Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አገር ድንበር ብቻ ሳይሆን ታሪክ ጠባቂም ያስፈልገዋል›› ሹመት ሺሻይ (ፕሮፌሰር)፣ የታሪክ መምህር

በአሜሪካ ለ25 ዓመታት ያስተማሩት የታሪክ ምሁሩ ሹመት ሺሻይ (ፕሮፌሰር)፣ የዛሬ ስድስት ዓመት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ሲሆኑ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ታሪክን ማዕከል ስላደረገው የፖለቲካ ውዝግብ ምሁራዊ ዕይታቸውን አጋርተዋል፡፡ ከዚህና ከሌሎችም የታሪክ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ዮናስ አማረ ፕሮፌሰሩ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ታሪክን መሠረት በማድረግ የፖለቲካ ቁርቁስ  የተለመደ ነው፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? መነሻውስ ምንድነው?

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- ወደኋላ ተመልሶ የዚህን ምክንያት ማፈላለግ ይጠይቃል፡፡ አውሮፓዊያን ‹‹አፍሪካዊያን ታሪክ የላቸውም›› ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ቀደም ያለ ሥልጣኔና የአገረ መንግሥትነት ባህል ያላት መሆኑ፣ እንዲሁም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ልክ እንደ እነሱ መንግሥታዊ ተቋማትን መገንባት መጀመሯ አውሮፓዊያኑን አልተመቻቸውም፡፡ ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ያላት አገር ናት የሚለውን መቀበል ባለመፈለግም ይህን የሚክዱ ብዙ የተዛቡ ታሪኮች ጽፈዋል፡፡ በዓድዋ ጊዜም ሆነ ከዚያም በፊትና በኋለኛው ጊዜ በጣሊያን ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የሌላት መሆኑን ጽፈዋል፡፡

ታሪክ መጋጫና መወዛገቢያ የሆነበት መነሻው ምንጩ ከዚያ የተቀዳ ነው፡፡ በተለይ ለብሔር ነፃነት እንታገላለን የሚሉ ቡድኖች ብዙዎቹ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለማቸውን የተዋሱት ከተዛቡ የአውሮፓ የታሪክ ጸሐፊዎች ነው፡፡ አንዳንዶቹ ቃል እንኳን ሳይቀይሩ ከአውሮፓ መጻሕፍት ተቀድተው የመጡ ነበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት ያልነበራቸውና የኢትዮጵያን የቆየ ህልውና የማይቀበሉ የአውሮፓ ጸሐፍት ተፅዕኖ ያረፈበት ፖለቲካችን መወዛገቢያ የሆነው በዚህ የተነሳ ነው፡፡

የነበረውን አፍርሰን አዲስ አገር እንሠራለን የሚሉ ኃይሎች የተፈጠሩት በተውሶ ሐሳብ ነው፡፡ አሁን ያለውን ለማፍረስ ወደ አውሮፓዊያኑ የታሪክ ውሰት የሚሄዱት ለዚህ ነው፡፡ ያኔ ልክ ጦር እንዳዘመቱብን ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይም ዘመቻ ተከፍቶበት ነበር፡፡ አሁን ያሉ ፀረ ኢትዮጵያ ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የእኛው ወገኖች ደግሞ ያንኑ ተውሰው ነው ፖለቲካ የሚያራምዱት፡፡

የኢትዮጵያ የአገር ምሥረታ ታሪክ እንደ አብዛኛው የዓለም አገሮች ምሥረታ ታሪክ ነው፡፡ ማንኛውም የተሳካለት አገር ታሪክን የሚመስል ነው፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመንም ሆነ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አገር በሪፈረንደም ሲመሠረት አይታወቅም፡፡ በአብዛኛው በጦር ዘመቻ የሚፈጠር ነው፡፡ የተለያዩ ሕዝቦችን ወደ አንድ አምጥቶ በአንድ አገረ መንግሥት ሥር የማኖር ጉዳይ ኃይል የቀላቀለ ዘመቻን መጠየቁ የማይቀር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የተመሠረተ አገር የለም፡፡ አውሮፓም ሆነ ሌላ አካባቢ ኃይል መጠቀም ግድ ያለበት የታሪክ አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

በኢትዮጵያም ውስጥ የተደረገው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የጦር ዘመቻዎች ነበሩ፡፡ የተለያዩ አካባቢዎችንና ሕዝቦችን በአንድ አስተዳደር ሥር ማምጣትም ይጠይቅ ነበር፡፡ ነቀፋው ከአመሠራረቱ የመነጨ ሳይሆን፣ የተቀበልነው ሰዎች የተቀበልነውን ወግ ማስያዝና ተቀባይነት እንዲያገኝ አለማድረጋችን ነው ችግሩ፡፡ ለምን በዚህ መንገድ አገረ መንግሥቱ ተመሠረተ የሚባለው ግን የሞኝ ጥያቄ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታሪክን የፖለቲካ መታገያ ማድረጉ ያለፈ ቁስልን ተመልሶ በማከክ ለፖለቲካ ማዋል ምን ዓይነት የፖለቲካ አደጋ አለው?

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- ከፍተኛ አደጋ አለው፡፡ ታረክ የማያቋርጥ ውይይት ውጤት ነው ይባላል፡፡ አንድ ጊዜ ተነግሮ የሚያበቃ ወይም የተፈጸመ ታሪክ የሚባል ነገር የለም፡፡ ታሪክ በየጊዜው የሚጎበኝ ነው፡፡ በየጊዜው እየተከለሰም የተሳተው እየተቃና፣ የጎደለው እየተጨመረና የተጣመመው እየተስተካከለ በየጊዜው እየተስተካከለ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ የአገረ መንግሥቱ ግንባታም ከዚህ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ የአገር ግንባታውም ብዙ ጉድለቶች ሊኖሩበት፣ ብዙ ህፀፆች ሊገኙበትና ለማስተካከልም ብዙ ጉልበት ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን በማያቋርጥ ለውጥ በሒደት ማሻሻል ይቻላል፡፡

ድሮ በኃይል የመጣው የበለጠ ሰብዓዊነትና ሥርዓት እየተላበሰ እንዲሄድ ይደረጋል፡፡ በሒደት በሐሳብና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ወደ መሆን ይሸጋገራል፡፡ ነገር ግን ታሪክን መጨቃጨቂያ ካደረግነውና ቀደም ሲል የነበረ ቁስልን በማከክ ቁርሾውን ካሰፋነው ችግራችን ከመሻሻል ይልቅ ይባባሳል፡፡ በስንት ጣርና ምጥ የተፈጠረን አገር ዳግም ስናፈርስ እንደገና ሌላ ዙር መስዋዕትነት ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አገር ለመመሥረት የተደረጉ ጦርነቶችን እንወቅሳለን፡፡ ነገር ግን አገረ መንግሥቱን ስናፈርስ ዳግም ሌላ ዙር ጦርነት ይደገም እያልን ነው፡፡ ለሌላ ቁስልና ለሌላ ኪሳራ ራሳችንን እያዘጋጀን ነው ማለት ነው፡፡

ማንም አገር ያለፈበትን የአገረ መንግሥት ምሥረታ ሒደት በማነወር ለሌላ ዙር ኪሳራ መዘጋጀት አደገኛ ነው፡፡ ይህን የአገረ መንግሥት ሒደት የሚያነውሩት ወገኖች የተሻለ ሰብዕና የላቸውም፡፡ ያኔ ሰው ሞተ እያሉ ቢጮሁም እነሱ በዚህ ዘመን ሰው ዘቅዝቀው ሲሰቅሉ እናያለን፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ ሰቆቃ የሚፈጽሙ ኃይሎች ያለፈውን ታሪክ እያነሱ መውቀሳቸው ፍፁም የሚጋጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ናት፡፡ ከዚያ ውስጥ አብዛኛው ሥራ አጥ ወጣት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አገር አስታሞ የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከመሥራት ይልቅ፣ ባለፈ ታሪክ መቆራቆስ ለዕልቂት ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡

አገር ፈርሶ ራሱን አያድስም፡፡ አገር ለመፍጠር ብዙ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይ ያለፈውን ዘመን የሚወቅሱ አሁን ያሉ ፖለቲከኞች ሊያዩት የማይፈልጉት ነገር አገር በምጥ መወለዱን ነው፡፡ አንዴ ተገላገልን ያለውን እያሻሻሉ መሄድ ይሻላል ስንል፣ እያፈረሱ ሌላ ዙር አገር ልገንባ ማለት ለከፋ ቀውስ ይዳርጋል፡፡ ለማያባራ ቀውስ አገሪቱን እያዘጋጁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የማያስማሙ ትርክቶች አሉ፡፡ አንዱ ከንግሥተ ሳባ ይነሳል፣ ሌላው የ150 ዓመት አገር ያደርጋታል፣ የብሔር ፖለቲካ ወይም ሃይማኖት አላብሶ የሚያቀርብም አለ፡፡ የጋራ ትርክት መፍጠር ለምን አልተቻለም?    

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- የጋራ ትርክት እንዳይኖረን ያደረጉት በኢትዮጵያ ላይ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ናቸው፡፡ ያለፈ ታሪክን አምጥተው አሁን ላይ ለራሳቸው ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ያለፈውን ገልብጠው ስለሚያቀርቡ ነው፡፡ በጋራ ትርክት መስማማት ያቃተን ውይይቱን እየመሩት ያሉት በታሪክ ፖለቲካ ላይ የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ የሚፈልጉ ኃይሎች በመሆናቸው ነው፡፡

ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት ያለፈ ታሪክ የላትም ይላሉ፡፡ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ተይዘን ቆይተናልና ሌሎቹ ነፃ ከወጡ እኛም ነፃ መውጣት አለብን የሚል እንቅስቃሴ አንዳንዶቹ ያደርጋሉ፡፡ የኢትዮጵያን የአገረ መንግሥት አመሠራረት ከአውሮፓው ኢምፔሪያሊዝም ጋር እንዲገጣጠም ለማድረግ ሁሉ ጥረት ይደረጋል፡፡

ይህ ያለመታደል ፖለቲካ የፈጠረብን ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ያለውን ተክለ ቁመና ይዛ እንድትኖር ለማድረግና በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ለመፍጠር በተደረገው ረዥም የታሪክ ሒደት፣ የእነዚህ ኃይሎች አባቶች ጭምር ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ አገር መሆንም ሆነ ራስን ከሌሎች ጥቃት ተከላክሎ ህልውናን አፅንቶ ለብዙ ዘመናት ለመኖር በዘፈቀደ የሚገኝ ነገር ሳይሆን ታላቅ መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ብርቱ ዕቅድ፣ መዋቅርና ሥልት የሚጠይቅ ጥረት ነው፡፡

የተለያየ ቋንቋ የምንናገር፣ የተለያየ ባህል ያለንና ከተለያየ ዋሻ የወጣን ሕዝቦች አንድነት መፍጠር መቻላችን ደግሞ ትልቅ ጥንካሬ ነው የሰጠን፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉና በየጎጡ የቀሩ ማኅበረሰቦች ግን የውጭ ኃይል መጫወቻ ሆነው ነው የቀሩት፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ ራሷን ማስከበር የቻለችው ያን ዝግመተ ለውጥ አልፋ አገረ መንግሥት ቀድማ በመፍጠሯ፣ አንድነትና ጥንካሬን በማምጣቷ ነበር፡፡ ይህን ያላሳኩ 90 በመቶ የአፍሪካና የእስያ አገሮች ግን የቅኝ ግዛት ቀንበር አርፎባቸዋል፡፡ እርስ በእርስ የተከፋፈሉ ነበሩ፣ ከመንደር ወጥተው ሁሉንም የሚያቅፍ መዋቅርና አገር አልፈጠሩም፡፡ በዚህ የተነሳ በቀላሉ የሌሎች ምርኮኛ ሆነዋል፡፡ ይህን ፈተና ያለፈች አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ይህ እንደ ነውር ተቆጥሮባት ታሪኳ ዳግም መዋጊያና መሟገቻ እንዲሆን ማድረግ የሚያስቆጭ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንዳለመታደል ሆኖ ይህን ዓይነት የታሪክ ውዥንብር ሊቋቋም የሚችል መዋቅር የላትም እንጂ፣ ይህ ዓይነቱ ችግር በሌሎች አገሮችም የተለመደ ነው፡፡ በየትም አገር እንዲህ ያለ የታሪክ ንትርክ ሲከሰት ማዕከሉ እንደ ፀና እንዲቆይ የሚዳኝ ወገን አለ፡፡ መሀል ቆሞ ለአገር አንድነት መፅናት የሚታገል መንግሥት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ለየት የሚለው የትም አገር አጋጥሞት በማያውቅ ሁኔታ፣ አገሪቱ ትፍረስ የሚል ኃይል ለ30 ዓመታት አገር መምራቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ዋና ጉዳይ የሆነው ኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት በላይ ታሪክ የላትም የሚለው ኃይል አገር በመያዙ ነው፡፡ የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው የሚል ኃይል ነው አገር ሲመራ የቆየው፡፡  

ሕዝቦች አንድ የሚሆኑት መጀመሪያ በጦርነት ቢሆንም በሒደት ግን የሚያግባቡ ትርክቶችን እየፈጠሩ በመሄድ ነው፡፡ ይህን ደግሞ መንግሥት ነው ዋናው ሥራው አድርጎ የሚሠራው፡፡ በአውሮፓ ብናይ የአንድነት ጦርነት ከተደረገ ወዲህ መንግሥታቱ፣ በትምህርት ሥርዓት ጭምር ሥራዬ ብለው ታዳጊዎችን ከታች ጀምሮ ስለአገር አንድነት በማስተማር ነው ጠንካራ አገረ መንግሥትን መፍጠር የቻሉት፡፡ የአንድነት ስሜት የሚፈጥሩት፣ የዜግነትና አገር ወዳድነት ስሜት እየገነቡ የሚመጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ይህን የሚሠራው ደግሞ ራሱ መንግሥት ነው፡፡

ለምሳሌ ጣሊያን አገር የሆነችው እ.ኤ.አ. በ1860 በጦርነት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሮም፣ ኔፕልስ፣ ፍሎረንስ፣ ጄኖዋና ሌሎች የተበጣጠሱ ትንንሽ ግዛቶች (ፕሪንሲፓሊቲስ) እንጂ አንድ ጣሊያን አልነበረችም፡፡ አገሩን ከፈጠሩ ወታደሮች አንዱ ጣሊያንን ፈጥረናል፣ አሁን የቀረን ጣሊያናውያንን መፍጠር ነው ይል ነበር፡፡ ይህ ማለት አንድ አገር ከተፈጠረ በኋላ አገር ወዳድ የሆኑና አንድነታቸው የተጠናከረ ዜጎችን ለመፍጠር ሥራ ሊሠራ ይገባል ማለት ነው፡፡ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን ወይም ጀርመን ቢባል በታሪክ ወደ አንድነት የመጣ አገር ነው፡፡ የጦር ሥራው ካለቀ በኋላ አንድነታቸውን የሚያጠናክር ሥራ በታቀደ መንገድ በመሥራትና በማስተማር ያመጡት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ይህ ነገር ሊደረግ ቀርቶ የተሻለ ትምህርትም እንዳይሰጥ ለ30 ዓመታት ተከልክሎ የቆየበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሁን የምናየው ውጥንቅጥ የዚህ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ የተፈጠረው በውጭ ኃይሎች አሻጥርም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው የጎረቤት አገሮችና የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያ አንድነት እንዳይፀና ብዙ ሥራ ሠርተውበታል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተም ጀምሮ የምናያቸው በአገር ውስጥ ያሉ አለመረጋጋቶች የዚያ ውጤት ናቸው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄዎች ወደ ሽፍትነት መቀየራቸው ከውጭ የመጣ ተፅዕኖ ውጤት ነው፡፡ ከኤርትራ ጀምሮ እስከ መሀል አገር የተነሱ የብሔር ጥያቄዎችን ተገን ያደረጉ ግጭቶች ምንጫቸው ከውጭ በሚገኝ ስፖንሰርሺፕ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ታሪክ የእኛን ታሪክ አያቅፍም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የጋራ ታሪክም ሆነ የጋራ ጀግና የለንም የሚሉ አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ገናና ሆኖ የሚቀነቀነው ትርክት አይወክለንም የሚሉም አሉ፡፡ እርስዎ ታሪክ እንደሚያጠና ሰው የጋራ የሆነ የታሪክ አሻራ የለም ይላሉ?

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- ይህ ቁንጽልነት ነው፡፡ አገርን አንድ ቋንቋና ባህል ብቻውን ሊመሠርተው አይችልም፡፡ የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት ታሪክ ካየን ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ኅብረ ብሔራዊ የሆነ መንግሥት ነው፡፡ በድንጋይና በብራና ላይ የተጻፉ ብዙ ማስረጃዎች አቆይተውልናል፡፡ አንድ ቋንቋና ባህል ብቻ ሆኖ ቀረ ሳይሆን፣ በየጊዜው እያደገና አዳዲስ ማንነቶችን እየጨመረ እንደተስፋፋ ብዙ መረጃ አለ፡፡ እንኳን የኋለኛው የ19ኛውና የ20ኛው ክፍለ ዘመን ይቅርና ከአክሱም ጊዜ ጀምሮም ቢሆን ኅብረ ብሔራዊነት የነበረው ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአንድ ቋንቋና ማንነት ላይ ብቻ የተመሠረተ አገረ መንግሥት በታሪክ አልነበራትም፡፡ የአገረ መንግሥት ግንባት ሒደት ልክ እንደ ታላቁ ወንዝ ዓባይ ፍሰት ሊመሰል ይችላል፡፡ ዓባይ ከምንጩ ሰከላ ላይ እረኞች የሚዘሉት ወንዝ ነው፡፡ ወደ ታች ሲወረድ ግን ዓባይ ግዝፈቱም ሆነ ጉልበቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ታላቁን ዓባይ ዓባይ ያስባለው በየቦታው ያሉ ወንዞችና ጅረቶች ተቀላቅለው ነው፡፡ ዓባይን በምንጭ ልንመስለው አንችልም፡፡ ዓባይን መጀመሪያ በሚታየው ምንጭ እንደማንመስለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያንም መነሻው ላይ በነበረው ውስን ማንነት አንለካም፡፡ የኢትዮጵያ ማንነትም ልክ እንደ ዓባይ ሁሉ በየአቅጣጫው መጋቢ ያለው፣ ብዙ ሕዝቦች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ተዋህደው የተፈጠረ ሰፊና ጠንካራ ማንነት ነው ማለት ነው፡፡

ይህ ሕዝብ በረዥም ጊዜ ታሪክ፣ በጦርነት፣ በንግድም በጋብቻም ለመለየት ከሚቻለው በላይ የተቀላቀለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጽሑፍ ታሪክ ከተጀመረበት ከ2000 ዓመት ጀምሮ ያለውንና የጽሑፍ መረጃ የምናገኝበትን ጊዜ ብቻ ስንናገር ነው፡፡ ከዚያ በፊት ያለውን የታሪክ ኡደት እናካት ብንል ደግሞ የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊነት ጥልቅ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ማስረጃ የኮሰሰ በመሆኑ አይደለም ዛሬ ቅቡልነት የለውም የሚባለው፡፡ ይህን ሁሉ ማስረጃ ለመቀበል ስለማይፈልጉ ነው በየጊዜው እየፈበረኩ አዳዲስ ታሪክ የሚጽፉትና ሙግት የሚገጥሙት፡፡ በብሔር ነፃ አውጪዎችና በደጋፊዎቻቸው የተፈበረኩ ብዙ ታሪኮች አሉ፡፡ ሀቁን ማረጋገጫ ጠፍቶ ሳይሆን ታሪክን ፖለቲካ ስላደረጉት ሆን ተብሎ የሚፈጠር ነው፡፡

አንድን ቡድን የሚያስደስት፣ ለአንድ የፖለቲካ ኃይል እርካታ ወይም የፖለቲካ ትርፍ የሚሰጥ ሆኖ ታሪክ ይቀርባል፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው መካከል ላይ ሆኖ ሀይ ባይ በመጥፋቱ ነው፡፡ ሊዳኝ የሚገባ መንግሥት ወይም ሥርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ አለበለዚያ አገር የለንም ማለት ነው፡፡ አገር ጠባቂ ያስፈልገዋል፡፡ የሚጠበቀው ደግሞ የአገር ድንበር ብቻ ሳይሆን ታሪክም ጭምር ነው፡፡ ልብ ያላቸውና ሀቀኛ መሪዎች አገር ጠባቂ ከሌለው የሚመጣውን አስከፊ ውጤት በደንብ ያውቁታል፡፡ የሚገዙት ኅብረተሰብ እርስ በእርሱ እንደ ውሻ ሲናከስ ዳር ቆሞ ዝም አይባልም፡፡ መሀል ገብተው መዳኘትና ሕዝቡን ወደ ልቦናው መመለስ ሥራቸው ነው፡፡

ብዙ አገሮች ሀብታቸውን ወደ አንድ የሰበሰቡትና አገር የለወጡት ሕዝቡን ከመበታተን ወደ አንድ በመሰብሰብ ነው፡፡ እኛ ጋ ግን የማዕከል ወይም የጋራ ሀብት የሆነውን አገር ለማፈራረስ ሥራ እየዋለ ይገኛል ብዬ ነው የምገምተው፡፡

 

ሪፖርተር፡- አንድ ማኅበረሰብ የእኔ ባህል፣ ቋንቋ፣ ማንነትና እሴት ከሌላው እኩል ሊወከልልኝ ይገባል ቢል ይህን ለማድረግ በኢትዮጵያ አመቺ ዕድል አለ?

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- ሁሉም እንዲወከል፣ በተለይ የጥቅምና የመብት መበላለጥ እንዳይፈጠር ተብሎ እንደ ኢትዮጵያ ያህል ሥር ነቀል ለውጥ የተካሄደባት አገር በዓለም ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በመሬት ሥሪት ብንመለከት፣ በባህል እኩልነት ብንመለከት፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትም ሆነ በአስተዳደር ብንመለከት በኢትዮጵያ ብዙ ተራማጅና ሥር ነቀል ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በ1960ዎቹ ከተካሄደው የወጣቶች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጀምሮ ብዙ ሥር ነቀል አብዮቶች በኢትዮጵያ ተካሂደዋል፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ በተለይ በመሬት ሥሪቱ ላይ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት የታወጀው የመሬት አዋጅ በዓለም ላይ በተራማጅነት አቻ አለው ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ሁሉ የተደረገው ከዚያ ቀደም እኩልነት አልነበረም፣ የሕዝቦች መከፋት አለ በሚል  ችግሩን ለማስተካከል ንቃቱን ያዳበረ ወጣት በሙሉ በተሳተፈበትና ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ በመጣ ሥር ነቀል ለውጥ የተነሳ ነው፡፡ ያን ያመጡት ኢትዮጵያዊ ነን ብለው የሚያምኑና ለኢትዮጵያ መቃናት መስዋዕት ለመክፈል የተዘጋጁ ወጣቶች ነበሩ፡፡

አሁን ያንን ረስቶ ምንም እንዳልተደረገ ከአዲስ ሀ ብሎ ሌላ ዙር ሰቆቃ ለመፍጠር ሲሞከር ነው የሚታየው፡፡ ያ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ በዚያ ላይ ለመጪው ዘመን የሰመረ ሥራ እንሥራ ቢባል ጥፋት አልነበረውም፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው መተፋፈግና መገፋፋት ከዚያ ይልቅ ያለፈውንም ሆነ የወደፊቱን የሚያበላሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ የታሪክ ጉዳዮች አለመግባባት የሚፈጠረው ከታሪክ አጠናን፣ ከምሁራኑ ወይም ከትምህርት ተቋማቱ በመነጨ ችግር ነው ይባላል፡፡

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- ችግሩ የአመለካከት ነው፡፡ እኛ ታሪክን የምናይበት መንገድ እንጂ ታሪክማ አንዴ ሆኖ ያለፈ ነው፡፡ መሠራት ያለበት በእኛ ግንዛቤና አዕምሮ ላይ እንጂ ታሪክ አንዴ ሆኗል ሊቀየር አይችልም፡፡ ለምሳሌ የ19ኛው ክፍለ ዘመንን ሁኔታ መተቸትና አሁን ላይ አምጥቶ የፖለቲካ መነታረኪያ ማድረግ የታሪክን ምንነት አለመገንዘብ ነው፡፡ መጪውን ጊዜ ለመቅረፅ ምን ላይ መመርኮዝ አለብን የሚለውን ከመሳት የሚመነጭ ነው፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የነበሩ ሰዎችን ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መለኪያ አንዳኛቸውም፡፡ በጊዜው በኢትዮጵያ የነበረውን ሒደት ከሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር በማነፃፀር የሚጎድለውንና የሚሻልበትን ነገር ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የእኛ ትልቁ ችግራችን በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዕይታ መነጽር ያለፈውን ዘመን መመልከት ሲሆን፣ ይህን ማድረጉ ደግሞ ትልቅ የታሪክ ስህተት ነው፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች ሌሎች ሰዎችን ይጨቁኑ ነበር፣ ያስሩና ያሰቃዩ ነበር የሚለው ሙግት የታሪክን ምንነት ካለመረዳት የመነጨ አስተሳሰብ ነው፡፡ በጊዜው ያን ማድረግ ነውር ላይሆን ይችላል፡፡ ነውር የሚሆነው እኛ ከዚያ ሳንማር ያለፈውን ዓይነት ስህተት ዛሬ እንፈጽም ያልን እንደሆነ ነው፡፡ እኛ ዛሬ ማድረግ ያለብን የ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች ያላደረጉትን ነው፡፡ ያለፉ ዘመን ሰዎች ሆን ብለውም ሆነ በስህተትና በግንዛቤ ዕጦት ያልተሟላ፣ ሁሉንም የማይወክል፣ የተዛባና የተሳሳተ ታሪክ አስተላልፈውልን ከሆነ ተመልሶ ታሪኩን መከለስና ማስተካከል ነው ያለብን፡፡ ታሪክ የማያቋርጥ ውይይት ነው ብያለሁ፡፡ የተሻለ መረጃ በእጃችን በሚገባ ጊዜ የሚጻፈውን ታሪክ እያሟላን መሄድ እንችላለን፡፡

ነገር ግን ታሪኩ እኔን አይወክልም ብለን ያለችውን ታሪክ ደምስሰን ከዜሮ እንጀምር የምንል ከሆነ፣ አውሮፖዎቹ አፍሪካዊያን ታሪክ አልባ ናቸው እንዳሉት ሁሉ ኢትዮጵያም ታሪክ አይኖራትም፡፡ ታሪክ በየጊዜው በምርምር የሚሻሻል፣ የተረሳውን በማስታወስና የተሳተውን በመጨመር የሚፈስ ጅረት ነው፡፡ የነበረውን ካላጠፋን የሚሉ ኃይሎች ግን ታሪክ አፍራሾች ናቸው፡፡ ይህም አውዳሚና ጥፋቱ ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን ዓይነት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነው የምንገኘው?

