በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)
በክፍል አንድ ጽሑፌ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ቀደም ብሎ ከነበሩት የተለየ እንደሆነ፣ በአገራችን ህልውና ላይ ያንዣበበውንና “በብሔር ፖለቲካ” ተመርኩዞ የቆመውን “የዘረኝነት ሥርዓት” አደገኛነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የእዚህ አስከፊ ሥርዓት መርዝ በሃይማኖት ተቋማት ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ዘርፎች በሚባል ደረጃ ማለትም በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በመንግሥት መዋቅር፣ በፍትሕ፣ በትምህርት፣ በፋይናንስና በሌሎችም እንደተሠራጨ ግልጽ ነው፡፡ አገራችን ከድህነት ተላቃ እንዳታድግና እንዳትገነባ፣ ወደፊትም እንዳትራመድ ሰቅዞ እንደያዛት ምንም አያጠራጥርም፡፡ በውስጧ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ ለህልውናዋም ፀር እንደሆነ፣ በቅርቡ በትግራይ ጦርነት በደረሰባት አደገኛ ፈተና እንኳን ለመረዳት ይቻላል፡፡
ባለፈው ክፍል ለእዚህ ሁሉ ውስብስብ የአገራችን ችግር መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ ለአንባብያን አቅርቤ ነበር ጽሑፌን ያቆምኩት፡፡ ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ቢያግዝ በሚልም የአቅሜን አስተያየት ለመስጠት በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ ብዬ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ይኸውና ዛሬ ይህችን አጭር ጽሑፍ በትህትና አቀርባለሁ፡፡ የጽሑፌ ዋና ዓላማ በተለይም በእዚህ ከባድና ውስብስብ በሆነው የአገራችን አንገብጋቢ የፖለቲካ ጥያቄ “በብሔር ፖለቲካ” ላይ የቆመውን “የዘረኝነት ሥርዓት” መዘዙን እንዴት እናስወግደው በሚለው፣ ከተቻለ ሰፊና ጠለቅ ያለ አገር አቀፍ ውይይት “በብሔራዊ ምክክሩ” አማካይነት እንዲከፈት በትህትና ለማሳሰብም ነው፡፡ በተጨማሪ አገራቸውን አፍቃሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፣ በሚችሉት ሁሉ አቅም ሐሳባቸውን እንዲያበረክቱ ለማበረታታትና በጋራ መፍትሔ እንድናፈላልግ በትህትና ለማሳሰብና ድርሻዬን ለማበርከት በሚል ነው ይህችን አጭር ጽሑፍ የማቀርበው፡፡
የብሔር ፖለቲካ መነሾው ከየት ነው?
በቅድሚያ ይህን የመሰለ በጣም አስቸጋሪና አወዛጋቢ አስተሳሰብ ያዘለ “የብሔር ፖለቲካ” ወይም “ርዕዮተ ዓለም” ሊባል የሚችል ዘይቤ ወደ አገራችን እንዴት ሊገባ ቻለ የሚል ጥያቄ፣ በብዙ ኢትዮጵያውያን ስለሚነሳና ያለፈውን ትውልድ “እሱ የተከለው መርዝ” ነው በሚል ብዙ ትችትም ስለሚቀርብ፣ ታሪኩን አጠር አድርጌ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ “የብሔሮች እኩልነት በኢትዮጵያ” የሚለውንና ሌሎችንም ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች፣ በዋነኝነት “መሬት ለአራሹን” እና “ሕዝባዊ መንግሥት” የሚሉትን አንግቦ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከድህነት፣ ኋላቀርነትና ባላባታዊ (ፊውዳል) የግፍ አገዛዝ፣ እንዲሁም ከኢምፔሪያሊዝም የእጅ አዙር ተፅዕኖ ነፃ ለማውጣትና ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ዓላማ በመከተል ከፍተኛ ትግል ካደረገውና ከባድ መስዋዕትነትም በሕይወቱ ሳይቀር ከከፈለው ትውልድ የወጣሁ፣ በዕድልና በተዓምር ሊባል በሚችል አጋጣሚም ከተረፉት ጥቂቶቹ አንዱ መሆኔን አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ይህንንም የምገልጽበት ዋናው ምክንያት፣ ከሌሎች በተለይም በመስዋዕትነት ከወደቁት በሺዎች የሚቆጠሩ አገራቸውን አፍቃሪ ጀግኖች ወጣቶች የራሴን ኢምንት ታሪክ አጉልቼ ለማሳየት ሳይሆን፣ ዛሬ አገራችን ለገባችበትና መውጫው ለጠፋበት “የብሔር ፖለቲካ አዙሪት” የአሁኑ ትውልድ በደፈናው እኔ ያለፍኩበትን ትውልድ ዋነኛ ተጠያቂ ስለሚያደርግ ያንን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል ቢረዳ በሚል ነው፡፡ በመሠረቱ ማንኛውም ትውልድ አገሩን በየጊዜው ለሚያጋጥሟት ውስብስብ ችግሮች፣ በስሜት ሳይሆን በዕውቀት፣ በስማ በለው ሳይሆን በጥናትና በምርምር ላይ የተመሠረተ መፍትሔ በማፈላለግ በበኩሉ የራሱን ድርሻ ማበርከትና የአገሩንና የታሪክን አደራ ለመወጣት መጣር ይኖርበታል፡፡
ሁልጊዜ ያለፈውን ትውልድ በጭፍኑ ማውገዝ ለአገራችን ችግሮች መፍትሔ አያመጣም፡፡ ለአገራቸው ሲሉ በሕይወታቸው መስዋዕትነትን እየከፈሉ አገራችንን ተንከባክበው አቆይተው ያወረሱንን ወላጆቻችንና አያት ቅድመ አያቶቻችንን በደፈናው እያማረሩ መኖሩም ትክክል አይደለም፡፡ ጥፋትም ፈጽመው ከሆነ ከስህተታቸው በመማር፣ ጥሩም ከሠሩ በእነሱ ስኬትና ተሞክሮ ላይ እየገነቡ አገራችንን ለማሳደግ በመጣር ፈንታ፣ በቂም በቀል ባለፈው ትውልድ በአያት ቅድመ አያቶቻችን ላይ ጥርስን እየነከሱ መኖሩ መፍትሔ አያመጣም፡፡ ስንፍናን፣ የአስተሳሰብ ድህነትንና አቅም ማጣትንም ያዳብራል፡፡ ዕድል ብሎላት ታዲያ አገራችን በተደጋጋሚ በትውልዶቿ እየደረሰባት ያለውና እስከ ዛሬም መውጫ ያላገኘችለት የቀውስ አዙሪት፣ በድህነትም ወደኋላ ያስቀራትና ብዙ ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ያለው አንዱም ይህ ጎጅና መጥፎ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡
የሆነው ሆኖ እኔ ያለፍኩበት ትውልድ “በብሔር ጥያቄ ላይ” የነበረው አመለካከት በጥቅሉ በሁለት ሊከፈል የሚችል ይመስለኛል፡፡ እርግጥ የሁለቱም ምንጭ በ1960ዎቹ ካደገውና በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ካሳደረው የተማሪዎች ንቅናቄ ነው፡፡ አንደኛው አመለካከት አገራችን ኢትዮጵያ ብሔሮቿ ወይም ብሔረሰቦቿ በእኩልነት የሚኖሩባት አይደለችም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሕዝባችን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በፆታ፣ በባህልና በሃይማኖት ቢለያይም ሁሉንም እኩል የሚያይና የሚያስተናግድ ዴምክራሲያዊና ሰብዓዊ ሥርዓት ባለመኖሩ ነው ይልና ለዚህም መነሾው በኅብረተሰባችን የመደብ ልዩነት ስላለ፣ የመንግሥት አውታሩን የሚቆጣጠረው ኋላቀሩና በሕዝብ ላይ ግፍ የሚያደርሰው የባላባታዊው (የፊውዳል) ገዥ መደብ ስለተንሰራፋ ነው የሚል እምነት ነበረው፡፡
በእዚህ ገዥ መደብም ከአንድ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ወይም አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ ይብዛም ይነስም ከተለያዩ ብሔሮች የመጡ አባላት አሉበት ይልና በአጭሩ በኅብረተሰባችን የሰፈነው ዋነኛ ቅራኔም በመደቦች መሀከል ያለው እንጂ፣ በብሔሮች መሀል ያለው አይደለም ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህን ኋላቀርና ፍትሕ የለሽ የባላባታዊ (ፊውዳል) ሥርዓትም አስወግዶ፣ ለሁሉም ዜጎች የብሔር፣ የቋንቋ፣ የፆታ፣ የሃይማኖትና የባህል እኩልነትን የምታስተናግድ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ በነፃ በሚመርጡት መንግሥት የምትተዳደር፣ ኅብረ ብሔርና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በምትኩ መገንባት አለብን የሚል ዓላማ አንግቦ ነበር ትግሉን ያካሄደው፡፡ እርግጥ ይህ አስተሳሰብ የአጭር ጊዜ ግቡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በአገራችን ለመገንባት ይሁን እንጂ፣ የረዥም ጊዜ ግቡ መዳረሻ ግን የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን ዋና መመርያው አድርጎና በውስጡም ይዞ ነበር የሚጓዘው፡፡ በእዚህ አመለካከት ዙሪያ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቁት ኢሕአፓና መኢሶን የነበሩ ሲሆን፣ ሌሎችም ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩበት፣ እኔም የኢሕአሠ (የአሲምባ ሠራዊት) መሥራች አባል እንደ መሆኔ መጠን፣ የኢሕአፓም አባል ነበርኩ፡፡
በአንፃሩ የእዚህ ትውልድ ሌላው ካምፕ ዘግየት ብሎ ከተማሪዎች ንቅናቄ የተወለደውና በዋነኝነት በሕወሓት የሚመራው፣ በአገራችን ዋናው ትግል በመደቦች ሳይሆን በብሔሮች መሀከል ያለው ነው የሚል እምነት ይዞ ነው ትግሉን የጀመረው፡፡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት በኅብረተሰባችን ውስጥ የሰፈነው ዋናው ቅራኔ በመደቦች ሳይሆን በብሔሮች መሀል ያለው በመሆኑና ትግላችንም የብሔር ጭቆናን ለማጥፋት መሆን አለበት በሚል ነው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ሕወሓት “ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔር” ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጥቅሉ በሁለት በመክፈል ነበር የሚያየውና የትጥቅ ትግሉንም የቀጠለው፣ በኋላም የመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቆናጠጠው ይህን የተዛባ አመለካከት እንደያዘ ነው፡፡ ጨቋኝ ብሔር የሚለውም በተናጠል አማራን ሲሆን፣ በተጨቋኝ ወገን ግን ሌሎችን በሙሉ (ትግራይንና ኦሮሞንም ጨምሮ) ያካትታል፡፡ በአማራ ብሔር ውስጥ ያለው አብዛኛው ደሃ ገበሬ ሕዝብም “ከጨቋኙ የአማራ ብሔር” ከሚለው ጋር ይጠቃለላል፡፡
