Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሥነ ጽሑፉ ደብር፡ ዘሪሁን አስፋው (ፕሮፌሰር) ሲታወሱ

የሥነ ጽሑፉ ደብር፡ ዘሪሁን አስፋው (ፕሮፌሰር) ሲታወሱ

ቀን:

ኢትዮጵያና ሥነ ጽሕፈት ይበልጥ የተዋወቁት በተለይ ከድንጋይ ላይ ጽሑፍ በብራና ላይ መጻፍ በተጀመረበትና የግእዝ ሥነ ጽሑፍም በተወለደበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ ግእዙ ከአራተኛው እስከ አሥራ ዘጠነኛው ምታመት የዘለቀ ልዕልና እንዳለው የታወቀ ነው፡፡

ከ19ኛው ምታመት ወዲህ ከጋራ ቋንቋነት እስከ ሥነ ጽሑፍ ቋንቋነት አምሮና ሰምሮ የዘለቀው አማርኛን በተመለከተ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ምሁራን በሥርዓተ ቋንቋው፣ በሰዋስው እንዲሁም በሥነ ጽሑፍ ዙሪያ ሲያጠኑና ሲመራመሩ አዝማናትን አሻግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባው ‹‹ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ›› እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ቀጥሎም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፈለቁ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ምሁራን በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዘመናዊ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች አኳያ ልብ ወለድ፣ አጭር ልብ ወለድና ሌሎችም በአማርኛ፣ በተለይ ከ1940ዎቹ ወዲህ እያደጉ እስከ ወርቃማ ዘመን ለመድረሳቸው የምሁራኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የመጀመርያው የአማርኛ አጭር ልብ ወለድ ማነው? ለሚለው ጥያቄ ሲሰጥ የነበረው ምላሽ የታደሰ ሊበን ‹‹መስከረም›› የተሰኘውና በ1949 ዓ.ም. የታተመው መድበል ነው፡፡

ይሁን እንጂ የለም፣ መስከረም ከመታተሟ ስምንት ዓመት በፊት (1941 ዓ.ም.) ‹‹የጉለሌው ሰካራም›› የተሰኘች የተመስገን ገብሬ አጭር ልብ ወለድ አለች ብለው በአደባባይ፣ በሥነ ጽሑፍ መድረክ ካስተጋቡትና ካስተዋወቁት ሁለት ምሁራን አንዱ አቶ ዘሪሁን አስፋው ሲሆኑ፣ ሌላኛው ቀዳሚው ተጠቃሽ አቶ አስፋው ዳምጤ ናቸው፡፡

አቶ ዘሪሁን የጉለሌው ሰካራምን በማስተዋወቁ ብቻ አልተወሰኑም፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነታቸው ተጨማሪ ጥናትንና ምርምርን ሻቱ እንጂ፡፡ ቅድመ ተመስገን ገብሬና ታደሰ ሊበን የአማርኛ አጭር ልብ ወለድ ጥንስሶች ወይም ጥንታዊ መልኮች ሊኖሩ ይችላሉ በማለትም ዘለቁበት፡፡ የኢትዮጵያ ጥናትም ምርምር ተቋም ቤተ መጻሕፍት ጓዳን ፈተሹት፡፡ ግኝታቸውንም ‹‹ቀደምት የአማርኛ ትረካዎች ምንነትና ዓበይት ባህርያት›› በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት (ጆርናል) በ1999 ዓ.ም. ለኅትመት አበቁት፡፡ በከፊል እንዲህም ይላል፡-

‹‹በኢትዮጵያ አጭር ልብ ወለድ በ1949 ዓ.ም. በታደሰ ሊበን መስከረም ነው የተጀመረው ያሉት አጥኚዎች፣ ከ1949 ዓ.ም. በፊት ስለነበረው የሥነ ጽሑፍ ሁኔታ የገለጹት ነገር የለም፡፡ ማንኛውም የሥነ ጽሑፍ ዘር በተወሰነ ወቅት ብቅ ያለ ድንገቴ ክስተት ባለመሆኑ፣… ቀድመውት የኖሩና በተወሰነ ወቅት ብቅ እንዲል አስተዋጽኦ ያደረጉ ጥንታዊ መልኮች ወይም ዝርያዎች ይኖሩታል፡፡ በጥንታዊ መልኮቹና ዝርያዎቹ ለተወሰነ ዘመናት ከቆየ በኋላ በራሱ የዕድገት ሒደት ተጉዞ ነው ዘመናዊ መልኩን ለመያዝ የሚበቃው ማለት ይቻላል፡፡

‹‹ለምሳሌ አጭር ልብ ወለድ በፈረንሣይ አገር በ1930 ዓ.ም. ብቅ ያለው፣ ከዚህ ዘመን ቀደም ብሎ በተለይ በ1920ዎቹ በመጽሔቶችና በጋዜጦች በተለያየ ስያሜ የሚጠሩ አጫጭር ትረካዎች ከታተሙ በኋላ ነበር፡፡ አንድ ሥነ ጽሑፍ የደረሰበት ደረጃ የሚደርሰው ዘመናዊ ቅርፁን ከመያዙ በፊት በነበሩና ለመፈጠሩም ይነስም ይብዛም፣ ይቅረብ ይራቅም አስተዋጽኦ ባደረጉ ቀዳሚ ዝርያዎች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡

በዚሁ አቅጣጫ የአማርኛ አጭር ልብ ወለድም መነሻ ያደረጋቸው ወይም የተንደረደረባቸው ቀዳሚ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ወይም ጥንታዊ መልኮች ነበሩት ማለት ይቻላል፡፡››

የመምህሩና የተመራማሪው ዘሪሁን ብርዕ በእነዚህ የአማርኛ አጭር ልብ ወለድ ቀዳሚ ወይም ጥንታዊ መልኮች ባሏቸው አጭር ትረካዎች ላይ ቅኝት ያደረገው፣ የፍለጋ ትኩረት ያደረገው ከ1949 በፊት በተከታታይ በታተሙት፣ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› እና ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጦች ላይ ነው፡፡

‹‹ብርሃንና ሰላም›› ከተጀመረበት ከሐሙስ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 23 ቀን 1942 ዓ.ም. 524 ጋዜጦች፣ ‹‹አዲስ ዘመን›› ከተጀመረበት ከግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜን 1949 ዓ.ም. ድረስ የተገኙትን 728፣ በጠቅላላው 1,252 ጋዜጦችን በመመልከት 146 አጭር ትረካዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡

በእሳቸው አገላለጽ፣ ‹‹እነዚህ ጽሑፎች እንደሚሳዩዋቸው ገጽታዎች ሦስት ዓይነት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ የመጀመርያዎቹን ተረት ተረት፣ ሁለተኛዎቹን ተረት ሐተታ፣ ሦስተኛዎቹን ደግሞ ራስ ትረካ ብዬ መድቤያቸዋለሁ፡፡

‹‹ሦስተኛዎቹና ራስ ትረካ ያልኳቸው በሁለቱ ውስጥ የማይመደቡ ራሳቸውን ችለው የተተረኩ ወይም ለታሪካቸው ሲባል የተጻፉ አጭር ትረካዎች ናቸው፡፡ ይህ ጥናት በዋናነት የሚያተኩረውም በእነዚህ በቁጥር 113 በሆኑት አጭር ራስ ትረካዎች ላይ ነው፡፡ 113ቱ አጭር ትረካዎች የአማርኛ አጭር ልብ ወለድ ከመምጣቱ በፊት ተጽፈው የተገኙ የዘመናዊው አጭር ልብ ወለድ ጥንስሶች ወይም ጥንታዊ መልኮች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹የልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ቀዳሚ ባህሪ አንድ ዓይነት ታሪክ መተረክ ነው፡፡ ይህ ታሪክ በጊዜ ቅደም ተከተል ተቀናጅተው የሚፈጸሙ ሁነቶች ወይም ድርጊቶች ትረካ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ከ250 እስከ 1,100 በሚደርሱ ቃላት የተጻፉት አጭር ትረካዎች አንድ የሆነ ታሪክ የሚተርኩና ታሪኩንም በጊዜ ቀደም ተከተል በተሳሰሩ ድርጊቶች ወይም ሁነቶች የሚቀርቡ በመሆናቸው በልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍነት ይመደባሉ፡፡ የአማርኛ አጭር ልብ ወለድ ጥንስሶች ወይም ጥንታዊ መልኮች ተብለውም እንደ ልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሊጠኑና ሊመረመሩ ይችላሉ፡፡

‹‹ስለዚህ በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ጥናት በተለይ የአጭር ልብ ወለድ አነሳስና ዕድገት ሲጠና የእነዚህን ቀደምት አጭር ትረካዎች ምንነትና መልክ ማውሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ እስከ ዛሬ በእነዚህ አጭር ትረካዎች ላይ የተደረገ ጥናት ስላጋጠመኝ የተወሰኑ ገጽታዎቻቸውን በዛሬ ጥናት ለማሳየት ተነሳሁ፤›› ብለው በዋናነት  ራስ ትረካ ያሏቸውን ጽሑፎች በታሪክ፣ በገጸ ባህሪና በመቼት ረገድ ያላቸውን ገጽታ በመጽሔቱ ውስጥ አሳይተዋል፡፡

 በመደምደሚያቸውም ‹‹በአጠቃላይ እነዚህ በቅድመ ተመስገን ገብሬና ታደሰ ሊበን ተጽፈው የተገኙ አጭር ትረካዎች በኢትዮጵያ የአጭር ልብ ወለድን አነሳስና ዕድገት ለሚመረምሩ የሥነ ጽሑፍ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች የሚጤኑ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ናቸው፡፡››

ለአምስት አሠርታት ያህል የዘለቀ፣ እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት የደረሰ ከጥናትና ምርምር ሥራዎች እስከ መማርያ መጻሕፍት ማሳተም ድረስ የበለፀገ መምህርነትን ዘሪሁን ጨብጠዋል፡፡ ‹‹የስነጽሁፍ መሰረታውያን›› የተሰኘው ዓቢይ መጽሐፋቸው ለዘርዐ ሥነ ጽሑፍ የተላለፈ፣ ሲተላለፍ የሚኖር፣ ለመረመረውም በእርግጥም ‹‹የሥነ ጽሑፍ ዘርዕ›› ይሆኑ ዘንድ ነው፣ የተጸውዖ ስማቸው ዘሪሁን የተባለው፣ ያሰኛል፡፡

ከመጻሕፍት ትሩፋቶቻቸው መካከል የዘመናዊ የአማርኛ ልብ ወለድ ፈርጦችን የዓረፍተ ዘመን ማሳያ ያደረጉበትና ‹‹ከበአሉ ግርማ እስከ … አዳም ረታ (ስነ ጽሁፋዊ ተሐዝቦት) ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌሎቹ ሥራዎቻቸው ‹‹የልብ ወለድ አዋጅ የቀደምት ደራስያን አጫጭር ትረካዎች››፣ ‹‹ስነጽሁፍ ለማህበራዊ ለውጥ››፣ ‹‹በስነጽሁፍና በፎክሎር የተሠሩ የዲግሪ ማሟያ ጥናቶች ጭምቃሳብ›› ናቸው፡፡ ‹‹የአጭር ልብ ወለድ ኪነጥበብ ጥቂት ገጽታዎችና ሌሎች 11 ስነጽሁፋዊ መጣጥፎች›› (1986) የሚል ድርሳንም አላቸው፡፡

በብዙኃኑ ዘንድ እምብዛም የማይታወቀው ዓቢይ ሥራቸው ከሦስት አሠርታት በፊት ‹‹በኣይነቱ ኣዲስ የሆነ እጅግ በጣም ጠቃሚ ስእላዊ መዝገበ ቃላት›› ከሌሎች ምሁራን ጋር በ30 የዕውቀት ዘርፍ (ዲሲፕሊን) ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የሚመልስ ማዘጋጀታቸው ነው፡፡

ይህም ‹‹ሥዕላዊ መዝገበ ቃላት ‹‹Visual Dictionary›› የተሰኘውና የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት በ1984 ዓ.ም. ያሳተመው ነው፡፡ አቶ ዘሪሁን ከአቶ በላቸው በቀለ፣ ከበኩረ ወልደሰማያት (ዶ/ር) ጋር በመሆን የተረጐሙት የጂኦግራፊ(ያ)ን ዘርፍ ነው፡፡

የአቶ ዘሪሁን ቡድን ከሰየማቸው ቃላት መካከል፣ ለ‹‹Meteorology›› ስነ አየር፣ ለ‹‹barograph›› መዝጋቤ ኣየር ግፊት፣ ለ‹‹Sunshine›› ብርሃነ ፀሃይ፣ ለ‹‹Mountain Slope›› የተራራ ቆለቆል፣ ለ‹‹swallow Hole›› ዋጤ ጉድጓድ ይገኙበታል፡፡

‹‹ኣለም ኣቀፋዊ ኣየር ሁኔታ ምልክቶች›› በሚለው ንዑስ ክፍል ውስጥም ለ‹‹Sky Coverage›› ከፈነ ሰማይ፣ ለ‹‹Scattered Sky›› ብትን ደመናማ ሰማይ የሚሉትም ይጠቀሳሉ፡፡

የሥነ ጽሑፉ ደብር (ተራራ) ዘሪሁን፣ ‹‹ወግር›› (ኮረብታ) ያይደለ ተሚያሰኟቸው አንዱ ገጣሚነትንም፣ ተርጓሚነትንም፣ አርታዒነትንም ሐያሲነትንም መያዛቸው ነው፡፡

አንዱ ማሳያ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የጀርመን ባህል ተቋም በ1993 ዓ.ም. ያሳተመው ‹‹የጀርመን ቅኔያት ከወልፍጋንግ ገተ እስከ ጉንተር ግራስ›› የግጥም መድበል ከተረጐሙት ዘጠኝ ባለሙያዎች አንዱ ዘሪሁን አስፋው ናቸው፡፡ መተርጐም ብቻ ሳይሆን የመድበሉም አርታኢ ጭምር ናቸው፡፡ 

የሥነ ጽሑፍ ፕሮፌሰሩ ዘሪሁን አስፋው፣ የአጭር ልብ ወለድ ንድፍና ተግባራዊነት ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ማጠናቀቃቸውና ለኅትመት በማሰናዳት ላይ እንደነበሩ ተወስቷል፡፡  

ገጸ ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ ከአባታቸው ከአቶ አስፋው ጎበናና ከእናታቸው ከወ/ሮ ስህን ጎበና እሑድ፣ ጥቅምት 10 ቀን 1944 ዓ.ም. በደሴ ከተማ የተወለዱት አቶ ዘሪሁን አስፋው፣ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ መምህር አካለ ወልድና በወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ልዑል በዕደ ማርያም የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪ፣ በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከሦስተኛ ዓመት በኋላ በነበረው ብሔራዊ አገልግሎት በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በከረን ከተማ ለአንድ ዓመት አስተምረዋል፡፡ በ1967 ዓ.ም. በታወጀው የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻም ተሳታፊ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በዓድዋ አውራጃ ተመድበው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል::

አቶ ዘሪሁን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ፣ በዩኒቨርሲቲው ሥር በነበረው የዓለማያ እርሻ ኮሌጅ በረዳት ምሩቅነት ደረጃ በ1971 ዓ.ም. ተቀጥረው ሕይወታቸው እስካለፈበት ድረስ በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል::

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የ44 ዓመታት ቆይታቸው ከመጀመርያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በርካታ ተማሪዎችን ሲያስተምሩ በየደረጃቸው የመመረቂያ የምርምር ሥራዎቻቸውንም አማክረዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን አስፋው ከትምህርቱ ዘርፍ በተጨማሪ፣ ከፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ጋር በመሆን የተለያዩ የሥነ ሕዝብ ጥናቶችን የሠሩ ሲሆን፣ ወጣት ደራስያንና ተመራማሪዎችን በማማከርና በመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይወሳል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን የሰነዱ›› ተብለው የተቀጸለላቸው ዘሪሁን (ፕሮፌሰር)፣ ከሠሯቸው ጥናቶች መካከል በ1980ዎቹ በግእዝ የዜና መዋዕል አጻጻፍ ሥልቶች ላይ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ያቀረቡት ይጠቀሳል፡፡

የምርምርና የጥናት ሥራዎቻቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በባህር ማዶ ዩኒቨርሲቲዎች በታወቁ የጥናት መጽሔቶችና መድበለ ጉባዔዎች ላይ ታትመውላቸዋል፡፡

በድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በ71 ዓመታቸው ሰኞ፣ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ያረፉት አቶ ዘሪሁን አስፋው፣ ከማረፋቸው ሦስት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሰው መሆን ፊልሞች ጋር በመተባበር ለሚሠራው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ባለ 48 ክፍል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ሙያዊ ሐሳባቸውን አካፍለው ነበር።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ዘሪሁን አስፋው ሥርዓተ ቀብር ረቡዕ፣ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ ግብዓተ መሬቱ በካቴድራሉ መስዕ አቅጣጫ (ሰሜናዊ ምሥራቅ) የተፈጸመው ከመምህራቸው አብርሃም ደመወዝ (ፕሮፌሰር) አጠገብ ነው፡፡

ነፍስ ኄር አቶ ዘሪሁን አስፋው ለ40 ዓመት በትዳር ከቆዩት ከባለቤታቸው ከወ/ሮ የትምወርቅ አካሉ ሦስት ወንድና አንድ ሴት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፣ አንዱ ወንድ ልጃቸው ዓምና አርፏል፡፡

እንጉርጉሮ

ወንድማቸው አቶ ገበየሁ አስፋው ‹‹ደፋሩ ሞት›› ብለው የጻፉትን እንጉርጉሮ በዓውደ ምሕረቱ አንዱ ዓለም አባተ (ዶ/ር) ያቀረበ ሲሆን፣ አንዱ አንጓ እንዲህ ይላል፡-

‹‹አቤት አቤት አቤት

መስክሩልኝ እባካችሁ

ዘሪሁንን ያወቃችሁ

ቀና ብሎ ሰውን ሳያይ

የሆዱንም ሳያወያይ

ሳያስረዳ ሳይናገር

ትቶ ሄደ ሌላ አገር፡፡››

በማኅበራዊ ትስስር ገጿ ደራሲት ውድ አላት ገዳሙም እንዲህ አንጎራጉራለች፡-

‹‹እልፍ አዕላፍ በረከት — አሻራ ያኖረ፣

የዕውቀት ሊቃውንትን — አገር የዘከረ፣

ትናንትን ከዛሬ፣ የዛሬን ከነገ — እያስተሳሰረ፣

የጥበብ አሰናጅ — ዕውቀት የሰደረ፤

ወግና ትውፊትን፣ ከባህል አዛምዶ – ኩሎ የቀመረ፣

የሰውን አዕምሮ – አልሚ የነበረ።

መኸር ሳይሰበስብ — እንደዋዛ ቀረ!።

ድርሰት ሙሾ ታውርድ — ጽሑፍ ደረት ትድቃ፣

ጥበብ ‹ምር› ታልቅስ – ሒስ ትሸሸግ ዐውቃ፤

የሞሸራት ምሁር – በውብ አንደበቱ፣

ላይመለስ ሄዷል – መሬት ሆኗል ቤቱ።

ቢሮውን ሳይዘጋ፣ ስንብት ሳያደርግ – ቸኩሎ መሄዱ፣

ይኖርበት ይሆን? አይቀሩት ቀጠሮ – ከልጅ ከዘመዱ?!››

‹‹ዘርዕ ይሁን በልዕልና›› ብለን ያወደስነውን ማዕምረ ጽሑፍ ዘሪሁንን ሸኝተን፣ መምህራችንን ፕሮፌሰር አብርሃም ደመወዝንም እጅ ነስተን፣ ካቴድራሉን ከመልቀቃችን በፊት ከትውፊታችን የተቀዳውን መንቶ ግጥም እንዲህ ታወሰን፡፡

        ‹‹አፈር መልሱ እንጂ ድንጋይ ለምናችሁ፣

        የቀለም ቀንድ ነው ትሰብሩታላችሁ።››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...