Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በስንዴና ጤፍ ላይ የታየው የዋጋ ንረት መንግሥት የፈጠረው ነው ሊባል ይችላል!

ወቅታዊውን የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት አባብሰዋል ተብለው የሚመታኑ የተለያዩ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ ዓለም አቀፋዊው ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ መሆኑ ለአገራችን የዋጋ ንረት መባባስ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ሰበቦች አንዱ ነው፡፡ በእርግጥም በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ግብይቶችን ዋጋ አንሯል፡፡ 

የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ብቻ ሳይሆን የማጓጓዝና የሌሎች አገልግሎቶች ዋጋ ጨምሯል፡፡ ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ ኢትዮጵያም እንደሌላው የዓለም አገሮች ትጋራለች፡፡ ስለዚህ ወቅታዊውን የዓለም ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ላለው የዋጋ ንረት አንድ ምክንያት ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም ቢሆን ለዋጋ ንረቱ መባባስ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ተርታ ይደመራል፡፡ የጥቁር ገበያ መስፋፋትና ለአንድ ዶላር ከ100 ብር በላይ ዋጋ እየተሰጠ መሆኑም ሲታሰብ፣ የዋጋ ንረቱ ሰበቦች በርካታ ስለመሆናቸው ያመለክታል፡፡ 

በአገራችን ያለው እጅግ የተበላሸ የግብይት፣ ሥርዓትና ሕገወጥ ንግድም ለዋጋ ንረቱ መባባስ የየድርሻውን ይወስዳሉ፡፡ የባንኮች የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ ልጓም የሌለው ሆኖ መቀጠሉም ራሱ ከዋጋ ንረቱ መባባስ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ 

እንዲህ እንዲህ ያሉ ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት የሆኑ ክፍተቾችን ወይም ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙና በአጠቃላይም የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ አልተሳኩም ማለት ይቻላል፡፡ መንግሥትም ይህንን ያምናል፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንሰማቸው አንዳንድ ጉዳዮች ለዋጋ ንረት መንስዔ ብለን የምንጠቅሳቸውን ምክንያቶች ከፍ እያደረጉ መምጣታቸው ደግሞ ችግሩን እያወሳሰበው ነው፡፡ 

ለአዳዲሶቹ የዋጋ ንረት መንስዔ ደግሞ መንግሥት ሆኖ መገኘቱ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ እንደ ስንዴና ጤፍ ያሉ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው ሰሞናዊ የዋጋ ዕድገት በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ የመንግሥት እጅ አለበት። በመሆኑም መንግሥት የፈጠረው የዋጋ ንረት ሊባል ይችላል፡፡ የስንዴ ተትረፈረፈ በተባለበት ወቅት ገበያ ላይ እንደ ልብ ላለመገኘቱ አንዱ ምክንያት በዚህ ግብይት ውስጥ መንግሥት እጁን ስላስገባ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የስንዴን ገበያን በተመለከተ እየተተገበረ ያለው አሠራር ገበያውን በእጅጉ ረብሾታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ምርት ዙሪያ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪና እጥረት መንግሥት የተከተለው አሠራር በመሆኑ፣ የመንግሥት ውሳኔ ያስከተለው የዋጋ ንረት ነው ቢባልም ማጋነን አይሆንም፡፡

ከሰሞኑ እንደ ትልቅ አጀንዳ እየተነሳ ያለው የጤፍ እጥረትና እየተጠየቀበት ያለውም ዋጋ መናር ከመንግሥት አሠራር ጋር ይያያዛል፡፡ ምርቱ በተፈለገው መንገድ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ መደረጉ አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የጤፍ ዋጋ እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ፣ ሕገወጦች ገበያ ላይ ያለውንም እንዲሸሽጉ ምክንያት እየሆናቸው ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ምርት ይዘን ለመግባት አልቻልንም የሚሉ አቅራቢዎች መበራከት ብሎም ምርቱን ለማስገባት መንገድ ተዘጋብን የሚሉ ምክንያቶችን ሰምቶ መንግሥት የዕርምት ዕርምጃ ያለመውሰዱ ለዋጋ ንረት ምክንያት ሆኗል ብለን ለመደምደም እንገደዳለን፡፡ ‹‹አንዳንድ ምርቶች ፈቃድ ሳያገኙ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ተደርጓል›› መባሉ በራሱ በነፃ ገበያ ግብይት እንዳያካሂድ እየተደረገ መሆኑን የሚያሳይ ሆኗል፡፡   

በገበያ ውስጥ ዋጋ መወሰኑም ሆነ ምርት ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በነፃነት እንዳይጓዝ የሚያደርጉ ችግሮችን መቅረፍ ካልተቻለ መንግሥት ለዋጋ ንረቱ ማባባስ ቀዳሚ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡   

በመሆኑም የክልል መንግሥታት በነፃ ገበያ መሠራት ያለበት ገበያ እንዳሻቸው እንዲያደርጉ የሚፈቅላቸው ከሆነ፣ ወይም ወደ ገበያ የሚገባውን ምርት እየመጠኑና እየለኩ ይግባ ይውጣ የሚሉ ከሆነ፣ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ ተበላሸ ማለት ነው፡፡ ነፃ ገበያ አዲዮስ እንደማለት ነው፡፡ አርሶ አደር ምርቱን በሚያዋጣው ዋጋ መሸጥ ካልቻለና አስገዳጅ በሆነ ዋጋ ምርቱን እንዲሸጥ ከተወሰነበት ይህ አርሶ አደር ለከርሞ በየትኛው ወኔ ሊያመርት እንደሚችል ሁሉ ያሳስባል፡፡ እና መንግሥት ይህንን ሁኔታ በቅጡ ሊያስብበትና አሠራሩንም ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን በመጠቀም ምርት የሚሸሽጉ ሊበዙ ከመቻላቸው በላይ፣  ከሰሞኑ በተፈጠሩ ችግሮች ጣራ እየነካ ያለውን የስንዴና የጤፍን ገበያ ወደኋላ ለመመለስ ከባድ ይሆናል፡፡ 

ኢትዮጵያ የግብይት ባህል የሚነግረን አንዴ የተሰቀለን ዕቃ ለመመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ በእነዚህ ምርቶች ዋጋ መወደድ ብቻ የአገሪቱ የዋጋ ንረት እስካሁን ካየነው በላይ ሊወጣ ይችላል፡፡ ሸማቹንም የበለጠ የሚያራቁት ይሆናል፡፡ አሁን ላይ አብዛኛው ሸማቹ አንድ ኪሎ ጤፍ 100 ብር የሚገዛበት አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ወይም በተሻለ መንገድ መሥራት አለመቻሉን እያስተዋልን ነው። ከመገለጫዎቹም አንዱ ሰሞነኛው የስንዴ ግብይት ላይ የሚስተዋለው ተገቢ ያልሆነ ግብይት ነው። መንግሥት ይህንን ያልተገባ የስንዴ ግብይት በማረም ገበያውን ማስተካከል አለበት፡፡ የጤፍም ገበያ ቢሆን አሁን ኩንታሉ እስከ አሥር ሺሕ ብር ዋጋ እየተጠራበት የመሆኑ ጉዳይ ምርቱ ጠፍቶ ሳይሆን፣ ምርቱን ለማንቀሳቀስ ሰላም መጥፋት፣ ብሎም ምርቱን ለማጓጓዝ እየተፈጠሩ አስገዳጅ ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው፡፡ በግብርና ምርቶች ላይ ከልክ ያለፈ ቁጥጥር ማድረግ፣ ምንም ዝግጅት ሳይደረግ የነበረውን የግብይት ሰንሰለት ለበመጣጠስ ከመነሳት ሌላ ችግር ሊያመጣ ስለሚችልም፣ የመንግሥት ዕርምጃዎች የተጠኑና ግራና ቀኝን የተመለከቱ መሆን አለባቸው፡፡ 

በተለይ የግብይት ሥርዓቱ በነፃ ገበያ የማይመራ ከሆነ አደጋ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በግብርና ምርቶች ላይ እየታየ ያለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለማርገብ መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው የዋጋ ንረቱን የሚያባብሱ ቡድኖችንም አደብ ማስገዛት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት