Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ባለሙያዎች መንግሥት ያቀረበውን ረቂቅ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ተቃወሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ  በርካታ አነጋጋሪ የሚባሉ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ይዞ መምጣቱ በተለያየ መንገድ እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ የኢንሹራስ ኩባንያዎችን በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተካተተው አንቀጽ ፈጽሞ ሊተገበር የማይገባው ስለመሆኑ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበርም በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኩባንያዎች ካሳ ሲከፍሉ ካሳ የተከፈለው ደንበኛ ከተከፈለው ካሳ ላይ 15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ ታሳቢ ተደርጎ ለመንግሥት ገቢ መደረግ እንዳለበት የሚያመለክተው አንቀጽ፣ ለኢንዱስትሪው አደገኛ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ማኅበሩ ይህንኑ ሥጋት በመንተራስ በመረጃ በማስደገፍ ሊያቀርብ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በነባሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ የኢንሹራንስ ዘርፍ ያልተካተተበት ዋናው ምክንያት በየትኛውም አገር ኢንሹራንስ ላይ የታክስ ዓይነት የማይመለከትው፣  ‹‹የአሁኑ ታክስ ሲወጣ ምን ታስቦ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ ስለዚህ የኢንሹራንስ ባለሙያዎችና የሕግ ባለሙያዎች ጉዳዩን እያጠኑ ስለሆነ፣ በረቂቁ ላይ ያላቸውን ሐሳብ አቅርቡ ስለተባለ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሐሳባቸውን እያዘጋጀን ነው፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ይህንን አንቀጽ ከረቂቁ ውስጥ ያወጡታል፡፡ ምክንያቱም ኢንሹራንስ ቫልዩ አድ ስለላልሆነና ኢንሹራንስ ጉዳት ካሳ ስለሆነ መተግበር ስለሌለበት ነው፡፡ 

ስለዚህ በዚህ ረቂቅ አዋጅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የተመለከተው አንቀጽ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ቀላል አይሆንም ይላሉ፡፡

የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ አሰግድ ገብረ መድህንም በአዲሱ ረቂቅ ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲመለከተው መደረጉ በተለይ ከካሳ ክፍያ ላይ 15 በመቶ ተቀናሽ ሆኖ ለመንግሥት ይግባ መባሉ ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም፡፡ 

‹‹ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው፡፡ ከደንበኞች ሥጋት ተቀብለው አደጋ ሲደርስ ለደንበኞች ካሳ ይከፍላሉ፡፡ ለሚሰጡት አገልግሎትም ተጨማሪ ዕሴት ታክስን (ቫትን) ጨምሮ የተለያዩ ታክሶች ይከፍላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡ ስለዚህ በድጋሚ ሌላ ታክስ በዚህ አገልግሎት ላይ ሊከፈልበት አይገባም፤›› ብለዋል፡፡ 

በተለይም በንብረታቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ደንበኞች ትክክለኛውን የንብረት ዋጋ መካስ የኢንሹራንስ አገልግሎት መሠረታዊ መርህ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ አሁን የቀረበው የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚከፍሉት የጉዳት ካሳ ላይ 15 በመቶ ታክስ የሚጥል ድንጋጌ መካተቱ የኢንሹራንስ መርህን እንደሚያዛባ አስረድተዋል።

‹‹የኢንሹራንስ አገልግሎት መርህ በንብረታቸው ላይ አደጋ የደረሰባቸውን ድንበኞች ወደ ነበሩበት የገንዘብ ወይም የንብረት ይዞታ እንዲያመጡ ማደረግ ነው። በመሆኑም ደንበኛው ከአደጋ በፊት ወደነበረ የገንዘብ ወይም የንብረት ይዞታ ለመመለስ የማያስችል የገንዘብ መጠን በካሳ መልክ ሊከፈለው አይገባም፡፡ በመንግሥት የቀረበው የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው፤›› ብለዋል።

አንድ ግለሰብ ለመኪናው የኢንሹራንስ ሽፋን ከመግዛቱ አስቀድሞ መኪናውን ሲገዛ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ (ቫት) እንደሚከፍል የገለጹት አቶ አሰግድ፣ ተሽከርካሪው መጀመርያውኑ ቫት የተከፈለበት በመሆኑ በጉዳት ምክንያት ካሳ ሲከፈለው እንደገና ቫት እንዲከፍል ማድረግም ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጉዳት ለደረሰበት አንድ ደንበኛ ካሳ የሚከፍሉት ደንበኛው ወደ ነበረበት የንብረት ይዞታ ለመመለስ ከመሆኑ ባሻገር ደንበኛው ጉዳት የደረሰበትን ንብረት ለመተካት ግዥ ሲፈጽም ቫት መክፈሉ እንደማይቀር ገልጸዋል። በመሆኑም አንድ በጉዳት ምክንያት ንብረቱን ያጣ ደንበኛ የኢንሹራንስ ካሳ ተከፍሎታል በሚል ዕሳቤ ቫት እንዲከፍል መጠየቅ ፈጽሞ ፍትሐዊ አይሆንም ሲሉ ምክንያታዊ ክርክራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ኢንሹራንስ ኩባንዎች ይህ ቫት ከካዝናቸው ወጥቶ በካሳ ክፍያ በኩል ስለሚከፈል እንደ የካሳ ክፍያ ወጪ አድርገው ነው እንጂ የሚዩያት፣ ለእነሱ ተጨማሪ እሴት ባለመሆኑ በረቂቅ አዋጅ ሕጉ ላይ የተመለከተውን አንቀጽ መተግበር አግባብ አይሆንም በማለት ሙያዊ ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

‹‹በመሆኑም የጉዳት ካሳ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ክፍያው ወጪ ነው እንጂ፣ የሚባለው 15 በመቶ ቀንሰን ለመንግሥት ገቢ የሚደረግበት አሠራር ትክክል አይሆንም፤›› ያሉት አቶ አሰግድ፣ በረቂቁ የተቀመጠው አንቀጽ ይተግበር ማለት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከስረው ደንበኞቻውን ካሳ ክፍያ ይክፈሉ እንደማለት መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መጀመሪያውንም የመድን ሽፋን ውል ሲያስሩ የጉዳት ካሳ በሚከፍሉበት ወቅት እንዲሰበስቡ የሚጠበቅባቸውን 15 በመቶ ቫት ታሳቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ አንደምታ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሰግድ፣ ይህ ማለት አሁን ለመድን ሽፋን በሚከፈለው ዓረቦን ላይ 15 በመቶ ዋጋ ጭማሪ ያስከትላል፣ ይህም በየትኛውም መንገድ ቢታይ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ አሁን በሚደነግገው መሠረት ይተግበር ቢባል ሁሉም የኢንሹራስ ኩባንያዎች ነባር ውሎቻቸውን አፍርሰው አዲስ ውል እንዲያስሩ የሚያስግድድ አስቸጋሪ ተግባር እንደሚሆን ገልጸዋል።

የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢብሳ መሐመድም፣ የኢንሹራንስ ካሳ ቀድሞ ቫት የተከፈለበት በመሆኑ ድጋሚ ቫት ማስከፈል ተገቢ አለመሆኑን በአጽንኦት ይናገራሉ።

በተለይ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያ አቅም ባልዳበረበት ሁኔታ ኢንሹራንስ ተጠቃሚው ላይ ተጨማሪ 15 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍል የሚያስገድድ አዋጅ ማውጣት ኢንዱስትሪውን የበለጠ እንደሚጎዳው አመልክተዋል፡፡ 

በቅርቡ ዝቅተኛ የኢንሹራንስ ዓረቦን ዋጋን ለመተመን እንዲወጣ ከሚፈለገው መመርያ ጋር ጉዳዩን ካየነው ደግሞ፣ የዓረቦን ዋጋን ስለሚያንረው ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ የታክስ ድንጋጌዎችን መተግበር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አቶ ኢብሳ አብራርተዋል፡፡ 

አቶ ያሬድም ቢሆኑ ይህ ረቂቅ መሠረታዊ የሚባለውን የኢንሹራንስ መርህ የሚገፋ ሁኔታ ከመሆኑ ባላይ፣ 15 በመቶ ዓረቦኑ ላይ ይታከል ቢባል፣ ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራና የገበያ ችግር እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

ለምሳሌ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ዋስትና የተገዛላቸው እንደ አውሮፕላን፣ መርከብና የመሳሰሉ የመድን ሽፋኖች የገንዘብ መጠናቸው ከፍተኛ ስለሚሆን፣ እዚህ ላይ 15 በመቶ መጫን የኢንሹራንስ ሽፋን ወጪን ስለሚያንር ድንበኞችን ያሸሻል ብለዋል።

