ከሄዪ ኤሌሞ
የሶቪየት ኅብረት ከመፍረሱ በፊት አገሮች ባላቸው የፖለቲካ መሳሳብ ዓለም ጎራ በሁለት ምዕራባውያን (አሜሪካ፣ ምዕራብ አውሮፓና ተባባሪዎቻቸው)፣ ምሥራቅ ዘመም አገሮች (ሩሲያ፣ ቻይና፣ ምሥራቅ አውሮፓ፣ ኩባና ተባባሪዎቻቸው) ሲከፈል፣ ከእነዚህ ጎራ የወጡት ደግሞ ‹‹ሦስተኛው ዓለም›› በመባል ይከፋፈል ነበር፡፡ የሶቪየት ኅብረት መፍረሱን ተከትሎ፣ የዚህ ዓይነት አከፋፈልን በማስቀረት የዓለም ባንክ አገሮች በሚፈጥሩት ገቢ በሦስት ደረጃ ማለት ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ በማለት ይከፍላቸዋል፡፡ እኛም ይህንን በመከተል ለይስሙላም ቢሆን ዕቅድ አውጥተን መካከለኛ ደረጃ ደርሰዋል ከሚባሉት አገሮች ተርታ ለመድረስ ስንጥር ነበር፡፡ የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተንተርሶ ያወጣው አከፋፈል ትክክል ቢሆንም፣ በተጨባጭ ለሚመለከተው ግን ከዓለም አገሮች ቁጥር ሲታይ፣ የዓለም ባንክ አገሮችን የከፈላቸው በጥቅሉ በመሆኑ፣ በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉት አገሮች ያሉበትን ደረጃ በደንብ አይገልጽም፡፡ ምክንያቱም ቢባል የየአገሮቹ ነባሪ ሁኔታ የተራራቀ ስለሆነ በዚህ ሁኔታ በጥቅል ማሰቀመጡ ሁኔታውን አያሳይም፡፡ ብዙ ጸሐፍት አገሮችን በተለያዩ መሥፈርቶች በማስቀመጥ ደረጃ ለማውጣት እየሞከሩ ነው ያሉት፡፡
በዝቅተኛ ደረጃ ብሎ በጥቅሉ መክፈሉ እኔን አያረካኝም፡፡ ከእነዚህ አገሮች በጥሩ ዕድገት ያሉ አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወደ መጥፋት ወይም እየጠፉ ያሉ አገሮች አሉ፡፡ ይህንን ከግንዛቤ በመክተት አገሮችን ባላቸው የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ ዕድገትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በጥቅሉ በስድስት ደረጃ ሊከፈሉ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንደኛ ደረጃ የሚቀመጠው አሁንም ቢሆን አሜሪካ ሲሆን፣ በሁለተኛነት ቻይና ስትመጣ፣ በሦስተኛነት ደግሞ አንድ አምስት የሚሆኑት የአውሮፓ አገሮች እነ ጃፓን፣ ሩሲያና ህንድ የተካተቱበት ይሆናሉ፡፡ የተቀሩት አገሮች ከአራት እስከ ሰድስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ እነሱም፣ በአራተኛ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አገሮች ማለትም የሕዝባቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ያሟሉ ሲሆኑ፣ በአምስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሕዝቡ መሠረታዊ ፍላጎት ካለመሟላቱም በተጨማሪ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካ ችግር ያልተቀረፉባቸው አምባገነን መንግሥት በቀላሉ የሚሰፍርባቸውና በስድስተኛ ደረጃ ከአገርነት ወርደው በመበታተን የእርስ በርስ ጦርነት የሚካሄድባቸው (ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ወዘተ.) ናቸው፡፡
እኔ ላተኩር የፈለግሁት፣ ከዓለም ደረጃ በአምስተኛ ያስቀመጥኳት በመኖርና ባለመኖር እየተወዛወዘች ያለችውን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋርም በርካታ የአፍሪካ አገሮች ይጨመራሉ፡፡ የእነዚህ አገሮች መገለጫ አብዛኛው ሕዝባቸው በምግብ፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ዕጦት የሚሰቃይ፣ በድህነት ኑሮውን የሚገፋ፣ ባልተረጋጋ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖር የመንግሥት ለውጥ በጡንቻ የሚሆን፣ ወዘተ. ነው፡፡ በተጨማሪም በእነዚህ አገሮች ውስጥ ሰላምና ዴሞክራሲ የሌለ በመሆኑ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በብሔርና በጎሳ በመለያየት ሸርተት ብለው በቀላሉ ወደ ስድስተኛው መደብ ጎራ በመሄድ ከአገርነት ወርደው ወደ መበታተን ሊሄዱ ይችላሉ፡፡
የሚያሳዝነው አገራችን ሦስት ሺሕ ዓመት የሚቆጠር ሥርወ መንግሥት እንዳላት ሳትሆን፣ በአሁኑ ጊዜ መንግሥቷ ይቀጥላል ወይስ አገሪቱ ትፈራርሳለች የሚለው ቢሆነኝ፣ የየዕለቱ መወያያ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል፡፡ አንዱ ማሳያ አገራችንን ባለፈው የሰሜኑ ጦርነት አሜሪካ ኢትዮጵያን አገኘኋት ብላ፣ በእሷ ፊታውራሪነት ወደ መበታተን ልትለን ስትል ሕዝቡና የመከላከያ ሠራዊቱ፣ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ አገሪቷን ከአንበሳ አፍ ሥጋ እንደመንጠቅ በሚመስል መሠረት በማዳን፣ ሙከራውን አክሽፎበታል፡፡ ይህ መክሸፉ ብቻ ግን ዘላቂ አይሆንም፡፡ ሰላም የሚያደፈርሱ የፖለቲካ ችግሮች ካሉ ዕድገት ቢመጣም፣ በማዕበል በሚጠቃ ባህር ዳር አጠገብ ቤት እንደ ተገነባ ሆኖ ይጠፋል፡፡ ይኼንንም ለማየት ከአሥር ዓመት በፊት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ እያደገች እንደነበረች ዓለም የመሰከረው ነው፡፡ ይኼንን ግን የሰሜኑ ጦርነት መጥቶ ወደ ኋላ ጎተተው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ሰላሙን ከዕድገት ጋራ ለማስቀጠል ኢትዮጵያን ለመበታተን አደጋ የሆኑትን ምክንያቶች ከእነ ምንጫቸው በቶሎ አድርቆ፣ ሰላም በመፍጠር ወደ ልማት በመሄድ አስተማማኝ አገር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
በአገራችን ውስጥ ለሰላምና ለዕድገት እጦት፣ ብዙ ችግሮች አሉ ብንልም፣ በዋናነት በአሁኑ ጊዜ የሚጠቀሱት ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ‹‹የእኔ ብሔር›› በማለት ‹‹የእኔነት›› ጥያቄ የሚያነሱና ‹‹አንድ የፖለቲካ ሥርዓት›› ዘርግቶ አገሪቷን መምራት ያልቻለው መንግሥት ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ከፈታንና ካስተካከልን ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ የተለያየ ጥያቄ ‹‹የእኔ ብሔር›› ብለው የሚያነሱ ቢኖሩም፣ በአሁኑ ጊዜ ለአገሪቷ አለመረጋጋት ብቸኛ አደገኛ ሆነው የቀረቡት የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው፣ የኦሮሚያ ክልል ያለችው መሀል አገር ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ጽንፈኞች ኦሮሚያ ከተካለለቻቸው ክልሎች ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ይህም የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቷ ላይ ለመቀስቀስ በር ይከፍታል፡፡ ይኼንን በመመልከት ነው፣ አንዳንድ ፖለቲከኞች በኦሮሚያ ያለው የሰላም መደፍረስ ከቀጠለ፣ ውጤቱ ከሰሜኑም ጦርነት የከፋ ይሆናል የሚሉት፡፡ በዚህ ብቻ ሳይቆም፣ የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞች የሰይጣናዊ ተልዕኮ ተሳክቶላቸው ኦሮሚያን ቢያስገነጥሉ ዞር ብለው ኦሮሚያን በአስከፊ ጦርነት እርስ በርስ ሸዋን፣ ወለጋን፣ ባሌን፣ አርሲን፣ ሐረርን ወዘተ. ወደ መንደርነት በመማገድ የጎበዝ አለቆች መፈንጫ ያደርጓታል፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹ሌቦች ሲሰርቁ ይስማማሉ፣ ሲከፋፈሉ ይጣላሉ›› እንደሚባለው የብዙ ነፃ አውጪ ድርጅቶች የመጨረሻ እጣ ፈንታ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንን፣ አንጎላን ወዘተ. ያየዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ግምቶችን በመውሰድ ለኢትዮጵያና ለራሷም ኦሮሚያ ሰላም መሆን፣ የግድ ጽንፈኞቹን ማስቆም አስፈላጊ ነው፡፡
ስለዚህ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ከአሁን ወዲያ በቃ ብሎ ለአገሪቷ ሰላምና ልማት አስቸጋሪ የሆኑትን የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞችን አንድ ነገር ማድረግ አለበት፡፡ ቢቻል ወደ ሰላም ማምጣት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን አለበት፡፡ ከጽንፈኛ ብሔርተኞች ጋራ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ሰላም ማምጣት አዳጋች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይኼንንም የሰሜኑ ብሔርተኞች አስተምረውናል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሰላም ይለቅ ሲባሉ፣ ጽንፈኛ ብሔርተኞቹ አሻፈረኝ ብለው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሞትና ስደት ምክንያት ሆነዋል፡፡
ከኦሮሞ ጽንፈኞች ጋራ ሰላምን በውይይት ብቻ ለማምጣት አዳጋች የሚያደርገው ጽንፈኞቹ ከአርባ፣ ሃምሳ ዓመት በፊት የያዙትን አጀንዳ የአሁኑን ነባራዊ ሁኔታ ተመልክተው ባለመቀየራቸው ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ትዝ ከሚለኝ፣ ከአርባ ዓመት በፊት በአውሮፓ በትምህርት ቤት እያለን ተሰባስበን ስንጫወት ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ደጋፊ ነኝ›› የሚል ጓደኛችን ‹‹በአዲስ አበባ የገነባችሁት ቤት፣ በኦሮሞ አገርና ድንጋይ ስለሆነ፣ መንግሥት ስንይዝ ታስረክቡናላችሁ›› ብሎ ሲናገር በአግርሞት ጮክ ብለን ሳቅን፡፡ ይኼንን አስተሳሰብ የሚመስል በዚያን ሰሞን አንደኛው ጽንፈኛ ‹‹የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ)›› ከመንግሥት ጋራ የምንነጋገረው አዲስ አበባ የኦሮሚያ መሆኗን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው ብሎ መግለጫ ሲሰጥ፣ እንደዚያኔው ወጣትነቴ ባያስቀኝም እንዴት ከተቸነከሩበት ፈቀቅ እንዳላሉ በመስማቴ ብዙ ችግር እንዳለብን በመገንዘብ ሐዘኔ የላቀ ሆነ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰላምን ለማምጣት ሌላው ችግር፣ በኦሮሞ ስም በሰላማዊና በትጥቅ የሚታገሉ ብዙ ስብስቦች መኖራቸው ነው፡፡ በእነዚህ ድርጅቶች መካከልም ልዩነታቸው፣ ዓላማቸው፣ ግባቸው፣ ወዘተ. በግልጽ የተቀመጠ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞም ሕዝብ ግራ ተጋብቷል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የኦሮሞ ሕዝብ ያነሳቸው ነበር የሚባሉ ጥያቄዎችን በአሁኑ ጊዜ ስንመረምራቸው ማለትም ኦሮሞ ራሱን ማስተዳደር አለበት ማለት ከሆነ፣ ራሱን ከማስተዳደር በላይ ኢትዮጵያንም እያስተዳደረ ነው፡፡ ኦሮሞ በቋንቋው መጠቀም አለበት ከሆነ፣ እንዲያውም የኦሮሞ ወጣት፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋራ እንዳይግባባ፣ ተከልክሎ በኦሮምኛ ብቻ እንዲናገር ሆኗል፡፡ የኦሮሞ ባህል፣ ወግ፣ አልተስፋፋም ከሆነ፣ በአሁኑ ጊዜ ከኦሮሚያ አልፎ በሌላው ኅብረተሰብ ላይ መጫን ነው የሚስተዋለው፡፡ እንግዲህ ሌላ የተደበቀ ጥያቄ ከሌለ በአንድ ብዙ ብሔሮች ባሉባት አገር ውስጥ የተለየ የአንድ ብሔር ጥያቄ በኦሮሚያ በኩል ተነጥሎ የሚነሳ አለ ብሎ አብዛኛው ሕዝብ አያምንም፡፡ ይኼም ቢሆን ያልተመለሰ ጥያቄ የለም ብለን ብቻ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን የኦሮሚያ ብሔርተኞች ቤታችሁ ግቡ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ‹‹ፖለቲከኞች፣ ከፖለቲካ ተገለሉ ሲባሉ አንገለልም፣ ከዚያ ውጭማ ለመኖር አንችልም፤›› ነው የሚሉት፡፡ በዚህም ምክንያት ወይም አዲስ አጀንዳ ይፈጥራሉ፡፡ ወይም የተመለሰውን እነሱ ተጠቃሚ እስካልሆኑ ድረስ ይክዳሉ፡፡ ስለዚህም ሊሆን ይችላል ብዙዎቹ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች በመመለሳቸው የኦሮሚያ ብሔርተኞች አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ አገር የሚያምሱት፡፡ ከነዚህም ውስጥ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት፣ የምትተዳደረውም በኦሮሚያ ሥር ነው፣ በአዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያ መዝሙር ይዘመር፣ የኦሮሚያ ባንዲራም በየትምህርት ቤቶች ይሰቀል፣ የአዲስ አበባ የሥራ ቋንቋ ኦሮምኛ መሆን አለበት፣ የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ አቋቁመን ፓትርያርክና ጳጳሶች እንሾማለን፣ ኦሮሚያ አቃፊ በመሆኗ የተቀሩት ኢትዮጵያውያን ከተቀበሉ፣ በእኛ መሪነት አብረን ልንኖር እንችላለን፣ ካለበለዚያ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ እንመሠርታለን የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የኦሮሚያ ብሔርተኞች አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ፣ ኢትዮጵያን የመበጥበጥ ተግባር ተጧጥፎ የመጣውን ለማሳየት ሰሞኑን የኢትዮጵያ እሴት በሆኑት ‹‹ምኒልክ- ዓድዋና ኦርቶዶክስ ሃይማኖት›› ላይ ያደረጉትን ልናነሳ እንችላለን፡፡ አፄ ምኒልክ የዓድዋን ዘመቻ ባያዙ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ በጣሊያን አስተዳደር ትሆን ነበር፡፡ ውጤቱም እኛ ባህላችንም፣ ቋንቋችንም፣ ባንዲራችንም ወዘተ. ይቀየር ነበር፡፡ ሄዪ፣ ኤሌሞ፣ ጠንክር፣ አደፍርስ፣ ሙስጠፋ፣ ኬሎ ወዘተ. ብለን አሁን የምንጠቀምባቸው የአገራችን ስሞች ሳይኖሩ ሮኮ፣ ቹሊ፣ ሊቻኖ ወዘተ. እያልን እንጠራ ነበር፡፡ ዛሬ የምንኮራበት ቋንቋችን አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ ወዘተ. ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ጣልያንኛ ይሆን ነበር፡፡ ለዋቢነት የማቀርበው ቅኝ የተገዙ አገሮችን ነው፡፡ የእኛም አዝማሪ ምኒልክ ባያሸንፍ ‹‹አበሻ ለጣሊያን የሚገብረው ዕንቁላል ነበር፤›› ያላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ምኒልክ ከነገሡ አሥር ዓመት ያልዘለለው በመሆኑ፣ በመላ ኢትዮጵያ ከሚገኙ የሥልጣን ተቀናቃኞች ጋራ ቁርሾ እንዳለባቸው ዕሙን ነው፡፡ ምኒልክ ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ባንዳ ሳይፈጠር፣ ሁሉም ማለትም አማራን፣ ትግሬን፣ ኦሮሞን፣ ሶማሌን፣ ወላይታን፣ ጉራጌን፣ አፋርን፣ ሲዳማን፣ ቤኒሻንጉልን፣ ጋምቤላን ወዘተ. አሰባስበው ሁሉም ደማቸውን በዓድዋ አፍስሰው፣ ዛሬ ያለችውን ብቸኛ በቅኝ ግዛት ያልተገዛችውን ለጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያን አቆይተውልናል፡፡ እንግዲህ ዛሬ ምኒልክን የምትጠሉ ለምን ቋንቋችንን፣ ባህላችንን፣ ኢሬቻን ወዘተ. ሳይበላሽ አስቀመጡልን ብላችሁ ነው፣ ወላጆቻችሁ ዓድዋ ድረስ ሄደው ለኢትዮጵያ አገር ደማቸውን ያፈሰሱት በከንቱ ነው ብላችሁ ነው፡፡ እውነተኛ ለባህል፣ ለቋንቋ፣ ወዘተ. የምትታገሉ ከሆነ፣ ይኼንን የምትሉትን ባህልም ሆነ ቋንቋ ተጠብቆ እንዲቀመጥ ያስቻሉት በዋነኛነት ምኒልክ ናቸው፡፡ ብንታደል ኖሮ ምኒልክን ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ በላይ ብሔርተኞች ምኒልክን ማክበር ነበረባችሁ እንጂ ሌላውን ሰላማዊ ሕዝብ ለማወክ የመታገያ አጀንዳ ባልፈጠራችሁ ነበር፡፡
ሌላው ከዓድዋ በዓል ጋራ ብሔርተኞች የማይወዱት በጊዮርጊስ የምኒልክ ሐውልት ባለበት ቦታ ማክበርን ነው፡፡ የምኒልክ ሐውልት በጊዮርጊስ የተቀመጠው ታስቦበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም አገሪቷ ውስጥ ችግር ሲመጣ እንደምታደርገው ዓድዋ ላይ ታቦት ይዛ፣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተዋግታለች፡፡ ውጊያውም ተካሄዶ ጣሊያን የተሸነፈው በጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያኑ እምነትም ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ተዋግቷል ተብሎ ይታመናል፡፡ እነዚህን ለመዘከር፣ የድል አድራጊው ምኒልክ ሐውልት በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንዲቆም ተደረገ፡፡ ጊዮርጊስንም ለማመስገን በዓመት ዓመት ታቦት እንዲወጣ ተደረገ፡፡
እንግዲህ ኢትዮጵያውያን ምኒልክና ጊዮርጊስን ለማስታወስ፣ በዓመት ዓመት ወደዚህ ቦታ እየሄዱ ያከብራሉ፡፡ መንግሥት ይኼንን ቦታ ለመቀየር እንደሚፈልግ ግልጽ ምልክቶች አሉ፡፡ ከንቱ ልፋት ነው፡፡ ከሃይማኖትም ጋራ መላተም ነው፡፡ ዘንድሮ መከላከያ እንዲያዘጋጀው ተብሎ የበዓሉን ድባብ ለመቀየር ተሞክሯል፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ በዓልን በፈለገ ቦታ ማለትም በሠፈሩ በአካባቢው፣ መንግሥት በሚያዘጋጀው አደባባይ ወዘተ. በዚህ ብቻ ሊባል አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ የድል በዓልን ነው የምታከብረው፡፡ ሁሌም በነበሩ ጦርነቶች የመከላከያ ሠራዊቱ ደሙን ከፍሎ ነው ድል የመጣው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ድሎች የመከላከያ ሠራዊቱ አንድ ቀን በዓመት በዓል ማክበሩ አይበዛበትም፡፡ የዓድዋ ድልን ቀን መምረጡ የሚያመሰግነው ነው፡፡ ይኼንን ለፖለቲካ ጨዋታ የምኒልክን ክብረ በዓል ለማደብዘዝ ግን መጠቀም የለበትም፡፡ ሁሉንም ባቀናጀ መልኩ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ለምሳሌም የካቲት 23 ቀን ጠዋት (ከሰዓት በፊት) በምኒልክ አደባባይ ሕዝቡ ምኒልክንና ጊዮርጊስን በተቀናጀ ሁኔታ በሚፈልገው ዓይነት በደማቅ ካከበረ በኋላ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ዘንድሮ እንደተደረገው፣ የመከላከያን ጥንካሬ ማሳየት፣ ለምኒልክም ለሕዝቡም ክብር ነው፡፡ ይኼንን ጉዳይ ከመዝጋቴ በፊት የደኅንነት አካላት ዘንድሮ በጊዮርጊስና በምኒልክ ሐውልት ሊያከብሩ የወጡትን ወጣቶች፣ ከሕግ በላይ ዕርምጃ መውሰድ ትክክል ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው ሳልል አላልፍም፡፡ ከምኒልክ አደባባይም አልፎ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብተው አስለቃሽ ጢስ መተኮስ ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ነው፡፡ የሃይማኖት ሥፍራዎች የሰላም ቦታ ናቸው፡፡ የጦር መሣሪያ ሊገባም፣ ሊተኮስም አይገባም፡፡ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አጥፊ፣ ባጠፋው ምክንያት በግፍ እንዳይቀጣ ዘሎ ቤተ ክርስቲያን በመግባት ይማፀናል፡፡ ሹሙም ሆነ፣ ጉልበት ያለው፣ በተቀደሰ ቦታ በቤተ ክርስቲያን ምንም አይሠራም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይኼንን ታስከብራለች፡፡ መንግሥት ሰሞኑን የሰብዓዊ መብትን ጥሰው ይኼንን ዕርምጃ የወሰዱትን ወደ ሕግ ማቅረብ አለበት፡፡ ይኼንኑም ለሕዝቡ ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ብሔርተኞች ከላይ ያየነውን አዳዲስ አጀንዳ እየፈጠሩ፣ ሕዝቡን ያምሳሉ እንደሚባለው ሁሉ፣ በሌላ በኩል የኦሮሚያ ብሔርተኞች የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች የሏቸውም፣ ሁሉም ሥልጣን ስለሚፈልጉ ነው በኦሮሚያ ስም ሕዝቡን የሚያስጫርሱት የሚሉም አሉ፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ለፕሬዚዳንት የተዘጋጀው አንድ ወንበር ነው እንደሚባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩም ወንበር አንድ ነው፡፡ እሱንም የኦሮሚያው ዓብይ (ዶ/ር) ተቀምጠውበታል፡፡ ሌላም የቀድሞ ጽንፈኞችም ትግላቸውን ትተው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ኦሮሞን በመወከል ሥልጣን ይዘው ይገኛሉ፡፡ እኛም ይድረሰን ከሆነ እንዳለመታደል ሆኖ ሥልጣን በውክልና የሚያዝ ከሆነ፣ ከክልሉና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ በሰላም ተደራድሮ መውሰድ ነው እንጂ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የሚታመሱበት ምክንያት የለም፡፡
ኢትዮጵያን ሰላም ያሳጡት የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ብቻ ሳይሆኑ እነሱን በኅቡዕ የሚደግፉ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ባሉ ልዩ ልዩ ቦታዎች የተሰገሰጉ የኦሮሞና የብልፅግና ባለሥልጣናት ናቸው ተብሎ ይተቻል፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ናቸው ለጽንፈኞቹ ታማኝነታቸውን ለመግለጽ፣ ሰሞኑን በተከሰቱት በአዲስ አበባ፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በምኒልክ ዓድዋ ችግር መሪ ሆነው እሳት የለኮሱት፡፡ ይኼንንም ማሳያ በማቅረብ ነው በአንዳንድ ተቺዎች ብልፅግና ራሱ ይጭርና የሕዝቡ ተቃውሞ ሲነሳበት ራሱ ያጠፋዋል በማለት የሚገለጸው፡፡ ይህም የኦሮሞ የብልፅግና ባለሥልጣናት፣ የቤተ ክርስቲያንን ችግር አባባሱ፣ ሕዝቡም ለሃይማኖቴ እሞታለሁ ሲል፣ አስታራቂ ሆነው ቀረቡ የሚባለው፡፡
እዚህ ላይ ብልፅግናን በምንልበት ጊዜ በሁለት ማለትም የክልሉና የፌዴራል ብለን መለየት አለብን፡፡ የክልሉ ብልፅግና ብቸኛው ተመራጭ ሆኖ ክልሉን ከማስተዳደሩም በላይ፣ በአገሪቷ የኦሮሞ ሕዝብ ወኪልና ጠበቃ ነኝ በማለት ራሱን ሾሞ ይንቀሳቀሳል፡፡ ፌዴራል እንደ ስሙ ጠቅላላ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር ቢሆንም፣ በክልሉ ውስጥ የሚደረጉትን ሕገወጥ ድርጊቶች የማስቆም ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ ተሰጥቶታል፡፡
ክልሉን የሚያስተዳድረው የብልፅግና ቡድን፣ በክልሉም ሆነ በውጭ ሆነው የኦሮሞ አጀንዳ ይዘናል ብለው ለሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞቹ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ በፌዴራሉ ውስጥ ኦሮሞ አውራ ብሔር ሆኖ መውጣት አለበት ብሎ ይታገላል በማለት ብዙዎች ይተቹታል፡፡ ከሚተችባቸውም ውስጥ፣
- በጭፍኑ ‹‹የኦሮም ጠል ነህ›› በማለት የዜጋውን መብት ይጋፋል፣
- የአዲስ አበባ አስተዳደርን በመቆጣጠር፣ የኦሮሞን አጀንዳ በአዲስ አበባ ያስፋፋል፣
- የአዲስ አበባ ከተማን ቦታዎች ለራሱና ለሚፈልጋቸው በመስጠት ይቸበችባል፣
- የኦሮሞን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ ፖሊሶች በአዲሰ አበባ በማሰማራት፣ ሰው ያፍናል፣ በዚህም የአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የሰላም ሥጋት ይፈጥራል፣
- ከአዲስ አበባ በማፈን ኦሮሚያ ክልል ወስዶ ይዶላል፣
- የፌዴራል ሕግን በመጣስ፣ በማንአለብኝነት ይንቀሳቀሳል፣
- በኦሮሚያ የሚገኙ ጽንፈኛ ብሔርተኞችን ለማግባባት፣ የእነሱን አጀንዳ በማምጣት፣ ለማስፈጸም ይሠራል፣
- ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ውጪ ያሉትን የኢትዮጵያ ዜጎች፣ በክልሉ ውስጥ ጽንፈኞች ሲያርዱ፣ ሲያፈናቅሉ፣ ሕገ መንግሥቱን አያስከብርላቸውም፣
- በክልሉ ውስጥ ለሚጣሱ ሰብዓዊ መብቶች ግድ የለውም፣ በዝምታ ይመለከታል፣
- የክልሉ ልዩ ኃይል አድሎ ሲያደርግና ከኦሮሞ ኅብረተሰብ ውጪ ያለው ዜጋ ሲጠቃ ከለላ አያደርግም፣
- የመከላከያ ሠራዊት ሕዝቡን ሊያድን ሲሄድ፣ ከወረዳ እስከ ላይ ያሉ የክልሉ የብልፅግና ሰዎች፣ ሠራዊቱ መጣ ብለው ጽንፈኞች ዞር እንዲሉ በማድረግ፣ የመከላከያን ሥራ ያጨናግፋሉ፣ ወዘተ. የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በኦሮሚያ ያለውን ሰቆቃ የፌዴራል መንግሥቱ ይፈተዋል ተብሎ ሲጠበቅ፣ በፌዴራል ደረጃ ያሉት የኦሮሞ ብልፅግና አባላት፣ የኦሮሞ ጽንፈኞች የያዙትን አጀንዳ በመልበስ፣ መንግሥቱን በማሽመድመድ ‹‹ተረኛ መንግሥት›› የሚል ስም እንዲሰጠው አስደረጉ፣ በኦሮሚያም ዜጎች እንዲገደሉና የሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ፣ አስደረጉ፡፡ በጥቅሉ የፌዴራል መንግሥቱ ቆሞ ተመልካች ሆኗል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ተቺዎች የፌዴራል መንግሥቱን የሚተቹት ያለምክንያት አይደለም፡፡ የአሁን የዓብይ መንግሥት ሲመጣ የአገሪቷን ችግር ይፈታል በማለት ከፍተኛ እምነት አሳድረው ነበር፡፡ ይኼም እምነት የመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ የንግግራቸውም ጭብጥ በጥቅሉ ‹‹ቀድሞ የተሄደበት የብሔርተኛ መንገድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ስለሆነ፣ የዜጋ ፖለቲካ አመጣለሁ›› የሚል ስለነበር ነው፡፡ ይኼንንም ንግግር የሰማ በኢትዮጵያዊነቱ ሲሸማቀቅ የነበረው ሕዝቡ ሆ! ብሎ ከመደገፉም በላይ፣ በእሳቸው ላይ የተቃጣባቸውን አመፅ በመመከት ሕይወቱን በመክፈል አድኗቸዋል፡፡ ይኼ እምነት ግን በአሁኑ ጊዜ ‹‹ዓብይ ከብሔርተኞች ጋራ ይሞዳሞዳሉ፣ ቃላቸውንም በተግባር አያሳዩም ወዘተ.፤›› በሚል ተሸርሽሮ እንዳለ ምልክቶች አሉ፡፡ ይኼም የሆነበት፣ ዓብይ ራሳቸው የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ በመሆናቸውና በሚመሩት መንግሥትም የኦሕዴድ መሪ ስለሆኑ ‹‹ላሟ እሳት ወለደች፣ ጥጃዋን እንዳትልሳት አቃጠላት፣ እንዳትተዋት ልጇ ሆነች፤›› እንደሚባለው በኦሮሞ አካባቢ ለሚደርሰው ሰቆቃ እንዳላየ ያልፉታል ተብለው ይታማሉ፡፡ ለዚህም በአዲስ አበባ ላይ ለተነሳው፣ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ መንግሥት ያሳየው ጣልቃ ገብነት እንደማሳያ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በተጨማሪም፣ የዓብይን አካሄድ ‹‹አንድ የፖለቲካ ሥርዓት›› የሌለው እንዳመቺነቱ ከሁሉም ጋራ የሚያጣቅስ፣ ሥልጣኑን ለማራዘም ብቻ የሚሠራ አድርገው የሚመለከቱ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡
ከዚያም ከዚህ የሚነሱትን ወሬዎቹን ትተን፣ ዓብይ በአሁኑ ጊዜ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥተው በኦሮሚያ ያለውን ችግር በኢትዮጵያዊነት መፍታት አለባቸው፡፡ ይኼንን ለማድረግ ሳይውል ሳያድር በመጀመርያ ቀን በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር ተሞርኩዘው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የወደፊቷን የኢትዮጵያን ስትራቴጂ የሚያሳይ ጽሑፍ ከእነ የሥራ አፈጻጸም ሰሌዳ በማቅረብ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኞች ቦታ እንደሌላቸው፣ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች አገር እንደሆነች ግልጽ ማድረግ አለባቸው፡፡ ለማስታወስ ያህል በዚያን ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ንግግር ሕዝቡ የተረዳው በኢትዮጵያ
- ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት አገር፣
- ማንኛውም ዜጋ የሚፈልገውን ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህል የሚያከብርባት፣
- ዜጎች የመኖር፣ ሀብት የማፍራት፣ የመምረጥና የመመረጥ አካባቢውን የማስተዳደር መብታቸው የተጠበቀባት፣
- ክልሎቿ የሚከፋፈሉት ብሔርንና ቋንቋን ተመርኩዞ ሳይሆን፣ ለአስተዳደር ምቹ ተደርጎ የተዋቀረባት፣
- ክልሎቿ የሚተዳደሩት በራሳቸው ቋንቋ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ፣ መዝሙር ወዘተ. የሚጠቀሙባት፣
- አንድ ዋና መዲና እንደሚኖርና ከተማዋም የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም፣ ወዘተ. እንደምትሆን የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
እነዚህ መርህዎች ፖለቲከኞች ሲያስጮኋቸው፣ ለመፍታት ከባድ ይመስላሉ እንጂ ብዙ ብሔሮችና ሃይማኖቶች ባሉባቸው አገሮች ውስጥ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ አንድ መዲና ወዘተ. የተለመደ ነው፡፡ እነዚህን ደግሞ በአጋጣሚም ይሁን በሌላ ከምዕት ዓመት በላይ ስንጠቀምባቸው የኖርን ነን፡፡ ብሔርና ሃይማኖት ከፖለቲካ መውጣትም የዓለም መሥፈርት ነው፡፡ ስለዚህ ዓብይ እነዚህን መርህዎች በሰነድ ማውጣታቸው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎናቸው ከማሠለፍ በላይ በየቦታው በየጊዜው አጀንዳ እየጫሩ ኢትዮጵያን ለሚያምሱ ፖለቲከኞችና ጽንፈኛ ብሔርተኞች ‹‹ቀይ መስመር ያለባቸውን አጀንዳዎች›› ከማንሳት ይገታሉ፡፡ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሥራውን ሊያቀልለት ይችላል፡፡
ለማጠቃለል አንዲት ባልቴት፣ በሹም ግፍ ተፈጽሞባት አምላኳም ዝም ብሎ በማየቱ ግራ ተጋብታ፣ አንገቷን ወደ ላይ ቀና በማድረግ ‹‹አለህም እንዳይባል ይኼ ግፍ ይፈጸማል፣ የለህም እንዳይባል ይመሻል ይነጋል፡፡›› እንዳለችው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹የፌዴራል መንግሥት አለ እንዳንል ጽንፈኞች ይፈነጩብናል፣ የለ እንዳንል ብልፅግና ይመጣል እያለ ያጽናናናል፤›› እያለ የሚጮኸውን ሕዝብ ሰምተህ፣ መንግሥት አገሪቷ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ሰቆቃ አስቁመህ፣ ሁሉም ሰላም አግኝቶ የተረጋጋች ኢትዮጵያን መልሶ በማምጣት ሕዝቡን ወደምትለው ብልፅግና ለመውሰድ ግልጽ ያለ የፖሊሲ መርሐ ግብርህን በሰነድ አሳይ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