ሹመት (ፕሮፌሰር)፡- ፖለቲከኞቹ የሞዴል ቀውስ ይሉታል፡፡ አንድ ሲሠራበት የቆየ ሥርዓት አልሠራ የሚልበት ጊዜ ይኖራል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ከፍተኛ የግንዛቤ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ አሁን መላ ቅጡ የጠፋበት ጊዜ ላይ ነው የደረስነው፡፡ ትምህርትና ዕውቀት ባላደገበት እንደኛ ባለ ማኅበረሰብ ደግሞ እንዲህ ያለ ቀውስ እንዳይፈጠር ሥርዓት የሚያስጠብቀው፣ አቅሙና ጉልበቱ ያለው መንግሥት ነው፡፡ ወደ ተሻለ መንገድ አገር የሚመራውም እሱ ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ይህ የገጠመን ውጥንቅጡ የወጣ የሞዴል ቀውስ ከመሀል የራሱ ኃላፊነት ካለበት መንግሥት የመነጨ ነው፡፡ እኔ በግሌ እንደምታዘበው ቀውሱን ማረጋጋት ያለበት ኃይል (መንግሥት) ችግሩን ለመፍታት ወይ ቅንነቱ ጎድሎታል፣ አልያም አቅም አጥሮታል ማለት ነው፡፡

ይህ ሁሉ መታመስ በኢትዮጵያ ሲፈጠር የራሳችንን ጥቅም እናገኛለን ብለው የተሠለፉ የውጭ ኃይሎችም አሉ፡፡ መሀሉንም በመቀልበስ ሁኔታውን በማባባስ የተሠለፉ ኃይሎች ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከውጭ ተሠልፈዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ዋናው ይህን የሚመልሰው ግን ይህንን ከባድ ኃላፊነት የወሰደው አካል ነው፡፡ አሁን አገር የመምራቱን ኃላፊነት የተሸከሙ ኃይሎች ተወደደም ተጠላም እየሆነ ላለው ሁሉ ኃላፊነት መውሰዳቸው ግዴታ ነው፡፡ ከባድ ጫናም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ጫና ተቋቁመው ኃላፊነታቸውን በሀቅና ብዙ ጥፋት ሊከላከል በሚችል መንገድ ማስታመም አለባቸው፡፡ ነገር ግን አሁን በግሌ እሱን እያየሁ አይደለም፡፡ ኃላፊነትን በአግባቡ ከመወጣትና የአገር ህልውናን ከመታደግ ይልቅ፣ ቢፈርስ የተሻለ ጥቅም አገኛለሁ ወደሚል ዝንባሌ ያጋደሉ ይመስለኛል፡፡

ነባሩን የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ህልውና ለማፍረስ አሁን ብዙ ርብርብ ያለ ይመስላል፡፡ ይህ በርክቶ እየሆነ ያለው ደግሞ መሀል የቆመውና መዳኘት ያለበት ወገን ቸልታን ስለመረጠ ነው፡፡ መሀሉ ላይ ያለው ቆፍጠን ቢል ሁለት ሦስት ጊዜ የማሰብ ነገር ይኖር ነበር፡፡ ይህ ባለመኖሩ ግን አገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ የትም አገር ተደርጎ በማያውቅ መንገድና በከፍተኛ ድፍረት እየተካሄደ ነው የሚገኘው፡፡ እንደሚካሄደው የማፍረስ ጥረት አገሪቱ እስከ ዛሬ በፅናት በመቆየቷ እኔ እንዲያውም በጣም ይገርመኛል፡፡ ለረዥም ዘመናት ያቆየችው የህልውና እሴት ክምችት በመኖሩ እንጂ እስከ ዛሬ ባበቃላት ነበር፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...