ደንበኛው 100 ብር መካስ ሲገባው የቫት 15 በመቶ ተቀንሶ ቢከፈለው እጁ ላይ የሚደርሰው ከጉዳቱ ካሳ ንብረቱን ለመመለስ የማያስችልና አክሳሪ ይሆንበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዓረቦኑ ላይ 15 በመቶ ይጨመር ቢባል የመንድን ሽፋን አገልግሎት ዋጋን ውድ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ኢኮኖሚው ዋስትና እንዳይኖረው ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል።

‹‹የመድን ሽፋንን በመኪና ብቻ መመልከት ተገቢ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ በቢሊዮን ዶላር ጭምር ኢንሹራንስ የሚገባላቸው ትልልቅ ሀብቶች በመኖራቸው፣ ይህ አዋጅ ይተግበር ከተባለ የንብረቶቹን ባለቤቶች ዋስትና እንደሚያናጋ ገልጸዋል። በተለይ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ባለቤት መንግሥት ስለሆነ መንግሥትንም እንደሚፈተን ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹እኔ ይህ ረቂቅ መተግበር የለበትም የምልበት ሌላው ዋነኛ ምክንያት ደግም በየትም አገር በአሁኑ ሰዓት የኢንሹራን ትራንዛክሽን ተጨማሪ እሴት ታክስ አይከፈልበትም፡፡ ነባሩ አዋጅም ይህንን ያላደረገው ይህንን በመገንዘብ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በታክስ ድንጋጌዎች ዙሪያ ተጨማሪ ሐሳብ የሰጡት አቶ አሰግድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የታክስ ትዕዛዝ ፕሮግሬሲቭ ነው ይላሉ፡፡ 

አንዳንድ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላቸውን ዜጋ ተኮር ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የዘረጉ አገሮች አንዳንድ ጊዜ የሚተዋቸው ታክሶች አሉ፡፡ የአገራችን የታክስ ሥርዓት ፕሮግሬሲቭ ቢሆንም፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የተለያዩ ታክሶችን መደራረብ የአገልግሎትና የሸቀጥ ዋጋን ይጨምራል፡፡ ይህንን ደግሞ ተሸካሚው ሸማቹ ነው ወይም ተገልጋዩ ስለሚሆን ጉዳት እንዳለው ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ 

‹‹የትኛውንም ታክስ መጨረሻ ላይ የሚሸከመው ተገልጋይ ነውና አንዳንድ ጊዜ ተገልጋዩን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታል፤›› ያሉት አቶ አሰግድ፣ የትኛውም ዓይነት ለለውጥ ይጠቅማል ተብሎ የሚተገበር የታክስ ማሻሻያ የአገልግሎትና ምርትን ከፍ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መታየት እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ፡፡  

ታክስ መክፈል የግድ መሆኑንና የታክስ መሠረቱን ማስፋት ተገቢ ቢሆንም፣ መሠረቱን ሲያሰፉ ግን ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ማሰብና መጠንቀቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የታክስ መሠረትን ለማስፉት ቀጥተኛ በሚባሉ የታክስ ዓይነቶች ላይ በርትቶ መሥራት እንደሚሻል መክረዋል፡፡ ኢኮኖሚው ሲያድግና ሠራተኞች በብዛት ተቀጥረው መሥራት ሲችሉ፣ እንዲሁም ምርት ሲጨምር መንግሥት የሚያገኘው ታክስ የሚጨምር በመሆኑ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ባይኖረው እንኳን ከእነዚህ ቀጥታ ታክሶች ብቻ የሚገኝ ገቢ አገሪቱን ይቀይራል የሚል ጠንካራ አቋም እንዳላቸው አቶ አሰግድ ገልጸዋል። ታክስ ፍትሐዊ ሊሆን እንደሚገባ በመግለጽም፣ መንግሥት ገቢውን ለመጨመር በማሰብ ብቻ ተደራራቢ ታክሶችን መጣል የለበትም ብለዋል።

ታክስ የተከፈለበት ወይም የተቀረጠ ዕቃ እሴት ሳይጨምር በኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ ሲዘዋወር ስለተገኘ ብቻ ታክስ ሊከፈልበት አይገባም፡፡ በመሆኑም የታክስ ድንጋጌዎች ሲወጡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከሰሞኑ ይፋ ተደረገው የተጨማሪ እሴት ታክስ የታሰበው የመንግሥትን የታክስ ገቢ ለማሳደግ ቢሆንም፣ ጉዳት ያመጣል? አያመጣም? የሚለው በደንብ መፈተሽ አለበት፡፡ ምክንያቱም በውጤቱ ወገቡ የሚደቃውና መጨረሻ ላይ ታክሱን የሚሸከመው ኅብረተሰቡ ነው ብለዋል።