ለሕወሓት የመደብ ትግል የሚለው በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ሲሆን፣ ለትግሉም ወሳኝ አልነበረም፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን እንዴት የአማራን ብሔር ወይም ደሃውንና ሰፊውን ሕዝብ በሙሉ ጨቋኝ ትላላችሁ ሲባል ሌላ ቃል መወርወር ጀመረ፣ “የአማራ ጨቋኝ ገዥ መደብ” የሚል፡፡ በእዚህ አባባል እኛ መጥተን እስክናድናችሁ ድረስ የአገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን የያዘው አማራ ብቻ ነው (እኛ ትግሬዎች ወይም ሌሎች እንደ ኦሮሞ ያሉት) አልነበርንበትም ማለቱ ነው፡፡ በዚህም አለ በዚያ እስከ ዛሬ አገራችንን እሳት ውስጥ የከተታትና እያመሳት ያለው ይህ ከጅምሩ የተዛባ በጥላቻና “በጠባብ የብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብ” ላይ የቆመ መርዘኛና ከፋፋይ ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ፣ ባለፉት 30 ዓመታት የነገሠው የሕወሓት “የዘረኝነት አገዛዝ” ራሱ በቂ ምስክር ነው፡፡
ምናልባት “የብሔር ጭቆና” የሚባል ካለም ከኃይለ ሥላሴና ከደርግ ዘመነ መንግሥት ይልቅ፣ በበለጠ በሕወሓት አገዛዝ ነው ሥር የሰደደው ቢባል ከእውነት የራቀ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ለምን ቢሉ ሕወሓት ብሔርን ተገን አድርጎ ሁሉንም ዘርፎች የአገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የሚሊታሪና የደኅንነት፣ የክልል፣ የእምነት ተቋማት ሳይቀር ከራሱ ብሔር በወጡ ሹመኞችና ካድሬዎች ይቆጣጠር ነበርና ለእዚህ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ካላፉት መንግሥታት ግን ሌላው ቢቀር በአጭሩ ለማሳየት የንጉሡን ባላባታዊ ሥርዓትና የደርግን መንግሥት ቁንጮ የያዙት፣ ኃይለ ሥላሴና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንኳን ሙሉ በሙሉ አማራ አልነበሩም፡፡
የሚያሳዝነው ሕወሓት ለጊዜው ቢነቀልም፣ መርዘኛውና ለዓመታት ሥር የሰደደው “የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት” ግን ከአገራችን እስካሁን ሊነቀል አልቻለም፡፡ ልክ እንደ ሕወሓት ሌላ ብሔርን ተገን አድርጎ በተራው የአገሪቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የመንግሥት መዋቅርና ተቋማት በሙሉ ለመቆጣጠር እየታተረ ያለ “የገዥ መደብ” ተተክቷል፡፡ ለእዚህ ሁሉ መንስዔ ‹‹ለብሔር ፖለቲካውና ዘረኛው ሥርዓት›› ሥረ መሠረቱና ግንዱ ደግሞ ሕወሓት የተከለው ሕገ መንግሥት እንደሆነ ምንም አያሻማም፡፡ በነገራችን ላይ ደርግ እንደወደቀ ሥልጣን ለመያዝ ሕገ መንግሥቱን ሲያረቅ በተቻለው መጠን ሌሎችን ተቀናቃኝ ድርጅቶች አግልሎ ወይም በሥሩ አድርጎ፣ “የትግራይ ልሂቃንን” ወደ ሥልጣን እንዲያወጣ አመቻችቶ ነበር ያነፀው፡፡ ይህ እንዲሳካለት ከመጥፋት በተዓምር የዳኑትን የኅብረ ብሔር ድርጅቶች ኢሕአፓንና መኢሶንን የመንግሥት ሥልጣን መጋራቱ ቀርቶ ሕገ መንግሥት በሚያረቀው ጉባዔ ላይ እንኳን እንዲሳተፉ አልፈቀደላቸውም፡፡ ሕዝቡም በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፋና ጠለቅ አድርጎ አልተወያየበትም፡፡
ሕወሓት የመንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣም በኋላ፣ በተለይም በአማራ ብሔር ላይ ያለውን የከረረ ጥላቻ በአገር ደረጃ የፖሊሲ መመርያ በማድረግ ነው የቀጠለው፡፡ በሌሎች ብሔሮች በተለይም በኦሮሚያ የተለያየ ስም ለምሳሌ “ነፍጠኛ”፣ “ወራሪ” የሚሉ ቅጽሎች እየተለጠፈበት ምስኪኑ የአማራ ሕዝብ እንዲሸማቀቅ፣ በሕዝብ እንዲጠላና እንዲወገዝ “መጤ” እየተባለም ወልዶና ተዋልዶ ተዛምዶ በሰላም ለዓመታት ከኖረበት አካባቢው ዘሩ እየተቆጠረ ሳይቀር ተለይቶ እንዲፈናቀል በግፍ እንዲጨፈጨፍ ነው የተፈረደበት፡፡ ዛሬ “ሸኔ” በሚል ስም የሚጠራው የኦነግ ክንፍም የአስተሳሰብ ምንጩ የዚያ ሰይጣን አመለካከት ነው፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 30 ዓመታት ሕወሓት በአገራችን በዘራው መርዘኛ “የብሔር ፖለቲካ”ና ባንሰራፋው “የዘረኝነት ሥርዓት” የተነሳ በብሔር፣ በመሬትና በሕዝብ ለሕዝብ ግጭትና መፈናቀል በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ንፁኃን ኢትዮጵያውያን፣ ከሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች አልቀዋል ቀዬአቸውን እየለቀቁ በበረሃ ተሰደዋል፡፡ ለረሃብ፣ ለበሽታና ለሞትም ተዳርገዋል፡፡
በተለይም በኦሮሚያ ክልል ለብዙ ዓመታት የኖሩ አማሮችን በመጨፍጨፍና በማፈናቀል ብዙ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የሚያሳዝነው ዛሬም በሁለቱ ክልሎች በተለይ በኦሮሚያና በትግራይ “ጠባብ ብሔርተኞች” እና ጠባቂዎቻቸው በተሰገስጉባቸው የክልል መንግሥታት፣ ይህ የዘረኛና ኋላቀር አስተሳሰብ መርዝ ሊገታ አልቻለም፣ የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ የትግራይና የኦሮሚያ “ጠባብ ብሔርተኞችና ጽንፈኞች” በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ከህሊናቸው ጨርሰው ሊፍቁት አልቻሉም፣ ጭራሽ ባሰባቸው፡፡ የሚያሳዝነው አልሆንላቸው ብሎ ነው እንጂ፣ ለዘመናት ተስማምተውና ተግባብተው በሰላም የኖሩትን ሦስት ታላላቅ ሕዝቦች (ኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ) ለመነጣጠልና በመሀላቸው አንድነት እንዳይኖር ለማድረግ፣ ብሎም አገራችን ኢትዮጵያን ለመሰነጣጠቅና ለማፈራረስ እስከ ዛሬ ያልሸረቡት ሴራና ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም፡፡ ሕወሓት በቀሰቀሰው የትግራይ ጦርነት በአፋርና በአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ ራሱ ታሪክ አይረሳውም፡፡ በአጋሩ “ሸኔ” በኦሮሚያ በተለይም በወለጋ እስካሁን የሚካሄደው የአማራ ድሆች ጭፍጨፋና ማፈናቀልም ታሪክ ምንጊዜም ይቅር አይለውም፡፡ ምስኪኑ የትግራይ ሕዝብም አልቀረለትም፡፡ ለእዚህ መርዘኛ “የብሔር ፖለቲካ” ሰለባ በመሆን በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ልጆቹን በጦርነቱ ገብሯል፡፡ እንግዲህ የትኛውን “ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” ነው “የብሔር ፖለቲካውና ዘረኛ ሥርዓቱ” የጠቀመው? ከገዥዎቹና የሥርዓቱ ጥቅም ተካፋዮች፣ ከሌቦችና ዘራፊዎች በስተቀር፡፡
ሕወሓት በዘረጋው “የብሔር ፖለቲካ” መርዝና “የዘረኝነት ሥርዓት” ሳቢያ፣ ባለፉት 30 ዓመታት (በተለይም በቅርቡ አምስት ዓመታት) በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩትም ዜጎች በደቡብ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በክልል፣ በመሬት፣ በድንበርና በዘር ግጭት የተነሳ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በጭፍጨፋና በመፈናቀል ምክንያት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አልቀዋል፣ ቀዬአቸውን እየለቀቁ ተሰደዋል፡፡ በዚያ ሰቆቃ ላይ ድህነቱ፣ ሙስናና ዝርፊያው፣ የኑሮ ውድነቱ ተደራርቦ ሕዝቡ ይሰቃያል፡፡ ይህ መጥፎ “የብሔር ፖለቲካና ዘረኛ ሥርዓት” ካልተቀየረ ወይም ካልተወገደ፣ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት መቼም አይመጣም፡፡ ሕወሓት በሕዝብ አመፅ ተነቅሎ በ“ብልፅግና” ተተክቶም እንደሚታየው መሠረታዊ ለውጥ እስከ ዛሬ ድረስ አልመጣም፣ የሚያሳዝነው “የብሔር ፖለቲካ”ን ያስቆማሉ በሚል ሕዝቡ ትልቅ ተስፋ የጣለባቸው የብልፅግና መሪዎችም ታሪክ ሊሠሩ ሲችሉ ዕድሉን እስከ ዛሬ አልተጠቀሙበትም፡፡ ፓርቲያቸው ለራሱ “በብሔር ፖለቲካ” ወገቡን ተተብትቦ ያንን መፍታት አቅቷቸው ወደፊት ለመራመድም አቅቶት መሀል መንገድ ላይ ቆሞ ግራና ቀኝ እየተንገዳገደ፣ አገሪቱንም ይዟት እንዳይወድቅ እያሠጋ ነው፡፡ ከሕወሓት ስህተት ተምሮ አቅጣጫውን በቶሎ እንደማስተካከል እሱም በ‹‹ኢሕአዴግ የቁልቁለት ጉዞ›› በፍጥነት እየተንደረደረ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የ“ብሔር ፖለቲካውና የዘረኝነት ሥርዓቱ” የማያባራው መዘዝ
በ1960 ዎቹ መጀመርያ ላይ በኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ስማር ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የደቡብ አፍሪካን የነጮች ዘረኝነት ሥርዓት ተቃውመው በስብሰባና በሰላማዊ ሠልፍ ሲያወግዙ፣ እኔም አብሬ ለመሳተፍ ዕድል አጊንቼ ነበር፡፡ በወቅቱ እናት አገራችን ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን የነጮች ዘረኛ ሥርዓትና የምዕራባውያንን የአፍሪካ ቅኝ አገዛዝ በመቃወም አኅጉሩን በመምራት ግንባር ቀደም ነበረች፡፡ በቅርቡ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ስንቱን በረሃና ዱር አቋርጠው መጥተው ኦሮሚያ ድንበር ሲደርሱ መታወቂያቸው እየታየ ኦሮሞ የሆኑት እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው፣ የአማራ መታወቂያ የያዙት ግን በክልሉ ፖሊሶች አትገቡም እየተባሉ ወደመጡበት እንዲመለሱ ሲገደዱ ሳይ ያ የረሳሁት ከ50 ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ላይ በዘረኝነት ሥርዓቱ ይደርስባቸው የነበረው ግፍ በህሊናዬ ድቅን እያለብኝ ውስጤን ሕመም ይሰማኝ ነበር፡፡ ከእዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያውም በኢትዮጵያ የነጭ ሳይሆን የጥቁር በጥቁር ዘረኝነት አያለሁ ብዬ በህልሜም ሆነ በዕውኔ አስቤው አላውቅም ነበር፡፡ እነዚያ ለአገራቸው ነፃነትና ለሕዝባቸው ሰብዓዊ መብት ሲታገሉ ሕይወታቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው የሰጡት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች (የሁሉም ብሔር ልጆች) በተዓምር ከመቃብራቸው ተነስተው፣ አገራቸውን ዛሬ ምን እንደምትመስል ቢያዩዋት ምን ይሉ ይሆን ነው ያልኩት፡፡
በደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ1950 ዘረኛው የነጮች መንግሥት ባወጣው ሕግ (Group Areas Act) መሠረት፣ በሁሉም የለሙ ከተሞች አካባቢዎች የሚኖሩት ጥቁሮችና ህንዶች በዘራቸው እየተለዩ ተነቅለው፣ ልክ እንደ ዛሬይቱ “አዲሲቱ ሸገር ከተማና አዲስ አበባ” እንዲሁም በ”ብሔርና በቋንቋ” የታጠሩት የኢትዮጵያ ክልሎች ከነጮች ርቀው እርስ በርስ እንዳይገናኙም ተደርገው እንዲሰፍሩ ነበር የተገደዱት፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር “ሸገር” የሚል ስም በተሰጠውና አዲስ አበባን እንደ ቀለበት ዙሪያዋን ባጠራት አዲሱ ከተማ ኦሮሞ ያልሆኑት በዘራቸው እየተለዩ ቤታቸው በሌሊት በግሬደር በላያቸው ላይ እየፈረሰ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰደዱና እንዲሰፍሩ እንደተደረጉት፣ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችም ተመሳሳይ ዕጣ ነበር የገጠማቸው፡፡ በተግባር ሲውል የነበረው ጭካኔና በንፁኃን የሰው ልጆች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ ግን የኢትዮጵያው ይብሳል፡፡ ሌሎችንም በርካታ ምሳሌዎችን የደቡብ አፍሪካውን የዘረኝነት ሥርዓትና በኢትዮጵያ አሁን የተንሰራፋውን “በብሔር ፖለቲካ” ስም የቆመውን “የዘረኝነት ሥርዓት” የሚያመሳስሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለጊዜው ግን እዚህ ላይ ላቁምና ወደ እኛው የጉድ ታሪክ ላተኩር፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ “የብሔር ፖለቲካውና የዘረኝነት ሥርዓቱ” በፖለቲካው መስክ ላይ ብቻ እንኳን ያደረሰውን ጉዳት ብንወስድ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ለምሳሌ በክልሎች የእዚያው ብሔር “ተወላጅ” ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች ዘራቸው እየታየ መሪ መሆን አይፈቀድላቸውም፡፡ በሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነቶችም ከተመደቡ ዕድለኞች ናቸው፡፡ በመንግሥት መዋቅሮች በተለይ ዜጎች በችሎታቸው፣ በተሞክሮአቸውና በዕውቀታቸው ሳይሆን በአብዛኛው ዘራቸው (ብሔራቸው) እና ዘውጋቸው እየታየ ነው ኃላፊነት የሚሰጣቸው፡፡ ምንም እንኳን ቁጥራቸው ቢበዛም በተለይ የአማራ ተወላጆች በከፍተኛ አስተዳደር እርከን እንዲመደቡ አይፈቀድላቸውም፡፡ ለምሳሌ በትንሹ እንኳን የድሬዳዋን ከተማ ብንወስድ አማራ የሚባሉት ቁጥራቸው የኗሪውን አንድ ሦስተኛ ያህል ሆኖም እንኳን ከተማዋን ማስተዳደር አይፈቀድላቸውም፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ብሔር ተወላጆች ናቸው በየአራት ዓመቱ እየተፈራረቁ ከተማዋን የሚመሯት፡፡ ሌሎችንም በርካታ የዘረኛ ሥርዓቱ በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ያስከተለውን መጥፎ ክስተቶች፣ በሕግ ተደግፈው የሰፈኑትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቦታ ስለማይበቃኝ እዚህ ላይ ልተወውና ለእዚህ ሁሉ ምክንያት “የብሔር ፖለቲካው” እና “የዘረኝነቱ ሥርዓት” መሠረት ወደ ሆነው በሕገ መንግሥቱ ላይ ላተኩር፡፡ ከእዚያ ቀጥዬም የመፍትሔ ሐሳቦች የሚመስሉኝን ጠቁሜ ጽሑፌን ለጊዜው አቆማለሁ፡፡
ሕወሓት የተከለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና እሱ የወለደው “የብሔር ፖለቲካና የዘረኝነት ሥርዓት” መዘዝ
ገና ከጅምሩ የሕገ መንግሥቱ አንዱ ዋነኛ ችግር “ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ” ማለት ምን ማለት ነው? አንድነታቸውና ልዩነታቸውስ ምንድነው? ለምንስ የሕገ መንግሥቱ አውታር ሊሆኑ ቻሉ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ በግልጽ አለማስቀመጡ ነው፡፡ ይህን በታዋቂው አንቀጽ በ39 (ቁ፡5) ሥር ለማብራራት ቢሞክርም በቂ አይደለም፡፡‹‹ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ማለት፣ ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶችና ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፤›› ይላል ሕገ መንግሥቱ፡፡
እስኪ እግዚአብሔር ያሳያችሁ፡፡ እያንዳንዱን ቃል ወይም ሐሳብ አተኩራችሁ እዩትና ከላይ በተጠቀሰው መሥፈርት በኢትዮጵያ ከ80 በላይ አሉ የሚባሉትን “ብሔር ብሔረሰቦች” ወስዳችሁ ይህ ብሔር ነው ወይም አይደለም፣ ብሔረሰብ ነው ወይም አይደለም፣ ሕዝብ ነው ወይም አይደለም ብላችሁ በጥቂቶቱ ከቻላችሁ ብታስረዱኝ እንዴት ደስ ባለኝ፡፡ ለምሳሌ እዚህና እዚያ ተቆርጠውና ተቀጥለው ብሔር ናቸው ተብለው የተካለሉትን የኦሮሚያንና የአማራን ክልል እንኳን ብንወስድ በውስጣቸው የሚኖሩት ዜጎች በሙሉ ከላይ የተዘረዘሩትን መሥፈርቶች ሙሉ በሙሉ አያሟሉም፡፡ አንዱን መሥፈርት “ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው” የሚለውን ብንወስድ፣ በኦሮሚያ ክልል በበርካታ ቋንቋዎች አማርኛንና ኦሮሚኛን ጨምሮ ሕዝቡ ለመግባቢያ ይጠቀማል፡፡ ከእዚያ በላይ ቀደም ብሎ በሁለቱም ክልሎች፣ በተለያዩና አንዳንዶቹ ጨርሶ በማይዋሰኑ ወይም በማይገናኙ አካባቢዎች፣ አውራጃዎችና “ክፍለ ሀገሮች” ነው ሕዝቡ የኖረው፣ ስለዚህ እንዴት ብሎ ነው በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 39 ቁ 5) በተሰጠው መሥፈርት (ለምሳሌ በቋንቋ)፣ አንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ አንተ የኦሮሞ፣ የአማራ ወይም የቤኒሻንጉል ብሔር አባል ስለሆንክ የእዚህ ክልል አባል ነህ ብለን ልንለየውና ልንመድበው የምንችለው? የዘሩንስ እንተወው፡፡ “የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና” “የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ” የሚለውንም እንዴት ነው ለማወቅና መለየት የሚቻለው? እንደ ድሬዳዋ፣ ሐረርና አዲስ አበባ ባሉ የብዙኃን ከተሞች በተለይ፣ ከተለያዩ ብሔሮች ተጋብተው፣ ወልደውና ተዋልደው የሚኖሩትን እንዴት ብለን ነው ብሔራቸውን የምንለየው? በአጠቃላይ ሕወሓት ባስቀመጠው መሥፈርት እንኳን ብንሄድ፣ መጀመርያ የተካለሉት ዘጠኙ ክልሎች በቂ ጥናት ተካሂዶባቸው “ራስን በራስ ለማስተዳደር” ወይም “ለፌዴራል አስተዳደር” አመቺ ብሔሮች እንዲሆኑ ታስቦ ሳይሆን፣ ለሌላ አጀንዳ ነበር የተዋቀሩት፡፡ እሱን ከታች በኋላ እመለስበታለሁ፡፡
በተጨማሪ ሕገ መንግሥቱ “በብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ” ተወካዮቻቸው ነው የፀደቀው የሚለውም ፍፁም ስህተትና ከታሪክ ጋር የማይገናኝ ሐሰት ነው፡፡ ብሔርን፣ ብሔረሰብንና ሕዝብን እንወክላለን የሚሉ “የብሔር ፖለቲከኞች” ያፀደቁትና ቀስ በቀስ “የዘረኝነት ሥርዓት” በአገራችን የተከሉብን መዘዝ እንደሆነ ያለፉት 30 ዓመታት ምስክር ናቸው፡፡ ከሁሉም የከፋው ደግሞ፣ ሕገ መንግሥቱ በተለይም አንዳንድ አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾቹን (ለምሳሌ አንቀጽ 39) በቀላሉ እንዳይሻሻሉ ተብትቦ ማሰሩ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሚደነገግበት አንዱ ዋና ምክንያት በዜጎች መሀል ብሔራዊ ስሜትንና መግባባትን እያዳበረ፣ የሕግ የበላይነትን እያስከበረ፣ አገርን በጋራ ለመገንባትና ለማሳደግ መሠረት እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ግን እንኳን ብሔራዊ መግባባት ሊፈጥርና አገር ለመገንባት ሊያግዝ ቀርቶ፣ ሆነ ተብሎ ዜጎችን ለማራራቅና ለመከፋፈል ብሎም ካስፈለገ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የታቀደ ሴራ እንደሆነ በተግባር ባለፉት 30 ዓመታትና በቅርቡም በትግራይ ጦርነት በግልጽ ታይቷል፡፡
የሚገርመው ታዋቂው አንቀጽ 39 ራሱ “የብሔሮችን የራስን በራስ የማስተዳደርና የመገንጠልን መብት ጨምሮ” የሚለው፣ መብት በሕገ መንግሥቱ የተካተተው በቀላሉ ከማይቀየሩት በምዕራፍ ሦስት (“መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች”) ከገቡት አንቀጾች ጋር ተሰንቅሮ ነው፡፡ ይህንን አንቀጽ ለማሻሻል ለዚያውም ከተቻለ ብዙ ውጣ ውረድ አለው፡፡ በአሁኑ ሕገ መንግሥትና በብሔር (ዘር) ላይ በቆመው “የፌዴራል አወቃቀር” እሱን ለመንካትና ለማሻሻል በጣም አዳጋች ነው (አንቀጽ 104 እና አንቀጽ 105ን ይመልከቱ)፡፡ በአጠቃላይ ከሕገ መንግሥቱ በርካታ መሻሻል የሚገባቸው አንቀጾችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እሱን ለማድረግ ግን የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሙያዬም አይፈቅድልኝም፡፡ ከተሳካልኝ “ለብሔራዊ ምክክሩ” እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ሐሳቤን አቀርባለሁ፡፡ አሁን የሚያስጨንቀኝ “ብሔራዊ ምክክሩስ” ቢሆን ራሱ ይካሄዳል ወይ የሚለው ነው፡፡ አንድ ለአገራችን ሰላምና ህልውና የቀረን መፍትሔ እሱ ብቻ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እሱም አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ በአገራችን በሙሉ ሰላምና መረጋጋት በጊዜያዊ መልክ እንኳን ካልሰፈነ፣ እንዴት ብሎ “ብሔራዊ ምክክር” እና ሕዝባዊ ውይይት ማድረግ እንደሚቻል አንዱ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፡፡
የ“ፌዴራል” አወቃቀሩ
የ“ብሔር ፖለቲካው ሕገ መንግሥት” አንዱ ዋና በአገራችን ላይ የፈጠረው ጦስ፣ የብሔር ጥያቄን ጭራሽ በአገራችን ለዘመናት ገና ዘላቂ መፍትሔ ካልተገኘለት “ከመሬት ጥያቄ” ጋር ማወሳሰቡና መተብተቡ ነው፡፡ ለዚያም ነው አንዱም መፍትሔ ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ የሚያደርገው፡፡ ሕወሓት አገሪቱን በብሔር (ዘር) ከከፋፈለ በኋላ፣ ክልል በሚል ስም መሬቷን በመሸንሸን አድሎ፣ “ይኸውላችሁ እንደ ፈለጋችሁ አስተዳድሩ” ሲላቸው፣ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ እነዚህ የ“ክልሎች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች” ፖለቲከኞች አንዳንዶቹ ወሰናቸውን ለማስፋፋት፣ ሌሎቹ በድንበርና በግዛት በመጣላት ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨታቸውን ቀጠሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የአገሪቱን ዋና ከተማ ምናልባትም ከ80ዎቹ “ብሔሮችና ብሔረሰቦች” የመጡ ዜጎች ያለ ሥጋት በሰላምና በፍቅር ተዋህደው የሚኖሩባትን አዲስ አበባን “ፊንፊኔ የእኛ ክልል ሀብት” ናት የሚሉ ተነሱ፡፡ ገና ከጅምሩ የሕወሓት መሪዎች ኢትዮጵያን ማስተዳደሩ አንሷቸው ለመጠባበቂያ የራሴ የሚሉትን የትግራይን ክልል አስፋፍተው፣ ተከዜን ተሻግረው፣ ወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን፣ እንዲሁም ከላይ ራያን በጉልበት ነጥቀው “ሕገ መንግሥቱ የሰጠን” የእኛ ሀብት ነው ሲሉ ነው ነገር የተበላሸው፡፡ ለዘመናት በሰላም አብረው ጎን ለጎን የኖሩትን ሁለቱን ሕዝቦች፣ አማራንና ትግራይን ደም አቃብተው ለመለያየትና አገራችንን ለማፍረስ ስንት ወጣት አስጨረሱ፡፡
ስለዚህ የኋላቀር ሥርዓት መቆሚያ የሆነውና ፍትሕ የጎደለው ሕገ መንግሥትና “የፌዴራል ክልል አወቃቀር” የተተከሉት፣ በዋነኝነት በአገራችን ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ ወይም “ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ” ታስቦ ሳይሆን፣ አገሪቱን በዘርና በብሔር በክልል ከፋፍሎ፣ በሥልጣን እስካሉ ድረስ መሬትና ሀብት ያለገደብ እየዘረፉ ለመግዛት፣ አለዚያም ካልተቻለ የራስን ሰፊ ክልል ወይም ብሔር ይዞ ለመገንጠል ነው ቢባል ከእውነት የራቀ ሚሆን አይመስለኝም፡፡ ለእዚህ ነው በብሔር ፖለቲካና በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተው “የፌዴራል ሥርዓት” ተብየው የክልል አስተዳደር መዋቅርም፣ ዛሬ ጭራሽ የአገሪቱን ህልውና እየተፈታተናት ያለው፡፡
ሕወሓት (ኢሕአዴግ) ኢትዮጵያን ለ27 ዓመት በገዛበት ወቅት “ብሔሮችና ብሔረሰቦች” የተባሉት ራሳቸውን በራሳቸው ሊያስተዳድሩ ቀርቶ፣ በላያቸው ላይ የአንድ ብሔር የገዥ መደብ (የሕወሓት) ወኪሎች በፓርቲ ስም እየተመደቡላቸው፣ የራሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ በአምባገነንነት የሚገዙና የክልሉንና የሕዝቡን መሬትና ሀብት የሚዘርፉ ነበሩ የሚያስተዳድሯቸው፡፡ የሚያሳዝነው ባለፉት አምስት ዓመታት ሕወሓት ከማዕከላዊ ሥልጣኑ ተወግዶም ስርቆቱ፣ የአገሪቱን ሀብትና መሬት መዝረፉና በሕዝቡ ላይ ግፍ መሥራቱ ሊቆም ቀርቶ ጭራሽ ባሰበት፡፡ የሕወሓት ተማሪዎች ተተኩበት፡፡ አዲሱ የብልፅግና ፓርቲም “ከብሔር ፖለቲካው” (“ዘረኝነት ሥርዓቱ”) ሊላቀቅ አልቻለም፡፡ ሕዝቡ እንደዚያ የጓጓላትን ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት፣ ትክክለኛውን አቅጣጫ መያዝ አልቻለም፡፡ ዛሬ ሕዝቡ በእሱም ተስፋ እየቆረጠ ነው፡፡ እንደ ሕወሓት ጊዜው ሳይመሽበት በቆራጥነት ተነሳስቶ አቅጣጫውን ያስተካክላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ አለዚያ እሱም የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል፡፡
“የብሔር ፖለቲካውንና ዘረኝነቱን” አስወግደን ኢትዮጵያ አገራችንን በአገር ፍቅር ስሜት በጋራ ለመገንባት መፍትሔው ምንድነው? ምን ማድረግ ይሻለናል?
በሚቀጥለው ጽሑፌ (ክፍል ሦስት) ይህን ትልቅ አርዕስት በተለይም በሕገ መንግሥቱና “በፌዴራል ሥርዓቱ” ዙሪያ ላይ በማተኮር በምችለው አቅም ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያ ግን አጠር አድርጌ የሚከተሉትን መንደርደሪያ ሐሳቦች በትህትና አቀርባለሁ፡፡
- 1. የ”ብሔራዊ ምክክሩ” ስኬታማ እንዲሆን በሚገባ መምራትና ሕዝቡን በሰፊው ማሳተፍ፣ በተለይም መንግሥት በቆራጥነት፣ በቅንነትና በግልጽነት ምክክሩ እንዲሳካ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ከልቡ መሥራት ይኖርበታል፣
- በሕገ መንግሥቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ፣ ካለፈው ስህተት በመማር፣ ሕዝቡ ያለ ፍርኃት በነፃ እንዲወያይበት ማድረግ፣
- 3. በክልሎች መሀል አወዛጋቢ የሆኑትን የማንነትና የመሬት ጥያቄዎች፣ በሰላምና በውይይት፣ በሕዝቡ በራሱ ፈቃድ እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ብሔራዊ ምክክሩን “የብሔር ፖለቲከኞች” ከሕዝቡ ጠልፈው እንዳያመክኑት መጠበቅ፣
- 4. በ”ፌዴራል” (ክልል) አወቃቀሩ ሕዝቡ በሰፊው እንዲወያይበትና ሐሳቡን እንዲሰጥበት ማድረግ፣ የአገሪቱን መሬት “በብሔር ብሔረሰብ መከፋፈሉ” ተሻሽሎ ለአገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ለጋራ ዕድገትና አንድነት፣ “ኅብረ ብሔርና ፌዴራል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ”ን ለመገንባት አመቺ የሆነ ፍትሐዊ የክልል አስተዳደር እንዲመሠረት ተግቶ መሥራት፣
- 5. “ሕገ መንግሥቱ አይነካም ወይም ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት የሚሉትን ሁለት ጫፍ ይዘው “ገመድ የሚጎትቱትን” ማዳመጥ ትተን፣ “ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል” በሚለው አቋም እንፅና፡፡ በ230 ዓመት ዕድሜው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ሳይቀየር 27 ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ ከማሻሻያዎቹ አንዱ (Amendment 13) ባርነትን በአሜሪካ ያስቀረው አንቀጽ ነው፡፡ ሕዝባችን ከተስማማ በኢትዮጵያም ሕገ መንግሥቱ “ፖለቲካ በብሔር፣ በሃይማኖትና በዘር ጣልቃ እንዳይገባ” ወስኖ በአገር ላይ ብቻ ያተኮሩ፣ አገር አቀፍና ኅብረ ብሔር የሆኑ ፓርቲዎች እንዲመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ መሻሻል (Amendment) ራሱ ትልቅ ዕፎይታና ሰላም በአገራችን ያሰፍናል፡፡
እነዚህን ሐሳቦች በክፍል ሦስት ለማብራራት እሞክራለሁ፣ በደህና ቆዩኝ፣ እስከዚያ ለአገራችን ቸር ወሬ ያሰማን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ! ሰላም ያውርድልን!
ከአዘጋጁ፡፡ ጸሐፊው “በአገር ፍቅር ጉዞ መጽሐፍ ደራሲ” ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