ሥራ በእኛ በኩል እንሠራለን፡፡ አንዴ የፕሮጀክት አጭር መግለጫ ከመጣ በኋላ የማስተካከል ሥራውን እናግዛለን፡፡ የራሳቸውን ብቁ ንግድ ሐሳብ ይዘው የሚመጡ ደግሞ በዚያው ይቀጥላሉ፡፡ የእኛ ዕገዛ ካስፈለጋቸው የስትራቴጂና የፕሮጀክት ዴቨሎፕመንት ክፍል አለን፡፡

ሪፖርተር:- ከላኪዎች ማኅበር ወይም ከንግድ ማኅበራት ጋር ያላችሁ የሥራ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ አክሊለ– ከማኅበራት ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ በዋነኝነት በቅርበት የምንሠራው ከማኅበራትና ከመንግሥት ጋር ነው፡፡

ሪፖርተር:- በወጪ ንግድ ላይ በሚፈለገው መጠንና የጥራት ደጃ የማቅረብ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በእናንተ በኩል የምታደርጉት ድጋፍ ምን ይመስላል?

አቶ አክሊለ– ከኢትዮጵያ ያለው መሠረታዊ ችግር በብዛትና በጥራት የማቅረብ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የውጭ ገዥዎች ትልልቅ መጠን ያላቸውን ነገሮች የመግዛት ፍላጎት ሲያሳዩ በዚህ ደረጃ ለማቅረብ የአቅም ውስንነት ብዙ ጊዜ ይስተዋላል፡፡ ይህ በሒደት ይቀየራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተለይ አሁን ለግብርና የተሰጠው ትኩረት በብዛት ማቅረብን ወደተሻለ ደረጃ ያመጣዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህ አማካይነት ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ በእኛ በኩል ከፕሮጀክት ጥናት ጀምሮ ኔትወርክ ማድረግ፣ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር መሥራት፣ ንግዱን ከዚህ ወደ ውጭ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ ማድረግ፣ ዘንድሮ በአሜሪካ ወይም በካናዳ የምናዘጋጀውን ዝግጅት በሌላ ጊዜ ኢትዮጵያ እንዲመጣ የማድረግ ሥራ እንሠራለን፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚዘጋጀውን በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያ እንዲሁም ካናዳ የሚዘጋጀውን በሦስት የአፍሪካ አገሮች እንዲዘጋጅ እናደርጋለን፡፡ ውጭ ያሉ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማስቻልም ጎን ለጎን የምንሠራው ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...