‹‹ባለኝ መረጃ መሠረት መንግሥት ወደ 45 ቢሊዮን ብር ከተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ ይፈልጋል፡፡ የታቀደው ይህ ነው፡፡ ይህንን ለመድረስ ግን ጫና መፈጠር የለበትም፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ የበጀት ጉድለቱ 309 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህንን የበጀት ጉድለት መሙላት አንዱ መፍትሔ ታክስ መሰብሰብ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንዱ የተጨማሪ እሴታ ታክስ ነው፤›› ብለዋል። 

የተጨማሪ እሴታ ታክስን በኢትዮጵያ ለመተግር እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት ብዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይህንን ታክስ መተግበር ከባድ መሆኑን ጠቅሰው እንደነበር ያስታወሱ አቶ አሰግድ፣ ‹‹በእርግጥም ይህ ታክስ ከባድ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ አንዳንድ ሸቀጦችን መተው አለበት፡፡ ምንም እሴት ሳይጨመርላቸው ለምን ይከፈልባቸዋል ሲሉ ነበር፡፡ አሁንም ይህ ረቂቅ በተገልጋዩ ላይ ጫና ሊያሳርፍ እንደሚችል በማሰብ መንግሥት ሰፊ የበጀት ጉድለት አለበት፡፡ የበጀት ጉድለቱን እንዴት ነው የምናጠበው ብሎ በግልጽ ተወያይቶ ረቂቁን ደግሞ አይቶ ካልተቀየረ በቀር እንዲያውም ኅብረተሰቡን ይጎዳል፡፡

በረቂቁ ላይ በተቀመጠው መንፈስ አዋጁ ቢፀድቅ ኢኮኖሚውን ሊያቀዛቅዝ ይችላል፣ ኅብረተሰቡንም ይጫናል ያሉት አቶ አሰግድ፣ ደንበኞች ባንኮችንም ሆነ ኢንሹራንሶችን ከመጠቀም ሊቆጠብ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ደንበኞች በአስገዳጅ ሕግ እንጂ በትክክለኛ የንብረት ግምት እየተስተናገድን አይደለም በማለት ሊሸሹ ይችላሉ፣ ይሄ ደግሞ ትልቅ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል በማለት መንግሥት ያመነጨውን ረቂቅ አዋጅ እንዲከልስ መክረዋል።

‹‹በመመርያ የንብረትን ወይም የአገልግሎት ዋጋን ከፍ ማድረግ አይገባም፣ መሬት ላይ ባለው ትክክኛ ሕጋዊና እውነተኛ የኢኮኖሚ ዋጋ ላይ የተመሠረተ እንጂ አንድ ቦታ ላይ ያለን ክፍተት ለመሙላት ሲባል አዋጅ ማውጣት ተገቢ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ስለዚህ ይህ ረቂቅ አዋጅ ቢተገበር ጉዳት ስላለው መንግሥት ጉዳዩን ደግሞ ደጋግሞ ማጤን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ 

በረቂቁ ላይ ማኅበሩ በቂ መረጃ በማቅረብ ከአንቀጹ እንዲወጣ ይደረጋል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ያሬድ፣ ይህንንም ረቂቁን ላዘጋጀው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ይህ ረቂቅ ለምን መተግበር እንደሌለበት በጥናት ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

አቶ አሰግድና አቶ ኢብሳም ቢሆኑ ይህ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ መተግበር የለበትም ያሉትን አንቀጽ ለማስቀረት ተጨማሪ ውይይቶችና ምክክር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ባለው ሳምንት የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ዋስይሁን አባተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ የኢንሹራስ ኩባንያዎችን እንዲመለከት ታስቦ የነረበው ከ20 ዓመት በፊት ነበር ብለዋል፡፡

በዚያን ወቅት ግን ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ አቅማቸው አነስተኛና ያልዳበሩ በመሆኑ የቀሪ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ 

አሁን ግን አቅማቸው ከፍ ስላለ እንዲመለከታቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡ በረቂቁ ላይ ቅሬታ ካለም እንቀበላለን ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

   

 

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች