Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቅጥፈት!

እነሆ ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ሰው ብርቱው በመጓዝ ምኞቱ መንገድ አበጅቶ መራመድ አይታክተውም። ወዲህ ይመጣል ወዲያ ይሄዳል። የመገንባት ጥረቱ ሳይነጥፍ የማፍረስ ጥበቡም አይቅርብኝ እንዳለ በመንታ ማንነት ይወዛወዛል። ‹‹ታክሲ! ታክሲ!›› ይጮሃል አንድ ሰው። ሾፌራችን የታክሲዋን ፍጥነት ይቀንሳል። የተጣራው ሰው ሊደርስብን ይሮጣል። ‹‹በዚህ አሯሯጣችን ሁላችንም አትሌት አለመሆናችን ብቻ ይገርመኛል፤›› ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ተሳፋሪ። ‹‹ሜዳሊያ ማጥለቅና ዝና ቀረብን እንጂ አትሌቶች እኮ ነን…›› ይላታል አጠገቧ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ኧረ ዞር በል፣ ደሃ አትሌት ዓይተንም አናውቅ…›› ይለዋል መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹በቃ የእኛ ሰው ከገንዘብ ጋር ሳያገናኝ ወግ መጠረቅ ተሳነው ማለት ነው?›› ያለችው ከጀርባችን የተቀመጠች ደማም ናት፡፡ ሰው ሁሉ ሳንቲም ቅጭል ባለበት ማንጋጠጥን ልማድ ሲያደርገው ምን ትበል ታዲያ!

‹‹የጨረሽው ዓረፍተ ነገር ላይ ‘ማለት ነው’ ብሎ ማለት ምን ያስፈልጋል? እንዲያው ዝም ብዬ ሳስብሽ በድፍረትና በፈጣጣነት ባልተገራ አማርኛ፣ ሲያደናቁሩን የሚውሉ አንዳንድ የኤፍኤም ሰዎችን ትመስይኛለሽ…›› ይላል አጠገቧ ያለው ጓደኛዋ ለቀልድ ያህል። ልጅት እየሳቀች፣ ‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ ለምን የአማርኛ መምህር ሳትሆን እንደቀረህ እኮ ነው?›› ስትለው፣ ‹‹ትቀልጃለሽ? አበበ እኮ እስከ ዛሬ የሚበላው በሶ አለው። እኔ በዚህ የተቃጠለ ኑሮ ምንም ሳልበላ የአበበን ጉርሻ ልቆጥር ነው የአማርኛ መምህር የምሆነው? ወይስ ጫላ የዛሬ ስንትና ስንት ዓመት የጨበጠውን ጩቤ በክላሽ መቀየሩን እያወቅኩ፣ ዛሬም ያንኑ ስደጋግም ልኑርልሽ?›› ይላታል። ሁለቱ ሲሳሳቁ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ አዛውንት፣ ‹‹አይ የዛሬ ልጆች ቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ብልጥ ስትመስሉኝ ለካ ነገርም ታውቃላችሁ…›› ይላሉ። ‹‹ምን እናድርግ አባት እናት የሚያወርሰን ሀብት ብናጣ እኮ ነው?›› ብሎ አጠገባቸው የተቀመጠ ተሳፋሪ ይመልሳል። በዚህች ቅፅበት ያስቆመን ተሳፋሪ እያለከለከ ገብቶ ጣውላ አግዳሚ ላይ እየተቀመጠ፣ “ተመሥገን!” አለ። ምን ያድርግ ታክሲ እንደ አበበ ቢቂላ ማራቶን ሮጦ እየያዘ እንዳትሉ ብቻ!

ታክሲያችን ከቆመችበት ተንቀሳቅሳ ጉዞዋን ቀጥላለች። አዲስ የተቀላቀለው ተሳፋሪ ማመሥገኑን አላቆመም። መጨረሻ ወንበር በጋቢናው ትይዩ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ ‹‹ምን ተገኘ ወዳጄ? የኮንዶሚኒየም ዕጣ ወጥቶልህ ይሆን?›› ሲል ጨዋታ ጀመረው። ‹‹የድምፁ መጎርነንና መኩራራቱ ከአቀማመጡ ያስታውቃል…›› ይለኛል አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ አንዴ እሱን አንዴ እኔን እያየ። አብራራው ሳልለው እንደገና፣ ‹‹አሁን እኮ በእሱ ቤት ከፍ ብሎ ተቀምጦ ልጁን ቁልቁል ማየቱን እንደ ፅድቅ ይቆጥረው ይሆናል። ምነው ሰው ከፍ ብሎ በተቀመጠ ቁጥር ሰው መናቅ ይከጅለዋል?›› ሲለኝ ለማለት የፈለገው ይገባኛል። የምሥጋናውን መንስዔ ለማወቅ ሁላችንም ጆሯችን ጣውላው ላይ ወደ ተቀመጠው ወጣት ተጥዷል። ‹‹ለእኔ ነው ቤት የሚደርሰኝ?›› ብሎ ስቆ ሲያበቃ፣ ‹‹እኛ ቤት እኮ ፈጣን ሎተሪ ፍቆ አንድ ብር ደርሶት የሚያውቅ የለም፡፡ ሁሌም የደረሳቸው ሲዘሩት ነው በሩቅ ሆነን የምናየው…›› እያለ በጠማማ ዕድሉ ይሳለቃል። ምን ያድርገው ታዲያ የአርባ ቀን ዕድሉ ከሆነ!

‹‹ታዲያ ለምንድነው አሥር ጊዜ ተመሥገን የምትለው?›› ጅንኑ ተሳፋሪ መጀነኑ እየጨመረ ጠየቀው። ‹‹ፓስፖርት ስላወጣሁ ነዋ። አስጀምሮ ያስጨረሰኝ እሱ ምሥጋና ይግባው…›› ብሎ ሲመልስ አንዳንዱን ሳቁ በትንታ አጣደፈው። ሌላው እርስ በርሱ ተያየ። ‹‹እንዴ ፓስፖርት አውጥተህ እንዲህ ከሆንክ ቪዛ ሲመታልህ እንዴት ልትሆን ነው?›› ብሎ ሳይጨርስ ያ ቀብራራ፣ ‹‹ዋው፣ ዋው፣ ያኔማ ሁዳዴን ‘ደብል’ ነዋ የምፆመው…›› ምስኪኑ ልጅ የልቡን ይናዘዛል። አብዛኛው ተሳፋሪ ‘ሙድ’ ይይዛል። አዛውንቷ እናት፣ ‹‹ይቅናህ እስኪ እሱ ባለቤቱ። የሰው እህል ውኃ የት እንዳለ መቼም አይታወቅ። መጀመርያስ ፈጣሪ ምድርን ግዙ አለን እንጂ በኬላና በድንበር ተጣጥራችሁ እርስ በርስ ተገዛዙ አላለን። ድንበር ላይ የተተከለ ድንጋይ ነው ቦታውን የማይለቅ…›› ይላሉ። በስላቅ የተሟሸው ጨዋታ ወደ ስደት አቅጣጫ ሲያመራ ታክሲያችን መብራት ይዟት ቆመች። አንዳንዴማ ቆም እንበል እንጂ!

‹‹አልገባኝም እማማ ሠርቶ በአገር መለወጥ፣ ወገን መሀል ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ሀብት ማፍራት አለብን እየተባለ እርስዎ ስደትን ይደግፋሉ ማለት ነው?›› አለቻቸው ወጣ ብላ ጎናቸው ከተቀመጠው ተሳፈሪ አጠገብ የተቀመጠች ጠይም ዓሳ መሳይ። ‹‹ስደት? የምን ስደት አመጣሽ ደግሞ? ያልኩት ኬላና ድንበር የሴራ ፖለቲካ ውጤቶች ናቸው ነው። ምድር የሰው ልጆች በሙሉ ናት። አንቺ እዚህ ተወለጂ እንጂ እህል ውኃሽ ያለው አሜሪካ ወይም አውስትራሊያ ሊሆን ይችላል። እፍኝ በማታህል የእግዜር ሥራ ፓስፖርትና ቪዛ መጠያየቃችን ይገርመኛል። ግን መቼስ የሰው ልጅ ምን ቢደላው ሁሉ ቢሳካላት፣ ፀጋውን በእኩይ ሥራው ስለሚንደው ይኼው የወሰንና የክልል፣ የጎሳና የሃይማኖት ወሰን ተበጅቶለት እንደ አውሬ ጦር እየሰበቀ ይኖራል። ይኼን ነው እኔ የምለው። አጓጉል ፖለቲካ ማጣመም ለምዶባችሁ ሐሳብ የመረዳት አቅማችሁ ቀነሰና አረፈው መሰል?›› ብለው አዛውንቷ ዝም አሉ። ልካችንን የሚነግረን አያሳጣን!

ጥቂት ዝምታ ተራውን ታክሲያችን ውስጥ ናኘ። ጎልማሳው ብቻ አፍታ እያረፈ ያንሾካሹካል። ‹‹አየህ? ሰው አበቃለት ደከመ በሚባልበት ዘመን ሳይማር ኬላ ጥሶ ‘ዓለም የሁላችንም ናት’ ብሎ ሲያስብ፣ ፊደል ቆጠርን የሚለው በጎን በኩል በጎሳና በሃይማኖት ይናከሳል። አይገርምም?›› ይለኛል። ከኋላችን ከተሰየሙት ወጣቶች መሀል አንዱ፣ ‹‹ያለ ፓስፖርትና ቪዛ ሰው ያሻው ሥፍራ ሄዶ መኖር ይችላል ቢባል…›› እያለ በተምኔታዊ ዕሳቤ ፓሪስ ቤት ይገዛል፣ ለንደን ሆቴል ከፍቶ ሞስኮ ቮድካ ይጠጣል። ይኼን አስቂኝ ቅዠት ሾፌሩ በየት በኩል እንደሰማ አይታወቅም፡፡ ‹‹ስማ ምነው የምርቃና ወሬ በዛ? ታክሲዋን መቃሚያ ቤት ልታደርጋት ነው እንዴ?›› ብሎ ወያላውን ያሽሟጥጠዋል። ወይ ታክሲ፣ እንኳንም ቪዛና ፓስፖርት አታስጠይቅ ያሰኛል እኮ አንዳንዱ አጋጣሚ!

እየተጓዝን ነው። ወያላው ሒሳብ ይቀበላል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ክፉኛ ተግባብተዋል። ‹‹የገዥው ፓርቲ አባል ነሽ እንዴ?›› ድንገት ይጠይቃል። ‹‹ምን ማለትህ ነው? እንኳንስ እርስ በርሱ የማይግባባ ፓርቲ አባል ልሆን፣ ወሬያቸውን ስሰማ ጋዝ ጋዝ ይለኛል…›› ልጅት ተንገፍግፋ ትመልሳለች። ልጁ ስቆ ሲያበቃ፣ ‹‹ቆይ ግን ይህን ያሀል ምን አንገፈገፈሽ?›› ይላታል። ‹‹አንተ ደግሞ ትገርማለህ፣ ርዕዮተ ዓለማቸውና የቆሙለት የኅብረተሰብ ክፍል ጠርቶ የማይታወቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል ከመሆን ዳር ሆኖ መታዘብ አይቀልም እንዴ…›› ሲል አንዱ ጎልማሳ ጣልቃ ገባባቸው። ልጅት ከት ብላ እየሳቀች፣ ‹‹ምን እሱ ብቻ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት የደም ዓይነት ምርመራ በሚያስፈልገው በዚህ አሳዛኝ ዘመን፣ ዳር ሆኖ መታዘብ ብቻ ሳይሆን በሩቅ ሆኖ ጭምር እግዜሩ ይይላችሁ ማለትም ያሰኛል…›› ስትል ብዙዎች ግራ ተጋብተው ነበር ነገሩን ሲከታተሉ የነበሩት፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!

ልጅትን ደህና እያባበላት የነበረው ወጣት ዝም አለ። ሦስተኛ መቀመጫ ላይ የተሰየመ ወጣት ነገሩን ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ምናልባት ፖለቲካው ዜሮ የሆነው እንደ ጤፋችን በማዳበሪያ ተዘርቶ እየበቀለ በጄሶ ተጋግሮ ስለሚበላ ይሆናል፡፡ እስኪ እሱን መጀመርያ እናጣራ፣ አይመስላችሁም?›› ብሎ ሁላችንንም ቃኘ። ‹‹ኧረ ዞር በል ስንትና ስንት አጣሪ ኮሚቴዎች መቼ ሪፖርት አቅርበው ተበትነው ነው ደግሞ ሌላ አጣሪ ኮሚቴ የምናቋቁመው?” ስትለው ልጅት በኃፍረት ዞሮ አያት። ኃፍረቱን ለመጋራት ይመስላል ፌስቡክ ላይ ያነበብኩት ነው ብሎ ወዳጁ፣ ‹‹በመስኖ የበቀለች የፋፋች ስንዴ ደቃቅ የሆነችውን ጤፍ ዓይታ ‘አሁን እዚህ ውስጥ እህል አለ?’ ብትላት፣ ‘ሁላችንም ስንፈጭ ዱቄት ነን’ አለቻት…›› ብሎ አስቀየሰለት። የዘመኑ ሰው ግን የራሱ አልበቃ ብሎት ስንዴና ጤፍ መሀል እሳት ሲለኩስ ምን ይባላል? የለኳሾች ዘመን ሆነ እኮ እናንተ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሾፌራችን ባለቀ ሰዓት ወሬያችን ሰልችቶት ይሁን የዓመሉ ሰዓት ደርሳበት፣ እሱም እኛም የማንሰማውን ‘ራፕ’ ከፍቶ ጆሯችንን ያደነቁረው ጀመር፡፡ ‹‹እባክህ ቀነስ አድርገው በለው። ገንዘባችን መቀለጃ የሆነው አንሶ በጆሯችን ልትቀልዱ ትፈልጋላችሁ ደግሞ?›› ጎልማሳው ይንጣጣል። ሾፌሩ ባልሰማ ያሽከረክራል። ‹‹ለምን ይቀነሳል፣ አሁን ማን ይሙት ከዘንድሮ ቅጥፈት ‘ራፕ’ ቢያደነቁረን አይሻልም?›› መጨረሻ ወንበር ጅንኑ ተሳፋሪ ተራውን ይጮሃል። ከጎኑ የተቀመጠችው፣ ‹‹ይቅርታ ቅጥፈት የድሮና የዘንድሮ ተብሎ አልተለየም፡፡ ቅጥፈት ያው ቅጥፈት ስለሆነ እየተስተዋለ…›› ትለዋለች። እሷን ቢሰማም እንዳልሰማ ሆኖ ጎልማሳው ዘፈኑን ለማስቀነስ ይነታረካል። በ‘ቀንስ! አትቀንስ!’ ንትርክ ታክሲያችን ታመሰች። ‹‹ኧረ ተው ዘመኑን የአምባገነኖች መፈንጫ አታስመስሉት…›› ሲሉ አዛውንቷ ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹አይቀነስ የምትሉ እጃችሁን አውጡ…›› ይላል። አዛውንቷ የሕፃናት ድራማ በሚመስለው የቅጥፈት ትዕይንት ይደነቃሉ። ወዲያው ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆመች። ወያላው እየተንጠራራ ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን የቅጥፈት ጉዳይ ውስጣችንን እያሳመመው ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት