Thursday, June 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹የዘሩት ሲያፈራ››

የመጽሐፍ ዳሰሳ፡ በፕሮፌሰር አበበ ዘገዬ

የመጽሐፉ ርዕስ፡ የዘሩት ሲያፈራ

ጸሐፊ፡ አቶ ደመቀ ዘነበ

የታተመበት ዓመት፡ 2011 ዓ.ም.

የገጽ ብዛት፡ 176

አሳታሚ፡ ቢሹ አሳታሚ

‹‹የዘሩት ሲያፈራ›› በሚል ርዕስ የቀረበው የአቶ ደመቀ ዘነበ መጽሐፍ፣ በደርግ ዘመን የኩባ መንግሥት ለኢትዮጵያ ካደረገው አስተዋጽኦ ዋነኛውን ከትቦ በሚያምር አቀራረብና ትውስታን ባዘለ አገላለጽ ለአንባቢያን አቅርቦልናል፡፡ ይህ መጽሐፍ በዋነኛነት የኩባ መንግሥት ለኢትዮጵያ ያደረገውን ድጋፍ የሚገልጽ፣ በዘመኑ በኩባ የተማሩ ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን የአገር ፍቅር፣ ዘመናዊና ቅምጥል ኑሮ ሳያማልላቸው ወደአገራቸው ተመልሰው ያደረጉትን ወገናዊ አስተዋጽኦ በብዙው ይነግረናል፡፡

‹‹የዘሩት ሲያፈራ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የኩባ መንግሥት ዕድሚያቸው ከ9 እስከ 16 ዓመት የነበሩ ልጆችን ከኢትዮጵያ በመውሰድ እንደ እናትና አባት ተንከባክቦ አስተምሮ ለቁምነገር ማድረሱ ታሪክ የማይረሳው ውለታ መሆንኑ መጭው ትውልድ እንዲረዳ ይህ መጽሐፍ የበኩሉን ኃላፊነት ተወጥቷል፡፡ በውጭ አገር ተምሮ ወደ እናት አገር ተመልሶ አገራዊ ግዴታን መወጣት ከቀድሞ የኩባ ተማሪዎች የምንማረው ትልቅ የዜግነት ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ መጽሐፍ ከታሪክ ማስታወሻነት አልፎ የአሁኑና የመጭው ዘመን ዳያስፖራን ወደ አገር ተመልሶ አገርን ማሳደግ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ፋይዳ ያሳያል፡፡

የመጽሐፉ ጭብጥ ግለ ታሪክ (ማስታወሻ) ሲሆን በ17 አነስተኛ ምዕራፎች የተከፋፈለና የሕይወት ዘመን ትዝታ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ጸሐፊው አቶ ደመቀ ዘነበ በመምህርነት ሙያ በኩባ በነበሩበት ወቅት በሥራ ስለነበራቸው ተሳትፎ፣ ስለኢትዮጵያውያን የኩባ ተማሪዎች፣ ስለኢትዮ-ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና ወታደራዊ ድጋፍ ውለታ አሻራ ይዘክራል፡፡

ግለ ታሪኩ ለትውልድ የሚጠቅም መሆኑን በማመን ተዳፍኖ እንዳይቀርም በጽሑፍ ለማስተላለፍ መፈለጋቸውን የጫረባቸውን ቁጭት ያመላክታሉ፡፡ የመጽሐፍ ዳሰሳው ዓላማም ይህንኑ እሳቤ ለማጠናከርና አንባቢው ተገቢውን ቁም ነገር እንዲቀስምበት ለማበረታታት ጭምር ነው፡፡ 

ደራሲው በተወለዱበት የወሎዋ ደሴ ከተማ ከቄስ ትምህርት ፊደል ጥናትና ግብረ ገብነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት መዝለቅና በመምህርነት ሙያ ተሠማርተው አገራቸውን ማገልገላቸውን በመጽሐፋቸው ያወሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ስሙ ጎልቶ ከሚነገርለት የወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት ካፈራቸው ተማሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡ ቀጥለውም በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋ መምህር ሆነው እያስተማሩ ሳለ በተካሄደው የሥርዓት ለውጥ ምክንያት ሥራቸውን ለመልቀቅ ጫና እንዳሳደረባቸው ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም በአንድ ወቅት የኩባ መንግሥት ባመቻቸው ዕድል ወደ ኩባ ሄደው እንዲማሩ የተመለመሉትን አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ተማሪዎች ይዘው በሚወዱት የማስተማር ሙያ እንዲሳተፉ ከደርግ መንግሥት ጥሪ ተቀብለው ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ በዚያ ስለነበሩ የኩባ ተማሪዎችና መምህራን ማኅበራዊ ትስስርና ውጣ ውረድ፣ በሶማሊያ ወረራ ወቅት መስዕዋትነት ስለከፈሉት የኩባ ወታደሮች ያልተቆጠበ ውለታ በሰፊው ያልተነገረው ታሪክ እንዲሁም የሕይወት ልምዳቸውን በማስታወሻ ያሰፈሩትን በመጽሐፋቸው አካፍለዋል፡፡

መጽሐፉ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ለማያያዝ ጸሐፊው የተጠቀሙባቸው ለአብነት፡- ጦርነት፣ ስደት፣ ረሃብና ኋላ ቀርነት በአገር ኢኮኖሚ ያስከተለውን ተፅዕኖ በውጭ አገሮች ወዳጅ ፍለጋ ያስገድድ እንደነበርና የኩባ ወዳጅነትና ዕርዳታም የዚሁ አካል መሆኑ መዘንጋት የለበትም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

የመጽሐፉ ጠንካራ ጎኖች በቀላል አማርኛ መጠቀማቸውና በርካታ ተዛማጅ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች የተደገፈ መሆኑ በማናቸውም ዕድሜ ደረጃ ለሚገኝ አንባቢ ሳይሰለቸው በአዕምሮ ውስጥ እንዲቆይ ማድረጉ ነው፡፡ በተጨማሪም የተጠቀሙት ዋቢ መጻሕፍትና በወቅቱ የዘገቡት ጋዜጦች ሳቢና ከርዕሱ ጭብጥ ጋር የተጣጣሙ ናቸው፡፡

ምዕራፍ አንድ ከኢትዮጵያውያን ቀደምት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ታላቅነት ባሻገር በየጊዜው የተካሄዱ አሰልቺ ጦርነቶች ለአስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት መጋለጥ፣ ከመካከለኛው ዘመን የፖርቱጋል ድጋፍ እስከ ሶማሊያው ዚያድ ባሬ የዕብሪት ወረራ የኩባ ሶሻሊስት ወታደራዊ ድጋፍ በአጭሩ ያትታል፡፡ ምዕራፍ ሁለት ስለኩባና ሕዝቧ ታሪክ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ኢኮኖሚ እንዲሁም ቀደም ሲል ከስፔን ቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ እ.ኤ.አ. በ1898 የተደረገው የነፃነት ትግል ሒደት ወደ ብሔርተኝነት መሸጋገሩ ያስገኘው ውጤት፣ ከአሜሪካ አፍንጫ ሥር ስለተወለደው የኩባ አብዮተኞችና የነፃነት ታጋዮች ሆ ማርቲ፣ ፊደል ካስትሮና ቼ ጉቬራ ዓይነተኛ ሚና በሰፊው ይተርካል፡፡ ምዕራፍ ሦስት የኢትዮጵያና የኩባ ወዳጅነት፣ የባህል ትስስር መጠናከሩ በተለይም አምባሳደር ካሳ ከበደ (ዶ/ር) የሕፃናትና ጀግኖች አምባ በመልካም እሴት እንዲደራጅ በማድረግ በሶማሊያ ወረራ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት ወደ ማሳደጊያ አምባው እንዲገቡና በኋላም ተመልምለው ወደ ኩባ ጭምር እንደተላኩ የነበራቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ ዘርዘር አድርጎ ያስረዳል፡፡

ከምዕራብ ከአራት እስከ ስምንት ያለው የመጽሐፉ ይዘት በአጠቃላይ ወደ ኩባ አገር ለትምህርት የተላኩ ወጣት ተማሪዎችና መምህሮቻቸው የጉዞ ሁኔታ፣ ውጣ ውረድና ገጠመኞች፣ የኩባውን የሥራ ባህል እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ተማሪዎች ጋር መስተጋብር ምን እንደሚመስል በደምሳሳው የተመላከተበት ነው፡፡ ምዕራፍ ዘጠኝና አሥር በኩባ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ስለመደበኛ ትምህርት አሰጣጥ፣ የትምህርት ቤቶቹ ሥነ ሥርዓት፣ ንድፈ ሐሳብ፣ የሙያ ክህሎት፣ የሰውነት ማጎልመሻ፣ የእርሻ ትምህርት፣ ሁለገብ ዕውቀት፣ ወታደራዊ ሥልጠና፣ ባህልና ስፖርት ነክ እንቅስቃሴ ተሳትፎን ለአገራችን የሚኖረውን ፋይዳ ያስረዳል፡፡ ምዕራፍ አሥራ አንድ ደግሞ በምዕራፍ ዘጠኝ ከተብራራው ስፖርትና የባህል ነክ እንቅስቃሴ ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

ምዕራፍ አሥራ ሁለትና አሥራ ሦስት በኩባ ተማሪዎችና መምህራን ቆይታ በማኅበራዊ ግንኙነት ረገድ ያጋጠማቸው ያለመግባባት ውዝግቦችን በተለይም የቡድን መሪ የነበሩትን ኮሎኔል አሰፋ በርሔ ጊላይን አያያዝ እንዲሁም፣ ችግሮች እንዲስተካከሉ ለአምባሳደሩና ለሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በማሳወቅ ጭምር የተወሰዱ ዕርምጃዎችን በተመለከተ ያብራራል፡፡ ምዕራፍ አሥራ አራትና አሥራ አምስት የሊቀመንበር መንግሥቱ በኩባ ያልተጠበቀ ጉብኝት በተማሪዎችና መምህራን በሠራተኞችም መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲኖርና ችግሮች እንዳይቀጥሉ ስለማገዙ እንዲሁም መምህራኑ ተማሪዎችን እንደወላጅ ሆነው በማነፅና በመንከባከብ ተሰጧቸውን እንዲያጎለብቱ ያበረከቱትን ጉልህ አስተዋጽኦ ዕውቅና አሰጣጥ በሰፊው ይገልጻል፡፡

ምዕራፍ አሥራ ስድስት የቤተሰብ ሕይወት በተመለከተ እንዲሁም የኩባ ተማሪዎች የተዋጣላቸው ስፔሻሊስት ሐኪም ሆነው በኢትዮጵያ ዝነኛ ሆስፒታሎች እያበረከቱት ስላለው ድርሻ በምሳሌነት ጥቂቶቹን (እነ ዶክተር ሙሉዓለም ገሠሠ፣ ዶክተር መብራቱ ጀምበሬ፣ ዶክተር ሸዋዓለም ነጋሽ፣ ዶክተር ሥዩም ካሳ፣ ዶክተር ዓለማየሁ ተገኝ የመሳሰሉትን) ጠቅሶ ቀደም ሲል ሲነዛ የነበረውን የትምህርት ጥራት ችግር አሉባልታና ገጽታ ለመቀየር ይሞግታል፡፡

በመጨረሻው ምዕራፍ አሥራ ሰባት የመጽሐፉ ማገባደጃ ላይ ዋና ፍሬ ሐሳቡ የሚገኝበት ነው፡፡ በአጠቃላይ የኩባ መንግሥት ለኢትዮጵያ የዋለው ዘርፈ ብዙ ውለታ ይዘክራል፡፡ በኩባ የትምህርት ዕድል አማካይነት በልዩ ልዩ ሙያዎች የሠለጠኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ አገራቸው ተመልሰው ለማገልገል ቢፈልጉም፣ ለምሥራቁ የሶሽያሊስት ርዕዮተ ዓለም በነበረ የተዛባ አመለካከት የተነሳ ሥራ ሳይመደቡ መጉላላት ቢያጋጥማቸውም በአገር ፍቅር ሚዛን አርዓያነታቸውን በኩራት ይገልጻል፡፡ ለኩባ ተማሪዎች አሉታዊ ዕይታ ሊፈጠር የቻለው አገራችን በሰሜኑ የፀረ ተገንጣይ ጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት የሐኪሞች እጥረት በማጋጠሙ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ከኩባ በመጡ ተማሪዎች በተፈጠረ የሕክምና ስህተት ምክንያት መሆኑን ጸሐፊው በጽሑፋቸው አልሸሸጉም፡፡

መደምደሚያ

የደራሲ ደመቀ ዘነበ አበርክቶት በኢትዮጵያና ኩባ መካከል የነበረውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በተለይም በሶማሊያ ወረራ ወቅት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸው፣ የትምህርት ዕድል መመቻቸትና ተመልሰው አገራቸውን ለማገልገል ያሳዩት ፍላጎትና ሌሎችንም ዝርዝር ጉዳዮች ጠቃሚ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ መጽሐፉ ብዙ ያልተነገረላቸው ዕውቅ ስፔሻሊስት የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች የኩባ ተማሪዎች አባል መሆናቸውና በውጭዎች አገር ምቾት ሳይማለሉ ወደ አገራቸው ተመልሰው ማገልገላቸው ፈጽሞ እንዳይዘነጋ፣ ብሎም ያልተገባ ገጽታ እንዲለወጥ ጉልህ ሚና አለው፡፡

በአጠቃላይ የኩባን ያልተቆጠበ ውለታና የታሪክ አሻራ በአግባቡ ጎላ ብሎ አለመነገሩ የፈጠረባቸው ቁጭት ሌሎች ባልደረቦቻቸው በጽሑፍ ሳያስተላልፉ ማለፍ የሚፈጥረውን ስሜት ታሳቢ ማድረጋቸው ተገቢ ነው፡፡ ይህ የግለ ታሪክ ማስታወሻ በሁለቱ አገሮች ያጠነጠነ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ ታሪክ አጠናን የሚኖረው ድርሻ ቀላል አይሆንም፡፡ በተጨማሪም ይህ በኩባ የተማሩ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ተግባር ለአሁኑ የኢትዮጵያውያን ፍልሰት የሚያስተምረው ትልቅም ነገር አለ፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያሉ ዜጎችን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ይፈልሳሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ ኢትዮጵያውያን በዚህ መጽሐፍ ከተገለጸው የቀድሞ የኩባ ተማሪዎች አገር ወዳድነትና ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው ያበረከቱት አስተዋጽኦ አርዓያ ቢያደርጉ ለትውልድ አገራቸው የሚኖረው ፋይዳ ብዙ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻ [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles